ኒያላ ኢንሹራንስ በ2015 የሒሳብ ዓመት ያገኘው የተጣራ 273.3 ሚሊዮን ብር ትርፍ ለባለአክሲዮኖች እንዳይከፋፈል ወሰነ። በዚህም መሠረት ኩባንያው በሒሳብ ዓመቱ ካገኘው ትርፍ ውስጥ አመዛኙ ለካፒታል ማሳደጊያ እንዲውል፣ ቀሪው ደግሞ በመጠባበቂያ ወጪነት እንዲያዝ ወስኗል።
ኩባንያው የ2015 የሒሳብ ዓመት አፈጻጸሙን ኅዳር 1 ቀን 2016 ዓ.ም. ይፋ ባደገረበት ጠቅላላ ጉባዔው ላይ ባሳለፈው ውሳኔ በሒሳብ ዓመቱ ከተገኘው 273.3 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ውስጥ ብር 254.5 ሚሊዮን በቀጥታ የኩባንያውን ካፒታል ለማሳደግ እንዲያውል የወሰነ ሲሆን፣ ቀሪው 18 ሚሊዮን ብር ደግሞ በመጠባበቂያነት እንዲያዝ ወስኗል፡፡ ኩባንያው በሒሳብ ዓመቱ ያገኘው 273.3 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ከቀዳሚው ዓመት በ15.4 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡
ይህ ውሳኔውም የኩባንያውን የተከፈለ ካፒታል ወደ 1.08 ቢሊዮን ብር የሚያሳድግለት እንደሆነ ታውቋል፡፡ ኩባንያው በቀዳሚው ዓመት የነበረው ካፒታል 830 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ ኩባንያው የተከፈለ ካፒታሉን ለማሳደግ በተከታታይ ዓመታት የተጣራ ትርፉን ለካፒታል ማሳደጊያ ሲያውል እንደነበር ይታወሳል፡፡
የኒያላ ኢንሹራንስ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር ሣራ ሱሩር (ዶ/ር) ባቀረቡት ዓመታዊ ሪፖርት፣ በአገሪቱ ውስጥ የቢዝነስ ዓውዱን የሚያውኩ በርካታ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ችግሮች የተከሰቱበት ዓመት የ2015 ሒሳብ ዓመት ኩባንያው ለመጀመርያ ጊዜ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ዓረቦን ገቢ ማግኘቱን አስታውቀዋል፡፡ የቦርድ ሊቀመንበሯ አክለው እንደገለጹት ኒያላ ኢንሹራንስ ከሁሉም የመድን ዘርፎች ያገኘው የዓረቦን ገቢ 1.3 ቢሊዮን ብር ነው። ከተገኘው አጠቃላይ የዓረቦን ገቢ ውስጥ 1.1 ቢሊዮን ብር ወይም 80 በመቶ የሚሆነው ከጠቅላላ የመድን ሽፋን ዘርፍ ነው፡፡
ኩባንያው በሒሳብ ዓመቱ ያገኘው የዓረቦን ገቢ አመርቂ መሆኑን የገለጹት የቦርድ ሊቀመንበሯ፣ ጥንቃቄ የተሞላበት የሥጋት አመራር ሥርዓት እንዲሁም የደንበኞችን ፍላጎት ያማከሉ አዳዲስ የዋስትና ዓይነቶችን በማቅረብ አዳዲስ ደንበኞችን ማፍራት የተቻለበት ዓመት እንደነበረም ጠቁመዋል።
እንደ ሣራ (ዶ/ር) ገለጻ፣ በከፍተኛ መጠን በመናር ላይ ያለውን የካሳ ክፍያ ወጪ ለመቆጣጠር ኩባንያው የተለያዩ አሠራሮችን መተግበር የተጀመረ ቢሆንም በበጀት ዓመቱ የነበረው የካሳ ክፍያ መጠን ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ77.1 በመቶ ከፍ ማለቱን ጠቅሰዋል፡፡ በመሆኑም ኩባንያው በሒሳብ ዓመቱ ለደንበኞቹ በጠቅላላው ከ370 ሚሊዮን ብር በላይ የጉዳት ካሣ መክፈሉን አመልክተዋል።
በሌላ በኩል ኒያላ ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበር ሙሉ በመሉ የዲጂታል ኢንሹራንስ አገልግሎት አሰጣጥን ታሳቢ ያደርገ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ቀርጾ ወደ ሥራ መግባቱን የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ያሬድ ሞላ ገልጸዋል። እጅግ በርካታ የሆነውን የኅብረተሰብ ክፍል በተለይም ‹‹ዲጂታል ኔቲቭ›› እየተባለ የሚጠራው ወጣቱ የኅብረተሰባችን ክፍል የኢንሹራንስ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ፣ አዳዲስ አገልግሎቶችን ለማቅረብ፣ ለደንበኞቹ ቀላልና ምቹ የሆኑ አሠራሮችን ለመዘርጋት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት ላይ ይገኛልም ብለዋል።
የኩባንያው ጠቅላላ የሀብት መጠን በቀዳሚው ዓመት ከነበረበት ሦስት ቢሊዮን ወደ 3.8 ቢሊዮን ማደጉን፣ ይህም ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ28.7 በመቶ ብልጫ እንዳለው የቦርዱ ሊቀ መንበር ካቀረቡት ዓመታዊ ሪፖርት መረዳት ይቻላል፡፡
ኒያላ ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበር በ1987 ዓ.ም በብር ሰባት ሚሊዮን የተከፈለ ካፒታል የተቋቋመ አንጋፋ የኢንሹራንስ ኩባንያ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ በ48 የአገልግሎት ማዕከላት በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች የተሟላ አገልግሎት መስጠት ላይ ይገኛል።