- በመሬት ጉዳይ በታችኛው የመንግሥት መዋቅር መደማመጥ የለም ተብሏል
ሕገወጥ የመሬት ወረራንና ግንባታን ይከላከላል የተባለውን የድሮን ቴክኖሎጂ በተያዘው ዓመት ሥራ ላይ ለማዋል መታቀዱን፣ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር አቶ ፋንታ ደጀን፣ በስፋት የሚስተዋለውን ሕገወጥ የመሬት ወረራና ግንባታ ለመከላከል፣ የአየር ላይ የመሬት ቅየሳ ሥራ ለማስጀመር ዝግጅት መጀመሩንና ዘንድሮ ወደ ሥራ ለማስገባት ዕቅድ መያዙን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
ሚኒስቴሩ በኤግዚም ባንክ ድጋፍ ተገዝተው በቀጣይ ወደ አገር ይገባሉ ያሏቸውን ድሮኖች ብዛት ባይናገሩም፣ ከቴክኖሎጂው ጋር የሚሄዱ የቅየሳ መሣሪያዎች ተገዝተው አገር ውስጥ ከገቡ በኋላ ሥራ ሲጀመር በሰው እጅ የሚከናወነውን የመሬት አጠራጣሪ ልኬት ያስቀራሉ ብለዋል፡፡
ይህ በብዙ አገሮች የተለመደ አሠራር ነው ያሉት ቴክኖሎጂ፣ በኢትዮጵያ መተግበር ሲጀምር፣ የመሬት ወረራንና ሕገወጥ ግንባታን በካሜራ ለመቆጣጠር ትልቅ ሚና እንደሚኖረው አቶ ፋንታ አስረድተዋል፡፡
የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በከተማና መሠረተ ልማት ለሙስና ተጋላጭ ያላቸውን አሠራሮችና ዘርፎች በሚመለከት ባደረገው የዳሰሳ ጥናት፣ በዘርፉ ለከፍተኛ ሙስና ተጋላጭ የሚያደርጉ አሠራሮች መኖራቸውን ከሰሞኑ ይፋ አድርጓል፡፡
ኮሚሽኑ በ2014 ዓ.ም. እና 2015 ዓ.ም. ብቻ በሁሉም ክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች ባደረገው ጥናት በከተሞች 922፣ እንዲሁም በገጠር 462 በመሬት ላይ የተፈጸሙ የሙስና ድርጊቶችና ብልሹ አሠራሮችን ሪፖርት ተደርገዋል፡፡
ከሙስናና ከብልሹ አሠራሮች ጋር በተገናኘ በከተሞች 2.7 ሚሊዮን ካሬ ሜትር፣ እንዲሁም በገጠር 2.8 ሚሊዮን ካሬ ሜትር በዕግድ ላይ መሆኑን ሪፖርቱ ያመላከተ ሲሆን፣ በተመሳሳይ በከተሞች 615 ሺሕ ካሬ ሜትር፣ እንዲሁም በገጠር ከሁለት ሚሊዮን ካሬ ሜትር በላይ በሕገወጥ መንገድ መያዙ ተገልጿል፡፡
በሕገወጥ የመሬት ማስተላለፍ ድርጊት ተሳትፈው የተገኙ በአዲስ አበባ 71፣ በኦሮሚያ ክልል 190፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል 70፣ እንዲሁም በሶማሌ ክልል 43 አመራሮችና ባለሙያዎች ተጠያቂ መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡
የቀረበው የዳሰሳ ጥናት እንደሚያሳየው ከመሬት አሰጣጥ ጋር የተያያዙ የመልካም አስተዳደርና የሙስና ድርጊቶችን በሚመለከት፣ የስም ዝውውርና የባለቤትነት ማረጋገጫ ካርታ አሰጣጥ፣ መሬትን በካዳስተር ሥርዓት መዝግቦ አለመያዝ የፈጠረው ብልሹ አሠራር፣ በተጨማሪም የማዘጋጃ ቤት አገልግሎት አሰጣጦች ለብልሹ አሠራሮች መጋለጣቸው ይጠቀሳሉ፡፡
የከተሞች ፕላን በአግባቡ አለመተግበር፣ ለልማት የሚውል መሬት ላልተፈለገ ዓላማ መዋል፣ ከካሳ ክፍያ ጋር የተገናኘ ማጭበርበር፣ ሀብትን ወደ ውጭ የማሸሽና የማሻገር፣ በትልልቅ ኮንትራክተሮች በፕሮጀክቶች ላይ የሚፈጸም ሙስና፣ ከሙያ ፈቃድ አሰጣጥ ጋር የተያያዘ ሙስና፣ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ደርቦ መስጠት፣ ከመሬት መጠቀሚያ ዓላማ ውጪ ለሌላ ዓለማ ደርቦ መስጠት፣ ሕግን ያልተከተለ የይዞታ መብት መስጠትና የመሬት ወረራ፣ እንዲሁም ሕግን ያልተከተለ ምትክ ቦታ መስጠት የሚሉት በዋቢነት ቀርበዋል፡፡
በተጨማሪም በተወሰኑ ተቋማት ጥሰቶች ሲታዩ ሕጋዊ አስተያየቶችን መስጠት የሚችሉ የሕግ ባለሙያዎች አለመኖር፣ የሚከሰቱ የሕግ ጥሰቶችን በሕግ አግባብ መዳኘት አለመቻል አሉታዊ ሥጋት መፍጠራቸውን የኮሚሽኑ ጥናት ያስረዳል፡፡
በከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የከተማ ፕላን ዝግጅትና ትግበራ ክትትል ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ገነት ገብረ እግዚአብሔር እንዳሉት፣ በመሬት ጉዳይ በተለይም በታችኛው የመንግሥት መዋቅር መደማመጥ ጠፍቷል፡፡ ‹‹ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል›› የሚባለው አስተሳሰብ ሊሰፋ የቻለው፣ በዘራፊዎች ላይ የሚወሰደው ዕርምጃ አስተማሪ ባለመሆኑ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
‹‹ከችግሩ ስፋት አኳያ አመራሮች ችግሩን በባለቤትነት መከታተል ካልቻሉ፣ የሆነ ሰው ሙስና በላ ወይም ዘረፈ ሲባል ነገር ግን የሚወሰደው ቅጣት አስተማሪ አይሆንም፡፡ በሙስና የሚፈለገው ግለሰብ በቀላሉ ከአገር ይወጣል፣ ወይም የተወሰነ ጊዜ ታስሮ ይለቀቃል፣ ጠያቂ ግን የለም፤›› ብለዋል፡፡
የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ለክልል ፕሬዚዳንቶች ጭምር ደብዳቤ ቢጽፍም ምንም መልስ እንደማይሰጡ ጠቅሰው፣ ‹‹ነገሩ ጉንጭ ማልፋት እየሆነ በተለመደው መንገድ እየሄደ በመሆኑ፣ ይህ በአሠራር ካልተፈታ መሬት ላይ የሚታየው ሙስና ሊጠፋ አይችልም፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የትም በየትኛውም ያለ እጅ መንሻ አገልግሎት አይሰጥም ያሉት ወ/ሮ ገነት፣ ያለው የመሬት ሀብት በሲስተም የሚቆጣጠር አሠራር እንዲዘረጋ በመንግሥት በኩል ቁርጠኛ አቋም ያስፈልጋል ብለዋል፡፡