ትልልቅና በርካታ ሕዝብ የሚኖርባቸው የአፍሪካ ከተሞች ያሏቸው የውኃ ልማት ተቋማት፣ አደረጃጀታቸውን ጠንካራ ለማድረግና የሚሰጡትን አገልግሎት ከበቂ የታሪፍ ክፍያ ጋር ለማሻሻል የግሉን ዘርፍ በሚያሳትፉበት ላይ ምክክር ተደረገ፡፡
የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ አገሮች የገንዘብና የውኃ ሚኒስትሮቻቸው የተገኙበት የዋሽ (Water, Sanitary and Hygiene – WASH) የመሪዎች ጉባዔ፣ በገንዘብ ሚኒስቴርና በዓለም ባንክ አዘጋጅነት እየተካሄደ ሲሆን፣ የጉባዔው ዋነኛ ዓላማም ለዋሽ ፕሮጀክቶች በሚቀርቡ ፋይናንሶች ላይ ለመምከር ነው፡፡
ማክሰኞ ኅዳር 4 ቀን 2016 ዓ.ም. የተጀመረው ጉባዔ የግል ባለሀብቶች በውኃ አቅርቦት ላይ ስለሚሳተፉበት ሁኔታ መንገድ ሲመክር ነበር፡፡ መንግሥታት ተበድረውም፣ ከሚሰበስቡት ታክስም ሆነ ከልማት አጋሮች ጋር አብረው በመሥራት በውኃ ልማት ላይ መዋዕለ ንዋይ ያፈሱ እንደነበር ይታወቃል ተብሏል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ፣ የፌዴራልና የክልል መንግሥታት በውኃ ላይ ኢንቨስት ያደርጉ እንደነበር፣ ነገር ግን በዘላቂነት በፋይናንስ ለመደገፍና የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማሳደግ መደረግ ስላለባቸው ጉዳዮች እየተወያዩበት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
‹‹የውኃ ልማት ተቋማቱ ለአስተማማኝ አቅርቦት በሚያስችል ሁኔታ፣ የብድር ብቁነትን ለማረጋገጥ ግምገማ ተሠርቶላቸው፣ የግሉ ዘርፍ በጋራ ኢንቨስት የሚያደርግበት አሠራር መምጣት አለበት፤›› ያሉት አቶ አህመድ፣ የውኃ አቅርቦትን በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ የፋይናንስ ትኩረት መኖር እንዳለበት አስረድተዋል፡፡
የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር)፣ በኢትዮጵያ በኩል አሁን ስላለው አሠራርና ስለወደፊት ዕቅድ በዝርዝር አብረርተዋል፡፡
በሌሎች የአፍሪካ አገሮች በግሉ ዘርፍ በሙከራ ደረጃ እየተሠሩ ያሉ የውኃ ልማት ሥራዎች እንዳሉና ትምህርት እየተወሰደ እንደሆነ ያስረዱት ሚኒስትሩ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የግል ባለሀብቶች እስካሁን በንፁህ ውኃ አቅርቦት ላይ የማሳተፍ አሠራርና ልምድ እንደሌለ ገልጸዋል፡፡
‹‹አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ቦታዎች ውኃን ከጉድጓድ እያወጡ ከሚሸጡ ኢመደበኛ ከሆኑ አካላት ውጪ ሕጋዊነት ኖሯቸው እየሠሩ ያሉ የሉም፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ይህንን ክፍተት ለመሙላት በመንግሥት ኢንቨስመንት ብቻ ሳይሆን የግሉም ባለሀብት መግባት ስለሚኖርበት፣ በቀጣይ እንደ ቤት ሥራ በመውሰድ እየተሠራ መሆኑን የተናገሩት ሀብታሙ (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያ ፖሊሲዋን እየከለሰች መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
‹‹አሁን ባለንበት ደረጃ የግሉን ባለሀብት ወደ ንፁህ ውኃ አቅርቦት ለማምጣት ሕጋዊ መሠረቶችን እያመቻቸን እንገኛለን፤›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ ነገር ግን ተጨባጭ ሊባል የሚችል ደረጃ ላይ እንዳልተደረሰ ገልጸዋል፡፡
እየተከለሰ ያለው ፖሊሲ ከውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ወጥቶ በፕላንና ልማት ሚኒስቴር አማካይነት እየታየ መሆኑንና ወደ ሥራ ለማስገባት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡