Thursday, December 7, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናጠቅላይ ሚኒስትሩ በባህር በር ጉዳይ ግጭት እንዳይከሰት እንነጋገር ሲሉ ጥሪ አቀረቡ

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በባህር በር ጉዳይ ግጭት እንዳይከሰት እንነጋገር ሲሉ ጥሪ አቀረቡ

ቀን:

ከቅርብ ወራት ወዲህ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ተነስቶ አጀንዳ የሆነውን የባህር በር ጉዳይ ከጎረቤት አገሮች ጋር ግጭት እንዳይከሰት መነጋገር ያስፈልጋል ሲሉ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጥሪ አቀረቡ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማክሰኞ ኅዳር 4 ቀን 2016 ዓ.ም. በፓርላማው ተገኝተው ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ መስከረም 28 ቀን 2016 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮችና ለፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ባቀረቡት የፌዴራል መንግሥት ዓመታዊ ዕቅድ የመክፈቻ ንግግር ላይ፣ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹ወንድሞቻችን ጉዳዩን በከፋ መንገድ ከማየት ቁጭ ብሎ አጀንዳውን መነጋገርና በቢዝነስ ሕግ ማየት ጥሩ ነው፡፡ እኛ ግጭት አላልንም፣ ግጭት እንዳይመጣ እንነጋገር፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ሰው ከተራበ መጥፎ ነው፣ ራሱን ይበላል፣ ወደ ረሃብና ችግር እንዳንሄድ ተረዱን፣ የዓለም መንግሥታትም ኢትዮጵያ ያልተገባና ከሕግ ወይም ከቢዝነስ አሠራር ውጪና ሰላምን ከሚያረጋግጥ መንገድ ውጪ ጠይቃ ከሆነ ያነጋግሩንና እረፉ ይበሉን፣ እንተወዋለን፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የባህር በር ጥያቄን በሚመለከት ብዙ ዓይነት ንግግሮች፣ ትንበያዎች፣ ሴራዎችና ትንተናዎች እየተሰሙ መሆናቸውን አብራርተው፣ ‹‹የተከበረው ምክር ቤት፣ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ በአፍሪካ ቀንድ ያሉ አገሮች፣ የአፍሪካ ወንድሞቻችን፣ በምዕራብና በምሥራቁ የዓለም ክፍል ያሉ አገሮች እንዲገነዘቡ የምፈልገው የእኛን እውነተኛ ፍላጎትና ችግር ነው፤›› ብለዋል፡፡ በመሆኑም በጉዳዩ ላይ ሁሉም በቀና ልብ ተባባሪ እንዲሆን አደራ ሲሉ አሳስበዋል፡፡

የዛሬ 30 ዓመት ገደማ ኢትዮጵያ የሁለት ወደቦች ባለቤት እንደነበረችና በዚያ ጊዜ የአገሪቱ ሕዝብ 46 ወይም 47 ሚሊዮን እንደሚሆን፣ የአገር ውስጥ ምርቷም አሥር ቢሊዮን ዶላር ብቻ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

ከ30 ዓመታት በኋላ ከሁለት ወደቦች ባለቤትነት በንግድ ሕግ መሠረት አስረድተው፣ የአሰብና የጂቡቲ ወደቦችን በገንዘቧ ወደ የምትጠቀምበት ደረጃ ዝቅ ብላ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ይሁን እንጂ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ግጭት በማጋጠሙ ሁለተኛውን የአሰብ ወደብ በማጣቷ የጂቡቲ ወደብ ላይ ብቻ ተንጠልጥላ መቅረቷን አብራርተዋል፡፡

የጂቡቲን ወደብ ኢትዮጵያ ባሻት መንገድ እንድትጠቀም የጂቡቲ ሕዝብና መንግሥት ላደረገው አስተዋጽኦ፣ የኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ ሕዝብ ዕውቅና ይሰጡታል ብለዋል፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ በጂቡቲ መንግሥትና ሕዝብ ላይ ምንም ዓይነት ሥጋትም ሆነ ጥርጣሬ እንደሌላት ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን ጂቡቲም ሆነች ሌሎች እንዲገነዘቡት የሚፈለገው በጂቡቲ መቀመጫቸውን ያደረጉ የዓለም ትልልቅ አገሮች ቢጣሉና በጂቡቲ ባሏቸው የጦር ሠፈሮች መታኮስ ቢጀምሩ፣ ኢትዮጵያ ነዳጅ ወይም ማዳበሪያ ማስገባት እንደማትችል አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም በየመንና ጂቡቲ መካከል ባለው ቅሬታ ምክንያት የየመን ኃይሎች ካምፕ ፍለጋ ወደ ጂቡቲ ተኩስ ቢጀምሩ፣ ኢትዮጵያ አሁንም ወደብ መጠቀም አትችልም ብለዋል፡፡ ‹‹የጂቡቲ መንግሥትና ሕዝብ የሚያደርገው ጫና ሳይሆን፣ የጂኦ ፖለቲካው መሳከርና አንዳንድ ኃይሎች በርቀት የመተኮስና የመግደል አቅም በመፍጠራቸው፣ ኢትዮጵያ ይህ ችግር ቢገጥማት 120 ሚሊዮን ሕዝብ ምን እናደርገዋለን፤›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

‹‹አልሸባብ ሶማሊያን አስቸገረና አፈረሰ ሲባል ኢትዮጵያ ልጆቿ ሞተዋል፣ ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ ተቸግሬያለሁ ስትል ወንድም ጎረቤቶች ችግርሽ ምንድነው ብሎ ማድመጥና መወያየት ጠቃሚ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ባለፉት 20 ዓመታት የኢትዮጵያ ወጪና ገቢ በ20 እጥፍ ዋጋው መጨመሩን፣ የሕዝቡ ቁጥር 120 ሚሊዮን መድረሱን፣ ብሔራዊ ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት ከ160 ቢሊዮን ዶላር በላይ ማለፉን ጠቁመዋል፡፡ በዚህ የኢኮኖሚ ዕድገት ልክ የሚጣጣም መሠረተ ልማት ከሌለ የጊዜ ጉዳይ እንጂ ችግር መምጣቱ አይቀሬ መሆኑን አክለዋል፡፡

‹‹በቢዝነስ ሕግ እንወያይ እንመካከር›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹ቀይ ባህር ያስፈልገኛል፣ ጠቃሚ ነው የማይል ዓለም አለ እንዴ? ከምሥራቅ ጫፍ እስከ ምዕራብ ጫፍ እኮ እዚህ ሠፈራችን ውስጥ ናቸው፡፡ ምነው እኛ ስንፈልገው ነውር ሆነ?›› ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

‹‹በዚህ በኩል ዓለም ያስፈልገኛል ብሎ ሲናገር አግባብ አይደለም በማይባልበት ሁኔታ ውስጥ እናንተ ደሃ ናችሁና አይመለከታችሁም ካልሆነ በስተቀር፣ ቀይ ባህር ያስፈልገኛል ብሎ ባህር የማይጠብቅና የባህር ላይ ውንብድና አደጋ ነው ብሎ የማይጠብቅ ዓለም የለም፤›› ብለው፣ ለኢትዮጵያውያን ደግሞ ብቸኛ መተንፈሻ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ይህን የባህር በር ጉዳይ አዲስ ጥያቄ አድርገው የሚያወሩ ሰዎች እንዳሉ ጠቅሰው፣ ‹‹ከዚህ በፊት የባህር ኃይል ስንገነባ አልነበረም ወይም? ነው ወይስ በዚያ ጊዜ ዩቲዩብ አልነበራቸውም፤›› በማለት፣ ‹‹የባህር ኃይል ስንገነባ እኮ ሌላ አጀንዳ የለንም፡፡ የባህር ኃይል እንገነባለን ነው፣ ግልጽ እኮ ነው አጀንዳው፤›› ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኤርትራን ሉዓላዊነት ለመድፈር ነው የሚሉም እንዳሉ ገልጸው ‹‹እኛ ህዳሴ ግድብን የሠራነው የሱዳን ሉዓላዊነትን ለመዳፈር ነው እንዴ? እንደዚያ ይታመናል? እኛ ህዳሴን ያለማነው ኢነርጂ ለማምረትና ውኃውን ለወንድሞቻችን ለክተን ለመላክ ነው፡፡ ስለዚህ ህዳሴ ግድብ ለግብፅም፣ ለሱዳንም፣ ለኢትዮጵያም ሲሳይ እንዲሆን እንጂ እንዲጎዱ አንፈልግም፣ ቀይ ባህርም እንደዚሁ ማለት ነው፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

‹‹የማንንም ሉዓላዊነት የመንካት፣ ማንንም የመውረር ፍላጎት የለንም፣ በቢዝነስ ሕግ ግን የማያወላዳ ምርጫ እንፈልጋለን፤›› ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ወደ ኤርትራ፣ ሶማሊያ፣ ጂቡቲ፣ ኬንያ ወይም ወደ ሌላ ጎረቤቶች አንድ ጥይት የመተኮስ ፍላጎት እንደሌላትና በሉዓላዊነታቸው ላይ ጥያቄ የላትም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹ኢትዮጵያ እያለች ያለው በአፍሪካ ምርጥ አየር መንገድ አለን እሱን እንጋራና ውኃ አጋሩን፣ በአፍሪካ አንደኛውን ግድብ ገንብተናል እሱን እንጋራና ወደብ አጋሩን ተያይዘን እንደግ እያልን ነው፤›› ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የጦርነት ሥጋት እንደሌለባት፣ ከጎረቤት አገሮችም የሆነ ኃይል ተነስቶ ኢትዮጵያን ሊመታ ይችላል የሚል ሥጋት አለመኖሩን ገልጸው፣ ኢትዮጵያን ለመታደግ ከበቂ በላይ አቅም መኖሩን ተናግረዋል፡፡

‹‹ማንንም አንወርም፣ የመውረር ፍላጎት የለብንም፡፡ ረሃቡ ሳይመጣ፣ ችግሩ ሳይመጣ፣ መከራው ሳይመጣ፣ ተወያይተን መፍትሔ እናብጅ፡፡ ችግር ከመጣ ሕግ አይሠራም፣ ረሃቡ ከመጣ ምን ሕግ አለ? እኛ ምግብ ማስገባት ቸግሮን ከራበን የሚሠራ ሕግ አይኖርም፣ ያገኘነውን በልተን እንቋቋማለን፤›› ብለዋል፡፡ ይህ የሰው ልጆች ሁሉ ባህሪ በመሆኑ ያ ሳይመጣ ቀድሞ መነጋገርና ሕጋዊ መፍትሔ ማበጀት ጠቃሚ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...