Monday, April 15, 2024

የፕሪቶሪያ ስምምነት አንደኛ ዓመትና አወዛጋቢዎቹ አካባቢዎች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ጥቅምት ወር ባለፉት ጥቂት ዓመታት ጦርነትም ሰላምም ይዞ የመጣ ወር  ነበር፡፡ ለወትሮው ‘በጥቅምት አንድ አጥንት’ እየተባለ ስለብርዱና ቆፈኑ ይገጠምለት የነበረው ጥቅምት ከክረምት ወደ በጋ መሸጋገሪያ ወር ነበር፡፡ የመኸር ምርት የሚሰበሰብበት፣ አዝመራው፣ እሸቱና ማሩ የሚቆረጥበት ወር በመሆኑ ነበር ጥቅምት የሚታወቀው፡፡ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ግን የተለመደው ገጽታው ተለውጦ ከባድ የእርስ በርስ ግጭት ማስጀመሪያ ወር ሆነ፡፡ ሕወሓት በአገር መከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ በከፈተው ጥቃት የተለኮሰው ይህ ከባድ የእርስ በርስ ጦርነት ደግሞ፣ ለሁለት ዓመታት በሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች ሲካሄድ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ በስተመጨረሻ ግን ጦርነቱ በተጀመረ በሁለተኛ ዓመቱ ጥቅምት 23 ግጭት የሚያስቆም የሰላም ስምምነት ላይ ተደረሰ፡፡ በዚህ የተነሳ ጥቅምት ወር ባለፉት ሦስት ዓመታት የከባድ ዕልቂት ማስጀመሪያ ፊሽካ የተነፋበት ብቻ ሳይሆን፣ ታላቅ ትርጉም የሚሰጠው የሰላም ዜናም የተሰማበት ሆኖ ማለፉን ብዙዎች ያስታውሳሉ፡፡

የሰሜኑ ጦርነት በብዙ ጥረት ነበር የዛሬ አንድ ዓመት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከተማ በተፈረመ የሰላም ስምምነት የተገታው፡፡ ጦርነቱ በሰላም ዕልባት እንዲያገኝ ከውስጥም ከውጭም ብዙ ግፊቶች የነበሩ ቢሆኑም፣ ይሁን እንጂ ተፋላሚዎቹ ኃይሎች ወደ ድርድር ለመግባት ብዙ መቸገራቸው አይዘነጋም፡፡ በይፋ ድርድር መጀመሩ ከመነገሩ ቀደም ብሎ ይፋ ያልሆኑ የሰላም ጥረቶች በተለያዩ አደራዳሪዎች ሲሞከሩ መቆየታቸው ይነገራል፡፡ በስተመጨረሻ ፍሬ ለማፍራት የበቃው ግን በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥር የተመራው የድርድር ጥረት መሆኑ ይታወቃል፡፡ እንደ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆና ኡሁሩ ኬንያታ የመሳሰሉ የአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪዎች ነበሩ በኢትዮጵያ መንግሥትና በሕወሓት መካከል የተፈረመውን የፕሪቶሪያ ስምምነት ለማሳካት  የቻሉት፡፡ የፕሪቶሪያው ስምምነት ማስፈጸሚያ በኬንያ ናይሮቢ በሁለቱ ወገኖች የጦር መሪዎች መካከል እንዲፈረም ያስቻሉት፣ እነዚሁ አደራዳሪዎች ነበሩ፡፡

የፕሪቶሪያው ስምምነት በሥራ ላይ እንዲውል የማድረጉን ጉዳይም ይከታተል የነበረው የአፍሪካ ኅብረት ታዛቢ ቡድን እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ታዛቢ ቡድኑ በዋናነት የሕወሓት ታጣቂዎችን ትጥቅ አፈታትና መልሶ ማደራጀት ጉዳይ የመከታተል ኃላፊነት የተሰጠው ሲሆን፣ ሁለቱ ወገኖች የፖለቲካ ንግግር የሚሹ ጉዳዮችን ወደ መፍታት ሲገቡም ሒደቱን በቅርበት የመከታተል ኃላፊነት ነበረበት፡፡

የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ከተፈረመ አንደኛ ዓመቱን ቢደፍንም፣ እስካሁን ስምምነቱ በተጨባጭ መሬት ላይ አልወረደም የሚል ወቀሳ ከሁሉም አቅጣጫ እየተሰማ ነው፡፡ የትግራይ ክልል ባለሥልጣናትን ጨምሮ አንዳንድ ወገኖች የአፍሪካ ኅብረት የሰላም ስምምነት ከማፈራረም በዘለለ የሰላም ስምምነቱ በተጨባጭ መሬት ላይ እንዲወርድ በቂ የክትትል ሥራ አልሠራም የሚል ወቀሳ ያቀርባሉ፡፡ ሌሎች ወገኖች ግን ይህን ሲቃወሙት ነው የሚታየው፡፡

የሕወሓት ታጣቂዎችን ትጥቅ የማስፈታቱ ሥራ መገባደዱ ይፋ ቢደረግም፣ ነገር ግን ሕወሓት አሁንም ትጥቅ አልፈታም የሚለው ወቀሳ በአንዳንዶች ዘንድ ሲንፀባረቅ ይሰማል፡፡ ጊዜያዊ የሽግግር ጊዜ አስተዳደር በትግራይ መመሥረቱ ይፋ ቢሆንም፣ በአንዳንድ ወገኖች ዘንድ አስተዳደሩ አካታችነት የሌለው ስለመሆኑ ይነገራል፡፡ በስምምነቱ መሠረት ሁለቱ ወገኖች የፖለቲካ ውይይት ወደሚጠይቁ ጉዳዮች፣ ለምሳሌ አጨቃጫቂ የወሰን ጉዳዮችን በተመለከተ ወደ ንግግር ይገባሉ ተብሎ ቢጠበቅም ይህም በተጨባጭ ወደ መሬት አለመውረዱ ነው የሚነገረው፡፡

የፕሪቶሪያው ሰላም ስምምነት በተፈረመ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ብዙ ተጨባጭ ሥራዎች መከናወናቸውን የሚገልጹ መረጃዎች ከተለያዩ ወገኖች ቢሰሙም፣ ነገር ግን ከሕወሓትና ከመንግሥት ወገን ይህን የሚደግፍ መረጃ ሲሰጥ አልተደመጠም ይባላል፡፡ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማህማት ግን የስምምነቱን አንደኛ ዓመት አስመልክቶ ከሰሞኑ ባወጡት መግለጫ የስምምነቱን አተገባበር አወድሰዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የሚመራው የፌዴራል መንግሥትና የሕወሓት ባለሥልጣናት የአፍሪካ ኅብረት የመራውን የሰላም ስምምነት በተግባር በመተርጎም ያልተቋረጠ ተከታታይ ሥራ በመሥራታቸው፣ ሊቀመንበሩ እንደሚያመሠግኑ በመግለጫቸው ይፋ አድርገዋል፡፡ አስደናቂ የሰላም ስምምነት ትግበራ ግስጋሴ ሁለቱ ወገኖች አሳይተዋል ሲል የሚያደንቀው የሊቀመንበሩ መግለጫ፣ በትግራይ ክልል የስምምነቱን አተገባበር እንዲከታተል የተመደበው የአፍሪካ ኅብረት የባለሙያዎች ቡድንም አድናቆት እንደሚገባው ያብራራል፡፡ 

የአውሮፓ ኅብረት፣ የአሜሪካና አንዳንድ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ባለሥልጣናት ግን የሰላም ስምምነቱ ትግበራ ምሉዕ እንዲሆን ሊከወን ይገባል የሚሉትን ሥራ በማስቀደም ነው የስምምነቱን አንደኛ ዓመት የተመለከተ መግለጫ ይፋ ያደረጉት፡፡ ለምሳሌ የአውሮፓ ኅብረት የውጪ ግንኙነት ፖሊሲ ኃላፊ ጆሴፍ ቦሬል በተጠያቂነትና በፍትሕ ጉዳይ ላይ ትርጉም ያለው ውጤት ኅብረቱ ማየት እንደሚፈልግ ተናግረዋል፡፡ ሰብዓዊ መብቶችን የሚጥሱ፣ የሰብዓዊነት ሕጎችን የሚፃረሩና ሰቅጣጭ ወንጀሎችን የፈጸሙ ላይ ምርመራ ተደርጎ ለፍትሕ እንዲቀርቡ እንፈልጋለን በማለት ነበር ኃላፊው የተናገሩት፡፡ የአውሮፓ ኅብረት በቅርብ ወራት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የ650 ሚሊዮን ዩሮ የልማት ድጋፍ ስምምነት ቢፈራረምም፣ የትግራይ ክልል ጦርነትን ተከትሎ እስካሁን ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን የበጀት ድጋፍ እንዳቋረጠ መቀጠሉ ይታወቃል፡፡

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን የሰላም ስምምነቱ ከእነ እክሎቹ አተገባበሩ በጎ እመርታ እንዳሳየ ገልጸዋል፡፡ ብሊንከን የስምምነቱን አንደኛ ዓመት አስመልክቶ እንደተናገሩት፣ የኤርትራ ኃይሎች ከትግራይ አለመውጣታቸው ዋና ችግር መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ኤርትራ በአስቸኳይ ከኢትዮጵያ ድንበር ለቃ እንድትወጣ ያስጠነቀቁት ብሊንከን፣ የሰላም ስምምነቱ አተገባበር ከእነ ችግሮቹ በጎ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ በሽግግር ፍትሕ አስፈላጊነትና በብሔራዊ ምክክር አስፈላጊነት ላይ የሚያተኩረው የብሊንከን መግለጫ ከትግራይ ክልል በተጨማሪ በአማራ፣ በኦሮሚያና በሌሎችም ክልሎች ሰላም የማስፈን ጉዳይ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ጨምሮ አሳስቧል፡፡ 

ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ድርጅት ሂዩማን ራይትስ ዎች በበኩሉ፣ በትግራይ አሁንም የሰብዓዊ መብቶች መጣስ ስለመቀጠሉ ማስታወቅን ነው የመረጠው፡፡ በአፍሪካ ምክትል ዳይሬክተሩ ሌቲሻ ባድር በኩል መግለጫ የሰጠው ድርጅቱ፣ የኤርትራ ኃይሎች አሁንም ቢሆን በተቆጣጠሯቸው ቦታዎች የመብት ጥሰጥ እያደረሱ በመሆናቸው ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይህን ማስቆም ይገባዋል ብሏል፡፡  

ከዓለም አቀፍ መግለጫዎች በመለስ በትግራይ በኩል ያሉ የተለያዩ የፖለቲካ ልሂቃን የሰላም ስምምነቱ ሙሉ ለሙሉ በተግባር መተርጎም አለበት የሚለውን ጉዳይ በሰፊው ግፊት ሲያደርጉበት ከሰሞኑ እየተሰማ ነው፡፡ በአውሮፓ ኅብረት መቀመጫ ቤልጄም ብራሰልስ ይህንኑ የሚያስተጋባ ሰላማዊ ሠልፍ መደረጉ ተነግሯል፡፡ የትግራይ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖችም የተለያዩ መግለጫዎች እያወጡ ናቸው፡፡   

በሕወሓት በኩል አንዱ ተደራዳሪ የነበሩት ፍሰሐ አስገዶም (አምባሳደር) የሰላም ስምምነቱ አንደኛ ዓመትን በተመለከተ ለትግራይ ቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫ፣ የኤርትራ ሠራዊትና የአማራ ኃይሎች ያሏቸው ከትግራይ አለመውጣት የሰላም ስምምነቱን ትግበራ እያደናቀፈው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሕወሓት ሙሉ ለሙሉ ከባድ መሣሪያ ቢያስረክብም ነገር ግን ከመከላከያ ውጪ ያሉ የታጠቁ ኃይሎች ክልሉን ለቀው ባለመውጣታቸው፣ በትግራይ ሕዝብ ላይ ጥቃት መፈጸሙ ቀጥሏል ብለዋል፡፡ የፌዴራል መንግሥት በዚህ ላይ ያለውን አቋም አናውቅም ብለው መናገራቸውም ተሰምቷል፡፡

ከሰሞኑ የአሜሪካ ኤምባሲ ልዑካንን በመቀሌ ተቀብሎ ያስተናገደው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደርም የፕሪቶሪያ ስምምነት አተገባበርን የተመለከተ ሪፖርት ማቅረቡን የትግራይ ቴሌቪዥን ዘግቧል፡፡ በዘገባው የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት አማካሪ አቶ ጎይቶም ታጠቅ ምዕራብ ትግራይ፣ ሰሜን ምዕራብ፣ ምሥራቅና ደቡብ ትግራይ አካባቢዎች በኤርትራና በአማራ ኃይሎች እጅ ሥር ሆነው መቀጠላቸው የሰላም ስምምነቱ ሙሉ ለሙሉ ላለመተግበሩ ዋና እንቅፋት በማለት ጊዜያዊ አስተዳደሩ ለኤምባሲ ልዑካኑ እንዳቀረበ መናገራቸው ተነግሯል፡፡ እነዚህ ኃይሎች ላለመውጣታቸው ዋና ተጠያቂው የፌዴራል መንግሥት ስለመሆኑም ይህ ዘገባ ይጠቁማል፡፡

በትግራይ ክልል ባለሥልጣናት የተነገረው አቤቱታ ደግሞ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት መድረክ ላይም ሲስተጋባ ነው የተሰማው፡፡ የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች አጣሪ ኮሚሽን በኢትዮጵያ ሊቀመንበር መሐመድ ቻንድ ከሰሞኑ የመጨረሻ ሪፖርታቸውን ለምክር ቤቱ ማቅረባቸው ታውቋል፡፡ በዚሁ ጊዜም ስምምነቱ ሙሉ ለሙሉ በተግባር አለመተግበሩንና ለዚህም ዋናው እንቅፋት የኤርትራና የአማራ ኃይሎች ከትግራይ ሙሉ ለሙሉ ለቀው አለመውጣታቸው እንደሆነ ገልጸው ነበር፡፡

ከሁሉ በላይ ‹‹በትግራይ ላይ የጄኖሳይድ ጦርነት የታወጀበትን ጥቅምት 24 በተመለከተ ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የተሰጠ መግለጫ›› በሚል የቀረበው የፕሪቶሪያን ሰላም ስምምነት የተመለከተው የጊዜያዊ አስተዳደሩ መግለጫ ደግሞ ብዙ ጠንከር ያሉ ጉዳዮችን የሚያነሳ ነበር፡፡

በመግለጫው እንደሚነበበው፣ ‹‹የትግራይ ሕዝብ ራስን በራስ የማስተዳደርና የመወሰን መብቴ ይከበርልኝ በሚል ስለጠየቀ ብቻ የጄኖሳይድ ጦርነት የታወጀበት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ሦስት ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ልዩነቶች በሰላምና በውይይት እንዲፈቱ የትግራይ ሕዝብ በተለያዩ መድረኮች ቢጠይቅም ሰሚ በማጣቱ ተገዶ ወደ ጦርነት ገብቷል፡፡ የጥፋት ኃይሎች ተባብረውና ሙሉ ዝግጅት አድርገው በከፈቱት ጦርነት በትግራይ ሕዝብ፣ በትግራይ ሀብትና ንብረት፣ በቅርሶችና ታሪኮች በአጠቃላይ በትግራይ ክብር፣ ማንነትና ታሪክ ላይ ይቅር የማይባል ግፍና በደል አድርሰዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በኤርትራ ሠራዊትና በአማራ ታጣቂዎች ሥር የሚኖረው ሕዝባችን አስከፊ ሕይወት እየኖረ ነው፡፡ ተፈናቃይ ወገኖቻችን ያሉበትን ሁኔታ መግለጽ ከባድ ነው፡፡ በትግራይም ሆነ በመላው ዓለም የሚኖረው ሕዝባችን ፖለቲካ፣ ሃይማኖት፣ ፆታ፣ ዕድሜ፣ ሙያና የትምህርት ደረጃ ሳይገድበው ህልውናውን ለማስቀጠል ባካሄደው ታሪካዊ ትግልና ባሳየው የአይበገሬነት ጽናት፣ እንዲሁም በፈጸመው አስደናቂ ጀግንነት ሙሉ ለሙሉ ከመጥፋት ድኖ የጠላቶቻችን ፍላጎት እንዲከሽፍ አድርጓል፡፡ አንድነታችንን አጠናክረን ለአንድ ዓላማ በከፈልነው ክቡር መስዋዕትነት የታወጀብንን የጄኖሳይድ ጦርነት በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት እንዲገታ አድርገንና አፈሙዝ ዘቅዝቀን ትግላችን ሰላማዊና የፖለቲካ ትግል እንዲሆን አድርገናል፤›› በማለት ይገልጻል፡፡

የጦርነቱን አጀማመርም ሆነ የጦርነቱን ምንነት በተመለከተ የፌዴራል መንግሥት ከሚናገረው ፍጹም የሚቃረን አዲስ ዓይነት ትርጓሜ ይዞ የቀረበው ይህ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር መግለጫ የፕሪቶሪያውን ስምምነት ‘የጄኖሳይድ ጦርነቱን መግቻ’ ሲልም ጠርቶታል፡፡ ቀሪ የሰላም ስምምነቱ ቁልፍ የትግበራ ምዕራፎች ወደ መሬት እንዲወርዱ በሰላም እንደሚታገል የገለጸው ጊዜያዊ አስተዳደሩ፣ በኤርትራና በአማራ ኃይሎች እጅ ሥር ያሉ አካባቢዎች መመለስ ጉዳይን ቁልፍ ነጥብ እንደሆነ ያስቀምጣል፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት የፕሪቶሪያ ስምምነት አንደኛ ዓመትን በተመለከተ በሰጠው መግለጫ ግን፣ የሰላም ስምምነቱ ሙሉ ለሙሉ ላለመተግበሩ ዋናው ዳተኛ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር መሆኑን አመልክቷል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ለመተግበር ከሚጠበቅበት በላይ ስለመሄዱ የጠቀሰው የመንግሥት መግለጫ፣ ከጦርነቱ አነሳስ ጀምሮ እስከ ድኅረ ፕሪቶሪያ የታለፉ ጉዳዮችን በሰፊው ይዳስሳል፡፡ በእንግሊዝኛና በአማርኛ የተለያየ ይዘት ያለው መግለጫ ያወጣው መንግሥት፣ ጦርነቱ ሕወሓት ሰላምን ወደ ጎን በማለቱና ፍላጎቱን በኃይል ለማስፈጸም በመፈለጉ የፈነዳ ቀውስ እንደሆነ በግልጽ አስቀምጧል፡፡ መንግሥት ተገዶ ወደ ሕግ ማስከበርና የአገር ህልውና ወደ ማስጠበቅ ጦርነት ስለመግባቱ የሚያትተው ይህ መግለጫ፣ ጦርነቱን በፍፁም የበላይነት የመቋጨት ዕድል በእጁ እያለ ነገር ግን ለዘላቂ ሰላም አይበጅም በሚል ወደ ሰላም ፊቱን አዙሮ በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ጦርነቱ እንዲያበቃ ዕድል መስጠቱን ይገልጻል፡፡ ከስምምነቱ በኋላ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲዋቀር ከማገዝ በተጨማሪ ክልሉ መልሶ እንዲያገግም መንግሥት ያልተቆጠበ ጥረት ማድረጉን የሚያስረዳው መግለጫው፣ በእነዚህ ሒደቶች ሁሉ ከዚያኛው ወገን እንቅፋት ሲገጥመው መቆየቱን ነው የዘረዘረው፡፡

አጨቃጫቂ የወሰን አካባቢዎችን በሚመለከት በአማርኛው መግለጫ ላይ፣ ‹‹አከራካሪ የሚባሉ አካባቢዎችን በተመለከተ የፌዴራል መንግሥቱ አቋም ወስዶ ሠርቷል። የፌዴራል መንግሥት በዚህ ረገድ ያለው አቋም ዘላቂ ሰላምን የሚያረጋግጥ፣ ሁሉንም ወገን በሚጠቅም መንገድ፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትና ብልፅግናን በሚያረጋግጥ መንገድ መፍትሔ መሰጠት አለበት። ክረምት ደርሶ የእርሻ ሥራ ከመጀመሩ በፊት ተፈናቃዮች ወደ አካባቢያቸው እንዲመለሱ፣ የአካባቢ ነዋሪዎች በመረጧቸው አካላት እንዲተዳደሩ፣ በመጨረሻም ደረጃ በደረጃ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ሕዝበ ውሳኔ እንዲደረግ አቅጣጫ ተቀምጧል። ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል። እነዚህን ሁሉ አቋሞችና ተግባራት የኢትዮጵያ ሕዝብና ዓለም አቀፉም ማኅበረሰብ በሚገባ ያውቃል። ይህ ሁሉ ቢደረግም እንኳን በዚያኛው ወገን እግር የመጎተት አዝማሚያ ይታያል። ይህ ግን ዘላቂ ሰላምን፣ ብልፅግናንና የሕዝቦችን ኅብረ ብሔራዊ አንድነት አያረጋግጥም። የፌዴራል መንግሥት የፕሪቶሪያውን ስምምነት በተመለከተ ከሚጠበቅበት በላይ ተጉዟል፤›› በማለት ነው መግለጫው የችግሩን አፈታት ሒደት የዘረዘረው፡፡

በእንግሊዝኛ መግለጫው ላይ ይህን ቅደም ተከተል ከመድገም በተጨማሪ፣ በእነዚህ አወዛጋቢ ቦታዎች የፌዴራል መንግሥቱ የፀጥታ እንዲሁም የሕግ ማስከበር ሥራዎችን የመቆጣጠር ኃላፊነቱን እንደሚወስድም አክሎ ይገልጻል፡፡ የፌዴራል መንግሥቱ በሰላም ስምምነቱ መሠረት ብዙ ኃላፊነቶች የተሰጡት ቢሆንም እንኳ፣ በትግራይ ክልል ካለው ተጨባጭ ነባራዊ ሀቅ ጋር ሁኔታዎችን ለማዛመድ፣ እንዲሁም የግጭትና ውጥረት ከባቢ አየርን ለመግፈፍ ሲል ብዙ ርቀት ስለመሄዱ በእንግሊዝኛው መግለጫ ላይ አክሏል፡፡ የትግራይ ኃይሎችን ትጥቅ የማስፈታቱ መርሐ ግብር የጊዜ ሰሌዳ እንዲከለስ ከማድረግ ጀምሮ፣ ወደ ትግራይ ግዙፍ የጦር ኃይል እንዳይገባ እስከ ማድረግ ያሉ ዕርምጃዎችን የወሰደው ውጥረት ሊያባብስ ይችላል በሚል አመዛዛኝ ውሳኔ እንደሆነ መግለጫው ያብራራል፡፡ በአጠቃላይ የመንግሥት መግለጫ ለሰላም ስምምነቱ ሙሉ ለሙሉ ላለመተግበር ዳተኛው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ስለመሆኑ ነው በግልጽ ያስቀመጠው፡፡

የፌዴራል መንግሥትና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የፕሪቶሪያ ሰላም ስምምነት አንደኛ ዓመትን አንዱ ሌላውን ተጠያቂ በሚያደርጉ መግለጫዎች ነው አስበው ያለፉት፡፡ መንግሥት ለሰላም ስምምነቱ ሙሉ ለሙሉ አለመተግበር ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ውጪ ተጠያቂ ብሎ የጠቀሰው ሦስተኛ ወገን ባይኖርም የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር፣ አሜሪካ፣ የአውሮፓ ኅብረትና ሌሎች ይመለከተናል የሚሉ ወገኖች ከውጭም ከውስጥም የአማራ ታጣቂዎችና የኤርትራ ሠራዊት ያሏቸውን የሰላም ስምምነቱ አደናቃፊዎች እንደሆኑ ጠቃቅሰዋል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን መንግሥት የአጨቃጫቂ አካባቢዎችን ጉዳይ አፈታት በተመለከተ ያስቀመጠው አቅጣጫ፣ የፕሪቶሪያው ሰላም ስምምነት አተገባበር ሒደት የሚፈትን ከባድ ራስ ምታት እንደሆነ ነው ታዛቢዎች የሚገምቱት፡፡

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የሕግ ባለሙያ መንግሥት የያዘው አቋም ከምን እንደሚመነጭ እንደሚረዱ ይገልጻሉ፡፡ ‹‹እንግሊዝኛውም ሆነ አማርኛው የመንግሥት መግለጫዎች ተደራሹን ኅብረተሰብ በደንብ በመለየት በጥንቃቄ የተዘጋጁ ይመስላሉ፤›› የሚሉት የሕግ ባለሙያው፣ የተለያዩ ግምቶችን የመንግሥት መግለጫ ቢያስነሳም ነገር ግን ሁሉንም የጉዳይ ባለቤት የሆነ ወገን ማርካቱን እንደሚጠራጠሩ ተናግረዋል፡፡

አጨቃጫቂ ቦታዎች በሕዝበ ውሳኔ ይፈቱ የሚለው ጉዳይ በአማራም ሆነ በትግራይ ክልሎች በኩል ተቀባይነት ማግኘቱን እንደሚጠራጠሩ የሚናገሩት የሕግ ባለሙያው፣ የፌዴራል መንግሥት ሕገ መንግሥት ይከበር ከማለት ውጪ ምርጫ ማጣቱን እንደሚረዱ ያስረዳሉ፡፡ ‹‹የትግራይ ኃይሎች በቅድሚያ ቦታዎቹ ወደ ነበሩበት ይመለሱ ሲሉ ቆይተዋል፡፡ ወደኋላ ተመልሰን አካባቢዎቹ ለእኛ ተሰጥተው በትግራይ ክልል መደበኛ አስተዳደር ከተቋቋመ በኋላ ነው የሪፈረንደም ጥያቄ ለክልሉ ቀርቦ በተዋረድ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት መሄድና መፈጸም የሚችለው የሚል አቋም ያንፀባርቃሉ፡፡ ከአማራ ወገን ግን በአንዳንድ ጉዳዮች ለሕዝበ ውሳኔ የተመቸ አቋም ሲንፀባረቅ አያለሁ፡፡ በተለይ በራያና በጠለምት በመከላከያ የሚመራ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲዋቀር የሚል ፍላጎት ይታያል፡፡ ይህ ሒደት ተጀምሮ ነበር፡፡ ነገር ግን በትግራይ በኩል ፍላጎት ባለመታየቱ ቆሟል፡፡ ከእነዚህ ውጪ ያለው የወልቃይት ጉዳይ ግን የተለየ ይዘት ያለው ጥያቄ ነው ያለው፡፡ በወልቃይት ሕዝበ ውሳኔ ይካሄድ የሚለውን የአማራው ወገን በቀላሉ ይቀበለዋል ብዬ አልገምትም፤›› ይላሉ፡፡

የሕግ ባለሙያው ለዚህ አለመግባባት ዋና ምክንያት ይሆናል የሚለውን ሲናገሩ፣ የተፈናቃዮች መልሶ ማስፈር ጥያቄ ቁልፉ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ በዓለም አቀፍ የዕርዳታ ድርጅቶችና ሲቪክ ማኅበራት ጭምር የወልቃይት ሕዝብ ተብሎ የተገመተ አኃዝ መኖሩን፣ የኢትዮጵያ የሕዝብና የቤት ቆጠራ መረጃና እሱን ተመርኩዞ የሚሰጥ የሕዝብ ቁጥር ትንበያ መኖሩን ያመለከቱት የሕግ ባለሙያው፣ በትግራይ በኩል ከወልቃይት የተፈናቀለው መልሶ መሥፈር አለበት ተብሎ የሚቀርበው አኃዝ ግን ከእነዚህ ግምቶች ጋር ፍፁም የማይጣጣምና የተጋነነ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ ከተፈናቀሉ ዜጎች መልሶ የማስፈር ጉዳይ በተጨማሪ የወልቃይት ጥያቄ የሚመነጭበት ታሪካዊ መነሻ ጭምር፣ ጉዳዩን በሕዝበ ውሳኔ ዕልባት ለመስጠት ቀላል እንደማይሆን ነው የሕግ ባለሙያው የተናገሩት፡፡

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ በአማራና በወልቃይት ጉዳዮች ብዙ በመጻፍ የሚታወቁት የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ሙሉዓለም ገብረ መድኅን በበኩላቸው፣ ‹‹የአማራ ክልል አሁናዊ ቀውስ የሩቅ መነሻው የወልቃይት ጥያቄ ነው፤›› ይላሉ፡፡ የፕሪቶሪያው ሰላም ስምምነት በፈጠረው የኃይል አሠላለፍ ለውጥ የተነሳ የአማራ ክልል ጦርነት ውስጥ መውደቁንም ይናገራሉ፡፡  

‹‹የአማራ ክልልን ጦርነት ፌዴራል መንግሥቱ ቁልፍ የፋኖ መሪዎችን በመግደል ለዘብተኛ ከሚላቸው ኃይሎች ጋር በመደራደር እንደሚወጣው በማሰብ ጠንካራ ዘመቻ እያደረገ ቢሆንም እስካሁን ግን የመጣ ለውጥ የለም፡፡ ችግሩን በጦርነት አልፈታውም ወደሚል ድምዳሜ በመድረሱ ሊሆን ይችላል መንግሥት አሁን የትግራይና የአማራ ክልሎችን የሚያጨቃጭቅ ጉዳይን ማንሳት የፈለገው፤›› ሲሉ የመንግሥት አቋም ወደ ሕዝበ ውሳኔ መፍትሔ እንዴት እንደመጣ ምልከታቸውን አጋርተዋል፡፡  

‹‹በኢትዮጵያ በሕዝበ ውሳኔ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል የሰላም ሁኔታ የለም፡፡ ይህ የሰላም ሁኔታ በአጭር ጊዜ ይመጣል የሚል ግምትም የለኝም፤›› በማለት የሚናገሩት አቶ ሙሉዓለም፣ በሕገ መንግሥት ችግሩ እንደሚፈታ መቀመጡንም ቢሆን የማይሆን ሲሉ ነው የተቹት፡፡ ሕገ መንግሥቱ ስለክልሎች ወሰንና መሬት ያስቀመጠው አንዳችም ድንጋጌ በሌለበት ይህ ሊሆን እንደማይችል ገልጸዋል፡፡

‹‹ሕወሓት ከኢትዮጵያ ጂኦ ፖለቲካዊ ጥቅም አንፃር ሁመራን መርገጥ የለበትም፤›› የሚሉት አቶ ሙሉዓለም፣ ‹‹የፌዴራል መንግሥት ተለሳልሶልኛል በሚል ብቻ ለሕወሓት ወልቃይትን በሕገወጥ መንገድ ካስረከበ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሆን ብሎ ራሱ እንደፈቀደ ይቆጠራል፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ሕወሓት ሁመራን የረገጠ ቀን ነው ኢትዮጵያን ቻው ብሎ የራሱን አገር ለመፍጠር ጥረት የሚጀምረው፤›› ብለዋል፡፡

የወልቃይት ጉዳይ የሚቋጨው በምን መንገድ ነው ተብለው የተጠየቁት አቶ ሙሉዓለም፣ ‹‹በማን ቤት ማን ይወስናል? ለ30 ዓመታት በኃይል ተረግጠው ሲገዙ የነበሩ የወልቃይት ነዋሪዎች ባለፉት ሦስት ዓመታት በራሳቸው ልጆች መመራት ጀምረዋል፡፡ ሰላማዊ ትግል ሲያዳርግ የኖረው የወልቃይት የአማራ ማንነት ጉዳይ በልዩ የፖለቲካና የሕግ ውሳኔ ነው የሚቋጨው፡፡ አራት የከተማ አስተዳደርና አምስት ወረዳዎች ናቸው ወልቃይት ያሉት፡፡ በጀት አልበጅት ተብሎ ሕዝቡ በራሱ ብዙ የልማት ሥራዎችን እየሠራ ነው ያለው፡፡ በሰላም የሚኖሩ የትግራይና የሌሎች ተወላጆች አሉ፡፡ ሠርተው በሰላም ይኖራሉ፡፡ የትግራይ ፖለቲከኞች ግን አንድ ሚሊዮን የትግራይ ሕዝብ ከአካባቢው ተፈናቀለ እያሉ ነው ዓለምን ሊያደናግሩ የሚሞክሩት፣ ይህ ቅጥፈት ነው፡፡ ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የዘገቡት የአካባቢው ሕዝብ ከ480 ሺሕ የማይበልጥ መሆኑን የሚያመለክት ተጨባጭ ማስረጃ አለ፡፡ ብዙ ሕዝብ አስፍሮ በሕዝበ ውሳኔ ቦታውን ለመጠቅለል የሚሠሩት ብዙ አሻጥር አለ፤›› በማለት፣ የትግራይ ኃይሎችና ደጋፊዎቻቸው በሚሉት መንገድ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡   

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የአካባቢውን ሁኔታ፣ የሕዝብ አሰፋፈርና ሌላም መሠረታዊ ጉዳዮች ተመልክቶ በራሱ የሚፈታበት ሕጋዊ ሥልጣን እንዳለው የተናገሩት ተንታኙ፣ ይህ ለችግሩ መፍቻ አዋጪ መፍትሔ ስለመሆኑ ጠቁመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -