Tuesday, November 28, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

አስጨናቂውን የኑሮ ውድነት የማርገብ ኃላፊነት የመንግሥት ነው!

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ማክሰኞ ኅዳር 4 ቀን 2016 ዓ.ም. ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ካቀረቡላቸው ጥያቄዎች መካከል አንደኛው የኑሮ ውድነትን በተመለከተ ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የኑሮ ውድነት መኖሩን፣ ሰዎች በዚህ ምክንያት ለመመገብ እንደሚቸገሩና ጥያቄው እውነት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ‹‹…ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን እዚህ ከእኛ ቢሮ በመቶ ሜትር ርቀት ሰዎች ይቸገራሉ፡፡ ባለፉት 40 ዓመታት ያልታየ የዋጋ ግሽበት በዓለም ላይ አለ፡፡ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የዓለም ችግር ነው፡፡ የኢትዮጵያን ያባባሰው የዋጋ ግሽበቱ የገቢ አቅማችን ዝቅተኛ በሆነበት ሁኔታና ላለፉት በርካታ ዓመታት ሳይቋረጥ እያደገ ስለመጣ፣ የሰው ገቢና የግሽበት ዕድገት ምጣኔ በከፍተኛ ደረጃ በኑሮ ላይ ጫና አምጥቷል… የእኛ ችግር የሆነው ገቢያችን እያደገ ስለማይሄድ ነው…›› ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ዘንድሮ የዓለም ዋጋ ሁኔታ መረጋጋት እያሳየ እንደሚቀጥል ትንበያ መኖሩን፣ የኢትዮጵያ ችግር የተደመረ ውጤት መሆኑንና ነገር ግን ራስን ለፈተና በማዘጋጀት መፍትሔ መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የኑሮ ውድነቱን ለመቋቋም ምርትና ምርታማነትን የመጨመር አስፈላጊነት፣ አርሶ አደሩ አዲስ አበባ ውስጥ ምርቱን በቀጥታ የሚሸጥባቸው የገበያ ማዕከላት እየተገነቡ መሆናቸው፣ የቤት ኪራይ በትክክለኛ ሕግ የማይገራ ከሆነ በተከራዮች ላይ በየወሩ ኪራይ እየጨመረ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ላይ ችግር እየመጣ ስለሆነ ማስተካከያ እንደሚያስፈልግና ሌሎች ጉዳዮችን ጠቃቅሰዋል፡፡ መንግሥት ለኑሮ ውድነቱ መፍትሔ ለመፈለግ ሲነሳ ግን በተቻለ መጠን ተጓዳኝ ችግሮችን መቃኘት ይኖርበታል፡፡ በዓለም ላይ የሚስተዋለው የኑሮ ውድነት ከኢትዮጵያ ጋር ሲነፃፀርም ጥንቃቄ ያስፈልገዋል፡፡ እንደሚታወቀው በአሁኑ ጊዜ እጅግ በጣም ጥቂት ከሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች በስተቀር አብዛኛው ሕዝብ የመግዛት አቅሙ ተመናምኗል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዓመታዊ ነፍስ ወከፍ ገቢ ሌላው ቀርቶ ከጎረቤት አገሮች ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ የሚባል ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ገቢው የማያድግ ሕዝብ ለኑሮ ውድነት በቀላሉ ነው የሚጋለጠው፡፡ በግልም ሆነ በመንግሥት ተቀጣሪነት የሚያገለግሉ በርካታ ዜጎች ደመወዛቸው ከቤት ኪራይ አልፎ ለምግብ መሆን አልቻለም፡፡

መንግሥት በተለይ በተደጋጋሚ በተለያዩ አካላት የሠራተኞችን ደመወዝም ሆነ የግብር ክፍያ ወለልና ጣሪያን በተመለከተ የሚቀርቡለትን ምክረ ሐሳቦች በአንክሮ ማዳመጥ ይጠበቅበታል፡፡ አንድ ሰው የዜግነት ግዴታውን ከሚወጣበትና በኩራት መብቱን ከሚጠይቅባቸው ኃላፊነቶቹ መካከል አንዱና ዋናው ግብር መክፈሉ ነው፡፡ ግብር መክፈል ግዴታ ብቻ ሳይሆን የዜግነት መብትም ነው፡፡ ነገር ግን መንግሥት የገቢ ግብር ምጣኔውን ማስተካከል፣ እንደ ምግብና በጣም መሠረታዊ የሚባሉ አቅርቦቶች ላይ ሸማቾች ድረስ የሚዘልቅ እንደ ተጨማሪ እሴት ታክስ ላይ ያለውን ምጣኔ መቀነስና የመሳሰሉ ዕርምጃዎችን ጉዳይ ማጤን አለበት፡፡ የቤት ኪራይ ዋጋን ፈር ለማስያዝ የሕግ ማዕቀፍ ሲያዘጋጅም የሁለቱን ወገኖች ተጠቃሚነት ሚዛናዊ ማድረግ፣ ከቤት ኪራይ የሚሰበሰበው ግብር በኢፍትሐዊ ሥሌት እንዳይሆን ጥንቃቄ ማድረግና መሰል ጠቃሚ ዕርምጃዎችን መውሰድ የመንግሥት ኃላፊነት ነው፡፡ ከላይ የተጠቀሱትን ሐሳቦች በባለሙያዎች ዕገዛ በጥናት ላይ በመመሥረት ውሳኔ ላይ መድረስ ሲቻል፣ ዜጎችም በበኩላቸው የገቢ አማራጮችን የሚያገኙባቸውን ሥራዎች ለመፍጠር ትጋት ያሳያሉ፡፡

መንግሥት የዜጎችን ኑሮ ለማሳደግ የሚረዱ በርካታ ዕርምጃዎችን ለመውሰድ ሲዘጋጅ፣ የተቋማት ጥንካሬና የአመራሮቻቸው ብቃት ሊያሳስበው ይገባል፡፡ ጠንካራ ተቋማትና አመራሮች ሳይኖሩ እንኳንስ በርካታ ጥረቶችን የሚጠይቀውን የኑሮ ውድነት ለማርገብ፣ የዕለት ተዕለት ሥራን በአግባቡ ለማከናውን በእጅጉ ይፈትናል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የተቋማት ግንባታ ጉዳይ ሲነሳ ችላ ባይነት በስፋት ይስተዋላል፡፡ ኢኮኖሚው በጠንካራ ተቋማት ካልተመራ አገር እንደምትሽመደመድ ማንም አይስተውም፡፡ የትምህርት ዘርፍ የደረሰበት ስብራት ውጤቱ ምን እንደሆነ በሚገባ እየታየ ነው፡፡ የግብርናው ዘርፍ በሚገባ ባለመመራቱ ኢትዮጵያ ለማመን የሚያዳግት ወጣት የሰው ኃይልና የተፈጥሮ በረከቶች ታድላ በምግብ ራስን መቻል ከብዷል፡፡ ሌሎች ዘርፎችም ሲታዩ ኢትዮጵያ ደረጃዋ ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገሮች በታች ናት፡፡ ነገር ግን በዓለም አቀፍ ደረጃ ስሟን ለዓመታት እያስጠራ ያለው የኢትዮጵያ አየር መንገድን የመሰለ የሚያኮራ ተቋም ባላት አገር፣ የእዚህን አኩሪና አስመኪ ተቋም ልምድ ለመቅሰም ለምን ይቸግራል? አየር መንገዱን በትንሹ ለመምሰል ብዙዎቹ ተቋማት ርብርብ ቢያደርጉ እኮ ድህነት አይፈነጭም ነበር፡፡

ተቋማት ሲጠናከሩ የግልጽነት፣ የተጠያቂነትና የኃላፊነት መርህ እየተከበረ ብልሹ አሠራሮች ስለሚወገዱ፣ ከኪሳራ ይልቅ ትርፋማነት ይስፋፋል፡፡ ምርትና ምርታማነት ከመጨመሩም በላይ ብክነት፣ ሌብነት፣ አጭበርባሪነት፣ ኢፍትሐዊነት፣ አድሎአዊነትና የመሳሰሉ የክፋት ድርጊቶች ይወገዳሉ፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ ከተለያዩ አካባቢዎች የሚሰበሰቡ ምርቶች በጥቂቶች ቁጥጥር ሥር ይውሉና ዜጎች ለሰው ሠራሽ የዋጋ ንረት ይጋለጣሉ፡፡ በዚህ ላይ የአቅርቦት ሰንሰለቱን የተቆጣጠሩ ሕገወጦች መንግሥት ድጎማ የሚያደርግባቸውን ምርቶች በማገት የኑሮ ውድነቱን ያባብሳሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠረው የሰላምና የፀጥታ መናጋት ምክንያት ምርቶችን በአግባቡ ማቅረብ አልተቻለም፡፡ እንዲሁም በኮንትሮባንድ ንግድ የተሰማሩ ከልካይ የሌለባቸው ደግሞ የአገሪቱን ቡና፣ የቀንድ ከብቶች፣ ወርቅና ሌሎች ለኤክስፖርት የሚውሉ ምርቶች ወደ ጎረቤት አገሮች እያጋዙ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ጫና ሲደማመር ሸማቹ ሕዝብ ከሚሸከመው በላይ የኑሮ ውድነት እያጎበጠው ነው፡፡ መንግሥት ለነጋዴዎች የትርፍ ህዳግ ባለመውጣቱ ብቻ ሕገወጦች የኑሮ ውድነቱን እያባባሱት ነው፡፡ ለዚህም ነው ጠንካራ ተቋማት ይፈጠሩ የሚባለው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የባህር በር ጉዳይን አስመልክተው ማብራሪያ ሲሰጡ ኢትዮጵያ ከሕግ ውጪ ያልተገባ ጥያቄ አለማቅረቧን፣ ወደ ጎረቤት አገሮችም አንድ ጥይት የመተኮስ ፍላጎት እንደሌላት፣ ነገር ግን በሕግና በቢዝነስ ማዕቀፍ መወያየት እንደምትፈልግ አስረድተዋል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ እያደገ ነው፣ በመሆኑም ጉዳዩ ጊዜ ሳይሰጠው አሁኑኑ መፍትሔ ሊበጅለት ይገባል ብለን እናምናለን፡፡ ረሃብና ችግር ሳይመጣ ተነጋግረን መፍትሔ እናበጅ ነው ያልነው…›› በማለት ማሳሰባቸው ይታወሳል፡፡ የረሃብ አሳሳቢነት በዚህ ደረጃ ተገልጾ ለጎረቤት አገሮች ችግራችንን ተረዱልን ሲባል፣ በአገር ውስጥ ያለውን ዕምቅ ሀብትና አቅም የመጠቀም አስፈላጊነት በእጅጉ ያጎላዋል፡፡ የችግሩ ፅኑነት በዚህ ደረጃ ሲገለጽ በፍጥነት መፍትሔ ካልተፈለገለት ለአገር ህልውናም ቀውስ መሆኑን መረዳት የግድ ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያ ያሏትን የተፈጥሮ ፀጋዎች በሚገባ ተጠቅማ ከአሳፋሪው ምግብ ተመፅዋችነት ለመገላገል የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ አዋጭ ዕቅዶች እንደሚያስፈልጓት ግልጽ ነው፡፡ ነገር ግን አሁን ፋታ አልሰጥ እያለ ያለው አስጨናቂ የኑሮ ውድነት እንዲረግብ ፈጣን መፍትሔ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ከማንም በላይ መንግሥት ትልቅ ኃላፊነት አለበት!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ ሲኒመር ትሬዲንግ...

የባህር በር በቀጣናዊ ተዛምዶ ውስጥ

በበቀለ ሹሜ መግቢያ በ2010 ዓ.ም. መጋቢት ማለቂያን ይዞ ዓብይ አህመድ በጠቅላይ...

ሥጋት ያስቀራል ተብሎ የሚታሰበው የጫኝና አውራጅ መመርያ

በአዲስ አበባ ከተማ በሕገወጥ መልኩ በመደራጀት ማኅበረሰቡ ላይ እንግልትና...

ማወቅ ወይስ አለማወቅ – ድፍረት ወይስ ፍርኃት?

በአሰፋ አደፍርስ ወገኖቼ ፈርተንም ደፍረንም የትም አንደርስምና ለአገራችን ሰላምና ክብር...

ከድህነት ወለል በታች ከሆኑት አፍሪካዊያን ውስጥ 36 በመቶው በኢትዮጵያ ናይጄሪያና ኮንጎ እንደሚገኙ ተጠቆመ

‹‹ለሺሕ ዓመት በድህነት ውስጥ የነበረች አገርን በአሥር ዓመት ልንቀይር...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሔ ይፈለግላቸው!

መንግሥት ከኦነግ ሸኔ ጋር በታንዛኒያ ዳሬሰላም ከተማ ሲያካሂድ የነበረው ንግግር ያለ ውጤት መጠናቀቁን ካስታወቀ በኋላ፣ በኦሮሚያ ክልልም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ሰላም ለማስፈን የነበረው ተስፋ...

ኢትዮጵያን ከግጭት ቀጣናነት ማላቀቅ የግድ ነው!

ፍሬ አልባ ፖለቲካዊ ልዩነቶች ወደ ግጭት እያመሩ ለአገርና ለሕዝብ የማያባራ መከራ ሲያቀባብሉ፣ ከትናንት ስህተቶች ለመማር ፈቃደኛ ያልሆኑ ፖለቲከኞችና ተከታዮቻቸው በእሳት ላይ ቤንዚን እያርከፈከፉ ጠማማ...

የአገር ጉዳይ የሁሉም ዜጎች የጋራ ኃላፊነት ነው!

በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሙሉ፣ ለአገራቸው መፃኢ ዕድል ስኬት ሲሉ የሚፈለግባቸውን ሁሉ እንዲያደርጉ የሚፈለጉበት ወሳኝ ጊዜ አሁን ይመስላል፡፡ በኢትዮጵያ የቅርብ...