- በኢትዮጵያ ሐሳብ አመንጪ ባለሙያዎች ውስን መሆናቸው ተገልጿል
በኢትዮጵያ ምክረ ሐሳብ አመንጪ ተቋማትና ግለሰቦች ራሳቸው የሚተዳደሩበት የሕግ ማዕቀፍ እንዲኖራቸው ጥያቄ ቀረበ፡፡
ጥቄያው የቀረበው ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ (ኤፍኤስኤስ) ሐሙስ ኅዳር 6 ቀን 2016 ዓ.ም. 25ኛ ዓመቱን ባከበረበት ወቅት ሲሆን፣ በኢትዮጵያ የሚገኙ ሐሳብ አመንጪዎች ቁጥር እንዲጨምርና በዘርፉ ውስጥ ያሉ ችግሮች እንዲቀረፉ የራሳቸው የሆነ የሕግ ማዕቀፍ ሊኖራቸው ይገባል ተብሏል፡፡
ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ (ኤፍኤስኤስ) 25ኛ ዓመቱን ባከበረበት ወቅት ከፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት፣ ከኢትዮጰያ ሳይንስ አካዴሚ፣ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን የተገኙ ኃላፊዎች ለውይይት የሚሆኑ ሐሳቦችን ለታዳሚዎች አቅርበዋል፡፡
ለውይይት የሚሆኑ ሐሳቦችን ለታዳሚዎች ካቀረቡት ውስጥ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ፕሬዚዳንት አምዲሳ ተሾመ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ሐሳብ አመንጪ ተቋማትም ሆኑ ግለሰቦች ሐሳባቸውን በነፃነት እንዲያንሸራሽሩና ለመንግሥት የሚሆኑ ግብዓቶችን በተሻለ ሁኔታ እንዲያቀርቡ የራሳቸው የሆነ የሕግ ሥርዓት ሊኖራቸው ያስፈልጋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ ሐሳብ አመንጪዎች፣ በሕግ የሚተዳደሩት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባስቀመጡላቸው አሠራር መሠረት መሆኑን ጠቅሰው፣ በዓለም ላይ 6,500 ሐሳብ አመንጪ ባለሙያዎች መኖራቸውን አክለው ገልጸዋል፡፡
በዚህ መሠረት በአሜሪካ ብቻ 1,800 ሐሳብ አመንጪዎች እንዳሉ፣ በአፍሪካ ደግሞ ከ200 ያነሱ ባለሙያዎች መኖራቸውን አስረድተዋል፡፡
‹‹በኢትዮጵያ ውስጥ የተሻለ የሕግ አፈጻጸም ሥርዓት ስለሌለ የሐሳብ አመንጪ ባለሙያዎች ቁጥር ውስን እንዲሆን አድርጎታል፤›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ መንግሥት አስፈላጊውን የሕግ ሥርዓት በመዘርጋት ሐሳብ አመንጪዎች ለአገር የሚጠቅሙ ግብዓቶች ላይ ምርምር እንዲያደርጉ አሠራሩ መዘመን ይኖርበታል ብለዋል፡፡
በተለይ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ግብዓቶችን ለማቅረብና ተፈጻሚ ለማድረግ የሐሳብ አመንጪዎች ሚና ከፍተኛ እንደሆነ፣ ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ የሌሎች አገሮችን ተሞክሮ ማየት እንደሚያስፈልግ አምዲሳ (ዶ/ር) አብራርተዋል፡፡
ምክረ ሐሳብ አመንጪ የሆኑ ባለሙያዎች በይበልጥ በነፃነት እንዲሠሩ የራሳቸው የሕግ ማዕቀፍ ሊኖራቸው እንደሚገባ ገልጸው፣ መንግሥት በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች ያቀረቡትን ሐሳብ ተግባራዊ በማድረግ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮችን በዕውቀት የተሞሉ አሠራሮች እንዲካተቱ የሚረዳ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ በፊት ምክረ ሐሳብ አመንጪ የሆኑ ተቋማትም ሆኑ ግለሰቦች የሚመሩበት የሕግ ሥርዓት እንዲወጣ በየመድረኩ ሐሳቡ መነሳቱን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት የሚወጡ ፖሊሲዎች ሙሉ ለሙሉ ተቀባይነት እንዲኖራቸው ጥናት እንደሚያስፈልግና ይህም ዕውን እንዲሆን ዕውቀት ያላቸው ምክረ ሐሳብ አመንጪ ባለሙያዎች የሚሰጡት ግብዓት አስፈላጊ መሆኑን፣ የፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ መሥራችና የቦርድ ሊቀመንበር ባህሩ ዘውዴ (ፕሮፌሰር) ተናግረዋል፡፡
ከዚህ በፊት ምክረ ሐሳብ አመንጪ ባለሙያዎች በመንግሥት ደረጃ እንደማይታወቁ፣ ያላቸውም አመኔታ በጣም ዝቅተኛ የሚባል መሆኑን የቦርድ ሊቀመንበሩ ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ አንገብጋቢ የሚባሉ ጉዳዮች ላይ ጥናት አድርጎ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ ሐሳብ አመንጪ ባለሙያዎች ትልቁን ድርሻ እንደሚይዙ አስረድተዋል፡፡
አብዛኛውን ጊዜ የሐሳብ አመንጪ ባለሙያዎች ቁጥር እንዲጨምር ድጋፍ እንደማይደረግ ገልጸው፣ በኢትዮጵያ ጥቂት የሚባሉ ሐሳብ አመንጪ ባለሙያዎች መኖራቸውን አስረድተዋል፡፡
በተለያዩ ጊዜያት ለተለያዩ ተቋማት ለፖሊሲም ሆነ ለሌሎች ጉዳዮች የሚሆኑ ግብዓቶች ሲቀርቡ፣ ምን ያህሉ ተግባራዊ ሆነዋል የሚለውን መፈተሽ እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል፡፡
በዚህም መሠረተ ባለፉት ጊዜያት ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ የተለያዩ ምክረ ሐሳቦች ለተቋማት ማቅረቡን፣ ይህንን አሠራር በቀጣይ በስፋት ተግባራዊ ለማድረግ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡