Tuesday, November 28, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

በአገር ሰላም ላይ የተጋረጠው የጥፋት ጭጋግ ይገፈፍ!

ዓለም በሩሲያና በዩክሬን፣ በእስራኤልና በሐማስ አደገኛ ጦርነቶች፣ እንዲሁም በኮሪያ ልሳነ ምድር ውጥረትና በተለያዩ አካባቢዎች በሚቀሰቀሱ ግጭቶች፣ በተፈጥሮና በሰው ሠራሽ አደጋዎችና በተለያዩ ችግሮች ተቀስፋ ተይዛለች፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥም በትግራይ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያና በተለያዩ ሥፍራዎች ከፍተኛ ውጥረት ነው ያለው፡፡ የኢትዮጵያ ሰላም ደፍርሶ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ያለቁበት የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ለጊዜውም ቢሆን በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ጋብ ቢልም፣ በአማራ ክልል የቀጠለው ውጊያና በተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋሉ የሰላም ዕጦቶች ከተስፋ ይልቅ ሥጋት እያበራከቱ ነው፡፡ በመካከለኛው ምሥራቅ የተቀሰቀሰው የእስራኤልና የሐማስ ጦርነት ለአፍሪካ ቀንድ ጭምር ጦስ ይዞ ሊመጣ ይችላል ተብሎ ሥጋት ሲፈጠር፣ መንግሥት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተዳፍኖ የቆየውን የባህር በር ጥያቄ እንደገና ማንሳቱ ተጨማሪ ቀውስ ሊያመጣ እንደሚችል በጂኦ ፖለቲክስ ተንታኞች የሚቀርቡ ጽሑፎችና ትንታኔዎች ብዙ እየተባለ ነው፡፡ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤትም ኢትዮጵያና ኤርትራ ከግጭት ቀስቃሽ ድርጊቶች እንዲቆጠቡ ማሳሰቢያ መስጠቱ አይዘነጋም፡፡ የብዙዎች ሥጋት ጦርነት እንዳይነሳ ነው፡፡

በኢትዮጵያ በኩል ከጎረቤት አገሮች ጋር በሰጥቶ መቀበል መርህ የባህር በርን በጋራ የመጠቀም ፍላጎት እንዳለ በተደጋጋሚ መነገሩ መልካም ነው፡፡ ነገር ግን አገርን ለመጥቀም በሚል ሽፋን በአንዳንድ ወገኖች ከጎረቤት አገሮች ጋር ሊያጋጭ የሚችል የሚስተጋባ ፕሮፓጋንዳ መክሸፍ ይኖርበታል፡፡ በተጨማሪም ሰሞኑን መንግሥት ከኦነግ ሸኔ (የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ከሚባለው አካል) ጋር በታንዛኒያ ዳሬ ሰላም ከተማ የሰላም ድርድር መጀመሩ ይፋዊ ካልሆኑ ምንጮች ተሰምቷል፡፡ ለዚህ ድርድር እንደ አሜሪካ፣ ኬንያና ኖርዌይ የመሳሰሉ አገሮችና ኢጋድ አመቻች መሆናቸውም እንዲሁ፡፡ ለሰላም ሲባል የሚደረግ ማንኛውም ንግግር ሆነ ድርድር ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን መንግሥት በቀጥታ ለሕዝብ መንገር ሲገባው ከሦስተኛ ወገኖች መረጃው ሲሰማ ከማስገረም አልፎ ግራ ያጋባል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ሰላማዊ ድርድር በአማራ ክልል የትጥቅ ትግል እያደረገ ካለው ኃይል ጋርም ቢደረግ መልካም ነው፡፡ ለሰላም የሚደረገው ጥረት ሁሉንም ወገኖች አሳታፊና አካታች ሲሆን፣ በአገር ላይ የሚያንዣብበው የሥጋት ደመና በአስተማማኝ ሁኔታ ይገፈፋል፡፡

በዚህ ዘመን ኢትዮጵያ ውስጥ አላባራ ያለ ግጭት በየቦታው ሲንሰራፋ፣ የአገር ጉዳይ የሚመለከታቸው በሙሉ መላ መፈለግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ ፖለቲከኞች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች መሪዎች፣ ምሁራንና የተለያዩ አደረጃጀቶችን የሚወክሉ በሙሉ ከኢትዮጵያ ምድር ሊላቀቅ ያልቻለው ግጭት መንስዔዎችና መፍትሔዎች ላይ በስፋትና በጥልቀት መነጋገር አለባቸው፡፡ በአገራዊ የምክክር ኮሚሽን እየተደረገ ካለው ዝግጅት ጎን ለጎን፣ ሁሉም አለመግባባቶችና ግጭቶች በፍጥነት ቆመው ለንግግርና ለድርድር ምቹ መደላድል መፈጠር ይኖርበታል፡፡ በመንግሥት በኩል ደግሞ ሕግና ሥርዓትን ከማስከበር በተጨማሪ፣ ከታች እስከ ላይ ባለው መዋቅሩ ውስጥ የሚስተዋሉትን ንቅዘቶችና ዝንፈቶች መመርመር ይጠበቅበታል፡፡ የመንግሥትና የፓርቲ ኃላፊነትን ለማይገቡ ፍላጎቶች በማዋል፣ የአገርን ጤና የሚነሱ ግለሰቦችና ስብስቦች አደብ መግዛት አለባቸው፡፡ መንግሥት ውስጡን ሳያፀዳና ለሕግና ለሥርዓት መከበር ብቁ ቁመና ሳይኖረው፣ ለሰላማዊ ንግግርም ሆነ ለድርድር ዝግጁ ሆኖ መቅረብ አይችልም፡፡ ውስጡን አጥርቶና ተስተካክሎ ሲቀርብ ግን ሰላም ለማስፈን አይቸገርም፡፡

የተለያዩ ርዕዮተ ዓለሞችን በመያዝ ለሚፈልጉት ማኅበራዊ መሠረት ጥቅም ለመታገል የተመሠረቱ የፖለቲካ ድርጅቶችና መሪዎቻቸው፣ ከፓርቲ ዓላማና ፍላጎት በላይ አገር መኖሯን ይገንዘቡ፡፡ በየትም አገር ብሔራዊ ደኅንነትና ጥቅም ከፓርቲ ፍላጎት በታች ሆኖ እንደማያውቅ በመገንዘብ፣ ለአገር ሰላምና ለሕዝብ ደኅንነት ሲሉ ከአላስፈላጊ ድርጊቶች ይታቀቡ፡፡ ኢትዮጵያ ከቅርብም ሆነ ከሩቅ የሚነሱ ታሪካዊ ጠላቶች ያሏት አገር መሆኗን ለአፍታም ባለመዘንጋት፣ እጅግ አስመራሪና እልህ አስጨራሽ ቢሆንም ለሰላማዊ ፉክክር ዕድል እንደሚሰጡ በተግባር ያሳዩ፡፡ በጭካኔ፣ በቂም፣ በበቀል፣ በክፋትና በሥልጣን ጥማት በሚታመሰው የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ ብልጠትንና ጥበብን ምርኩዝ በማድረግ ብቃትን ማሳየት ተገቢ ነው፡፡ ገዥውን ፓርቲም ሆነ የሚመራውን መንግሥት መገዳደር የሚቻለው ከበፊት ጀምሮ በሚታወቀው አሰልቺ ሥልት አይደለም፡፡ ይልቁንም የሐሳብ ጥራትና የበላይነት ይዞ ተፎካካሪ በመሆን የሕዝብን ልብ ለመማረክ መትጋት ይለመድ፡፡ ጉልበተኝነትና ሕገወጥነት የሚሸነፉት በሐሳብ ጥራትና ልዕልና እንደሆነ ይታወቅ፡፡ ሕዝብ ምን ዓይነት ጠቃሚ ነገሮችን ይዛችሁ መጣችሁ እንጂ፣ ምን ዓይነት ጉልበት አላችሁ ብሎ በህልውናው ላይ አይቆምርም፡፡

ከኢትዮጵያ ሰላም ማጣት የመጀመሪያዎቹ ተጠቃሚዎች በዓባይ ወንዝ ምክንያት መቆሚያ መቀመጫ የሚያሳጡ ሲሆኑ፣ ቀጥሎ ደግሞ በዝርፊያ ንፋስ አመጣሽ ሀብት የሚያካብቱ ሕገወጦች ናቸው፡፡ ሰላም ሲጠፋ ተጠያቂነትና ኃላፊነት ስለማይኖሩ ሕገወጦች አገር እየዘረፉ ለታሪካዊ ጠላቶች መግቢያ ቀዳዳ ያመቻቻሉ፡፡ የመንግሥት መዋቅር ውስጥ ሆነው ሥልጣናቸው ላይ ተዘፍዝፈው መቆየት የሚፈልጉም፣ ሰላም ካለ መገምገምና መጠየቅ ስለሚኖር ግጭት ማባባስና ትርምስ መፍጠር የዘወትር ተግባራቸው ይሆናል፡፡ ይህም ችግር በፌዴራልም ሆነ በክልል ብሔራዊ መንግሥታት ጭምር በግልጽ የሚስተዋል ነው፡፡ ኃላፊነትን በሕጉ መሠረት ካለመወጣት ጀምሮ የመንግሥት በጀትና ንብረት የዝርፊያ ማዕድ ማድረግ፣ ብልሹ አሠራሮችን በማስፋፋት ተገልጋዮችን ማስመረር፣ ጉቦና ምልጃን እንደ መደበኛ ሥራ ክፍያ መቁጠር፣ ፍትሕን በገንዘብ መሸቀጥ፣ ዜጎችን በብሔርና በሃይማኖት ትስስር መከፋፈል፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን መደፍጠጥና የመሳሰሉ እኩይ ድርጊቶችን በመፈጸም የአገር ሰላምን ማወክ የተለመደ ሆኗል፡፡ በአንዳንድ ቦታዎች ሕገወጥነት መብት እስኪመስል ድረስ የሚፈጸሙ ወንጀሎች የሰላም ዕጦቱን እያባባሱ ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ ምድር ለዘላቂ ሰላም መስፈን የሚረዱ በጣም በርካታ ጠቃሚ ነገሮች አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል ዋናው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘመናት ያካበታቸው የጋራ ማኅበራዊ እሴቶች ናቸው፡፡ ከእሴቶቹ ውስጥ ተጠቃሽ የሚባለው ደግሞ ችግር ሲያጋጥም ሥርዓት ባለው መንገድ መፍታት መቻል ነው፡፡ ለዚህ እንደ ምሳሌ የሚቀርበው በሁሉም ክልሎች ተግባራዊ የሚደረገው ባህላዊ የዕርቅና የሽምግልና ሥርዓት ተጠቃሽ ነው፡፡ በተደጋጋሚ ለማስታወስ ጥረት እንደተደረገው እንዲህ ዓይነቱ አኩሪ ባህላዊ ሥርዓት፣ የሟችና የገዳይ ቤተሰቦችን አገናኝቶ ከማስታረቅ ባለፈ በጋብቻ እስከ ማስተሳሰር ድረስ ትልቅ ሥራ የሚከናወንበት ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ይህንን የመሰለ ተምሳሌታዊ እሴት ይዘው በማይረቡ ጉዳዮች ጭምር፣ በተደጋጋሚ እርስ በርስ ሲፋጁና ንብረት ሲያወድሙ ማየት ያስተዛዝባል፡፡ ኢትዮጵያ በግጭት ቀጣናነት ቀይ መስመር ከሚሰመርባቸው አደገኛ አገሮች ዝርዝር ውስጥ ስትመዘገብ፣ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች ዝምታ በእጅጉ ያሳስባል፡፡ መንግሥትም ሆነ የአገር ጉዳይ የሚመለከታቸው በሙሉ ቅድሚያ ለአገር ሰላም ይስጡ፡፡ በአገር ሰላም ላይ የተጋረጠው የጥፋት ጭጋግ እንዲገፈፍ የድርሻቸውን ኃላፊነት ይወጡ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ ሲኒመር ትሬዲንግ...

የባህር በር በቀጣናዊ ተዛምዶ ውስጥ

በበቀለ ሹሜ መግቢያ በ2010 ዓ.ም. መጋቢት ማለቂያን ይዞ ዓብይ አህመድ በጠቅላይ...

ሥጋት ያስቀራል ተብሎ የሚታሰበው የጫኝና አውራጅ መመርያ

በአዲስ አበባ ከተማ በሕገወጥ መልኩ በመደራጀት ማኅበረሰቡ ላይ እንግልትና...

ማወቅ ወይስ አለማወቅ – ድፍረት ወይስ ፍርኃት?

በአሰፋ አደፍርስ ወገኖቼ ፈርተንም ደፍረንም የትም አንደርስምና ለአገራችን ሰላምና ክብር...

ከድህነት ወለል በታች ከሆኑት አፍሪካዊያን ውስጥ 36 በመቶው በኢትዮጵያ ናይጄሪያና ኮንጎ እንደሚገኙ ተጠቆመ

‹‹ለሺሕ ዓመት በድህነት ውስጥ የነበረች አገርን በአሥር ዓመት ልንቀይር...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሔ ይፈለግላቸው!

መንግሥት ከኦነግ ሸኔ ጋር በታንዛኒያ ዳሬሰላም ከተማ ሲያካሂድ የነበረው ንግግር ያለ ውጤት መጠናቀቁን ካስታወቀ በኋላ፣ በኦሮሚያ ክልልም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ሰላም ለማስፈን የነበረው ተስፋ...

ኢትዮጵያን ከግጭት ቀጣናነት ማላቀቅ የግድ ነው!

ፍሬ አልባ ፖለቲካዊ ልዩነቶች ወደ ግጭት እያመሩ ለአገርና ለሕዝብ የማያባራ መከራ ሲያቀባብሉ፣ ከትናንት ስህተቶች ለመማር ፈቃደኛ ያልሆኑ ፖለቲከኞችና ተከታዮቻቸው በእሳት ላይ ቤንዚን እያርከፈከፉ ጠማማ...

አስጨናቂውን የኑሮ ውድነት የማርገብ ኃላፊነት የመንግሥት ነው!

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ማክሰኞ ኅዳር 4 ቀን 2016 ዓ.ም. ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ካቀረቡላቸው ጥያቄዎች መካከል አንደኛው የኑሮ ውድነትን በተመለከተ ነበር፡፡...