- የምን ደብዳቤ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- ከበላይ አካል የተወሰነ ነው።
- የምን ውሳኔ ነው?
- እስኪ ተመልከተው።
- እሺ… አዋከብኩዎት አይደል …. ምን? ምንድነው ክቡር ሚኒስትር? ከሥራ መሰናበትዎን ስለማሳወቅ ነው እኮ የሚለው፡፡
- እኔም ልክ እንደተነገረኝ በጣም ነው የተገረምኩት።
- ክቡር ሚኒስትር ምንድነው የተፈጠረው?
- አንተ አቅም ያለህ ባለሙያ በመሆንህ የትኛውም ቦታ ተቀጥረህ መሥራት የምትችል ነህ፣ የትኛውም ተቋም እጅህን ስሞ ነው የሚቀበልህ፣ ስለዚህ ብዙ ሊያሳስብህ አይገባም።
- ደብዳቤው እኮ የተባረርኩበትን ምክንያት አይገልጽም።
- ስለእሱ ብዙ ባትጨነቅ?
- እንዴት ክቡር ሚኒስትር? ስንት ዓመት ከሠራሁበት ተቋም በሁለት መስመር ደብዳቤ እንዴት በድንገት እባረራለሁ? ለዚያውም ምክንያቱ ሳይነገረኝ?
- ምክንያቱንማ ምን ብለው ይገልጹታል?
- እንዴት?
- የሚሆን ነገር አይደለማ… ያሳጣቸዋል።
- እና እርስዎም ምክንያቱን አያውቁትም ክቡር ሚኒስትር?
- እኔማ ምክያቱን በግልጽ ካልተነገረኝ ደብዳቤውን አልሰጥም በማለቴ ነግረውኛል።
- ምንድነው ምክንያቱ?
- ባለፈው ግምገማ ላይ በሰጠኸው አስተያየት ነው፣ በእርግጥ እኔም ምክንያቱ ይህ እንደሚሆን ጠርጥሬ ነበር።
- ለምን?
- ግምገማው ላይ የሰጠኸው አስተያየት ለችግሩ መንግሥትንና የመንግሥት ተቋማትን በቀጥታ ተጠያቂ ያደረገ ነው።
- እውነታው እንደዚያ ከሆነ ምን ማድረግ እችላለሁ ክቡር ሚኒስትር?
- ቢሆንም… ቢሆንም…
- በተጨማሪም መንግሥት በግልጽ እንድንነጋገር አቅጣጫ አስቀምጧል።
- ቢሆንም በዚያ ደረጃ በቀጥታ ትችትና ወቀሳ መሰንዘርህ ትክክል አይደለም።
- እና ምን ማድረግ ነበረብኝ ክቡር ሚኒስትር?
- ሐሳብህን በሥልት ማቅረብ ትችል ነበር።
- የምን ሥልት?
- ለምሳሌ የመንግሥት ተቋማትን ከፍተኛ አመራሮችን በቀጥታ ተጠያቂ ሳታደርግ ሐሳብህን ማቅረብ ትችል ነበር።
- ችግሩን መፍታት ያልተቻለው እኮ እነዚህ ተቋማት ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ባለመሆኑ ነው።
- ገብቶኛል።
- እና ኃላፊነታቸውን ባለመወጣታቸው መወቀስ የለባቸውም ክቡር ሚኒስትር?
- እንደዚያ ማለቴ አይደለም።
- እ…?
- ይህንኑ ሐሳብህን በሌላ መንገድ መግለጽ ትችል ነበር ማለቴ ነው።
- በሌላ መንገድ ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?
- መንግሥትንና ተቋማትን በጥቅሉ ከምተቸት ይልቅ በሌላ መንገድ መግለጽ ትችል ነበር።
- ለምሳሌ?
- ለምሳሌ አንዳንድ የመንግሥት ተቋማት ማለት ትችል ነበር።
- እህ…?
- እንዲያውም ከዚህ የተሻለ አገላለጽ መጠቀም ትችል ነበር።
- ቀደም ብለው ካነሱት ሌላ ማለት ነው?
- አዎ፣ በቀጥታ ተቋማቱን ከመተች ይልቅ በሌላ መንገድ መግለጽ ትችል ነበር።
- እንዴት?
- ድብቅ አጀንዳና ተልዕኮ ያላቸው አንዳንድ አካላት ማለት ትችል ነበር።
- እህ…?
- አንተ ግን ከዚያ አልፈህ ከፍተኛ አመራሩ ማዕድ ማጋራት ላይ ተጠምዷል ብለህ እኮ ነው ያፍረጠረጥከው?
- ቢሆንም አምኜበት ነው እንደዚያ የተናገርኩት ክቡር ሚኒስትር።
- ሊሆን ይችላል፣ ግን ደግሞ የበላይ አመራሩን እንደሚያስቆጣ ተረድተህ በሌላ መንገድ ብትገልጸው ይሻል ነበር።
- ቆይ ክቡር ሚኒስትር….
- እ….
- ዘርፉን የመከታተል ኃላፊነት የተጣለበት አካል ዋና ሥራውን ትቶ ትኩረቱን ማዕድ ማጋራት ላይ ማድረጉ መሠራታዊ ችግሩን ሊቀርፍ እንደማይችል አይታወቅም?
- ሐሳብህ እኮ ችግር የለበትም።
- ታዲያ?
- ይህንኑ ሐሳብህን በሌላ መንገድ መግለጽ ትችል ነበር እያልኩህ ነው።
- እንዴት አድርጌ?
- መጀመሪያ መንግሥት ምንም የማይወጣለት ፖሊሲና ስትራቴጂ ቀርጿል ብለህ በማወደስ ትነሳለህ።
- እሺ… ከዚያስ?
- ዘርፉን የሚከታተለው የበላይ አካል ግን ጉድለት አለበት ማለት ትችል ነበር።
- የምን ጉድለት ሲባልስ?
- መፍጠንና መፍጠር ላይ ጉድለት አለበት ብትል የተሻለ ይሆን ነበር።
- ያልኩት ይህንኑ ነው የሚያመለክተው።
- ይህንንማ አይደለም።
- መፍጠንና መፍጠር የሚል ቃል አልተጠቀምኩም እንጂ ያልኩት ይህንኑ ነው።
- እንዴት?
- አንድ ነገር ልጠይቅዎት ክቡር ሚኒስትር?
- እሺ፡፡
- አሁን የገጠመንን ችግር ማዕድ በማጋራት በዘላቂነት መፍታት ይቻላል ብለው ያምናሉ?
- አይቻልም።
- አመራሩ ማዕድ ማጋራት ላይ ተጠምዷል ስል ችግሩን በዘላቂነት የሚፈታ መፍትሔ ማፍለቅ ወይም መፍጠር አልቻለም ማለቴ ነው፣ በተጨማሪም…
- ምን?
- ማዕድ ማጋራት ችግሩን እያስታመመ ያቆየዋል፣ ይህ ደግሞ ከችግሩ ጋር አብሮ መዝለቅን እንጂ ፈጣን መፍትሔ አይደለም፣ በአጠቃላይ አመራሩ መፍጠርና መፍጠን አልቻለም ማለቴ ነበር።
- ቢሆንም….
- ቢሆንም ምን ክቡር ሚኒስትር?
- በዚህ መንገድ የተረዳህ ሰው ያለ አልመሰለኝም።
- እህ…
- ገባህ አይደል?
- አዎ ክቡር ሚኒስትር፣ መንግሥት መፍጠንና መፍጠር ይበል እንጂ የሚፈልገው ሌላ ነገር እንደሆነ ገብቶኛል።
- ምንድነው?
- ማጉረስና መወደስ!
- Advertisment -
- Advertisment -