Monday, November 27, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የአገር ጉዳይ የሁሉም ዜጎች የጋራ ኃላፊነት ነው!

በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሙሉ፣ ለአገራቸው መፃኢ ዕድል ስኬት ሲሉ የሚፈለግባቸውን ሁሉ እንዲያደርጉ የሚፈለጉበት ወሳኝ ጊዜ አሁን ይመስላል፡፡ በኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ የፖለቲካ ዘመን ውስጥ ያለፉት ሃምሳ ዓመታት በርካታ ክስተቶች የታጨቁባቸው ናቸው፡፡ በወርኃ የካቲት 1966 ዓ.ም. ድንገት እንደ ደራሽ ውኃ ኢትዮጵያን ያጥለቀለቀው አብዮት፣ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ሥርዓት ብቻ ሳይሆን የዘውድ አገዛዝን ከሥሩ መንግሎ ከጣለ ሃምሳ ዓመታት ሊቆጠሩ ጥቂት ወራት ቀርተዋል፡፡ ኢትዮጵያን ከባላባታዊ የፊውዳል ሥርዓት ወደ ሶሻሊስት አስተዳደር ለመለወጥ በወቅቱ ትውልድ የተለኮሰው አብዮት፣ አዋላጆቹንም ሆነ ተከታዮቻቸውን በደም ለውሶ እንዳይሆኑ ሆኖ ካለፈ በኋላ በርካታ መከራዎችና ሥቃዮች ተቆጥረዋል፡፡ የማርክሲዝም ሌኒኒዝም ርዕዮተ ዓለማዊ ቅኝት ውስጥ ሆነው በመስመር ልዩነት ምክንያት በቀይ ሽብርና በነጭ ሽብር ከፈሰሰው ደም በኋላ የተከተለው እስራት፣ ሥቃይ፣ መከራና ስደት የብዙዎችን ቤት አንኳኩቷል፡፡ መላ አገሪቱን የሐዘን ማቅ አስለብሶም ለተራዘመ ጦርነትና ፍጅት ዳርጓል፡፡ የዚያ አስከፊ ወቅት ጦስ አሁንም አለቅም እንዳለ ነው፡፡

ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ውስጥ በርካታ ጦርነቶች፣ ግጭቶች፣ ድርቆችና ረሃቦች በርካቶችን አርግፈዋል፡፡ ለልማትና ለዕድገት መዋል የነበረበት የደሃ አገር ወጣት ኃይልና ሀብት እሳት ውስጥ እንደገባ ፕላስቲክ ቀልጦ ቀርቷል፡፡ በዓለም በአንድ ወቅት የተረጋጉ ከሚባሉ አገሮች ተርታ ስሟ ይጠራ የነበረው ኢትዮጵያ፣ ላለፉት ሃምሳ ዓመታት ግን በተደጋጋሚ የምትታወቀው በአሉታዊ ነገሮች ነው፡፡ ለንጉሠ ነገሥቱ ሥርዓት መውደቅ እንደ ገፊ ምክንያት ተደርጎ ይቆጠር የነበረው የሰሜን ኢትዮጵያ ድርቅ፣ በየአምስትና በየአሥር ዓመቱ እየተከሰተ የብዙዎችን ሕይወት በረሃብ በማርገፉ ያስገኘላት ትሩፋት የገጽታ መጉደፍ ነው፡፡ በዓለም ታዋቂ በሆኑ የእንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት ‹‹ረሃብ›› የሚለው ስያሜ የ‹‹ኢትዮጵያ›› ማጣቀሻ መደረጉ ብዙዎችን ሲያንገበግብ የኖረ ነው፡፡ በተለይ ለኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት ዕርዳታ ከሚለግሱ አገሮች አንዷ በሆነችው አየርላንድ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች፣ ኢትዮጵያ ከተደጋጋሚ የድርቅ አደጋ ለመላቀቅ አለመቻሏን አስመልክቶ ይቀርቡ የነበሩ ሸንቋጭ ሒሳዊ መጣጥፎችና ዘገባዎች አንገት ያስደፉ ነበር፡፡ ‹‹ኢትዮጵያውያን በዕርዳታ ምግብ ተወልደው፣ አድገው፣ ተድረው የወለዷቸውን ልጆች ያሳድጋሉ…›› እየተባለ ኢትዮጵያ መዘባበቻ መደረጓ ብዙዎችን አሳፍሯል፡፡

ምንም እንኳ ጊዜው እየነጎደ ቢሄድምና አንዳንድ ተስፋ ሰጪ የልማት ጅምሮች እየታዩ ቢሆንም፣ በብሔራዊ ጉዳዮች ስምምነት መፍጠር ባለመቻሉ አሁንም ኢትዮጵያ የግጭት የስበት ማዕከል እየሆነች መቀጠሏ ለዜጎችም ሆነ ለውጭ ታዛቢዎች እንቆቅልሽ ነው፡፡ የውስጥ ችግሮቻቸውን በይደር አቆይተው ተስፋፊዎችንና ወራሪዎችን በጀግንነት እየመከቱ የአገር ፍቅር ስሜትን የውኃ ልክ ማሳየት የቻሉ ኢትዮጵያውያን በተፈጠሩባት አገር፣ ልዩነቶችን በማጥበብ ግጭቶችን ማስወገድና በተባበረ አንድነት ለልማት መነሳት አለመቻል የትውልዱን ታማኝነት ጥያቄ ውስጥ እየተከተተ ነው፡፡ ከአንድ አምባገነን ወደ ሌላ አምባገነን የመሸጋገርን የታሪክ አሽክላ ወደ ጎን በማለት፣ ለአፍሪካውያን ጭምር ተምሳሌት መሆን የምትችል ኢትዮጵያን ማሳየት ሲያቅት ለምን ማለት ካልተቻለ መከራው ይቀጥላል ማለት ነው፡፡ ለአፍሪካውያንና ለመላው ዓለም ጥቁር ሕዝቦች ዓይን ገላጭ የነበረውን ታላቁን የዓድዋ ድል የተጎናፀፈች ታላቅ አገር ኢትዮጵያ፣ በተለይ በአፍሪካውያን ፊት ከሚያስገምታት የእርስ በርስ ግጭት ውስጥ መውጣት ሲያቅታት በጣም ያስደነግጣል፡፡

ኢትዮጵያውያን ፖለቲከኞች በሙሉ አንድ ሊገነዘቡት የሚገባ ቁምነገር ቢኖር፣ ከዚህ ቀደም በተለያዩ መንገዶች ሥራ ላይ እንዲውሉ ተሞክረው የከሸፉ ተግባራትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ስለማቆም ነው፡፡ ከአንድ ስህተት ወደ ሌላኛው ስህተት ሲደረግ የነበረው አሰልቺና አስመራሪ ሒደት በፍጥነት ቆሞ፣ በጋራ መግባባት ላይ የተመሠረቱ ለአገር ልማትና ዕድገት የሚረዱ ጉዳዮች ላይ ቢተኮር መልካም ነው፡፡ ለዚህ ተግባራዊነት ደግሞ ለመቀራረብ፣ ለመነጋገርና ለመደራደር የሚያስችሉ በርካታ አገር በቀል ዕውቀቶችን ከዘመናዊው ጋር በማዳበል ወደ አማካዩ ሥፍራ መድረስ አያቅትም፡፡ ከዚህ ውጪ እንደ ባቢሎን ግንበኞች መሆን ያተረፈው ነገር ቢኖር የማያባራ ጭቅጭቅ፣ ግጭት፣ ጥላቻ፣ ቂም በቀልና በጭካኔ መፋጀት ነው፡፡ ያለፉት ሃምሳ ዓመታት የፖለቲካ ጉዞ በዚህ ዓይነቱ አላስፈላጊ ትርምስ ውስጥ እየቀጠለ ስለሆነ፣ አሁንም በርካታ ሚሊዮኖች የረባ ምግብና መጠለያ ማግኘት ተስኗቸዋል፡፡ አንድ ግጭት አባርቶ ወዲያው በሌላ እየተተካ ዜጎች ኑሮ ገሃነመ እሳት እየሆነባቸው ነው፡፡ በአዲስ መንፈስና በአዲስ ተስፋ ሰላም ለማስፈን መነሳት የግድ ይላል፡፡

ኢትዮጵያ ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑ ሁሉም ነገሮች እያሏት ምንም እንደሌላት በድህነት ተቆራምዳ ማየት ያሳዝናልም፣ ያሳፍራልም፡፡ ከዓለም አበዳሪ አገሮችና ተቋማት በተለይም ከቻይና ያገኘችውን ብድር ዕዳ ለመክፈል በጣም አጠራጣሪ አገር ተደርጋ ስትፈረጅ፣ ፍረጃውን እንደ አንድ ሰሞን የቡና ወሬ አድርጎ ለማለፍ መሞከር የሚያስከትለው መዘዝ ከባድ ነው፡፡ ይልቁንም ከዚህ በፊት ለተፈጠሩ ስህተቶችና ችግሮች በሙሉ ይቅር ተባብሎ በመተማመን መንፈስ ሰላም ለማስፈን ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያ በጣም ሰፊና ለም ያልታረሱ መሬቶች፣ በአፍሪካ አንደኛ ሊያደርጋት የሚችል የውኃ ሀብት፣ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የወጣት ኃይል፣ በርካታ ማዕድናት፣ የቱሪዝም መስህቦችና ሌሎች የተፈጥሮ በረከቶች ታቅፋ ስትራብና ስትጠማ፣ እንዲሁም የውጭ ዕዳ መክፈል ተስኗት ተንገዳገደች ሲባል፣ ልጆቿ ለሃምሳ ዓመታት ያህል ከቀጠለው የእርስ በርስ ንትርክና ፍጅት መላቀቅ አልቻሉም ተብሎ ሲለፈፍና ለጎረቤት አገሮች ጭምር ሥጋት ስትሆን ቆም ብሎ በሰከነ መንገድ መምከር ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ቀደም የተደረጉ ነገሮች ሁሉ ካልሠሩ አዲስ ዘዴ መቀየስ ያዋጣል፡፡

አገራዊ የምክክር ኮሚሽን በአገራዊ ሁለንተናዊ ጉዳዮች ላይ ለመነጋገር የሚያስችሉ መደላድሎችን እያመቻቸ መሆኑ በተደጋጋሚ እየተነገረ ነው፡፡ አገር የሚመራው መንግሥትም በመላ አገሪቱ ታጥቀው ከሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ጋር ለመነጋገርና ለመደራደር የሚያስችል መደላድል ማመቻቸት ይጠበቅበታል፡፡ በታንዛኒያ ከኦነግ ሸኔ (የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ከሚባለው ጋር) እየተደረገ ያለው ንግግር በመልካም ሁኔታ እየተካሄደ እንደሆነ በስማ በለው እየተሰማ ሲሆን፣ በአማራ ክልልም ሆነ በሌላ አካባቢ ካሉ አማፂያን ጋር በተመሳሳይ ንግግር ተጀምሮ ወደ ድርድር ቢገባ ለአገርም ሆነ ለሕዝብ ዕፎይታ ያስገኛል፡፡ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖችም፣ አሸናፊ የሌለበት ውጊያ በአስቸኳይ ቆሞ ሁሉን አሳታፊ የፖለቲካ ምኅዳር እንዲፈጠር የሚፈለግባቸውን ሚና ይወጡ፡፡ ከቅርብም ሆነ ከሩቅ በመሆን ከወላፈኑ ፈንጠር ብሎ የትጥቅ ፍልሚያን ማበረታታት፣ በቅርቡ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ያስገኘውን አደገኛ ውጤት ማንም አይዘነጋውም፡፡ የአገር ጉዳይ የሁሉም ዜጎች ኃላፊነት እንደሆነ በመገንዘብ አላስፈላጊ ጭቅጭቆችንና ግጭቶችን መግታት ይገባል፡፡ በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባዕድ መሆን ስለሌለበት፣ በብሔራዊ ጉዳዮች ላይ ዜጎች የጋራ ኃላፊነታቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል!   

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ ሲኒመር ትሬዲንግ...

የባህር በር በቀጣናዊ ተዛምዶ ውስጥ

በበቀለ ሹሜ መግቢያ በ2010 ዓ.ም. መጋቢት ማለቂያን ይዞ ዓብይ አህመድ በጠቅላይ...

ሥጋት ያስቀራል ተብሎ የሚታሰበው የጫኝና አውራጅ መመርያ

በአዲስ አበባ ከተማ በሕገወጥ መልኩ በመደራጀት ማኅበረሰቡ ላይ እንግልትና...

ማወቅ ወይስ አለማወቅ – ድፍረት ወይስ ፍርኃት?

በአሰፋ አደፍርስ ወገኖቼ ፈርተንም ደፍረንም የትም አንደርስምና ለአገራችን ሰላምና ክብር...

ከድህነት ወለል በታች ከሆኑት አፍሪካዊያን ውስጥ 36 በመቶው በኢትዮጵያ ናይጄሪያና ኮንጎ እንደሚገኙ ተጠቆመ

‹‹ለሺሕ ዓመት በድህነት ውስጥ የነበረች አገርን በአሥር ዓመት ልንቀይር...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሔ ይፈለግላቸው!

መንግሥት ከኦነግ ሸኔ ጋር በታንዛኒያ ዳሬሰላም ከተማ ሲያካሂድ የነበረው ንግግር ያለ ውጤት መጠናቀቁን ካስታወቀ በኋላ፣ በኦሮሚያ ክልልም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ሰላም ለማስፈን የነበረው ተስፋ...

ኢትዮጵያን ከግጭት ቀጣናነት ማላቀቅ የግድ ነው!

ፍሬ አልባ ፖለቲካዊ ልዩነቶች ወደ ግጭት እያመሩ ለአገርና ለሕዝብ የማያባራ መከራ ሲያቀባብሉ፣ ከትናንት ስህተቶች ለመማር ፈቃደኛ ያልሆኑ ፖለቲከኞችና ተከታዮቻቸው በእሳት ላይ ቤንዚን እያርከፈከፉ ጠማማ...

አስጨናቂውን የኑሮ ውድነት የማርገብ ኃላፊነት የመንግሥት ነው!

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ማክሰኞ ኅዳር 4 ቀን 2016 ዓ.ም. ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ካቀረቡላቸው ጥያቄዎች መካከል አንደኛው የኑሮ ውድነትን በተመለከተ ነበር፡፡...