- የማኅበራቱን ባንክ ለማቋቋም ፖሊሲ እንዲዘጋጅ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅጣጫ ሰጥተዋል ተብሏል
የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን በአግባቡ ሥራቸውን ያከናወኑ የኅብረት ሥራ ማኅበራትን ማዋሃድና ማፍረስ የሚያስችለውን ሰነድ እያዘጋጀ መሆኑን አስታወቀ፡፡
ኮሚሽኑ ባደረገው ጥናት የኅብረት ሥራ ማኅበራቱ ቁጥር በየጊዜው የመጨመር እንጂ የዜጎችን ተጠቃሚነትና ተደራሽነት በአግባቡ ባለመከናወኑ፣ ማኅበራቱን ለማዋሃድና ለማፍረስ የሚያስችል ሰነድ መዘጋጀቱን፣ የኮሚሽኑ የኅብረት ሥራ ማስፋፊያ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ድሪባ በቀለ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
ኮሚሽኑ ማኅበራቱን ያደራጀበት አዋጅን መሠረት በማድረግ የማዋሃድና የማፍረስ ሥልጣን ቢኖረውም፣ በማኅበራቱ ቅሬታ ተነስቶ ችግር እንዳይፈጠር አዋጁን የክልል ርዕሳነ መስተዳደሮችና የማኅበራቱ አባላት የሚያውቁት የማስፈጸሚያ ሰነድ ማዘጋጀት አስፈላጊ በመሆኑ የተዘጋጀ ነው ብለዋል፡፡
አዋጁ የራሱ መመርያና ደንብ እንዳለው ቢታወቅም ሰነዱ በዋናነት አሠራሩ ወጥ እንዲሆን ያስችለዋል ሲሉ አቶ ድሪባ አስረድተዋል፡፡
በኮሚሽኑ ጥናት መሠረት ብዙዎቹ ማኅበራት ከመጀመሪያው ጀምሮ ውጤታማነታቸው ታምኖበት የተደራጁ አለመሆናቸውን አቶ ድሪባ ገልጸዋል፡፡
አንዳንድ ማኅበራት ደግሞ ባሉበት አካባቢ በርካታ ችግሮች እያሉ አንዱን ችግር ብቻ ማለትም ስኳር ወይም በዓመት አንድ ጊዜ ማዳበሪያ ለማከፋፈል የሚደራጁ ናቸው ብለዋል፡፡
ማኅበራቱ በጣም ከመብዛታቸው የተነሳ ምን እንደሚሠሩ የማይታወቁ፣ አንዳንዶቹ ማኅበራት ከተቋቋሙበት ዓላማ ጋር የማይሄድ ሥራ ላይ የተሰማሩና የአደረጃጀት ችግር ያለባቸው በመሆናቸው፣ ኦዲት ለማድረግም አስቸጋሪ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
እየተዘጋጀ ያለው ሰነድ የማኅበራቱን አባላት ለማብዛትና የካፒታል አቅም ለመፍጠር፣ ሥራ ላይ ያልሆኑትን ደግሞ እንዲፈርሱ ማድረግ፣ ትንንሽ ሥራዎች ላይ የተሰማሩትን አንድ ላይ በማድረግ ማዋሃድ የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ማኅበራቱ የአሠራርና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር እንዳለባቸው የገለጹት አቶ ድሪባ ራሳቸውን ዘመናዊ በማድረግና አሠራራቸውን በቴክኖሎጂ በማዘመን ሸማቾች በየቤታቸው ሆነው እንዲጠቀሙ ማስቻል ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
ገጠር ያሉ ማኅበራት አመራሮቻቸው ያልተማሩ አርሶ አደሮች መሆናቸው፣ እንዲሁም ከተማ ውስጥ ያሉት የተማሩ ቢሆኑም ስለንግድ ዕውቀት ስለሌላቸው አንዱ ችግር ነው ሲሉ አቶ ድሪባ ጠቁመዋል፡፡
እነዚህ አመራሮች ትዕዛዝ የሚሰጡት ትልልቅ ካፒታል ባላቸው ማኅበራት በመሆኑ፣ ገለልተኛ አማካሪ እንዲኖራቸው የሚያስገድድና የኅብረት ሥራ ማኅበራትን ለማጠናከር የሚዘጋጅ ሰነድ ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑን አክለዋል፡፡
በኢትዮጵያ በግብርና፣ በሸማቾች፣ በቁጠባ፣ በዕደ ጥበብ፣ በቤቶችና በሌሎች በርካታ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ሲኖሩ፣ ቁጥራቸው በአጠቃላይ 106‚876 እንደሆነ የኮሚሽኑ መረጃ ያሳያል፡፡
ማኅበራቱ ከ26.9 ሚሊዮን በላይ አባላት በመያዝ በድምሩ 57.9 ቢሊዮን ብር ካፒታል እንደሚያንቀሳቅሱ ይነገራል፡፡ ከ100 ሺሕ በላይ ከሆኑት ማኅበራት ውስጥ ውጤታማ ሥራ እያከናወኑ የሚገኙት ጥቂቶች ብቻ በመሆናቸው፣ ከማኅበራቱ የአደረጃጀት ዓይነት አንዱ ከሆነው የቤቶች የኅብረት ሥራ ማኅበራት አብዛኞቹ ሥራ ላይ አለመሆናቸውን ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ባለሙያ ተናግረዋል፡፡
‹‹የቤቶች ኅብረት ሥራ ማኅበራት የሚደራጁት መሬት ለማግኘት ነው፡፡ የቤት መሥሪያ ቦታ ካገኙ በኋላ ግንባታ ይጀምራሉ፡፡ የተሠራውን ቤት በስማቸው ካርታ ካወጡ በኋላ ማኅበሩ ይረሳል፡፡ ይህን የተረሳ ማኅበር በአዋጁ መሠረት ማፍረስ የሚያስችል ሰነድ ተዘጋጅቷል፤›› ሲሉ ባለሙያው ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡
በተጨማሪም ሁለት በአግባቡ ሲሠሩ ያልነበሩ ማኅበራትን በማዋሀድ አዲስ ማኅበር ለመመሥረት ደግሞ የሁለቱም ማኅበራት የፋይናንስ ሪፖርት ኦዲት ከተሠራ በኋላ፣ የኦዲት ግኝቱን አንድ የፋይናንስ ቋት ውስጥ በማድረግ ካፒታላቸው እንዲጠናከር ይደረጋል ሲሉ ባለሙያው አብራርተዋል፡፡
አዲሱ ሰነድ ይፋ ከተደረገ በኋላ ማኅበራቱን ለማፍረስም ሆነ ለማዋሃድ ሒደቱ ከሦስት እስከ አምስት ዓመታት ሊፈጅ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም የኅብረት ሥራ ማኅበራት የራሳቸውን ባንክ ለመመሥረት ዕቅድ እንዳለ ያስረዱት አቶ ድሪባ፣ ነገር ግን ተግባራዊ ለማድረግ ፖሊሲ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በዚህም መሠረት ከሌሎች ንግድ ባንኮች የተለየ ሆኖ መንቀሳቀስ የሚያስችል ፖሊሲ እንዲዘጋጅ፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የፖሊሲ አቅጣጫ መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ተጠሪነቱ ለግብርና ሚኒስቴር ሲሆን፣ ከ100 ሺሕ በላይ የኅብረት ሥራ ማኅበራት በተጨማሪ 401 የኅብረት ሥራ ዩኒየንና አምስት ፌዴሬሽኖች አሉት ተብሏል፡፡