- ከተገነቡ አጠቃላይ ቤቶች 75 በመቶ የሚሆኑት ከደረጃ በታች ናቸው ተብሏል
በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ዘርፍ ውስጥ ላሉ ባለሙያዎች የብቃት ምዘና እንደሚጀመር ተገለጸ፡፡
በዘርፉ ብቃት ሳይኖራቸው፣ አቅማቸው ሳይረጋገጥና ማረጋገጫ ሳያገኙ ራሳቸውን መሐንዲስ እያሉ የሚጠሩበትን አሠራር ያስቀራል የተባለለትና የባለሙያዎችን አቅም ለመገንባት የሚረዳ የማሠልጠኛ ማንዋልና የሚመዘኑበት መመርያ መዘጋጀቱን፣ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ደኤታ ወንድሙ ሴታ (ኢንጂነር) ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
በኮንስትራክሽን ዘርፍ ተመርቆ ወደ ሥራ የሚገባ አንድ ባለሙያ በሚሠራበት ተቋም ውስጥ በቆየ ቁጥር የሙያ ደረጃዎች ከመስጠት ባለፈ መመዘኛ ሥርዓት ባለመኖሩ፣ ባለሙያው ለሚጠበቅበት ዕውቀትና ክህሎት ብቁ ነው ወይ የሚለው እንደማይታወቅ ሚኒስትር ደኤታው አስረድተዋል፡፡
ለዚህም ይረዳ ዘንድ ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር እየተዘጋጀ ያለው መመርያ በቅርቡ ለፍትሕ ሚኒስቴር ተልኮ እንደሚፀድቅና ወደ ሥራ እንደሚገባ፣ መመርያው ባለሙያዎች የሚሠለጥኑበት፣ የሚገመገሙበትና ዕውቅና የሚያገኙበት ከመሆኑም በላይ፣ የሙያ ግድፈት ሲገኝባቸውም የሚቀጡበትን አሠራር ማካተቱን አስታውቀዋል፡፡
አገሪቱ አሁን ባለችበት የኮንስትራክሽን ቁመና የግንባታ ጥራት አደጋ ውስጥ ነው ያሉት ሚኒስትር ደኤታው፣ ሥራ ከተጀመረ በኋላም ሆነ ከመጀመሩ በፊት የሚታየው የጥራት መጓደል አሁን ካልተፈታ በቢሊዮን ዶላሮች የሚፈስበት ዘርፍ ተመልሶ የማይወጣበት ችግር ውስጥ ይገባል ብለዋል፡፡
በኮንስትራክሽን ዘርፍ የባለሙያ አቅምና የሙያ ሥነ ምግባር እየተሻሻለ ከመሄድ ይልቅ እየባሰበት መሄዱን የተናገሩት ወንድሙ (ኢንጂነር)፣ ባለሙያው ከአዳዲስ ዕውቀትና ቴክኖሎጂ ጋር የሚተዋወቅበትና ራሱን የሚያበቃበት ሳይሆን እያጠፋ የሚማርበት ሆኖ መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡
በኮንስትራክሽን ዘርፍ በመካከለኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ባለሙያዎች አለመኖራቸውን ገልጸው፣ ባለሙያዎቹ ወደ ሥራ ከገቡ በኋላ ብቃታቸው ሊያድግ የሚችለው በራሳቸው ጥረት እንጂ፣ ከዘርፉ በሚያገኙት ትምህርትና ተቋማዊ ዕውቀት አይደለም ብለዋል፡፡
አሳሳቢ እየሆነ መጣ በተባለው በኮንስትራክሽን ዘርፍ በአገር ውስጥ የበቁ የሚባሉትና ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች ወደ ሌሎች አገሮች እየተሰደዱ መሆናቸውን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፣ በተለይም በምሥራቅና በደቡብ አፍሪካ አገሮች ተፈላጊ መሆናቸውንና በአገር ውስጥ ያሉ ባለሙያዎችም ባሉበት ተቋም ለረዥም ጊዜ ረግተው እንደማይቆዩ ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም በገበያ ውስጥ የዋጋ ጭማሪን በየጊዜው መተንበይ በማይቻልበት ሁኔታ የግንባታ መሣሪያዎች ዋጋ አልቀመስ ማለቱንም አስረድተዋል፡፡
ሜጋ (ግዙፍ) ፕሮጀክቶች አብዛኞቹ የውጭ ኮንትራክተሮች ብቻ የሚይዟቸው፣ የአገር ውስጥ ባለሙያዎች የውጭ ኮንትራክተሮች በሚይዟቸው ፕሮጀክት ውስጥ ገብተው ዕውቀት እንዲቀስሙ የሚያደርግ አሠራር አለመዘርጋቱ፣ የዘርፉ ሌላው ተግዳሮት መሆኑን ሚኒስትር ደኤታው አብራርተዋል፡፡
በተጨማሪም በኮንስትራክሽን ዘርፍ የግዥ ሥርዓትን ጠንቅቆ የሚያውቅ ባለሙያ አለመኖሩን፣ ሁሉም ባወቀውና በገባው ልክ እንጂ በትክክል ሥራውን ተገንዝቦ የሚሠራ የለም ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ በኮንትራት አስተዳደር የተሰማሩ ባለሙያዎች በአንድ ጉዳይ ባለመግባባታቸው ምክንያት ክስ ሲመጣ ተመልሶ ውልን ከመቃኘት ውጪ፣ ከጅምሩ የኮንትራት ውል አስተዳደርን ዝርዝር ጉዳይ ተረድቶ የሚያስረዳ ባለሙያ አለመኖሩን ገልጸዋል፡፡
ለኮንስትራክሽን ጥራት መጓደል በግዥ ሥርዓቱ ላይ ያለው አሠራር፣ የፕሮጀክቶች ዲዛይን የተሟላና የተደራጀ አለመሆን፣ የራሳቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ያብራሩት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ወደ አፈጻጸም ሲገባ ባሉት ኮንትራክተሮችና አማካሪዎች የአቅም ውስንነት የተነሳ የሚታሰበውን ጥራት ለማረጋገጥ አዳጋች ሆኗል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የግንባታ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከመሬት ልየታ ጀምሮ ሕንፃው ተገንብቶ እስኪጠናቀቅ ድረስ መሟላት ያለባቸው ዓለም አቀፍ መሥፈርቶች፣ አጠቃላይ ይዘትና ቁመናው ምን መምሰል እንዳለበት የተቀመጡ ስታንዳርዶች አለመኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡
ከዚህ አኳያ በኢትዮጵያ ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ ያሉ የመኖሪያ ቤቶች ሲገመገሙ፣ የመኖሪያ ቤት ለመባል የተሟላ ቁመና ያላቸው ከ25 በመቶ የማይበልጡ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ 75 በመቶ ያህሉ ከደረጃ በታች ናቸው ብለዋል፡፡
ለቤቶቹ ጥራት መጓደል ምክንያት ከመጀመሪያው የግንባታ ዕቅድ ጀምሮ ግንባታ እስከሚጠናቀቅ ድረስ፣ መሟላት ባለባቸው ዓለም አቀፍ መሥፈርቶች የተቃኙ አለመሆናቸው ነው ብለዋል፡፡
ይሁን እንጂ ከዚህ በኋላ በሚገነቡ ቤቶች ለሰው መኖሪያ ለመባል የሚያስችሉ ዓለም አቀፍ መሥፈርቶችን ባሟላ መንገድ እንዲሆን፣ የሕግ ማዕቀፍና ስታንዳርድ እንደሚዘጋጅ ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ አሠራር ግን ማንኛውም የሥራ ተቋራጭ ውል ገብቶ ግንባታ ከጀመረ በኋላ፣ በጥራትና በጊዜው ያጠናቅ ወይም አያጠናቅ መቆጣጠር የሚያስችል ሥርዓት የለም ብለዋል፡፡