የኢትዮጵያ አየር መንገድ ድምራቸው 67 የሚደርሱ አውሮፕላኖች ግዥ ለመፈጸም ተስማማ፡፡ የአውሮፕላኖቹ ምርት እንዲጀመር ከአሜሪካው አውሮፕላን አምራች ኩባንያ ቦይንግ፣ የግዥ ትዕዛዝ መፈጸሙን አየር መንገዱና ቦይንግ ትናንት አስታውቀዋል፡፡
ስምምነቱ የተፈጸመው እየተካሄደ ባለው የዱባይ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ዘርፍ ዓውደ ርዕይ ላይ ሁለቱም ድርጅቶች በሚሳተፉበት ወቅት ነው፡፡
በስምምነቱ መሠረት አሥራ አንድ የ787 ድሪም ላይነር (787 Dreamliner) ሞዴሎች፣ ሃያ 737 ማክስ (737 MAX) እንዲሁም 36 ዓይነታቸው በግልጽ ያልተለዩ ጀቶች ግዥ ይፈጸማል፡፡
ተጨማሪ ሃያ የማክስ አውሮፕላኖች ግዥ ስምምነት የተደረገው ተመሳሳይ ቦይንግ 737-ማክስ-8 አውሮፕላን በቢሾፍቱ (ደብረ ዘይት) ልዩ ስሙ ኤጀሬ ተብሎ በሚጠራው ቦታ መጋቢት 2012 ዓ.ም. ከተከሰከሰ ከአራት ዓመታት በኋላ ነው፡፡
አውሮፕላኖቹ ተመርተው በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ አየር መንገዱ እንደሚረከብ ሪፖርተር ከአየር መንገዱ ያገኘው መረጃ ያሳያል፡፡
ከአፍሪካ አየር መንገዶች እስከዛሬ ይኼን ያህል ቁጥር ያለው አውሮፕላን ግዥ በአንድ ጊዜ አለመፈጸሙንና የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመጀመርያ መሆኑን ቦይንግ ባወጣው መግለጫ ጠቅሷል፡፡
ዋጋዎቹን ለማወቅ ሪፖርተር ያደረገው ጥረት ያልተሳካ ሲሆን፣ የአውሮፕላኖቹ ዋጋ የሚወሰነው ርክክቡ በሚደረግበት ወቅት በሚኖረው ተመን እንደሚሆን የአየር መንገዱ ኃላፊዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
አዳዲሶቹ አውሮፕላኖች የተሻሻሉ ሞዴሎች መሆናቸውና በውጤታማ የነዳጅ አጠቃቀም 20 በመቶ በካይ ጋዞችን ልቀት እንደሚቀንሱና 50 በመቶ የድምፅ ብክለት እንደሚቀንሱ ተነግሯል፡፡
ከአንድ ዓመት በፊት የአሜሪካ መንግሥት ኤግዚም ባንክ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ የ281 ሚሊዮን ዶላር የብድር ዋስትና መስጠቱ ይታወሳል፡፡ ይህም ገንዘብ አየር መንገዱ ከቦይንግ ለሚገዛቸው አውሮፕላኖች መግዣ ሲሆን ይህም በቦይንግ በኩል ለ1,600 አሜሪካኖች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ተገልጾ ነበር፡፡ በወቅቱ በስምምነቱ መሠረት አየር መንገዱ አውሮፕላኖቹን ከተረከበ በኋላ እየሠራበት ዕዳውን ይከፍላል ማለት ነው፡፡
ይሁን እንጂ ባለፈው ዓመት የተደረገው ስምምነት አሁን የታዘዙትንም አውሮፕላኖች ወጪ ማካተት አለማካተቱን ሁለቱም ድርጅቶች ይፋ አላደረጉም፡፡
የገንዘብ ሚኒስቴር ሰኔ 2015 ዓ.ም. ያወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ አየር መንገዱ ወደ 522 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ብድር አለበት፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአሁኑ ሰዓት 147 አውሮፕላኖች ያሉት ሲሆን፣ ከቦይንግ የታዘዙት 67ቱ በጥቂት ዓመታት ሲደርሱ ቁጥሩ በግማሽ ያድጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይሁን እንጂ አየር መንገዱ አሁን ባለው የቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ሁሉንም አውሮፕላኖች ማስተናገድ መቻሉ ላይ ጥያቄ ያለ ሲሆን ተጨማሪ ማስፋፊያ ሥራዎች ይደረጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡