Thursday, November 30, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ዓባይ ባንክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአንድ ቢሊዮን ብር የተሻገረ ትርፍ አስመዘገበ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ዓባይ ባንክ በተጠናቀቀው 2015 የሒሳብ ዓመት በባንኩ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ የተሻገረበትን ትርፍ አስመዘገበ።

ባንኩ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት 1.55 ቢሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ያገኘ ሲሆን፣ ይህም ባንኩ በ2014 የሒሳብ ዓመት ካገኘው 933.26 ሚሊዮን ብር ጋር ሲነጻጸር በ618 ሚሊዮን ብር ብልጫ አለው፡፡ 

ባንኩ ባለፈው ቅዳሜ ጥቅምት 2016 ዓ.ም. ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ሪፖርታቸውን ያቀረቡት የባንኩ የዳይሬክተሮች ብርድ ሰብሳቢ የሆኑት አምላኩ አስረስ (ዶ/ር)፣ በባንኩ ታሪክ ከፍተኛ የሚባል ገቢ በ2015 የሒሳብ ዓመት መመዝገቡን ገልጸዋል። በሒሳብ ዓመቱ ከተገኘው ጠቅላላ ገቢ ውስጥ ባንኩ ከሰጠው ብድር ያገኘው የወለድ ገቢ ቀዳሚውን ድርሻ የሚይዝ ሲሆን፣ ይህም ከጠቅላላው ገቢ 78 በመቶ ድርሻ ይዟል፡፡ ቀሪው 22 በመቶ ገቢ የተገኘው ከኮሚሽን ከሌሎች የገቢ ምንጮች ነው፡፡ 

ባንኩ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ያስመዘገበው ትርፍ የባንኩ ባለአክሲዮኖችን የትርፍ ድርሻ በ2014 የሒሳብ ዓመት ካገኙት የተሻለ እንዲሆን አስችሏል።

በዚህም መሠረት አንድ ሺሕ ብር ዋጋ ያለው አንድ አክሲዮን 360 ብር የትርፍ ድርሻ ማግኘት ይቻለ ሲሆን፣ በ2014 የሒሳብ ዓመት አንድ የባንኩ አክሲዮን ያገኘው የትርፍ ድርሻ 295 ብር ነበር።

የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ የኋላ ገሠሠ እንደገለጹት፣ ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ አዲስ የትርፋማነት ከፍታ ሊያስመዘገብ የቻለው ገቢን በማሳደግና ወጪን በመቆጣጠር ባከናወኗቸው ተግባራት ነው። ባንኩ በተጠናቀቀው የ2015 የሒሳብ ዓመት ያገኘው ዓመታዊ ገቢ 7.1 ቢሊዮን ብር ነው።

ባንኩ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ከ9.6 ቢሊዮን ብር በላይ አዲስ ተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ የቻለ ሲሆን፣ ይህም የባንኩን አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን 41.8 ቢሊዮን ብር ማድረስ እንዳስቻለ ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል። ይህም ከቀዳሚው ዓመት 29 በመቶ ዕድገት እንዳለው አመልክተዋል፡፡ 

ባንኩ 817,573 አዳዲስ አስቀማጮችን በሒሳብ ዓመቱ ማፍራቱንና ‹‹ዓባይ ሳዲቅ›› በተሰኘው የወለድ ነፃ አገልግሎት የሚጠቀሙ ገንዘብ አስቀማጮችን ጨምሮ፣ አጠቃላይ የባንኩ ገንዘብ አስቀማጮች ብዛት 2.5 ሚሊዮን መድረሱን ተናግረዋል። ይህም ከ2014 የሒሳብ ዓመት አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸር የ49 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን ጠቁመዋል።

ዓባይ ባንክ በሐሳብ ዓመቱ በመደበኛውና በሳዲቅ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎቶቹ ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች የሰጠው አጠቃላይ ብድር በ37 በመቶ ዕድገት በማስመዝገብ፣ አጠቃላይ የብድር ክምችቱ 37 ቢሊዮን ብር መድረሱን ፕሬዚዳንቱ ያቀረቡት ሪፖርት ይገልጻል። 

ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ ከሰጠው ብድር ውስጥ ከፍተኛውን 38.8 በመቶ ድርሻ የያዘው በዓለም አቀፍ ንግድ ዘርፍ ላይ ለተሰማሩ ደንበኞቹ ያቀረበው ብድር ነው። ባንኩ በተጠቀሰው ዓመት በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎቱ የሰጠው ብድር 1.5 ቢሊዮን ብር ሲሆን ይህም ከቀዳሚው ዓመት በ106 በመቶ ዕድገት አስመዝግቧል።

ዓባይ ባንክ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት አጠቃላይ የሀብት መጠኑን 55 ቢሊዮን ብር ያደረሰ ሲሆን፣ ይህም ከቀዳሚው ዓመት የ35 በመቶ ዕድገት የተመዘገበበት ነው፡፡ የባንኩ የተከፈለ ካፒታልም በ19 በመቶ አድጎ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት 4.7 ቢሊዮን ብር ደርሷል።

የባንኩን ቀጣይ ዕቅድ በተመለከተ በቀረበው ሪፖርት የተሻለ ዕድገትና ለዘላቂ ውጤታማነት ያበቃኛል ያለው አዲስ የአምስት ዓመት መሪ ዕቅድ ወደ ሥራ ያስገባ መሆኑ ነው፡፡ 

ከ2016 እስከ 2021 ያገለግላል የተባለው መሪ ዕቅድ ‹‹ጉዞ ከፍታ›› የሚል ስያሜ እንደተሰጠው የቦርድ ሊቀመንበሩ ተናግረዋል፡፡ 

ዓባይ ባንክ በመላ አገሪቱ ያሉ ቅርንጫፎቹ 483 የደረሱ ሲሆን፣ በ2015 ብቻ 110 አዳዲስ ቅርንጫፎችን ከፍቷል፡፡ የሠራተኞቹ ቁጥርም 8,626 ሲሆን፣ የባንኩ ባለአክሲዮኖች ቁጥርም 4,437 ደርሷል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች