የኤችአይቪ ኤድስ ሥርጭት ከቦታ ቦታ ቢለያይም እየጨመረ ስለመምጣቱ ይነገራል፡፡ አዲስ አበባም የችግሩ ሰለባ ከሆኑ የአገሪቱ ክፍሎች አንዷ ናት፡፡ ሲስተር ፈለቀች አንዳርጌ በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የኤችአይቪ ኤድስ ዘርፍ ምላሽ ማስተባባሪያ ጽሕፈት ቤት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ናቸው፡፡ በከተማዋ የኤችአይቪ ሥርጭትን በተመለከተ ታምራት ጌታቸው አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- የአዲስ አበባ ከተማ በኤችአይቪ ሥርጭት ስንተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች?
ሲስተር ፈለቀች፡- ሥርጭቱ በአገር አቀፍና በክልሎች የተለያየ ገጽታ ያለው ሲሆን፣ እንደ አገር አቀፍ ባለፉት ዓመታት በተሠራው ሰፊ ሥራ አሁን ላይ እንደወረርሽኝ የሚቆጠር አይደለም፡፡ በክልሎች ግን የተለያየ ገጽታ አለው፡፡ በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በሽታው ይታያል፡፡ በተደረጉ ልየታዎችና በተሠሩ አገር አቀፍ ጥናቶችም ከጋምቤላ ቀጥሎ አዲስ አበባ በሁለተኛነት የቫረሱ ሥርጭት የሚታይባት ከተማ ነች፡፡
ሪፖርተር፡- እ.ኤ.አ. በ2025 የሚያበቃ 959595 የሚል ፕሮጀክት ተጀምሮ ሊጠናቀቅ ጥቂት ዓመታት ቀርተውታል፡፡ ፕሮጀክቱ በአዲስ አበባ ምን ደረጃ ላይ ደርሷል?
ሲስተር ፈለቀች፡- ፕሮግራሙ ዓለም አቀፍ ነው፡፡ እንደ አገርም ከዚያም እንደ ከተማ የሚተገበር ነው፡፡ 95 በመቶ እንዳይያዙ፣ 95 በመቶ የተያዙትን ፈልጎ ማግኘት፣ 95 በመቶ የተገኙትን በአግባቡ ክትትል በማድረግ እስከ 2025 የኤችአይቪ ሥርጭትን ወደ 90 በመቶ በማውረድ ከቫይረሱ ነፃ የሆነ ትውልድን ለመፍጠር የተቀረጸ ፕሮግራም ነው፡፡ ከዚህ አንፃርም በከተማችን በተሠሩ ሥራዎች በዓመት የሚያዙት ሰዎች ከ555 ያልበለጠ ሲሆን፣ የተያዙትን ፈልጎ የማግኘት ሥራ ደግሞ የዕቅዱን 85 በመቶ ሊሠራ ችሏል፡፡ የተገኙትን መድኃኒት በማስጀመር 95 በመቶ እየተከናወነ ነው፡፡ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘውና አሁንም ከፍተኛ ሥራ የሚጠይቀው ከእናት ወደ ልጅ በመተላለፍ የሚወለዱ የሕፃናት ቁጥር ሲሆን፣ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት 12 በመቶ ብቻ ነው ማሳካት የተቻለው፡፡ ይህንን ግብ ከማሳካት አንፃር እያጋጠሙ ያሉ ችግሮች የሴተኛ አዳሪዎች በሥራው ባህሪ ምክንያት ከቦታ መቀየር ይገኝበታል፡፡ እንገለላለን በሚል ፍራቻ፣ ድራግ ተጠቃሚዎች ደግሞ አንድ መርፌ ለብዙ በመጠቀም፣ ከማረሚያ ቤት ታርመው የሚወጡ በአብዛኛው ተጋላጭ ተብለው የተለዩትን የማኅበረሰብ ክፍሎች ማግኘት ከተግዳሮቶቹ ይገኙበታል፡፡
ሪፖርተር፡- ለኤችአይቪ መቀነስ ወይም መጥፋት ያለው የፖለቲካ ቁርጠኝነት ትልቁን ድርሻ ይይዛል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ በዚህ ላይ ምን እየሠራ ይገኛል?
ሲስተር ፈለቀች፡- ኤችአይቪ መንግሥት ለማኅበረሰብ ከሚሰጣቸው የጤና ጉዳዮች አንዱ ነው፡፡ በተለይ አምራቹን ክፍል የሚያጠቃ በመሆኑ ልዩ ትምህርት ሰጥቶናል ማለት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ከ1995 ዓ.ም. በፊት መድኃኒቱ ባለመኖሩ ብዙ ሕይወት ጠፍቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ዛሬ ግን የበሽታው ሕክምና በነፃ እየቀረበ ይገኛል፡፡ በሕክምናውም ማንም ችግር የሚያይበት አይደለም፡፡ ይህ የመጣው በአመራሩና በፖለቲካ በመጣ ቁርጠኝነት ነው፡፡ በሽታው የማይነካካው መሥሪያ ቤትና ቢሮ የለም፡፡ በከተማችን የሚገኙ 63 ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ለመከላከል የሚወጡ መመርያዎችንና ደንቦችን እንደ አንድ አመራር ሆነን ከተገበርን በመቀነሱ ያሳየነውን ቁርጠኝነት ፈጽሞ በማጥፋቱም ትልቅ ስኬት ማስመዝገብ ይቻላል፡፡
ሪፖርተር፡- በአዲስ አበባ የኮንዶም ሥርጭት ምን ይመስላል?
ሲስተር ፈለቀች፡- ኮንዶም የኤችአይቪ ሥርጭትን ለመቀነስ ከሚተገበሩት የመከላከያ መንገዶች ዋነኛና ትልቁን ድርሻ የሚይዝ ነው፡፡ አንድ ሴተኛ አዳሪም በዓመት 361 ኮንዶሞችን ትጠቀማለች ተብሎ ይገመታል፡፡ ቀድሞ ከተለያዩ አካላት ድጋፍ ይደረግበት ስለነበር በነፃ በቀላሉ ማግኘት ይቻል ነበር፡፡ አሁን ለመጠቀምና በሚፈለግበት ሰዓት እንደ ልብ ለማግኘት አስቸጋሪ ቢሆንም፣ ይህንን አገልግሎት ማግኘት የሚፈልግ በጤና ጣቢያዎች፣ ለሴተኛ አዳሪዎች በተዘጋጁ ማረፊያ ቦታዎች ይገኛል፡፡ በነፃ መምጣቱ ከቆመ በኋላ የኮንዶም እጥረቱ የሚታይ ሲሆን፣ ያለውም በውድ ዋጋ እንደሚሸጥ ለመታዘብ ይቻላል፡፡ በአሁኑ ወቅት ኮንዶምን ለገበያ እያቀረበ የሚገኘው ዲኬቲ ኢትዮጵያ ሲሆን፣ ሦስት ፍሬ ኮንዶም በ16 ብር ለፋርማሲዎችና ለግል የጤና ተቋማት እያቀረበ ይገኛል፡፡ ለተጠቃሚው ከ50 ብር በላይ ይቀርባል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ጭራሹንም ተደራሽ አይደለም፡፡ በዚህ ዋጋስ ገዝቶ የመጠቀም አቅም ምን ያህል ነው? ሲባል የሚጠቀም የለም፡፡ ሌሎች ባለሀብቶችና ነጋዴዎች እንደ አንድ የሕክምና መገልገያ ወደ ሥራው እንዲገቡና ያለውን ሰፊ ፍላጎት እንዲረዱት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይህ የሥርጭቱ ሁኔታ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ቢደረግ ችግሩን ለመቅረፍ የሚያስችል ነው፡፡ ዝም ተብሎ የሚታይ ከሆነ ግን ለበሽታው የመጋለጥ አመቺ ሁኔታ በሰፊው ባለበት በአሁኑ ወቅት፣ ከመቅጽበት ወደኋላ ሊመለስ ይችላል የሚል ፍራቻ አለኝ፡፡ የሚመለከታቸው አካላትም በሆቴሎች፣ በመኝታ ክፍሎች፣ በመዝናኛ ሥፍራዎች ኮንዶም በአግባቡ መኖሩን ማረጋገጥ ይገባቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ለኤችአይቪ ሥርጭት ተጋላጭ ተብለው ከተለዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች በተጨማሪ በተለያየ ሥራ፣ ዕድሜና ፆታ የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች እየተጠቁ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ቢሮው ይህንን የለየበት ሁኔታ አለ?
ሲስተር ፈለቀች፡- የተተነተነ መረጃ ባይኖርም፣ ዛሬ ላይ ያለው የኑሮ ውድነት፣ መፈናቀል፣ ከቤት ውስጥና ውጪ ባለው ግፊት ምክንያት ሴተኛ አዳሪነት ውስጥ ይገባል፡፡ ይህን ለመሥራት ምንም ዓይነት የትምህርት፣ የሥራ ልምድ ወይም ችሎታ የማይጠይቅ በመሆኑ፣ የሚከፈለው ክፍያ ከፍተኛና አማላይ እየሆነ በመምጣቱ ቀድሞ በሰዓት ይገደብ የነበረው የሴተኛ አዳሪነት ሥራ አሁን ላይ 24 ሰዓት ሆኖ በተፈለገው ጊዜና ቦታ መገኘት መቻሉ በርካታ ሰዎችን በተለይ ቀድሞ እዚህ ውስጥ ያልነበሩት እንዲገቡ እያደረገ ነው፡፡ የማኅበረሰብ እሴቶችም ከቀን ወደ ቀን እየተሸረሸሩ የሚሄዱበት ሁኔታም ችግሩን ሊፈጥር ይችላል፡፡ ሴቶችም በርካታ ችግሮች ስላሉባቸው ወደዚህ እየገቡ ነው፡፡ ችግሮችን ለመፍታት ይኼ ብቻ አማራጭ እንዳልሆነ ቆም ብሎ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ማኅበረሰቡም በዚህ ላይ የሚሠሩ ድርጅቶችም ሴቶች ወደዚህ ሥራ ከመውጣታቸው በፊት ሊደግፋቸው ይገባል፡፡ በቅርቡ የተደረገ ጥናት ሴቶች ወደዚህ ሥራ የሚገፋቸው ድህነትና የአቻ ግፊት እንደሆነ አሳይቷል፡፡ ውጪው ወይም የሚጠቀምባቸው ደግሞ በደስታ እንደሚቀበላቸው ቃለ መጠይቅ የደተረገላቸው ተናግረዋል፡፡
ሪፖርተር፡- የኤችአይቪ መድኃኒት ሥርጭትና የማኅበረሰጡ አጠቃቀም ምን ይምስላል?
ሲስተር ፈለቀች፡- በመድኃኒቱ ዙሪያ የአቅርቦትም ሆነ የአጠቃቀም ችግር በአሁኑ ሰዓት የለም፡፡ ተጠቃሚዎች የሚያቋርጡበት ሁኔታዎች ግን አሉ፡፡ ድኛለሁ፣ ተሸሎኛል በማለት ለሚያቋርጡት የሃይማኖት አባቶች፣ ማኅበራት እንዲሁም ሌሎች አካላት ያለማቋረጥ ትምህርትና ምክር መስጠት ይጠበቅባቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- በአዲስ አበባ ካሉ ወረዳዎች ምን ያህሉ የሥርጭት ሥጋት ይታይባቸዋል?
ሲስተር ፈለቀች፡- የኤች አይቪ ሥርጭት የሚጀምረው ከቦታ አቀማመጥ ነው፡፡ በፌዴራል ደረጃ በተደረገው አገር አቀፍ ጥናት በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ ከአንድ ሺሕ በላይ ወረዳዎች 222ቱ ከፍተኛ ተጋላጭ ተብለው ተለይተዋል፡፡ በአዲስ አበባ ከሚገኙ 121 ወረዳዎች ውስጥ 48ቱ አንደኛ ደረጃ፣ 51 ሁለተኛ ደረጃ፣ 20ዎቹ ደግሞ ሦስተኛ ደረጃ ተጋላጭ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ መጠጥ ቤቶችና መዝናኛ ቦታዎች በብዛት የሚገኝባቸው ሥፍራዎች ለሥርጭቱ ተጋላጭ ሆነው ተገኝተዋል፡፡
ሪፖርተር፡- በሽታውን በመቆጣጠር የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ያለበት ችግር ምንድነው?
ሲስተር ፈለቀች፡- የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ በተለይ ኤችአይቪ መቆጣጠርና መከታተል ክፍል ጤና ሚኒስቴርን ጨምሮ ከበርካታ በዚሁ ተግባር ከመሠማሩ ጋር የሚሠራ ነው፡፡ ኤችአይቪን በተመለከተ ጥናቶች፣ የውይይት መድረኮችና መመርያዎችን በማዘጋጀት ሥልጠናዎች በመስጠት እንደ ድልድይ እየሠራ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ችግሮች አሉበት ብዬ አላስብም፡፡ ተግዳሮቶች እየሆኑበት ያለው በአንዳንድ ሴክተር መሥሪያ ቤቶች የሚታይ ቸልተኝነትና ቀላል ሥራ አድርጎ ማየት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በአዲስ አበባ ባሉ ትምህርት ቤቶች የኤችአይቪ ክበባት እንደሚቋቋሙ ይታወቃል፡፡ ምን ላይ ይገኛሉ?
ሲስተር ፈለቀች፡- ኤችአይቪ ኤድስ ከ10 እስከ 24 ዓመት ዕድሜ ክልል የሚገኙ ታዳጊዎችና ወጣቶች ላይ በስፋት እንደሚታይ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ከዚያ የዕድሜ ክልል በላይ ካሉት የመያዝ ዕድላቸውም በሁለት እጥፍ ይጨምራል፡፡ በዚህ ዕድሜ ክልል የሚገኙ ልጆች የት እንደሚውሉ ግልጽ ነው፡፡ እነሱ በብዛት በሚገኙበት ትምህርት ቤቶች ከሁለተኛ ደረጃ ጀምሮ መቋቋም የሚገባው ይህ ክበብ ምን ያህል እንዳለ? ምን እየሠራ እንደሆነ? ምንም የምናውቀው የለም፡፡ ይህንን የማቋቋምና የመምራት ኃላፊነት የትምህርት ቢሮው ሲሆን፣ በእኛ በኩል ድጋፍ ከተጠየቅን ለማገዝ ዝግጁ ነን፡፡