Thursday, December 7, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየጥገና ሥራዎች መፍትሔ ያልሰጧቸው የአዲስ አበባ መንገዶች

የጥገና ሥራዎች መፍትሔ ያልሰጧቸው የአዲስ አበባ መንገዶች

ቀን:

በአዲስ አበባ ከተማ በየቦታው የሚታየው የመንገድ መጎዳት በርካታ አሽከርካሪዎችን ችግር ውስጥ መክተቱ በተደጋጋሚ ይነገራል፡፡ በከተማዋ ተጀምረው ያላላቁ፣ በየቦታው ተቆፋፍረው የቀሩና ብዙም አገልግሎት ሳይሰጡ ተቦርቡረው የሚገኙ መንገዶች የትራንስፖርት ፍሰቱ እንዲስተጓጎል ምክንያት ሆነዋል፡፡

እነዚህ ሁሉ ችግሮች የከተማዋን ውበት ከማጥፋት ባለፈ የትራፊክ አደጋ እንዲከሰት ምክንያት እንደሆኑ፣ በተለይ መንግሥት የሰጠው ትኩረት አናሳ በመሆኑ፣ የተለያዩ አሽከርካሪዎች ምሬታቸውን ሲገልጹ ይታያል፡፡

የጥገና ሥራዎች መፍትሔ ያልሰጧቸው የአዲስ አበባ መንገዶች | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

ወጣት በረከት ሰጠኝ በታክሲ ሹፍርና ሥራ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ስድስት ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ ከሀና ማርያም አንስቶ እስከ መገናኛ መስመር የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን የሚናገረው ወጣቱ፣ መንግሥት በተገቢ ሁኔታ የመንገድ ዝርጋታን ባለመሥራቱ ለተለያዩ ችግሮች እየተጋለጠ እንደሆነ ለሪፖርተር ያስረዳል፡፡

በተለይ ሳሪስ፣ አቦ፣ ኢምፔርያል፣ ማሞ አደይ አበባ፣ ሃና ማርያምና ሌሎች ቦታዎች መንገዱ አስፋልት ነው፡፡ ቢሆንም፣ አባጣ ጎርባጣ፣ ተቆፍሮ የቆመና ያላለቀ ስለሚገኝበት፣ በርካታ የታክሲ ሾፌሮችም ሆኑ ሌሎች አሽከርካሪዎች ላልተገባ እንግልት መዳረጋቸውን ይናገራል፡፡

መንገዱ የተመቸ ባለመሆኑ የተነሳ የመንገድ መዘጋጋት የሚከሰትበት አጋጣሚ ሰፊ መሆኑን ገልጾ፣ በዚህም የተነሳ አቦ አካባቢም እሱን ጨምሮ ሌሎች ጓደኞቹ ግጭትና የመኪና ዕቃ መሰበር እንዳጋጠማቸው ያስረዳል፡፡

መንግሥት የከተማዋን ውበት በጠበቀ መልኩ ለትራንስፖርት አገልግሎት የሚውሉ መንገዶችን መዘርጋት ይኖርበታል የሚለው ወጣት፣ በየዓመቱ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ መንገዶች ዕድሳት ሲደረግላቸው ማየቱን፣ ነገር ግን ዕድሳቱ ዘላቂ አለመሆኑን መታዘቡን ይናገራል፡፡

በመንገዶቹ በተለይ ማታ ማታ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት ከባድ መሆኑን ጠቅሶ፣ መንገዱን የማያውቁ ሌሎች አሽከርካሪዎች ሲጋጩና መኪናቸው ላይ ጉዳት ሲደርስ ይስተዋላል ይላል፡፡

በከተማዋ በየቦታው እንደዚህ ዓይነት ችግሮች እንዳሉ፣ ይህንንም መንግሥት ትኩረት እንዳልሰጠውና የይድረስ ይድረስ የሚደረገው ዕድሳት ዘላቂ መፍትሔ እንደማይሆን ይገልጻል፡፡

ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ጊዜ መኪናው ላይ ጉዳት ደርሶበት የቦዲ ዕድሳት እንዲሁም ለብዙ ጊዜ እጠቀምበታለሁ ያለው ጎማ አልቆበት ላልተፈለገ ወጪ መጋለጡን ለሪፖርተር ያስረዳል፡፡

በአዲስ አበባ አብዛኛውን የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ አሽከርካሪዎች በዚህ ጉዳይ መማረራቸውን የሚያስታውሰው ወጣቱ፣ መንግሥት የሌሎች አገሮችን ተሞክሮ በመውሰድ ጤናማ መንገድ መሥራት ይኖርበታል ብሏል፡፡

መንግሥት ለመንገድ ዝርጋታ ብሎ የሚመድበው ገንዘብ ትልቅ መሆኑን፣ ነገር ግን ከተማዋ ላይ የሚገኙ አብዛኛው መንገዶች ሲቦረቦሩ ማየት የተለመደ መሆኑን ወጣት በረከት ለሪፖርተር ገልጿል፡፡

በተመሳሳይ በታክሲ ሹፍርና ከአሥር ዓመት በላይ የሠሩና አሁን ላይ የራሳቸውን መኪና ገዝተው የሜትር ታክሲ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡት አቶ አብርሃም ያቆብ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ አብዛኛው መንገዶች ለትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ምቹ አይደሉም፡፡

ከአሥር ዓመት በላይ በታክሲ ሹፍርና ለማኅበረሰቡ የትራንስፖርት አገልግሎት ሲሰጡ አንድ ጊዜ ብቻ ከባድ የሆነ ግጭት እንዳጋጠማቸው የሚናገሩት አቶ አብርሃም፣ በወቅቱ ችግሩ የተፈጠረበት ዋነኛ ምክንያት መንገዱ የተበላሸ እንደነበር ያስታውሳል፡፡

ግጭቱ የተፈጠረው ገርጂ አካባቢ መሆኑን የሚያስረዱት አቶ አብርሃም፣ በተለይ ከቦሌ መስመር አንስቶ ገርጂ የሚወስደው መንገድ አባጣ ጎርባጣና አስፋልቱ የተቦረቦረ ስለሆነ፣ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ አሽከርካሪዎችን ማማረሩን ያስረዳል፡፡

በአሥር ዓመት የሥራ ቆይታቸውም በተለያዩ የትራንስፖርት የመስመር ቦታዎች ላይ መሥራታቸውን ያስታወሱት አቶ አብርሃም አቦ፣ ሳሪስ፣ ገርጂ፣ ቃሊቲ፣ ውኃ ልማት፣ ማሠልጠኛ፣ ሚካኤልና ሌሎች ቦታዎች ላይ ከሚገኙ መንገዶች የተቆፋፈሩ እንደሚገኙበት ይናገራሉ፡፡

ደኅንነቱ የተረጋገጠ መንገድ የሚገኘው ከስንት አንድ መሆኑን ጠቅሶ፣ ብዙ ጊዜም መንግሥት የችግሩን ክፍተት ዓይቶ መፍትሔ ከመስጠት ይልቅ በየዓመቱ የመንገዶች ጥገና ማድረጉን አማራጭ ያደርጋል ብለዋል፡፡

ከሁሉም በላይ መንገዱን ምንም ሳያውቁት በፍጥነት እየነዱ የሚጓዙ አሽከርካሪዎች ብዙ ጊዜ ለአደጋ ሲጋለጡ እንደሚያይና ማታ ማታም የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት ከባድ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

ይህም የትራንስፖርት ፍሰቱን ከባድ አድርጎታል የሚሉት አቶ አብርሃም፣ መንግሥት የተቋራጭ ሥራውን የሚሠሩ ተቋሞችን በመከታተል እንዲሁም ተገቢውን በጀት በመመደብ የከተማዋን ውበት ሊጠብቅ ይገባል ብሏል፡፡

የመኪና ዕቃ በተወደደበት ጊዜ በመንገድ ደኅንነት ችግር ምክንያት ያልተፈለገ ወጪ ማውጣት አስፈላጊ አለመሆኑን፣ ከዚህ በፊትም በመንገድ ችግር ምክንያት የመኪናው ዕቃ ተሰብሮ ከፍተኛ ወጪ እንዳወጣ አስታውሷል፡፡

የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ አሽከርካሪዎችና የተገልጋዮች ቁጥር የተመጣጠነ ባልሆነበት አገር፣ የመንገድ ችግሮች ሲኖር በፍጥነት ተመላልሶ መሥራት እንደማይቻልም አክለዋል፡፡

በተመሳሳይ ክረምት በመጣ ቁጥር ከተማዋ ከፍተኛ የትራንስፖርት መጨናነቅ እንደምታስተናግድ፣ በተለይ ከፍተኛ የሆነ ዝናብ በሚዘንብበት ጊዜ አብዛኛው የከተማዋ መንገዶች በቀላሉ የሚቦረቦሩ መሆኑን ለሪፖርተር ያስረዳሉ፡፡

‹‹በዚህ መሠረተ የትራንስፖርት ፍሰቱ ከፍተኛ ጫና ውስጥ ይገባል፤›› የሚሉት አቶ አብርሃም፣ ማንኛውም አሽከርካሪ አንድም ለትራፊክ አደጋ ይጋለጣል፣ በሌላ መልኩ ደግሞ የተሽከርካሪዎች ክፍል በቀላሉ ይጎዳል ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ኢያሱ ሰለሞን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ባለሥልጣኑ በ2016 በጀት ዓመት በከተማዋ በአጠቃላይ 902 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚሸፍኑ ልዩ ልዩ የመንገድ ግንባታና ጥገናዎች ለማከናወን ዕቅድ ይዞ እየሠራ ነው፡፡

በዚህ መሠረት በ2016 ዓ.ም. የሩብ ዓመት አፈጻጸም፣ 36 ኪሎ ሜርት የሚጠጉ የአስፋልት፣ የኮብል ስቶን፣ የጠጠርና ሌሎች የመንገድ ግንባታዎችን በመመልከት እየሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ከዚሁ ጎን ለጎን 272 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ልዩ ልዩ የመንገድ ጥገና ሥራዎችን ማከናወን መቻሉን ገልጸው፣ በአጠቃላይ እስካሁን 3.8 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የመንገድ ጥገናዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡

በተለይ ካለፉት ዓመታት ጀምሮ በግንባታ ሒደት ላይ የሚገኙ የመንገድ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ለአገልግሎት እንዲበቁ ተደርጓል ያሉት ኃላፊው፣ እነዚህንም ፕሮጅቶች ለማጠናቀቅ ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን ገልጸዋል፡፡ 

ከዚህ ጋር በተያያዘ እነዚህ ዘጠኝ የመንገድ ፕሮጀክቶች ከ20 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ያላቸውና 43 ሜትር ወደ ጎን ስፋት የያዙ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

በቀጣይም በሒደት ላይ ያሉ መንገዶችን ለአገልግሎት ለማብቃት ባለሥልጣኑ እየሠራ መሆኑን ገልጸው፣ ጥቅምት 4 ቀን 2016 ዓ.ም. ተመርቀው ለአገልግሎት የበቁ ዘጠኝ የመንገድ ፕሮጀክቶች፣ ሙሉ ለሙሉ በአገር ሀብትና በኢትዮጵያ ባለሙያዎች የተሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

እንደ ኃላፊው ገለጻም፣ መሠረታዊ ፍላጎትን ለማሟላት በስፋት መሥራት የሚጠይቅ ሲሆን፣ ከዚህ አንፃርም በከተማ በተለያዩ ቦታዎች ላይ የመንገድ ፕሮጀክቶች ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡

ቀደም ሲል ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ መንገዶችን በሙሉ አፍርሶ በድጋሚ ለመጠገን ትልቅ መዋዕለ ንዋይ የሚያስፈልግ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በከተማዋ በአሁኑ ወቅት ሰፊ የመንገድ ጥገና ሥራዎች ማከናወን መቻሉን ጠቅሰው፣ በአንዳንድ አካባቢዎች ውስጥ ለውስጥ የሚገኙ መንገዶችን እንደ አዲስ ለመሥራት ሲባል፣ የተቆፈሩ መንገዶች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡

ችግሮችን ለማለፍ ባለሥልጣኑ ትኩረት ሰጥቶ የሚሠራ መሆኑን ገልጸው፣ በከተማዋ በተደጋጋሚ ለብልሽት የሚጋለጡ መንገዶችም አሉ ሲሉ አስረድተዋል፡፡

አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ ዓይነት ችግር የሚከሰተው በዋነኛነት ለውኃ ፍሳሽ ተብለው የተዘረጉ መስመሮች በተለያየ ምክንያት ለጉዳት ስለሚጋለጡና የትኛውም ፍሳሽ በተዘጋጀለት መንገድ ብቻ ስለማይሄድ፣ መንገዶች ሊቦረቦሩ የሚችሉበትን አጋጣሚ ሰፊ እንዳደረገው ገልጸዋል፡፡

ችግሩ በከተማዋ በስፋት እንደሚታይ ጠቅሰው፣ ችግሩን ለመፍታት ባለሥልጣኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ቅንጅት በመፍጠር እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል በተሽከርካሪም ሆነ በእግረኛ መንገዶች የግንባታ ተረፈ ምርቶቾችን እዚያው መተውና ሌሎች ችግሮች ለረዥም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጡ የተገነቡ የከተማዋ መንገዶችን በቀላሉ ተቆፋፍረውና ተቦርቡረው የአገልግሎት መስጫ ጊዜያቸው እንዲያጥር አድርጓል፡፡

አብዛኛዎቹ የከተማዋ መንገዶች ግንባታቸው ከተከናወነ ረዥም ጊዜ እንደሆናቸው፣ መንገዶቹ በመልሶ ግንባታ ደረጃ መሠራት እንዳለባቸው የሚያሳይ መሆኑን ኃላፊው አስታውሰዋል፡፡

ባለሥልጣኑ ያለው ውስን ሀብት ከከተማዋ ከፍተኛ የመሠረተ ልማት ፍላጎት አንፃር ሲታይ፣ ሁሉንም መንገዶች በአንድ ጊዜ አፍርሶ በማሻሻያ ደረጃ መሥራት አስቸጋሪ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በዚህ መሠረት አንዱና ዋናው አማራጭ ተደርጎ የሚወሰደው ላሉት መንገዶች ወቅታዊና መደበኛ ጥገናዎች በማድረግ የአገልግሎት ጊዜያቸውን ማራዘም መሆኑን ሌሎችን ደግሞ በማስፋፍያና በማሻሻያ ደረጃ እየተሠራ እንደሆነ አክለው ገልጸዋል፡፡

በየዓመቱ ለመንገድ ግንባታና ጥገና ከተማ አስተዳደሩ ለባለሥልጣኑ የሚሰጠው በጀት እያደገ መምጣቱን፣ በ2016 በጀት ዓመትም ከከተማ አስተዳደሩና ከብድር የተገኘውን ጨምሮ በአጠቃላይ ከ12 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ተይዞ የግንባታ ሥራዎች እየተከናወነ እንደሚገኝ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

በከተማዋም በቸልተኝነት ምክንያትም ሆነ በሌሎች ችግሮች የተነሳ አብዛኛው መንገዶች ያለ ጊዜያቸው ጉዳት እየደረሰባቸው ሲሆን፣ ይህም ለትራፊክ አደጋ እንዲሁም ለሌሎች ተያያዥ ጉዳቶች ምክንያት በመሆኑ ጉዳዩን ማኅበረሰቡ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡

ሪፖርተርም በአቦ፣ በሳሪስ፣ በቃሊቲ፣ በውኃ ልማት፣ በሃና ማርያም፣ በዘነበ ወርቅ፣ በኢምፔሪያል፣ በገርጂና በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ መንገዶች ተቦርቡረው አንዳንዶቹም ተቆፋፍረው አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ለመመልከት ችሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...