Thursday, December 7, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ናይል ኢንሹራንስ ከመድን አገለግሎቱና ከተጓዳኝ ኢንቨስትመንቶቹ የተጣራ 298.3 ሚሊዮን ብር አተረፈ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከ28 ዓመታት በላይ የቆየው ናይል ኢንሹራንስ፣ በተጠናቀቀው የ2015 የሒሳብ ዓመት ከሰጠው የመድን አገልግሎትና ከተፈቀዱ ተጓዳኝ አንቨስትመንቶቹ የተጣራ 298.3 ሚሊዮን ብር አተረፈ።

ኩባንያው የ2015 የሒሳብ ዓመት አፈጻጸሙን ሰሞኑን በተካሄደው የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ በወቅቱም ኩባንያው ከሁሉም የመድን ሽፋን ዓይነቶቹ 1.09 ቢሊዮን ብር የዓረቦን ገቢ በሒሳብ ዓመቱ እንዳሰባሰበ አስታውቋል። በተጠቀሰው ዓመት ያገኘው አጠቃላይ የዓረቦን ገቢም በ2014 የሒሳብ ዓመት አግኝቶት ከነበረው 781.6 ቢሊዮን ብር የዓረቦን ገቢ የ40 በመቶ ብልጫ እንዳለው የኩባንያው ሪፖርት ያስረዳል።

ናይል ኢንሹራንስ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ መሐሪ ዓለማየሁ፣ በሒሳብ ዓመቱ የተገኘው የዓረቦን ገቢ፣ በገበያ ውስጥ በተስተካከለው ዋጋን መሠረት ያደረገ እልህ አስጨራሽ ውድድር ውስጥ የመጣ ነው ብለዋል፡፡ 

ኩባንያው በሒሳብ ዓመቱ ካሰባሰበው የዓረቦን ገቢ ውስጥ ከሞተር ኢንሹራንስ ዘርፍ ያሰባሰበው ገቢ 69.7 በመቶ ድርሻ መያዙ ተገልጿል፡፡

ኩባንያው ከተለያዩ የኢንቨስትመንቶቹ ያገኘው ገቢም የ52.2 በመቶ ዕድገት በማሳየት በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ 222.6 ሚሊዮን ብር ገቢ አስገኝቶለታል።

በቀዳሚው ዓመት የኢንቨስትመንት ገቢው 146.3 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ ከኩባንያው ዓመታዊ ጠቅላላ የኢንቨስትመንት ገቢ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው ከአቢሲኒያ ባንክ፣ ከኢትዮጵያ ጠለፋ መድንና ከዓባይ ኢንዱስትሪ የተገኘው ትርፍ ሲሆን፣ ከእነዚህ ኢንቨስትመንት ካደረገባቸው ሦስት ኩባንያዎች በዓመቱ ውስጥ 134.3 ሚሊዮን ብር ገቢ አግኝቷል፡፡ 

ከእነዚህ ሦስት ኩባንያዎች ያገኘው ገቢ በ2014 የሒሳብ ዓመት ከተገኘው በ93.7 በመቶ ብልጫ ያለው መሆኑን የቦርድ ሊቀመንበሩ ገልጸዋል፡፡ ኩባንያው በተለያዩ ኩባንያዎች ውስጥ ኢንቨስት ያደረገው የገንዘብ መጠን 711.2 ሚሊዮን ብር ደርሷል ተብሏል፡፡ 

በዚህም መሠረት ኩባንያው በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት 298.3 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ያገኘ ሲሆን፣ ይህም በ2014 የሒሳብ ዓመት ካገኘው ትርፍ የ40.7 በመቶ ብልጫ እንዳለው ተጠቅሷል።

የናይል ኢንሹራንስ የቦርድ ሊቀመንበር፣ ‹‹ኩባንያው የሥጋት ተጋላጭነቱን ለመቆጣጠርና የተሻለ የደንበኞች አገልግሎትን ለመስጠት የተከተለው ስትራቴጂ የትርፍ አፈጻጸሙን ከፍተኛ አድርጎታል፤›› ብለዋል፡፡ 

በሌላ በኩልም ኩባንያው በሒሳብ ዓመቱ ከኢንቨስትመንት ያገኘው ገቢ ለዕድገቱ አስተዋጽኦ እንደነበረው ገልጸዋል፡፡ ናይል ኢንሹራንስ በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ የተከፈለ ካፒታሉ 834 ሚሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ጠቅላላ የሀብት መጠኑም 3.6 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ናይል ኢንሹራንስ በአዲስ አበባ የፋይናንስ መንደር በሚጠራው አካባቢ እያስገነባ ያለውን ከምድር በታች ሦስት ወደ ላይ ደግሞ 25 ወለሎች ያሉትን ሕንፃ ግንባታ ሙሉ በሙሉ ከስድስት ወራት በኋላ እንደሚያጠናቅቅ አስታውቋል፡፡

የናይል ኢንሹራንስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ንጉሥ አንተነህ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ይህ ዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ግንባታ በአሁኑ ጊዜ የማጠናቀቂያ ሥራዎች የተሠሩለት ሲሆን፣ የተወሰኑ የሕንፃው ክፍሎችም ለአገልግሎት ዝግጁ ሆነው ተጠናቀዋል፡፡ በመሆኑም ቀሪውን የማጠናቀቅ ሥራ በስድስት ወራት ውስጥ ያልቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ አሁን ላይ ግን ለአገልግሎት ዝግጁ በሆኑት የሕንፃው ክፍሎች የኩባንያው የተለያዩ ዲፓርትመንቶች ሥራ እንዲጀምሩበት ተደርጓል፡፡ ባለፈው ቅዳሜ ኩባንያው ጠቅላላ ጉባዔውንም ያካሄደው በዚሁ ሕንፃ ላይ ባለ የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ ነው፡፡   

በአሁኑ ወቅት እየተገነቡና ከተገነቡ የፋይናንስ ተቋማት ሕንፃዎች በተለየ በአገር በቀል የግንባታ ሥራው በአገር በቀሉ ተቋራጭ ራማ ኮንስትራክሽን እየተገነባ ያለ ነው፡፡  እንደ አቶ ንጉሥ ገለጻ አጠቃላይ የኩባንያው ዋና መሥሪያ ቤት ከስድስት ወራት በኋላ ወደ እዚህ ሕንፃ ይዛወራል ተብሎ የሚጠበቅ መሆኑን ነው፡፡ 

ከሌሎች የአካባቢው ከሚገኙ የፋይናንስ ተቋማት ሕንፃዎች የግንባታ ጊዜው የዘገየው ይህ ሕንፃ፣ ግንባታው ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ አጠላቃይ ወጪ ከ1.6 ቢሊዮን ብር በላይ ሆኗል ተብሎ የሚገመት መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይህ ሕንፃ ግንባታው ከተጀመረ አሥር ዓመታት እንደሆነው ይታወቃል፡፡ ናይል ኢንሹራንስ ያስነገባው ሕንፃ እስካሁን በኢንሹራንሱ ኩባንያዎች የተገነባ ረዥሙ ሕንፃ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች