Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ብሔራዊ ባንክ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎትን ሊያግዙ የሚችሉ ወጥ የሆኑ ሕጎች ያስፈልጉታል›› አቶ ኑሪ ሁሴን፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት (ከወለድ ነፃ ባንክ ዘርፍ)

በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ኢትዮጵያ ውስጥ ለማስጀመር ብርቱ ትግል ተካሂዷል፡፡ ከብዙ ጥረት በኋላ አገልግሎት በመስኮት ደረጃ እንዲሰጥ ተወስኖ፣ ከዚያም ከለውጡ ወዲህ ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነፃ ባንክ እስከ ማቋቋም የሚያስችል ሕግ ወጥቶ ለዓመታት ሲቀርብ የነበረው ጥያቄ ምላሽ ማግኘቱ ይነገራል፡፡ በዚህ መሠረት 20 ያህል ባንኮች ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎትን በመስኮትና ራሱን በቻለ ቅርንጫፍ በመክፈት እየሠሩ ነው፡፡ ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሚሰጡ አራት ባንኮች ተመሥርተዋል፡፡ እነዚህና አገልግሎቱን በመስኮት የሚሰጡ ባንኮች አሁን ከወለድ ነፃ ያሰባሰቡት ተቀማጭ ገንዘብ መጠን ከ200 ቢሊዮን ብር በላይ መሻገሩ ታውቋል፡፡ በአንፃሩ ያሰባሰቡትን ያህል ብድር እየሰጡ አይደለም፡፡ ለምሳሌ ከተሰባሰበው ጠቅላላ ተቀማጭ ግማሽ ያህሉ ወይም አንድ መቶ ቢሊዮን ብር የሚሆነው የተሰባሰበው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ‹‹ሲቢኢ ኑር›› በኩል ነው፡፡ ባንኩ እስከ ጥቅምት 2016 ዓ.ም. አጋማሽ መጨረሻ ድረስ ያበደረው 25 በመቶ ያህል ብቻ ነው፡፡ እንዲህ ያሉ ጉዳዮች ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ያስፈልጋል የተባለውን ያህል፣ በተግባር ግን በታሰበው ደረጃ አልተራመደም የሚል አስተያየት እንዲሰነዘር እያደረጉ ነው፡፡ ይህ ለመሆኑ ብዙ ምክንያቶች የሚጠቀሱ ሲሆን፣ በዋናነት ግን ዘርፉን በአግባቡ ለማራመድ የሚያስችሉ ሕጎች በብሔራዊ ባንክ አለመውጣታቸው ነው ይባላል፡፡ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉ በርካታ የአገልግሎት ዓይነቶች ቢኖሩም፣ ብሔራዊ ባንክ ይህንን ፍላጎት ያገናዘበ ሕግ ባለማውጣቱ አገልግሎቱ በውስን ዘርፎች ላይ ብቻ እንዲሆን ወስኖታል የሚለው አመለካከትም ጎልቶ እየወጣ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት እንዴት ከማዕከላዊ ባንክ ጀምሮ ታች ድረስ መዋቀር እንደሚኖርበት በግልጽ የተቀመጠ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ይህ አለመኖሩ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ በሌላ በኩል ስለአገልግሎቱ ያለው ግንዛቤ አነስተኛ መሆን፣ ራሱን የቻለ የሸሪዓ አማካሪና የሱፐርቪዥን አካል በብሔራዊ ባንክ ውስጥ አለመደራጀቱ የሚጠቀሱ ተግዳሮቶች ናቸው፡፡ ይህም በአገር ደረጃ ከዘርፉ ሊገኝ የሚችለውን ጥቅም እንዳሳጣ የሚገልጹም አሉ፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት (ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ዘርፍ) አቶ ኑሪ ሁሴን፣ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎቶች ውስጥ አሉ የተባሉ ችግሮችን በአብዛኛው ከሚጋሩ የዘርፉ ባለሙያዎች መካከል አንዱ ናቸው፡፡ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ላለበት ደረጃ መድረስ ከሚጠቀሱ ጥቂት ባለሙያዎች መካከልም ናቸው፡፡ ከወለድ ነፃ ባንክ አጠቃላይ አገልግሎትና ተግዳሮቶች፣ እንዲሁም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ራሱን የቻለ ከወለድ ነፃ የሆነ መንግሥታዊ ባንክ መቋቋም አለበት በሚል ጥያቄና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ዳዊት ታዬ አቶ ኑሪን አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ኢትዮጵያ ውስጥ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል? በአጠቃላይ እንቅስቃሴው ምን ይመስላል? ከየት ተነስቶ የት ደረሰ ማለት ይቻላል?

አቶ ኑሪ፡- አገልግሎቱ መሰጠት ከጀመረ ከአሥር ዓመታት በላይ ሆኖታል፡፡ ከዚህ በፊትም በርካታ ፍላጎቶች ነበሩ፡፡ የወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ሕግ ባልነበረበት ጊዜሱ የደንበኞቻቸውን ፍላጎት ለማሟላት ወለድ የሌለው ሒሳብ በመክፈት እንዲስተናገዱ ይደረግ ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ ላስቀመጡት ተቀማጭ ገንዘብ ወለድ ሲታሰብላቸው ይህንን አስወግዱልኝ የሚሉ ነበሩ፡፡ አካውንታቸው ውስጥ የገባውን ወለድ ‹‹የእኔ አይደለም አስወግዱልኝ›› ሲሉ ወደ ተለያዩ ሒሳቦች ተቀንሶ ይላክ እንደነበር ይታወቃል፡፡ እንዲህ ያለው ነገር ለሥራውም ቢሆን አመቺ አልነበረም፡፡ በተለይ በሕግ የተደገፈ አልነበረም፡፡ የባንክ አዋጅ ሲሻሻል ይህ አገልግሎት ተካተተ፣ ከወለድ ነፃ መቆጠብ ተፈቀደ፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ በብዙ ግፊትና ጥረት ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በመስኮት መስጠት ተጀመረ፡፡ ቆየት ብሎ ከለውጡ በኋላ ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ ባንክ ማቋቋም እንደሚቻል ተፈቀደ፡፡ በዚሁ መሠረት እየተሠራ ነው፡፡ ነገር ግን ጥያቄው ለዘመናት ሲቀርብ የነበረ ነው፡፡ ‹‹በእምነታችን ምክንያት ባንክ መጠቀም አልቻልንም፣ በወለድ መሥራት አንፈልግም›› የሚል ግፊት መንግሥት ላይ ስለበዛ በመስኮት የተጀመረው አገልግሎት አሁን ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት መስጠት የሚቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ ነገር ግን እዚህ የተደረሰው በብዙ ትግል ነው፡፡ የሠለጠነ የሰው ኃይል ባልነበረበት ሁኔታ የተጀመረ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር በቂ የሕግ ማዕቀፍ አልነበረም፡፡ ምክንያቱም ዘርዘር ያሉ ሕጎች ያስፈልጉ ነበር፡፡ እያንዳንዳቸው አገልግሎቶች የተለያዩ ባህሪ ያላቸው በመሆናቸው፣ ከእነ ባህሪያቸው ዘርዘር ያለ ሕግ ማውጣት ያስፈልግ ነበር፣ ይህ አልነበረም፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ በብሔራዊ ባንክ ቅንነት ማጣት ሳይሆን የዕውቀት ችግር እንደነበር ይሰማኛል፡፡ ነገር ግን ለአገልግሎቱ ያስፈልጋሉ የተባሉ የተወሰኑ ጥረቶች ለማድረግ ይቻል ነበር፡፡ ፍላጎቱ ያላቸው ድጋፍ መስጠት የሚችሉ ተቋማት የነበሩ ቢሆንም ይህ ሳይደረግ ቆይቷል፡፡

ሪፖርተር፡- አገልግሎቱ በተጀመረበት አካባቢ ብዙም ግንዛቤ ካለመኖሩም በላይ፣ በዘርፉ የሠለጠኑ ባለሙያዎች አልነበሩም ሲባል ነበርና ድጋፍ ሊሰጡ ይችሉ የነበሩት እነማን ናቸው?

አቶ ኑሪ፡- ለምሳሌ በዓለም ባንክ በኩል ድጋፍ ለመስጠት ፍላጎት ነበር፡፡ በዩኤስኤአይዲ በኩልም ድጋፍ የመስጠት ፍላጎት ነበር፡፡ ምክንያቱም የፋይናንስ አካታችነት በተለይ በዓለም ላይ በወቅቱ ጎልቶ እየመጣ ስለነበር፣ አካታችነትን ከመፍጠር አኳያ ድጋፍ ለመስጠት ዓለም አቀፋዊ ተቋማት ፍላጎት ስለነበራቸው ነው፡፡ በአገር ውስጥም የተወሰኑ ኤክስፐርቶች ነበሩ፡፡ እነዚህን በመጠቀም ይህንን ጥያቄ መመለስ ይቻል ነበር፣ ያንን ማድረግ አልተቻለም፡፡ በዚህ ሒደት ደግሞ የፖለቲካ አለመረጋጋቱም የተወሰነ ተፅዕኖ ነበረው፡፡ ከወለድ ነፃ ባንክ ላይ ተረጋግተው እንዳይሠሩ አድርጓል፡፡ የዋጋ ንረቱም ለጉዳዩ ትኩረት እንዳይሰጠው አድርጓል ማለት ይቻላል፡፡ በሒደቱ ውስጥ የተከሰቱ እንደ ኮሮና ወረርሽኝ ያሉ ያልታሰቡ ክስተቶች ሳይቀሩ አገልግሎቱ በፍጥነት እንዳይመጣ አድርገውታል፡፡ የኢትዮጵያ የንግድ ባንክ ከወለድ ነፃ አገልግሎት በመጀመር ቀዳሚ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ነው አገልግሎቱ ትኩረት አግኝቶ ሌሎች ባንኮችም መከተል የጀመሩት፡፡ ከእኛ ቀጥሎ ሥራ የጀመረው ኦሮሚያ ባንክ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እኔ ባለኝ መረጃ ግን ከእናንተ ቀደም ብሎ ከወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎት በመስኮት ደረጃ መስጠት የጀመረው ኦሮሚያ ባንክ መሆኑን ነው፡፡

አቶ ኑሪ፡- መንግሥት አገልግሎቱ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል እንዲጀምር ፍላጎት ስለነበረው ቀድሞ የጀመረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው፡፡ የመንግሥት ባንኮችን የማስቀደም ፍላጎት ነበር፡፡ በዋናነት ከፕሮሲጀርና ከተለያዩ የዶክመንቴሽን ዝግጅት አንፃር ግን ኦሮሚያ ባንክ ይቀድም ነበር፣ ይህ ምንም ጥያቄ የለውም፡፡ ነገር ግን አንድ ላይ ለመጀመር በመንግሥት በኩል ፍላጎ ስለነበር ያ የተወሰነ መዘግየትን ፈጥሯል፡፡ ዞሮ ዞሮ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተደራጀና በተያያዥ ነገሮች በጣም ሰፊ ቅርበት ስለነበረውና ከሀብት አንፃርም በፍጥነት ለመሄድ ይችል ስለነበር፣ ቀድሞ ጀምሯል ማለት ይቻላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የንግድ ባንክን ወደ እዚህ አገልግሎት ቀድሞ መግባት ሁሉም ባንኮች ይፈልጉ ነበር፡፡  

ሪፖርተር፡- ለምን? ሌሎች ባንኮች ይህንን አገልግሎት ከጀመሩ በኋላስ የአገልግሎት አሰጣጡ  ምን ይመስል ነበር?

አቶ ኑሪ፡- ምክንያቱም የመንግሥት ባንክ ያልጀመረውን ሥራ ሌሎች ባንኮች በቀላሉ ይወጡታል ተብሎ ስለማይታሰብ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ከዓመት ዓመት ለውጥ እየታየ መጥቷል፡፡ ነገር ግን እስከ 2018 ዓ.ም. ድረስ የነበረው አፈጻጸም በጣም ዘገምተኛ ነበር፡፡ ይህ በሁሉም ባንኮች ላይ የታየ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አገልግሎቱ በተጀመረበት የመጀመሪያ ዓመታት የባንኮች ጉዞ በተፈለገው መጠን  አለመንቀሳቀሱና አዝጋሚ የሆነው ለምንድነው? አገልግሎቱ አዲስ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ነው? ወይስ ሌላ ችግር ነበር?

አቶ ኑሪ፡- አገልግሎቱ አዲስ ከመሆኑ አንፃር ነው የሚለው አንድ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ ግን እሱ ብቻ ሳይሆን የተለያዩ ፈተናዎችም ነበሩ፡፡ ያኔ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በተጀመረባቸው የመጀመሪያዎቹ ዓመታት የነበረው ፖለቲካ ትርምስም በተለያዩ አካባቢዎች ተንቀሳቅሶ አገልግሎቱን በቀላሉ ለማስተዋወቅ ከባድ ነበር፡፡ የግንዛቤ መጠኑም በጣም ዝቅተኛ ነበር፣ ከፍተኛ ጥርጣሬም ነበር፡፡ በመንግሥት በኩል የተወሰኑ ሥጋቶች ነበሩ፡፡ እውነት ለመናገር በተስፋና በሥጋት መካከል ሆነን ነው ሥራውን የጀመርነው፡፡ ለዘመናት ይህንን ጥያቄ ሲጠይቅ የነበረው ማኀበረሰብ መልስ አግኝቷል ብለን ተስፋ አድርገናል፡፡ ማኅበረሰቡ ተገልሎ ስለነበር አገልግሎቱ እንዲሰጥ መፈቀዱ ትልቅ ተስፋ ነበር፡፡ እነዚህ ማኅበረሰቦች በአገራቸው ኢኮኖሚ ውስጥ የበለጠ ለመሳተፍ ዕድሉ ተፈጥሮላቸዋል በሚል ዕድሉን በአግባቡ ለመጠቀም የተነሳንበት ወቅት ነበር፡፡ ከሥጋት አንፃር ደግሞ በወቅቱ የሠለጠነ የሰው ኃይል አለመኖር፣ ይህ አገልግሎት እጃችን ላይ ይወድቅ ይሆን ወይ? ኢኮኖሚውንም ይጥልብን ይሆን ወይ? የአደጋ ተጋላጭነት ይዞ ይመጣ ይሆን? በሚል በጣም ትልልቅ ሥጋቶች ነበሩብንና በሥጋትና በተስፋ መካከል ሆነን ነው ሥራውን የጀመርነው፡፡ በወቅቱ ለዚህ አገልግሎት የሚሆኑ ባለሙያዎችን ለማፍራት ራሳችን ሥልጠና በመስጠት ጭምር ነበር የገባንበት፡፡ አገልግሎቱ ስታንዳርዱን ጠብቆ እንዲሄድ በሰው ዘንድም እንዲወደድ ለማድረግ ብዙ ሥራዎች ሠርተናል፡፡ አንዳንድ ጊዜ የሸሪዓ ሕግ ሲባል በቀጥታ ከእምነት ጋር የሚያያይዙ ስላሉ ይህንን የማጥራቱ ሥራ ራሱ ቀላል አልነበረም፡፡

ሪፖርተር፡- እንዳሉት የሸሪዓ ሕግ ሲባል በቀጥታ ከእምነቱ ጋር የተያያዘ አድርገው የሚወስዱት ብዙ ናቸው፡፡ ከወለድ ነፃ ባንክ ከሸሪዓ ሕግ ጋር የተመሠረተው ነው ከተባለ ከእምነት ጋር አይያያዝም የሚባለው እንዴት ነው?

አቶ ኑሪ፡- እምነት ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ እምነትን ተመርኩዞ የሚሠራው የቢዝነስ ሥራ ደግሞ ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ይህንን ለይቶ ማስረዳት በራሱ ትልቅ ሥራ ነበር፡፡ በወቅቱ አቶ አቤ ሳኖ [የንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት] እና እኔ በግንባር ቀደምነት በሥልጠናውም ሆነ በዶክመንት ዝግጅቱ ስንሳተፍ የነበረው፡፡ ሥራውን ለመጀመር የሚያስችል እርሾ ሊሆን የሚችል ነገር አልነበረም፡፡ መነሻ የምናደርገው ተቋም ባልነበረበትና ምንም የምንጠቅሰው ዶክመንት ባልነበረበት ሁኔታ የተጀመረ ሥራ ነው ዛሬ እዚህ ደረጃ የደረሰው፡፡ በተለይ በእኛ አገር ቋንቋ የተዘጋጀ መረጃ ባልነበረበት ሁኔታ በአብዛኛው በዓረብኛ፣ በተወሰነ ደረጃ ደግሞ በእንግሊዝኛ የተዘጋጁ መረጃዎች ይዘን ከእኛ አገር ሕግ ጋር አጣጥመን ሥራውን ለመሥራት መነሳት ቀላል ነገር አልነበረም፡፡ ወደ ሥራ ከተገባ በኋላም ብድር የመስጠት ሥራውም በራሱ ቀላል አልነበረም፡፡ የብድር ማመልከቻ ስላስገባ ብቻ ዝም ብሎ አይሰጥም፡፡ ብሔራዊ ባንክ የሚያስቀምጣቸው መሥፈርቶች አሉ፡፡ የገቢዎች ሚኒስቴር የሚጠይቀው መሥፈርት አለ፡፡ ከሸሪዓ አንፃር ደግሞ የሚጠየቅ መሥፈርት አለ፡፡ ስለዚህ ከመደበኛ ባንክ የተለየ ብዙ የሚጠየቁ መሥፈርቶች አሉ፡፡ ከዚህም ባሻገር የደንበኛውን እምነት ማምጣቱ ራሱ ቀላል ነገር አይደለም፡፡ ቢሆንም አገልግሎቱን ሥርዓት አስይዞ ወደ መስመር ለማምጣት ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ አልነበረም፡፡ ይህም ሆኖ ግን ቀስ በቀስ እየተሸሻለ መጥቷል፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ‹‹ሲቢኢ ኑር›› በሚል መጠሪያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ከጀመረ ከአሥር ዓመታት በላይ ሆኖታል፡፡ አገልግሎቱ ከየት ተነስቶ የት ደረጃ ደርሷል? በመረጃ ቢገልጹልኝ?

አቶ ኑሪ፡- በሲቢኢ ኑር ሥራ በጀመርንበት የመጀመሪያ ዓመት አሰባስበን የነበረው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን 190 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ አሁን በጥቅምት 2016 ዓ.ም. አጋማሽ ላይ 98.2 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ይህ የሚጠበቀውን ያህል ባይሆንም ትልቅ ዕድገት ያለው መሆኑን ያሳያል፡፡ ከብድር አንፃርም ሥራው በጀመረበት የመጀመሪያ ዓመት ምን ዓይነት ብድር አልሰጠንም፡፡ አሁን ብድራችን 25.8 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ በብድር ሕግ ብድር ትሰጣለህ በመሀል ትሰበስባለህ፡፡ ስለዚህ የተለቀቀው ብድር ከዚህም ሁለትና ሦስት እጥፍ ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ በዓመት ውስጥ ከሰጠነው ብድር ከ25 እስከ 40 በመቶ መልሰን የምንሰበስብበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ ይህ ደግሞ እንደገና ለብድር ይውላል፡፡ ስለዚህ የለቀቅነው ብድር የተጠቀሰው ብቻ እንዳልሆነ መታሰብ አለበት፡፡ ብድር ደግሞ ጤናማነቱን መጠበቅ ያለበት በመሆኑ ትሰጣለህ፣ መልሰህ ትሰበስባለህ፡፡

ሪፖርተር፡- በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተበላሸ የብድር ምጣኔው እንዴት ነው ቁጥጥር የሚደረግበት? ከወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎት የተበላሸ ብድር ምጣኔ የሚመዘነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለመደበኛ ባንኮች ባወጣው ሕግ መሠረት ነው? ወይስ ራሱን የቻለ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሚገዛበት ሕግ አለ?

አቶ ኑሪ፡- ለዚህ ነው ብሔራዊ ባንክ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎትን ሊያግዙ የሚችሉ ወጥ የሆኑ ሕጎች ያስፈልጉታል የምንለው፡፡ ይህንንም የምንለው ከምናያቸው ክፍተቶች በመነሳት ነው፡፡ ብሔራዊ ባንክ ባወጣው መመርያ ወለድን ከሚመለከተው ጉዳይ ውጪ ሌላው መደበኛ ባንኮች የሚተዳደሩበት ሕግ በሙሉ ከወለድ ነፃ ባንክ ላይም የሚሠራ ይሆናል ነው የሚለው፡፡ ወለድ ብቻ እንጂ ለሌሎች አገልግሎት የወጡት ሕጎች ሁሉ ከወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎት ላይ እንደሚሠሩ ያመለክታል፡፡ በዚህ ድንጋጌ መሠረት አንድ ብድር ጤናማ ነው የሚባለው የተበላሸ የብድር መጠኑ ከአምስት በመቶ በታች ሲሆን ነው፡፡ ይህ ሕግ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ላይም ተፈጻሚ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ነገር ግን የተበላሸ ብድር ምጣኔን የሚያመላክተው ሕግ ከወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎት ጋር የተገናዘበ የማይሆንበት ሁኔታ አለ፡፡ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎቶች የቢዝነስ ባህሪ አላቸው፡፡ ‹‹ሬንታል ቤዝድ›› የምንለው ባህሪ አለው፡፡

‹‹የፓርትነርሺፕ ቤዝድ›› ባህሪ አለው፡፡ በአጠቃላይ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎቶች ከመደበኛው የባንክ አገልግሎት የሚለይ ሞዴል አላቸው፡፡ በተለይ በባንኩና በደንበኛው መካከል በሚደረግ ስምምነት በሸሪዓ መርሆዎች መሠረት በሽርክና የሚሠሩት ሥራዎች ጎልተው የሚታዩትበት የቢዝነስ አሠራር ሰፋ ተብሎ የሚተገበርበት ነው፡፡ ይህም ባንኩ ገንዘብ አዋጥቶ ከደንበኛው ጋር በመሆን አዋጭ በሚባሉ የተለያዩ የቢዝነስ ፕሮጀክቶች ላይ የሚሠራው ነው፡፡ ወይም ባንኩ ሙሉ ለሙሉ ፈንድ አድርጎ ደንበኛው የፕሮጀክት ሐሳብ ይዞ መጥቶ በመሥራት ትርፉን የሚጋሩበት አሠራር አለ፡፡ እንዲህ ዓይነት ፕሮጀክቶች ደግሞ በአጭር ጊዜ የምትሠራቸው አይደሉም፡፡ ረዥም ጊዜ የሚወስዱ ናቸው፡፡ በብሔራዊ ባንክ የሀብት ምደባ ግን ባንኮች ከሚሰጡት ጠቅላላ ብድር 40 በመቶውን ለአጭር ጊዜ፣ 40 በመቶውን ለመካከለኛ ጊዜ፣ 20 በመቶውን ደግሞ ለረዥም ጊዜ ኢንቨስትመንት ብድር መስጠት ይኖርባቸዋል ይላል፡፡ የአጭር ጊዜ ብድር የሚባለው የአንድ ዓመት ነው፡፡ የመካከለኛ ጊዜ ብድር የሚባለው ከአንድ ዓመት እስከ አምስት ዓመት ነው፡፡ የረዥም ጊዜ ብድር የሚባለው ደግሞ ከአምስት ዓመት በላይ የሆነውን ነው፡፡ ስለዚህ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ባህሪ በአብዛኛው የሚደረገው የሽርክና ቢዝነስ ላይ የበለጠ እንዲሠራ ስለሆነ፣ የብሔራዊ ባንክ መመርያ ብዙ የሚያሠራው አይሆንም፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ‹‹የሪስክ ሼር ስኪሙ›› የጎላ ነው፡፡ ትርፍን ብቻ አይደለም የምታጋራው፡፡ ሸሪዓን መሠረት ያደረገ የሽርክና ቢዝነሱ ኪሳራም መጋራት አለብህ የሚል ሕግ አለው፡፡ ስለዚህ የባንክ ሥራ ነባሩ ሥርዓት ከዚህኛው ቢዝነስ ጋር ብዙም የሚጣጣም አይሆንም፡፡ ሊያሠራው ቢችልም ቢዝነሱን ግን በሚፈለገው ደረጃ አያሳድገውም፡፡ ለዚህ ነው አንድ ቦታ ላይ ተይዘናል የምንለው፡፡ ሸሪዓን መሠረት ያደረጉ አገልግሎቶችን ለማስፋት ያልተቻለውም እንዲህ ያሉ ሕግጋት ባለመስተካከላቸው ጭምር ነው፡፡ አሁን ንግዱ ላይ ብቻ አተኩረን እንድንሠራ የተገደድነውም ለዚህ ነው፡፡ አሁን በአብዛኛው ሙረሃባ የሚባለው የንግድ ቢዝነስ ላይ ነው እየሠራን ያለ ነው፡፡ ሌሎቹ አገልግሎቶች ላይ እየሠራንባቸው አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ከአሥር ዓመታት በላይ የመቆየቱን ያህል፣ አሁን ደግሞ ራሱን የቻለ ባንክ እንዲቋቋም ከተፈቀደ በኋላም ቢሆን ቀድሞ በታሰበው ደረጃ እየተራመደ ያለመሆኑ ይነገራል፡፡ ለምሳሌ አሁን አለ በሚባለው የተቀማጭ ገንዘብ አገልግሎት ተጠቃሚ ይሆናል ከሚባለው የኅብረተሰብ ቁጥር ጋር የተጣጣመ አለመሆኑ ይጠቀሳል፡፡ በእርግጥ የሚሰባሰበው ተቀማጭ ገንዘብ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከፍተኛ ዕድገት እየታየበት ቢሆንም፣ ለብድር የሚውለው ግን አነስተኛ ነው፡፡ እንዲህ ለመሆኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስፈላጊ መመርያዎችን ባለማውጣቱ ብቻ ሊሆን ይችላል? ከሆነስ ብሔራዊ ባንክ ምን ማድረግ አለበት?

አቶ ኑሪ፡- ብሔራዊ ባንክን ለመተቸት ፍላጎት የለኝም፡፡ ነገር ግን መሆን ያለበትን ነገር ነው የማነሳው፡፡ አንድ አገር ውስጥ የተለያዩ የፋይናንስ ሞዴሎችን የምንጠቀም ከሆነ እነዚህን ሞዴሎች ተከትለን ሕጉን ሠርተን ነው መሄድ ያለብን፡፡ ይህ በእኛ አገር ብቻ የተከሰተ አይደለም፡፡ በተለይ በመደበኛው (ኮንቬንሽናል) እና ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ሥራ ለመሥራት እንደምትችል ፈቃድ ሰጥቶህ የሚያሠራ ከሆነ አሠራሩ ‹‹ዱዋል›› ሲስተም ነው፡፡ እዚህ አገር እስካሁን ያለው የ‹‹ኮንቬንሸናል›› ሲስተም ነው፡፡ ብሔራዊ ባንክ ለወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎት ያወጣው መመርያ በጣም አጭር ነው፡፡ ቀድም ብዬ እንደገለጽኩልህ ከወለድ ነፃ ከሆነው አገልግሎት ባሻገር ሌላው ለመደበኛ ባንኮች የወጣው መመርያ በሙሉ እዚህ ላይ ተፈጻሚ ይሆናል፡፡ ስለዚህ አሠራሩ መሆን ካለበት ‹‹ዱዋል›› ሲስተም ሆኖ ሊቃኝ ይገባዋል፡፡ ለምሳሌ ናይጄሪያ እንዳላት ዓይነት አሠራር ቢኖረን ነገሮችን ያስተካክላል ብዬ አምናለሁ፡፡     

ሪፖርተር፡- የናይጄሪያ ከወለድ ነፃ ባንክ አስተዳደርና አሠራር ምን ዓይነት ነው? በኢትዮጵያ ቢተገበር ያለውን ክፍተት ሊሞላ ይችላል ተብሎ ይታሰባል?

አቶ ኑሪ፡- የናይጄሪያ ብሔራዊ ባንክ ‹‹ዱዋል›› ሲስተም ነው የሚከተለው፡፡ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ራሱን የቻለ መመርያዎች አሉት፡፡ በሥርዓት የተዘጋጁ ዶክመንቶች አሉት፡፡ በእያንዳንዳቸው ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎቶች ላይ እንደ ቢዝነስ ባህሪው ተጽፎ የመቆጣጠሪያ መንገዶችንም ይዟል፡፡ አሁን በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሱፐርቪዥን ሥርዓትን የሚዘውረው ነባሩ ሥርዓት ነው፣ ይህ ከወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎት ባህሪ ጋር አብሮ አይሄድም፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ራሱን የቻለ የሱፐርቪዥን ሥርዓት የለውም፡፡ የሸሪዓ መርሆዎች የሚከተል የሱፐርቪዥን አካል ሊኖረው ይገባል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው አስተዳደር ይህ ነው፡፡ የሸሪዓ ጉዳይ ትልቅ ጉዳይ ነው፡፡ ሸሪዓ ስንል ቢዝነስ የምንሠራበት ሥርዓት ማለታችን ነው፡፡ እዚህ ጋ ሸሪዓ በሁለት ተከፍሎ በግልጽ እንዲታወቅ እንፈልጋለን፡፡ አንዱ ሸሪዓ የፀሎት አፈጻጸም እንዴት መሆን እንዳለበት፣ እንዴት ለፈጣሪ መገዛት እንዳለብን የሚያስተምር ነው፡፡ እኛ ስለዚህ አይደለም እያወራን ያለነው፡፡ ቢዝነሱን የሚመለከተውን ነው፡፡ ቢዝነሱ የራሱ ሥነ ምግባር አለው፡፡ ያንን የቢዝነስ ሥነ ምግባር እንዴት ጠብቆ መሥራት ይቻላል የሚል ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የተቀመጡ የሸሪዓ ሕጎች አሉ፡፡ የሸሪዓ ስታንዳርድ ተብለው የተቀመጡ ይህንን የሚገዙ ዓለም አቀፍ እስላሚክ ፋይናንሻል ስታንዳርድ የሚባለው ላይ በግልጽ አስቀምጧል፡፡ በአካውንቲንግ ሕጉም ደግሞ የአገልግሎቶች ዓይነት ጭምር ሊገዙበት የሚገባ ሕግጋትን ሁሉ ቀርፆ አስቀምጦታል፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክም የሸሪዓ ሕጉን ተከትላችሁ መሥራት አለባችሁ ብሎ ከፈቀደ የሸሪዓ ሕጉን የሚቆጣጠር ራሱን የቻለ አካል ሊኖረው ይገባል፡፡ አሁን እኮ የሸሪዓ ቦርድ እንኳን የለውም፡፡   

ሪፖርተር፡- ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሚሰጡ እናንተን ጨምሮና ሌሎችም ባንኮች ግን የሸሪዓ ቦርድ በማዋቀር እየሠሩ ነው፡፡ ይህንን ያደረጋችሁት በብሔራዊ ባንክ ድንጋጌ አይደለም ማለት ነው?

አቶ ኑሪ፡- አዎ፣ ባንኮቹ ይህንን ያደረጉት በራሳቸው ፍላጎት ነው፡፡ የሸሪዓ አማካሪ ቦርድ አቋቁመው እየሠሩ ያሉት ብሔራዊ ባንክ አስገድዷቸው አይደለም፡፡ ነገር ግን በዓለም አቀፍ ስታንዳርዱ በማዕከላዊ ባንክም ሆነ በባንኮች የሸሪዓ ቦርድ ሊኖር ይገባል ብሎ አስቀምጧል፡፡ ለዚህ ነው ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎትን በተመለከተ የብሔራዊ ባንክ መመርያ ሙሉ አይደለም የምንለው፡፡ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ከሚጠይቀው አንዱ የሸሪዓ ቦርድ ነው፡፡ ባንክ ውስጥ የሚሠራ ኤክስፐርት የሸሪዓ ሕጎችን ጠንቅቆ ላያውቅ ይችላል፡፡ የሸሪዓ ጉዳዮችን ደግሞ ውሳኔ ላይሰጥበት ይችላል፣ ፈታዋ ላይሰጥ ይችላል፡፡ ስለዚህ ሸሪዓን የተመለከቱ ጉዳዮችን ሁሉ ውሳኔ ፈታዋ የሚሰጠው የሸሪዓ ሱፐርቫይዘር ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ደንበኛ የዚህ አገልግሎት ሥርዓት ሳይኖር በመደበኛው የባንክ አገልግሎት ወለድ ያለበት ብድር ወስዶ ይሆናል፡፡ ከመደበኛው የባንክ አገልግሎት ወጥቶ ወደ ከወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎት ሊገባ ይችላል፡፡ ነገር ግን ከመደበኛው ወይም በወለድ ብድር ወስዶ ኢንቨስት አድርጓል፡፡ ይህንን ገንዘብ ከፍሎ ለመውጣት አይችልም፡፡ እዚያ መቆየትም አይችልም፡፡ ይህ የሆነው ቀድሞ አማራጭ ስላልነበረ ነው ብለን ከሸሪዓ አንፃር ትንሽ የምናይለት ሁኔታ ይኖራል፡፡ ይህ የእምነቱ አስተምህሮ ነው፡፡ ከመደበኛው ባንክ በወለድ ከወሰደው ኢንቨስትመንት ለመውጣት ዕዳውን መክፈል አለበት፡፡ መክፈል ካልቻለ ምን ይሁን ነው ጥያቄው፡፡ በዚህ ጊዜ የሸሪዓ አማካሪ መፍትሔ የሚሰጥበት መሆን አለበት፡፡ እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን ብሔራዊ ባንክ ሊፈታ አይችልም፡፡ ባንኮችም ለዚህ መፍትሔ ሊሰጡ አይችሉም፡፡ የሸሪዓ ጉዳዮችን ችግር ዓይቶና እንደ አገሪቱ ሁኔታ፣ እንዲሁም እንደ ነጋዴዎቹ ነባራዊ ሁኔታ መፍትሔ የሚሰጠው የሸሪዓ አማካሪው ነው፡፡ በማዕከልም የሸሪዓ ሱፐርቪዥን መቋቋም ይኖርበታል ተብሎ ከሚሞገትበት አንዱ እንዲህ ያሉ ጉዳዮች ስላሉ ነው፡፡ በአንድ ባንክ ፈታዋ የተሰጠው ጉዳይ በሌላም ባንክ እንዲሠራ ከተፈለገ ማዕከላዊ ባንኩ የሸሪዓ ሱፐርቫይዘር ሊኖረው ይገባል፡፡ እኛ ዘንድ የሚሠራ ሕግ ሌላው ባንክ ላይ የማይሠራ ከሆነ፣ ሌላው ባንክ ላይ የሚሠራ ሕግ እኛ ጋ የማይሠራ ከሆነ ወጥነት አይኖርም፡፡ ይህ ሁኔታ ለብሔራዊ ባንክ የቁጥጥር ሥራ ራሱ ተግዳሮት ይሆናል፡፡ ስለዚህ ማኅበረሰቡ ግንዛቤ ወስዶ ጥርጣሬ እንዳይኖረው፣ ወጥነት ያለው ሕግ ሆኖ መቀጠል እንዲችል ይህ አካል ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡– መደበኛ ባንኮች የገንዘብ እጥረት ቢገጥማቸው የመጨረሻ አማራጫቸው ከብሔራዊ ባንክ መበደር ይሆናል፡፡ እናንተስ ምን ታደርጋላችሁ? በዚህ ጉዳይ ላይ ከመደበኛው ባንክ ጋር ያለውን ልዩነት ቢያስረዱኝ?

አቶ ኑሪ፡- ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት እየሰጠን ባለበት ወቅት የገንዘብ እጥረት ገጥሞን መክፈል ባንችል፣ እንደ መደበኛ ባንኮች የገንዘብ እጥረታችንን ለመሸፈን ዘለን ከብሔራዊ ባንክ በወለድ ልንበደር አንችልም፡፡ ከወለድ ነፃ ባንክ ሆነን በወለድ ብድር መበደር አንችልም፡፡ ብሔራዊ ባንክ ለዚህም መፍትሔ ሊኖረው ይገባል፡፡ ለምሳሌ አንድ ባንክ የገንዘብ እጥረት (ሊኪውዲቲ) ሲፈጠርበት ብሔራዊ ባንክ ሄዶ በወለድ ይበደራል፡፡ አሁን በአገራችን አራት ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሚሰጡ ባንኮች አሉ፡፡ እንዲህ ያሉ ባንኮች ገበያው ውስጥ ተግዳሮት ሲገጥማቸው ሄደው መበደር የሚችሉበት አሠራር ሊዘረጋላቸው ይገባ ነበር፣ ግን የለም፡፡ እንዲህ ላለው ነገርም ከወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎት የተሟላ ሕግና አሠራር የለውም፡፡

ሪፖርተር፡-  የገንዘብ እጥረት ሲያጋጥም ባንኮች ወደ ብሔራዊ ባንክ በመሄድ በሕግ በተቀመጠው የወለድ መጠን መበደር የተለመደና እየተሠራበት ያለ ነው፡፡ ባንኮች በአንድ አጋጣሚ እጥረት ሊያጋጥማቸው እንደሚችል ይታመናል፡፡ ስለዚህ ከወለድ ነፃ ባንኮችም እጥረቱ ሲያጋጥማቸው የሚበደሩበት አሠራር ከሌለ አደጋ አይኖረውም? አደጋ ካለው ደግሞ መፍትሔ የሚሆነው ነገር ምንድነው? ዓለም አቀፍ ልምዶችስ ምን ያሳያሉ?

አቶ ኑሪ፡- ችግሩ መፍትሔ አለው፡፡ ባንኮች ችግር ቢገጥማቸው ከብሔራዊ ባንክ እንደሚበደሩ ሁሉ እርስ በርስም ይበዳደራሉ፡፡ በቀቀማጭ ገንዘብ ረገድም አንዱ ባንክ በሌላው ባንክ እያስቀመጡ የመተጋገዝ ነገሮችም አሉ፡፡ ይህም አማራጭ በሚጠፋበትና ከባንክ መበደር በማይቻልበት ጊዜ፣ ከግለሰብ መበደር በማይቻልበት ጊዜ በመጨረሻ መፍትሔው ብሔራዊ ባንክ ነው፡፡ አሁን ያለው የብሔራዊ ባንክ አሠራር ለመደበኛ ባንኮች ያስቀመጠው ነው፡፡ የብሔራዊ ባንክ ሕግ በመደበኛው የባንክ አገልግሎት ላይ ተግባራዊ የተደረገው ከወለድ ውጪ ባለው ባንክ ላይም ይሠራል ይላል፡፡ ስለዚህ የወለድ ሕጉ በዚህ መመርያ አይሠራም ማለት ነው፡፡ ከወለድ ነፃ ባንኮች ችግር ገጥሟቸው የመጨረሻ የመፍትሔ አካል ነው የሚባለው ብሔራዊ ባንክ ሄደው መበደር አይችሉም፡፡ ስለዚህ ብሔራዊ ባንክ መፍትሔ ስላላስቀመጠ ክፍተቱ እንዳለ ነው፡፡ ነገር ግን ለዚህ ክፍተት መፍትሔ ማስቀመጥ ይችላል፡፡ ዓለም አቀፋዊ ልምዶች ስላሉ እነሱን መተግበር አለበት፡፡ እንደ ተቆጣጣሪ ተቋም ሁሉንም በእኩል ደረጃ ማስተዳደር አለበት፡፡ አሁን ግን እያደረገ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት እንዲኖር የተፈለገውን ያህል በተገቢው መንገድ እየተሠራበት አይደለም ተብሎ ከሚገልጽባቸው ምክንያቶች አንዱ፣ በዓለም ላይ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ዓይነቶች በርካታ ቢሆኑም በኢትዮጵያ ግን በጣም ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው የተተገበሩበት ይባላል፡፡ በሁሉም ባንኮች የሚሰጡት ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎቶች ከውስንነታቸው ባሻገር ተመሳሳይ መሆናቸው እንደ ችግር የሚጠቀስ ነው፡፡ በዘርፉ የሚሰጡ አገልግሎቶችን በአግባቡ እየሰጣችሁ አለመሆኑ ሕጎች ባለመኖራቸው ብቻ ነው?

አቶ ኑሪ፡- በአጠቃላይ የአገሪቱን ሕጎች ከዚህ ከአገልግሎት ጋር ማቀናጀት ካለብን ወደኋላ ተመልሰው ነው ማቀናጀት ያለብን፡፡ አንድ ምሳሌ ብቻ ልንገርህ፡፡ ሙረሃባ የሚባለው አገልግሎት ዕቃ ገዝተህ መሸጥ ነው፡፡ ዕቃ ገዝቶ ትርፍ ጭምረህ መሸጥ ነው፡፡ አንድ ዕቃ ገዝተህ ትርፍ ጨምረህ የምትሸጥ ከሆነ ተጨማሪ እሴት ታክስ መሰብሰብ ሊያስገድድ ነው ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ይህ አገልግሎትን የባንክ ሥርዓት ነው፡፡ የባንክ ወለድ ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ አትከፍልም፡፡ እንዲያውም ከወጪ ላይ የባንክ ወጪ ተብሎ ይቀንስልሃል፡፡ ዕቃ በሙረሃባ ዕቃ ገዝተህ ትርፉን ጨምረን የምንሸጥ ከሆነ፣ ከሕጉ አንፃር ተጨማሪ እሴት ታክስ ሰብስበን መሸጥ አለብን፡፡ እንዲህ ያለውን ጉዳይ የገቢዎች ሚኒስቴር አያውቀውም ነበር፡፡ ሙረሃባ የባንክ ‹‹ፕሮዳክት›› ነው፡፡ የፋይናንሻል ሞዴል ነው፡፡ ይህንን አገልግሎት ለደንበኞቻችን እያቀረብን ነው፡፡ ይህ ሥርዓት ዕቃ ገዝቶ ትርፍ ጨምሮ መሸጥ ነው፡፡ በኋላ ቫት አልሰበሰባችሁም በሚል ባንኩ እንዳይቀጣ ብለን ከዓመታት በፊት ደብዳቤ ጽፈን ነበር፡፡ የገቢዎች ሚኒስቴር ይህንን ጉዳይ አላውቅም አለ፡፡ የገንዘብ ሚኒስቴርን ልጠይቅ አለ፡፡ የገንዘብ ሚኒስቴርም ብሔራዊ ባንክን ጠየቀ፡፡፡ ከዚያም ተነጋግረው ነገሩ እንደገና ወደ እኛ መጥቶ ማብራሪያ ሰጥተን መቋጫ አገኘ፡፡ ስለዚህ ከወለድ ነፃ አገልግሎት ባለድርሻ አካላት ሳይቀሩ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ያስፈልጋል፡፡ የተጣመረ የሕግ ሥርዓት ያስፈልጋል፡፡ በዓለም ላይ በጣም በቀላሉ ሊሰጡ የሚችሉ በጣም ብዙ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎቶችን እዚህ መስጠት ያልቻልነው ያሉት ሕጎች ስለማያሠሩ ነው፡፡ አሁን እየሠራን ያለነው ከአገሪቱ ሕጎች ጋር የሚጣጣሙ እጀግ በጣም ቀላል በሚባሉት አገልግሎቶች ነው፡፡ የብሔራዊ ባንክ የሕግ ጥበቃ ቢኖር ግን አገርንም የሚያግዝ ትልቅ ሥራ ይሠራ ነበር፡፡ በአንዳንድ አገሮች መንገዶች፣ ሆስፒታሎችና ትልልቅ ሜጋ ፕሮጀክቶች የሚሠሩት በባንኮች ነው፡፡ በተለይ ‹‹ስትስና›› የሚባለው ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ዓይነት እንዲህ ያለውን ሥራ መተግበር የሚያስችል ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- አሠራሩን በምሳሌ ቢገልጹልን?

አቶ ኑሩ፡- ለምሳሌ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወይም መንግሥት ከሜክሲኮ አደባባይ ሳር ቤት ድረስ ያለውን መንገድ ለመገንባት ቢፈልግ አጥንቶ ዋጋውን ያወጣል፡፡ ነገር ግን ገንዘቡ የለውም፡፡ ታክስ ሰብስቦ የግንባታውን ወጪ እንደሚከፍል ያውቃል፡፡ እንዲህ ሲሆን ለባንኮች ጨረታ ያወጣል፣ ባንኮች ይጫረታሉ፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከባንክ ጋር ሆኖ ያጫርትና ወደ ሥራ እንዲገባ ያደርጋል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ገንዘቡን የሚከፍለው በሁለትና በሦስት ዓመት ከሆነ ባንኩ ትርፉን ይጨምርና ፕሮጀክቱን ፋይናንስ ያደርጋል፡፡ አስተዳደሩም ታክሱን ይሰበስብና በተቀመጠው ጊዜ መሠረት ለባንኩ ይከፍላል፡፡ ፕሮጀክቱ በገንዘብ እጥረት ምክንያት የሚጓተትበት ምክንያት አይኖርም፡፡ እንዲህ ባለው አሠራር ባንኮች፣ የከተማ አስተዳደሩና ኅብረተሰቡ ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ እንዲህ ያሉ አገልግሎቶች ሁሉ አሉ፡፡ ግን ሕጉ ስለሌለ እየተሠራበት አይደለም፡፡ በነገራችን ላይ በዱባይ እንዲህ ባለው አሠራር እያተጠቀሙ ነው ትልልቅ ግንባታዎችን የሚያካሂዱት፡፡

ሪፖርተር፡- ከወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎት እንዲህ ባለ ደረጃ ጭምር ጥቅም ካለውና ሥራውን በአግባቡ መሥራት ጠቀሜታው ሰፊ መሆኑን የምትገልጹትን ያህል ከሆነ አስፈላጊ ስለሚሆን፣ ሕግ እንዲወጣ በእናንተ በኩል ምን ያህል ጥረት አድርጋችኋል? በተጨባጭ እንዲህ አድርገናል የምትሉትስ ነገር ምንድነው? አገልግሎቱ አዲስ ከመሆኑ አኳያ የብሔራዊ ባንክን ድጋፍ የሚፈልግ ሊሆን ስለሚችል ሥራው በደንብ የገባችሁ ባለሙያዎችስ ገፍታችሁ ሕጉ እንዲወጣ ምን ያህል ጥራችኋል?

አቶ ኑሪ፡- ይኼ አገልግሎት እዚህ አገር ገና ነው፡፡ አሁን ነው ዕድገት እያሳየ የመጣው፡፡ ማኅበረሰቡም በጣም የሚፈልገው ነው፡፡ በዚያ ደረጃ ግን የሠለጠነ የሰው ኃይል የለም፡፡ በዘርፉ ትልቅ ክፍተት አለ፡፡ ሁለተኛ ነገር ደግሞ ይህ አገልግሎት እንዲጀመር ይፈቀድ እንጂ የፈቀዱ አካላት ጭምር ጥቅሙን በደንብ አልተረዱትም፡፡ በእኛ በኩል ግን ጥረት እያደረግን ነው፡፡ ከአገሪቱ ሕጎች ጋር ሊሄዱ የሚችሉትን አገልግሎቶች እየሠራንባቸው ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የአገርን ኢኮኖሚ ሊያግዙ የሚችሉ አገልግሎቶች እንዳሉ በተቻለ መጠን ለማስረዳት ጥረት እያደረግን ነው፡፡ አንድ እርግጠኛ ሆኜ የምነግርህ ይኼ አገልግሎት በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ ፋይዳ አለው ብሎ መንግሥት ሲረዳ ትልቅ ትኩረት ያደርጋል ብዬ ነው የማስበው፡፡ ይህ የተወሰነ ጊዜ መውሰዱ አይቀርም፡፡ እኛ ግን ግንዛቤውን እየፈጠርን እንሄዳለን፣ እየገፋንም ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከመረጃዎቻችሁ መገንዘብ እንደሚቻለው ካሰባሰባችሁት ብድር አብዛኛውን እጅ መልሳችሁ በማበደር ሥራ ላይ ማዋል አልቻላችሁም፡፡ በዚህን ያህል መጠን ከፍተኛ መጠን ያለውን ገንዘብ መያዛችሁ በኢኮኖሚው ላይ ችግር አይፈጥርም? ገንዘቡንስ አያጋሽበውም?

አቶ ኑሪ፡- ተቀማጭ ገንዘቡ እዚህ የደረሰው በአጭር ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ በተለይ ባለፉት አራትና አምስት ዓመት ነው ትልቅ ለውጥ የታየው፡፡ ከዚህም በላይም በፍጥነት ሊያድግ ይችላል፡፡ የእኔ እምነት ይህ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በአጠቃላይ በአገሪቱ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ያለው ተቀማጭ ገንዘብ 2.2 ትሪሊዮን ብር ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ ከወለድ ነፃ የተሰበሰበው ተቀማጭ ገንዘብ 200 ቢሊዮን ብር ብቻ ነው፡፡ ሁለት ትሪሊዮን ብር ካስቀመጡ ደንበኞች ውስጥ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሚፈልጉ ደንበኞች የሉም ማለት አይደለም፣ ገና አልወጡም፡፡ ወደ ወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎቱ መምጣት ሲጀምሩ በእርግጠኝነት ቢያንስ ወደ አንድ ትሪሊዮን ብር ወደ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ይመጣል፡፡ ያኔ የት ኢንቨስት እናድርግ ይባላል፡፡ ስለዚህ የቴክኖሎጂና የሰው ኃይል ዝግጅት ይፈልጋል፡፡ በተለያዩ አገሮች የፋይናንስ ዓይነቶች የየራሳቸውን ልዩ አገልግሎት ይፈልጋሉ፡፡ በእኛ በኩል አሠራሩ አሁን ሥራ ላይ ያልዋለ ገንዘብ ቢኖርም ከሥር ከሥር እየሰጠን ነው፡፡ እኛ ዓምና ከወለድ ነፃ 17 ቢሊዮን ብር ብድር ሰጥተናል፣ ግን አልነካነውም፡፡ በሸሪዓ ሕግ እንኳን የት ኢንቨስት እንደምናደርግ አጥተነው ገንዘቡን ይዘን ያለነው፡፡ ይህንን ገንዘብ አንዳንዴ የውጭ ምንዛሪ ነው የምንገዛበት፡፡ የዋጋ ግሽበቱ እንዳይበላውና ‹‹ዲቫልዩ›› እንዳያደርግብን በውጭ ምንዛሪ እናስቀምጠዋለን፡፡ ባለው ገንዘብ ልክ የውጭ ምንዛሪ አግኝተን ግን ላንገባ እንችላለን፡፡ ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ ግን ይህንን እናደርጋለን፡፡ አሁን ከበቂ በላይ የምንለውን ገንዘብ በተቻለ መጠን ለማበደር ግን እየጣርን ነው፡፡ ብድር ግን ሁልጊዜ ጥንቃቄ ይፈልጋል፡፡ ገንዘቡ ስላለ ብቻ መበተን አንችልም፡፡ ብድር የምንሰጠውም የብሔራዊ ባንክን ፈቃድ እየጠየቅን ነው፡፡ የመንግሥት ባንክም ስለሆነ ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፍሰቱን ይቆጣጠራል፡፡ ገበያውንም እንዳያበላሽ እጥረትም እንዳይኖር በሚያስችል መንገድ ብሔራዊ ባንክ በሚሰጠው አቅጣጫ መሀል ላይ ሆነን ነው የምንጫወተው፡፡ ስለዚህ ተቀማጭ ገንዘቡ ዝም ብሎ አይቀመጥም፡፡ መሥፈርቱን ላሟሉ ብድሩን እንሰጣለን፡፡ በነገራችን ላይ የእኛን አገልግሎት እየተጠቀመ ያለው ሙስሊሙ ማኅበረሰብ ብቻ አይደለም፡፡ የሌሎች የእምነት ተከታዮችም አሠራሩን በመምረጥ እየመጡ ነው፡፡ ጉዳዩ ቢዝነስ ስለሆነ አንተ የምትጠብቀው ሥነ ምግባሩን ብቻ ነው፡፡ መርሁን ጠብቆ የመጣን ደንበኛ በሙሉ እናስተናግዳለን፡፡

ሪፖርተር፡- በነገራችን ላይ አንድ ከመደኛው ባንክ ብድር የተበደረ ደንበኛ ወደ ወለድ ነፃ ባንክ መጥቶ መበደር ይችላል?

አቶ ኑሪ፡- ሁለቱ ላይ መጫወት አይችልም፣ ያኛውን መዝጋት አለበት፡፡ በመደበኛ ባንክ ያለውን ብድር ዘግቶ ነው ወደ እዚህ መምጣት ያለበት፡፡ ካልሆነ እዚያው ነው መቆየት ያለበት እንጂ ሁለቱ ጋ መበደር አይቻልም፡፡

ሪፖርተር፡- በምን እርግጠኛ ልትሆኑ ትችላላችሁ? መቆጣጠር የምትችሉበት አሠራር አለ?

አቶ ኑሪ፡- አዎ፣ በማዕከል እኮ መረጃ አለ፡፡ ብሔራዊ ባንኩ አለው፡፡ አንደኛ ጤናማነቱን፣ አንድ ተበዳሪ ምን ያህል የብድር መጠን እንዳለበትና የአከፋፈል ሥርዓቱ እንዴት እንደሆነ መረጃ አለው፡፡ በእርግጥ አንድ ደንበኛ ብድር ሲጠይቅ ምን ያህል ብድር እንዳለበት ላይገልጽ ይችላል፡፡ ስላመለከተ ብቻ ብድሩ አይሰጥም፡፡ የተበደረው የብድር ታሪክ ይታያል፡፡ በብሔራዊ ባንክ የሁሉም ባንኮች መረጃ ስላለ ከማዕከሉ ስለምናረጋግጥ እንዲህ ያለ ችግር አይፈጥርም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ብድር የማይሰጥባቸው ዘርፎች አሉ፡፡ በግልጽ ለተከለከሉ ዘርፎች ደግሞ ፋይናንስ አይደረግም፡፡ ይህንን ዘልቀን ጭምር ስለምናይ ችግር የለውም፡፡

ሪፖርተር፡- የሲቢኢ ኑር አሥረዓመት ክብረ በዓል ላይ በግልጽ እንደተሰማው የእስልምና ጉዳይ ምክር ቤት ተወካይና የእናንተ የሸሪዓ ቦርድ አማካሪ፣ ሲቢኢ ኑር ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወጥቶ ራሱን የቻለ የመንግሥት ከወለድ ነፃ ባንክ ሆኖ ይቋቋም  የሚል ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ይህ ምን ማለት ነው? በእናንተ በኩልስ ሐሳቡን እንዴት ታዩታላችሁ?

አቶ ኑሪ፡- ይህ እንግዲህ በአንድ አገር ያለ ማኅረበሰብ የሚጠይቃቸው ነገሮች ብዙ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ከዚህ በፊት ይህ አገልግሎት እዚህ አገር እንዲኖር የሚል ነበር፡፡ ፍላጎት እየጨመረ ይሄዳል፣ መቆሚያ የለውም፡፡ ይህ ፍላጎታችን ነው፡፡ ራሱን የቻለ ከወለድ ነፃ የሆነ የመንግሥት ባንክ ይኑር ብሎ የሚወስነው ግን ባለቤቱ ራሱ መንግሥት ነው፡፡ ወይም ደግሞ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን በበላይነት የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ በሚያቀርበው መሠረት የሚከናወን ጉዳይ ነው፡፡ በእኛ በኩል ሐሳብ የለም፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በዚህ ጉዳይ ላይ የተመከረ ነገር የለም፡፡ የቢዝነሱ ዕድገት ግን ብዙ እየገፋ ነው፡፡ እንደ አንድ ባለሙያ ወይም እንደ አንድ ግለሰብ አስተያየት ስጥ ብትለኝ ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያ በመልክዓ ምድር አቀማመጥ ከመካከለኛው ምሥራቅ ጋር ብዙ ቅርርብ አላት፡፡ የጎረቤት አገሮችም ከወለድ ነፃ ባንኮች በበዙበትና ይህ አገልግሎት በዓለም ደረጃ ክፍት በሆነበት ሁኔታ፣ የውጭ ኢንቨስትመንት በተለይ ቀጥታ የውጭ ኢቨስትመንትን ለመሳብ ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ትልቅ የምትለው በሸሪዓ መርህ የሚሠራ ባንክ ኢትዮጵያ ውስጥ የለም፡፡ ገና አሁን የተቋቋሙ ትንንሽ ባንኮች ነው ያሉት፡፡ በመካከለኛው ምሥራቅ ካሉ ትልልቅ ኢንቨስተሮች የሚነሳው ኢንቨስትመንታቸውን ለማሳደግ አንዱ ጥያቄያቸው የወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎት ነው፡፡ ከመካለኛው ምሥራቅ ጋር ያለን የንግድ ትስስር ጠንካራ እየሆነ ነው፡፡ ብዙ ኢንቨስተሮችም ለመምጣት ፍላጎት አላቸው፡፡ በአካባቢያቸው ገበያውን እየያዙ ያሉት ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሚሰጡት ባንኮች እየሆኑ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥም እንደ መንግሥት ራሱን የቻለ ጠንካራ ከወለድ ነፃ ባንክ ቢኖር ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው የጎላ ይሆናል፡፡ ጠንካራ ከወለድ ነፃ ባንክ ብድር የተሻለ ኢንቨስት እናደርጋለን የሚለው ምልከታ እየጎላ ስለመጣ፣ እኔ የመንግሥት የሆነ ከወለድ ነፃ ባንክ ቢኖር ይዞት የሚመጣው አገራዊ ጠቀሜታ ይኖራል ብዬ አምናለሁ፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ከጨረታ በስተጀርባ ያሉ ድርድሮችን ለማስቀረት ጥረት እያደረግን ነው›› ሱሌማን ደደፎ (አምባሳደር)፣ የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ (የቀድሞ ሜቴክ) ዋና ሥራ አስፈጻሚ

ሱሌማን ደደፎ (አምባሳደር) በተባበሩት ዓረብ ኤሜሬትስ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ፣ ከጥር 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የቦርድ...

‹‹ባለፉት 25 ዓመታት ባለን አቅም ሁሉ የተለያዩ አጀንዳዎችን ለመዳሰስ ሞክረናል›› የራስወርቅ አድማሴ (ዶ/ር)፣ የፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ

‹‹ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ›› በመባል የሚታወቀውን በኢትዮጵያ ታሪክ ከመንግሥትም ሆነ ከሌላ አካል ገለልተኛ ሆኖ የተቋቋመ ሐሳብ አመንጪ የጥናት ተቋም (ቲንክ ታንክ) ከመሠረቱት አንዱ መሆናቸውን...

‹‹የሶማሌ ክልልን አካታች ዴሞክራሲያዊ ልምምድ በአገራችንም መተግበር አለብን›› አቶ ሙስጠፌ ዑመር፣ የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት

ከ2010 ዓ.ም. ለውጥ ማግሥት ወደ ኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ በጉልህ ብቅ ካሉ ፖለቲከኞች አንዱ የሆኑት አቶ ሙስጠፋ ሞሐመድ ዑመር ወይም ብዙዎች እንደሚጠሯቸው ‘ሙስጠፌ’ ራሳቸውን ጭምር...