Thursday, December 7, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበኢትዮጵያ የተስፋፋው ሕገወጥ የአህያ ዕርድ

በኢትዮጵያ የተስፋፋው ሕገወጥ የአህያ ዕርድ

ቀን:

በቻይና በስፋት ጥቅም ላይ ከሚውሉ ባህላዊ መድኃኒቶች ‹ኢጃዋ› የተሰኘ መድኃኒት አንዱ መሆኑ ይጠቀሳል፡፡ ኢጃዋ የተለያዩ በሽታዎችን ከመፈወስ ባሻገር በኮስሞቲክስ ኢንዱስትሪ ውስጥም ትልቅ ግብዓት ሆኖ ያገለግላል፡፡ ይህም መድኃኒት ከአህያ ቆዳ የሚሠራ መሆኑ ሕገወጥ የአህያ ዕርድ እንዲስፋፋ ምክንያት ሆኗል፡፡

የአህያ ዕርድም በበርካታ አገሮች የተስፋፋ ሲሆን፣ በኢትዮጵያን በመሰሉ አገሮች ላይ ግን ከፍተኛ የሆነ ችግር እያስከተለ መሆኑ በተደጋጋሚ ይነገራል፡፡

የ‹‹ዘ ብሩክ ሆስፒታል ፎር አኒማል›› ካንትሪ ዳይሬክተር አቶ ዮሐንስ ቃሲም እንደገለጹት፣ ብሩክ ኢትዮጵያ የጋማ እንስሳት ደኅንነትን በማረጋገጥና የከብቶቹን ባለንብረቶች ኑሮ ለማሻሻል የሚሠራ ዓለም አቀፍ ተቋም ነው፡፡

ተቋሙ በዓለም አቀፍ ደረጃ በ11 አገሮች ላይ የሚሠራ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ በኦሮሚያ፣ በአማራና በደቡብ ክልሎች ውስጥ በስፋት በመንቀሳቀስ ለጋማ እንስሳት ደኅንነቶች ትኩረት በመስጠት እየሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በተለይም በሦስት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ትኩረት በመስጠት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የገለጹት አቶ ዮሐንስ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ሕገወጥ የአህያ ዕርድ በመኖሩ ሥራቸው ላይ እንቅፋት መፍጠሩን አስረድተዋል፡፡

‹‹በቻይና በስፋት ጥቅም ላይ ከሚውሉ ባህላዊ መድኃኒቶች ኢጃዋ አንዱ ነው፤›› የሚሉት ዳይሬክተሩ፣ ባህላዊ መድኃኒቱ ከአህያ ቆዳ የሚዘጋጅ በመሆኑ፣ ሕገወጥ የአህያ ዕርድ በተለያዩ አገሮች ሊስፋፋ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

ቻይናን ጨምሮ ብራዚል ፔሩና ኮሎምቢያ የአህያ ቆዳን ለተለያዩ አገልግሎትነት እንደሚጠቀሙ፣ ይህንንም ጉዳይ በመረዳትና በዘርፉ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት ለማኅበረሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ እየተሠራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በኢትዮጵያ የእንስሳት ሕክምና አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድግ በባህር ዳር፣ በወሎና በጅማ ዩኒቨርሲቲ የሚማሩ የእንስሳት ሐኪሞች ጋር ቅንጅት በመፍጠር ጥራቱን የጠበቀ የሕክምና አገልግሎት እንዲኖር እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ በኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ የእንስሳት መድኃኒት አቅርቦት ችግር መኖሩን ጠቅሰው፣ ያለውንም ችግር ለመቅረፍ በሥልጠናና በገንዘብ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡  

በአዲስ አበባም ሆነ በተለያዩ አካባቢዎች መንገድ ላይ ቆመው የሚታዩ ፈረሶች አብዛኛዎቹ በበሽታ የተጠቁ መሆናቸውን፣ ፈረሶቹን ለመታደግና ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎችን ለማስቀረት የሕክምና አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ በፊት ከ2,500 እስከ 3,000 የሚሸጥ አንድ አህያ አሁን ከ9,000 እስከ 11,000 ብር እየተሸጠ መሆኑን፣ ይህም ሕገወጥ የአህያ ዕርድ በመስፋፋቱ ምክንያት መከሰቱን ተናግረዋል፡፡

በገጠራማ ቦታም ሆነ በከተማ ደረጃ የጋማ እንስሳት ለመጓጓዣነት የሚያገለግሉ መሆኑን፣ አገልግሎቱን ከሚሰጡ እንስሳት ውስጥ አንዱ በሆነው አህያ ላይ የሚፈጸመው ዕርድ ትልቅ ችግር እየፈጠረ ይገኛል ብለዋል፡፡

እነዚህ የጋማ እንስሳት ለተለያዩ አካባቢዎች የገቢ ምንጭ በመሆናቸው፣ የጋማ እንስሳት በተገቢ መንገድ በመንከባከብ የተሻለ አሠራር መዘርጋት ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ቻይና ከአህያ ቆዳ የምታዘጋጀው ኢጃዋ ምርት ከዚህ በፊት በኪሎ 20 ዶላር ይሸጥ እንደነበር፣ በአሁኑ ሰዓት ግን 8.30 ዶላር እየተሸጠ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ምርቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው፣ በዚህ ምክንያት ቻይና እ.ኤ.አ. በ1990 ከነበራት 11.1 ሚሊዮን አህያ በ2018 ወደ 2.3 ሚሊዮን ማሽቆልቆሏን ገልጸዋል፡፡

በተለያዩ የዓለም አገሮች የአህያ ዕርድ በስፋት መስፋፋቱን የተናገሩት ዳይሬክተሩ፣ በኢትዮጵያም በደብረ ዘይትና በአሠላ አካባቢ የአህያ ዕርድ የሚከናወንበት የቄራ ድርጅት ተከፍቶ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

በኢትዮጰያም የሚገኙ ሁለት የአህያ ዕርድ የሚከናወንባቸው ቦታዎች በመንግሥት የሚታወቁ ሲሆን፣ በደብረ ዘይት አካባቢ የሚገኘው የዕርድ ቦታ ሙሉ ለሙሉ ሥራውን ማቆሙን ገልጸዋል፡፡

በአሰላ አካባቢ የሚገኘው የዕርድ ቦታ በአሁኑ ወቅት በቀን ከ100 እስከ 300 አህያዎችን ዕርድ በማከናወን ለውጭ አገር እየላከ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ከ2016 እስከ 2019 ባለው ጊዜ ውስጥ በኬንያ በቀን 1,000 አህያዎች ይታረዱ እንደነበር፣ እነዚህ አህያዎች አብዛኛዎቹ የሚወሰዱት ከኢትዮጵያ በሕገወጥ መንገድ መሆኑን አቶ ዮሐንስ አስረድተዋል፡፡

ኬንያ በሁለት ዓመታት ውስጥ 15 በመቶ የሚሆኑ አህያዎቿን ማጣቷን ጠቅሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ መንግሥት ዕድሜያቸው የገፉ፣ በተለያዩ በሽታዎች የተጠቁ አህያዎች ለዕርድነት እንዲውሉ ቢፈቀድም ቦታው ላይ ያለው እውነት ግን ከዚህ የራቀ መሆኑን የብሩክ ሆስፒታል ፎር አኒማልስ አድቮኬሲና ፈንድ ሬዚንግ ከፍተኛ ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ፍቅር ሽፈራው ተናግረዋል፡፡

በተለይ ባለፉት አምስት ዓመታት የእንስሳት ደኅንነት ፖሊሲን በተመለከተ መመርያ ለማዘጋጀት ከግብርና ቢሮ ጋር ስምምነት ላይ ቢደርሱም እስካሁን መመርያው አለመውጣቱን ወ/ሮ ፍቅር ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በዓመት ከአህያ ሥጋና ከቆዳ 600 ሺሕ ዶላር ማግኘቷን፣ ይህንን መረጃ ሪፖርት ያደረገው የግብርና ሚኒስቴር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ብሩክ የተዳከመውን የእንስሳት ጤና ሥርዓት የማጠናከር፣ የእንስሳት ደኅንነትን ያገናዘበና ምቹ አገልግሎት መስጠት የሚችልበትን መፍትሔ የመስጠት ሥራ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተለይ የጋማ እንስሳት የጤና አገልግሎት ለማሻሻል ክትባቶች፣ መድኃኒቶችና ለሕክምና ቁሳቁሶ አቅርቦት የሚውል ተዘዋዋሪ ፈንድ እየሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...