Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበቀድሞው ሜቴክ ላይ በተደረገ የኦዲት ምርመራ 65 ቢሊዮን ብር የት እንደደረሰ አለመታወቁ...

በቀድሞው ሜቴክ ላይ በተደረገ የኦዲት ምርመራ 65 ቢሊዮን ብር የት እንደደረሰ አለመታወቁ ተገለጸ

ቀን:

በቀድሞ አጠራሩ የኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) በአዲሱ አወቃቀር ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ላይ የሒሳብ ምርመራ አገልግሎት ኮርፖሬሽን ባደረገው የሒሳብ ኦዲት ምርመራ፣ 65 ቢሊዮን ብር የት እንደደረሰ እንደማይታወቅ ተገለጸ፡፡

በአገሪቱ ከሚገኙ ትልልቅ ድርጅቶች መካከል አንዱ የነበረው ሜቴክ ከተመሠረተ ከ2002 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 2012 ዓ.ም. ድረስ የነበረው የሒሳብ ኦዲት ከተሠራ በኋላ ከፍተኛ ኪሳራ መገኘቱን፣ በቅርቡ የግሩፑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው የተሾሙት ሱሌማን ደደፎ (አምባሳደር) ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

‹‹የሒሳብ ምርመራ አገልግሎት ኮርፖሬሽን በሠራው ሪፖርት መሠረት 65 ቢሊዮን ብር የት እንደደረሰ ስለማይታወቅ፣ የኦዲት ሪፖርቱን መሠረት በማድረግ መንግሥት እንዲሽረው (Write off) ተጠይቆ ውሳኔ አግኝቷል፤›› ብለዋል፡፡

በዚህም መሠረት የተገኘው የኪሳራ ገንዘብ በዕዳ እንዳይመዘገብ መንግሥት ሽሮታል (Writeoff) ሲሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል፡፡

በኦዲት የተገኘው ገንዘብ ምንም ሥራ ላይ ያልዋለና በወቅቱ የነበሩ አመራሮች ተከፋፍለው የወሰዱት በመሆኑ፣ በዚህ ተቋም አማካይነት የአንድ ህዳሴ ግድብ መሥሪያ ብር መዘረፉን ሱሌማን (አምባሳደር) ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ለውጥ ከተደረገ በኋላ ወታደራዊ ምርቶች ለብቻ እንዲሆኑ በመክፈል እንደ አዲስ የተዋቀረው ግሩፑ፣ የደረሰበትን ሀብትና ዕዳውን የመለየትና ጥፋቶችን በመመርመር በሕግ የሚገዛ አገራዊ ተቋም ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የቀድሞው ሜቴክ ከተመሠረተበት ጀምሮ እስካሁን ያለውን አጠቃላይ ሒሳብ ኦዲት መደረግ የተጀመረ መሆኑን፣ እስከ 2012 ዓ.ም. ድረስ ያለውን በማጠናቀቅ ከ2012 ዓ.ም. በኋላ ያለው በሒደት ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በኦዲት ሪፖርቱ ግኝት መሠረት ከኪሳራው በተጨማሪ፣ በሀብት ደረጃ የተመዘገቡት እንዲሸጡ በማድረግ ለግሩፑ ገቢ እንዲሆን እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

በዚህም መሠረት በአሁኑ ወቅት ያለ አገልግሎት የተቀመጡ አምስት ቤቶችን ወደ ገንዘብ ለመቀየር፣ በቅርቡ ለሽያጭ እንደሚቀርቡ ገልጸዋል፡፡

‹‹የቀድሞ የድርጅቱ አመራሮች የዝርፊያ ሥልት አሁንም ድረስ በተለያዩ መንገዶች እየቀጠለ በመሆኑ፣ ከኪሳራ እንዳይላቀቅ ማነቆ እየሆነ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በቅርቡ ይፋ የተደረገው የፓወር ኢኪዩፕመንት ፋብሪካ ውስጥ የሚገኙ ስምንት አመራሮች ከብረት ስርቆት ጋር በተገናኘ መያዛቸው አንዱ ማሳያ መሆኑን፣ ሌሎች አመራሮችም ቀስ በቀስ ተጠያቂ እንደሚደረጉ አክለዋል፡፡

በተጠናቀቀው ሳምንት የሙስና ወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸው የነበሩትና ከአምስት ዓመታት በላይ በእስር ላይ የሚገኙት የሜቴክ የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ከ111 የራዳሮች ግዥ ጋር በተያያዙ በቀረበባቸው ክስ፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ የሙስና ወንጀል ችሎት የሦስት ዓመት ከሰባት ወር ፅኑ እስራትና የአንድ ሺሕ የገንዘብ መቀጮ መወሰኑ ይታወሳል፡፡

የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ዕዳ በመጠቅለል በየዓመቱ የዕዳ ክፍያ እየፈጸመ የሚገኘው የዕዳና ሀብት አስተዳደር፣ ከፍተኛ ዕዳ አለባቸው ብሎ ከያዛቸው ድርጅቶች አንዱ የቀድሞ ሜቴክ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

ከሦስት ዓመት በፊት በሜቴክ ማቋቋሚያ ደንብ ቁጥር 183/2002 ሥር ያሉት መብትና ግዴታዎች ለኢትዮጵያ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ መተላፋቸው ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ ሲኒመር ትሬዲንግ...

የባህር በር በቀጣናዊ ተዛምዶ ውስጥ

በበቀለ ሹሜ መግቢያ በ2010 ዓ.ም. መጋቢት ማለቂያን ይዞ ዓብይ አህመድ በጠቅላይ...

ሥጋት ያስቀራል ተብሎ የሚታሰበው የጫኝና አውራጅ መመርያ

በአዲስ አበባ ከተማ በሕገወጥ መልኩ በመደራጀት ማኅበረሰቡ ላይ እንግልትና...

ማወቅ ወይስ አለማወቅ – ድፍረት ወይስ ፍርኃት?

በአሰፋ አደፍርስ ወገኖቼ ፈርተንም ደፍረንም የትም አንደርስምና ለአገራችን ሰላምና ክብር...