Sunday, February 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

‹ኧረ እንዲያው ምን ይሻለናል?›

እነሆ ጉዞ ከፒያሳ ወደ ሜክሲኮ። ታክሲ የሚባል ነገር የለም፡፡ ረጅሙ የታክሲ ወረፋ ብሶት፣ እልህ፣ ታጋሽነት፣ አርቆ አሳቢነት፣ ተስፋ መቁረጥ፣ ከንቱ የመሆን ስሜት በየዓይነቱ ይንፀባረቃል። ‹ስሜት ነው የሰው ልጅ የራሱ ድምፅ› ያስብላል። ሁሉም በመሰለው ለመሮጥ አሰፍስፎ ግን የአቅሙን ያህል እንዳይሮጥ፣ ዙሪያውን ከትራንስፖርት ችግር እስከ አስተሳሰብና አመለካከት ችግር መንገድ ተዘግቶበት ቆሟል። ከሚታየው እስከማይታየው ሁሉም የመንገድ ጋሬጣ ነው። እንዲህ ነው የዚህ ጎዳና ውስጠ ሚስጥር። የፈቀዱትን ለመሆን ባልፈቀዱት ሥፍራና ሰርጥ ውስጥ ወድቀው የሚነሱበት። ለዚህም ነው በርካታ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ትንታኔዎች የሚቀርቡበት። ድንገት ከዚህ ሐሳባዊ ፍልስፍናና ምርምር ውስጥ ተሁኖ ድንገት ታክሲ ሲመጣ መጠነኛ ፈገግታ መታየት ይጀመራል። ቀደም ቀደም ያልነው በደረሰው ብቸኛ ሚኒባስ ታክሲ ውስጥ ገብተን ተሳፍረናል። ተመሥገን ነው ይህንንስ ማን አየው ያሰኛል!

ጉዟችን ተጀምሯል። አንድ ጎልማሳ በስልኩ መነጋገር ጀመረ። ‹‹እየመጣሁ ነው አልኩህ እኮ… ሃሎ… አይሰማም? አንተ ብቻ ፖሊሶች ፈልገህ አስይዝልኝ…›› ይላል። ንዴትና እልህ አወራጭቶት ስልኩን እየዘጋው። የታክሲዋ ተሳፋሪዎች በፀጥታ የሰውየውን ሁናቴ ይከታተላሉ። ‹‹ሰላም አይደለም?›› አለችው ከጎኑ የተቀመጠች ውብ ሽቅርቅር። ‹‹ኧረ ተይኝ የዛሬ ልጅ በየት በኩል ሰላም ይሰጣል?›› ብሏት ሐሳብ ጭልጥ አደረገው። ጥያቄዋን መግታት ያልቻለችው ዘናጭ፣ ‹‹እና ለራስህ ልጅ ነው እንዴ ፖሊስ የምታስጠራው?›› ብላ ብትጠይቀው፣ ‹‹አዎ… ይኼውልሽ የዘንድሮ ልጅ ገመናችን እንኳ እንዳንደብቅ በየመንገዱ ያዋርደናል…›› አላት እንደማፈር እያለ። ‹‹በዚህ በኩል ለእነሱ ማደጊያ የሚሆን ትንሽ ጥሪት ለመቋጠር ስንሮጥ፣ የእነሱ ነገር ግን እያደር ሥጋት እየሆነ መጣ…›› ብሎ እንደ መተከዝ አሰኘው። ‹‹አ…ሄ…ሄ… የዘንድሮ ልጅ አስተዳደግ ራሱ መቼ ሥርዓት አለው? እኛ እንኳ በዚያ በድንቁርናው ጊዜ እንዲህ እንዳሁኑ ወልደን አልተውናቸውም። የዛሬ ወላጅ ካበላ፣ ካለበሰና ትምህርት ቤት ከላከ በኋላ መቼ ዞር ብሎ ያይና?›› ብለው አንዲት እናት ትዝብታቸውን ተናገሩ። የልጅ ነገር ሆኖባቸው እኮ ነው!

‹‹ኧረ እውነትዎን ነው፣ ከግለሰብ እስከ ኅብረተሰብ ብሎም እስከ መንግሥት እውነት ለመናገር የመጪው ትውልድ አዝማሚያ ያሳሰበው ያለ አልመሰለኝም። መንግሥት ትኩረቱ ሁሉ ሌላ ነገር ላይ ሆኖ ታዳጊዎችንና ወጣቶችን በተመለከተ ማውጣትና ማጥበቅ ያለበትን ሕግ ከእነ ጭራሹ ረስቶታል። እኛም መቼም ሲፈጥረን አፍሶ መልቀም ነው የሚቀናን፡፡ ከሆነ በኋላ ካለቀ በኋላ መጮህ እንወዳለን…›› ብሎ ሳይጨርስ ከአጠገባቸው የተቀመጠ ወጣት፣ ‹‹ኑሮ ቀልባችንን ገፎት እንዴት ብለን እንዲህ ያለውን ጉዳይ እናስታውሰው እባካችሁ? በዚህ በኩል የፍትሕ ዕጦት፣ በዚያ በኩል የኑሮ ውድነት፣ በአንድ በኩል የሰላም ዕጦት፣ ዞር ሲባል ደግሞ ሐሜትና አሉባልታ ጨምድደው ይዘውን እኮ እንዴት ብለን ነው ለልጆቻችን የምንደርስላቸው?›› ብላ ጋቢና የተቀመጠች ወይዘሮ ብሶቷን ዘረገፈች፡፡ ‹‹ትምህርቱ መክኖ ትውልድ ሲጠፋ ሰበብ ይፈለጋል? ኧረ ሩጫው ለማን ነው ጎበዝ?›› ይላል ሌላው፡፡ ብሶት ብቻ!

ጉዞ ቀጥሏል፡፡ ከጥቅምት ማለዳ ያመረረ ቀዝቃዛ የአየር ፀባይ ይልቅ የትራንስፖርት ችግር ያማረረው በሆዱ እ….ህ…ህ…ህ… ይላል፡፡ በዚህ መሀል ድንገት፣ ‹‹አሁንስ እንዲያው ሆድ የሚሉት ነገር ባይኖር ምን ነበረበት?›› ትላለች ጠየም ያለች ቀጭን ቆንጆ። ከሁኔታዋ ነገር ዓለሙን የተፀየፈች ዓይነት ናት። ‹‹ሆድማ ባይኖር በዚህ አስመራሪ ቅዝቃዜ አንችን የመሰለችዋ መጥታ አጠገባችን መቼ ታሞቀን ነበር? አይደል እንዴ?›› ይላታል ከጎኗ የተቀመጠ ወጣት እያሳሳቀ ትፈቅደው እንደሆነ ለመሞከር ያህል። ‹‹የእኛ ነገር ለአንዴው አበሳጭቶ ለአንዴው ደግሞ ፈገግ የሚያደርገን ነገር ነው የሚገርመኝ እኮ። አሁን አጠቃላዩ ችግራችን ብሶቱ ተሰምቶ ሳያልቅ ከመቼው መሳቅ ተጀመረ?›› ይላሉ አንዲት አዛውንት ከሦስተኛው የታክሲዋ መቀመጫ ወንበር። ቋሚ የሚባል ነገር ከጠፋ ዘመን እንደሌለው የሚነግራቸው ያጡ ይመስላሉ። ‹‹አይ እማማ፣ ታዲያ እንዲህ ካልሆነ የዘንድሮ የኑሮ ውድነትና የትራንስፖርት ችግር አንድ ላይ አማረው አይገሉንም ነበር?›› ይላቸዋል አጠገባቸው ያለ ወጣት። አዛውንቷ ቀና ብለው ወጣቱን ለአፍታ ሲያስተውሉት ቆይተው፣ ‹‹ለመሆኑ እየተዘጋጀህ ነው አንተ?›› ብለው ጠየቁት። ድንገቴ በሉት!

ወጣቱ ከዕድሜያቸው አኳያ የጤንነታቸው ነገር አጠራጥሮት ጥያቄው ግራ እንዳጋባው ያስታውቅበታል። ‹‹ለምኑ ነው የምዘጋቸው?›› አላቸው ትህትናው የድምፁን ክሮች ክፉኛ እያርገበገባቸው። ‹‹ለምኑ? ለመኪናው ነዋ። ዘንድሮ አራት እግር የሌለው አራት እግሩን እስኪበላ ቆሞ ነው የሚቀረው ሲባል የትነው ያለኸው?›› ቢሉት የኮረኮሩትን ያህል ሳቀ። የልቡን ነው መሰል የነገሩት። ‹‹አትሳቅ ቀልዴን አይደለም የምነግርህ። ዛሬ ከታክሲና ከአውቶቡስ ጥበቃ ብስክሌትም ቢሆን ማለፊያ ነው…›› ሲሉት እንደገና የታክሲው ተሳፋሪዎች በሙላ ለሳቅ ተባበሩ። ይኼኔ ከኋላ መቀመጫ ተሸክሞት የገባው ብርድ የሚያንቀጠቅጠው ተሳፋሪ፣ ‹‹እማማ ዕድሜ ለፆታ እኩልነት የዘንድሮ ጥሎሽ እኮ የጋራ ሆኗል። አለበዚያማ ጥሎሹ የጋራ ባይሆን የአዳም ዘር በዚህ ዘመን ኑሮ መቼ ሞልቶለት ብለው ነው?›› ሲናገር፣ ከትራንስፖርት ችግር አንስቶ ትዳር ምሥረታ ድረስ የዘለቀው የታክሲያችን ጭውውት፣ እንዲህ የማይተዋወቀውን እያስተዋወቀ በረቀቀ ዘይቤው መንገዱን ያሳጥረው ነበር። ድንቅ ነው!

ወያላው ሒሳቡን እየተቀበለ ነው። ‹‹መቼም አገሩ በቆንጆዎችና በድንገተኛ ሀብታሞች ነው  የተጨናነቀው…›› የሚል ድምፅ ከመሀል ወንበር አካባቢ ይሰማል። አባባሉ ሁሉንም ተሳፋሪዎች ግር አሰኘ መሰል አንድ ዝምተኛ ወጣት፣ ‹‹ቆንጆዎቹ ከተፈጥሮ ያገኙት ከሆነ ይሁን ግድ የለም እንቀበላለን፡፡ ያልገባን ግን በአንድ አዳር ከምን ተነስተው ባለቪላ፣ ባለቪኤይት፣ ባለሕንፃ፣ ወዘተ የሚሆኑት መንግሥት የት ሄዶ ነው?›› ብሎ ከፊት ያልታሰበ ጥያቄ ሲያቀርብ፣ ‹‹እኔ እንጃ…›› አለች ፈጠን ብላ ያቺ ጠይም። ‹‹የምን እንጃ ነው?›› ቢላት ወጣቱ፣ ‹‹እኔ ግን እንዲህ መንግሥት የት እንዳለ አላውቅማ…›› ብላ ስትመልስለት ታክሲዋ ጥያቄና መልሱ በርዶላት በታላቅ የዝምታ ድባብ ተዋጠች። ከዚያ ሁሉ ውካታና የቃላት ምልልስ በኋላ የነበረው ዝምታ ያስፈራ ነበር፡፡ ‹‹ዝምታ ከጩኸት በላይ ያስፈራኛል›› ያለው ገጣሚ ነው ወይስ ደራሲ የሚለውን ብናውቅ መልካም ነበር፡፡ ግን ማንም ሆነ ማን ዋናው ሐሳቡ ላይ ነው ሊተኮር የሚገባው የሚሉ ሞጋቾች አይጠፉም፡፡ ይኑሩልን!

ወደ መዳረሻችን እየተቃረብን ነው። ወጪና ወራጁ በዕለታዊ እንቅስቃሴው ተመስጦ አንዱ አንዱን የማየት ትዕግሥት አጥቶ ይራወጣል። ሁሉም የሕይወቱን አቅጣጫ ለማስተካከል ሽር ጉድ ይላል። ታክሲያችን እኛን ወደ የሚያራግፍበት አካባቢ ለቁጥር የሚታክቱ ተሳፋሪዎች ለሌላ አዲስ ጉዞ አሰፍስፎ ይጠብቃል። የትራንስፖርት ችግር እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል። ‹‹ኧረ ጎበዝ በዚህ ዓይነት እስከ መቼ ልንዘልቅ ነው?›› ሲል አንዱ፣ ‹‹ማን አወቀ ብለህ ነው?›› ይለዋል ከወዲያ ሌላው። ‹‹አሁንማ የለም፣ አልቋል፣ ጠፍቷል፣ ዋጋው ጨምሯል፣ ወዘተ የሚሉ ቃላት ራሳቸው እንደሰለቹን ምንም አልሰለቸንም። ታክሲ ስትሉ የለም፣ ውኃስ ሲባል የለም፣ መብራት ጠፍቷል፣ የእህል ዋጋ በእጥፍ ጨምሯል። እንዲያው ምን እንደሚሻለን እንጃ ብቻ…›› ትላለች ሦስተኛ ወንበር ላይ ያለችው ቀዘባ። ከአፍታ ቆይታ በኋላ ብሶት ሲያገረሽ ግርም ድንቅ ይላል፡፡ መጥኔ ነው!

‹‹ወጡ ሳይወጠወጥ ወስከንባዩ ይሮጥ’ ስለሆነ እኮ ነው የዚህ ሁሉ ችግር መንስዔ። መንግሥት ሳያስበው ዘጠኝ ድስት ጣደና አንዱን ሲለው አንዱ፣ አንዱን ሲለው ሌላው ይኼው የሚያርበት በዛ። ሌላው ቢቀር ለትራንስፖርት አገልግሎት ቅድሚያ ሳይሰጥ እንዴት ተብሎ ስለስማርት ሲቲ ፕሮጀክት የሚወራው? ከክልል ከተሞች ወደ መሀል ከተማ ያለው መጠን አልባ የሕዝብ ፍልሰት ያስፈራል፣ የሕዝብ ቁጥር መጨመሩ ሥጋት ነው፣ ከቦታ ወደ ቦታ ተንቀሳቅሶ መሥራት የማይቻልበት ደረጃ ላይ ነው ያለነው…›› ብሎ ሲናገር ብሶተኛው ወጣት፣ ‹‹ሁሉንም ነገር መንግሥት ትከሻ ላይ ጥለን እኛስ ኃላፊነታችን የት ድረስ እንደሆነ መታወቅ የለበትም?›› ብሎ አንዱ ጎልማሳ ቱግ ሲል ከዚህም ከዚያም ድምፅ በዛ። ወያላችን ‹‹መጨረሻ…›› ብሎ በሩን ሲከፍተው ደጅ የነበሩ የታክሲ ሠልፈኞች እኛ እስክንወርድላቸው በትዕግሥት መጠበቅ አልቻሉም ነበር። እንደ ምንም ቀስ በቀስ ወርደን ስንበታተን አጠገቤ ተቀምጦ የነበረው ወጣት፣ ‹‹ኧረ እንዲያው ምን ይሻለኛል…›› የሚለውን የጥላሁን ገሠሠ ዕድሜ ጠገብ ዜማ በፉጨት እያሰማ ሲወርድ እየሰማነው ነበር። እኛስ ‹ኧረ እንዲያው ምን ይሻለናል?› ብንል ምን ይለናል፡፡ መልካም ጉዞ! 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት