Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናባለሥልጣናት ስለባህር በር የሚሰጡት መግለጫ የተጠናና በጥንቃቄ መሆን እንዳለበት ምሁራን አሳሰቡ

ባለሥልጣናት ስለባህር በር የሚሰጡት መግለጫ የተጠናና በጥንቃቄ መሆን እንዳለበት ምሁራን አሳሰቡ

ቀን:

የመንግሥት ባለሥልጣናት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የባህር በር ጉዳይን በሚመለከት የሚሰጧቸው አስተያየቶችና መግለጫዎች፣ የተጠኑና ጥንቃቄ የተሞላባቸው እንዲሆኑ ምሁራን አሳሰቡ፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዓርብ ኅዳር 7 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ስድስት ኪሎ በሚገኘው ዋናው ግቢ ራስ መኮንን አዳራሽ ባዘጋጀው የጥናት መድረክ ላይ፣ ጥናት ያቀረቡና ውይይት ያደረጉ ምሁራን፣ መንግሥት ስለባህር በር የሚሰጣቸው መረጃዎች የጎረቤት አገሮችን የማያሠጉና ጥንቃቄ የተሞላባቸው እንዲሆኑ አሳስበዋል፡፡

‹‹ፍትሐዊ የወደብ አጠቃቀም ለአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላምና ልማት›› በሚል ርዕስ በተስተናገደው በዚህ ዓውደ ጥናት ላይ፣ ኢትዮጵያ በሰላማዊ መንገድ የባህር በር ባለቤት መሆን ስለምትችልባቸው አማራጮች ሰፊ ምሁራዊ ውይይት ተካሂዷል፡፡

በጥናት መድረኩ ላይ ሦስት ምሁራን የውይይት መነሻ ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ በለጠ በላቸው (ዶ/ር)፣ የሎጂስቲክስ ምሁሩ ማቲዎስ እንሰርሞ (ዶ/ር) እንዲሁም የዓለም አቀፍ ሕግ ምሁሩና ዲፕሎማቱ ኢብራሂም ኢድሪስ (አምባሳደር) የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ በሰላማዊ አማራጮች እንዴት ይመለሳል በሚለው ጉዳይ ላይ ሦስት የተለያዩ የመነሻ ጽሑፎች አቅርበዋል፡፡

በቅርቡ የተሾሙት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) በከፈቱትና ታዋቂው የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁሩና የውኃ ፖለቲካ ተመራማሪው ያዕቆብ አርሳኖ (ዶ/ር) በአወያይነት በመሩት በዚህ ዓውደ ጥናት የተካፈሉ የተለያዩ ምሁራን በርካታ ሐሳቦቸን በነጻነት ሲያንሸራሽሩ ውለዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ሳሙኤል (ዶ/ር) ዩኒቨርሲቲያቸው ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ሆኖ የመቆም ሪፎርሙን አጠናክሮ መቀጠሉን በመጠቆም፣ በተለይ ኢትዮጵያ በምትገኝበት የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ጉዳዮች ላይ አትኩሮ መሰል የጥናት መድረኮችን ደጋግሞ እንደሚያዘጋጅ ቃል ገብተዋል፡፡

ከጥናት አቅራቢዎቹ የመጀመሪያው የፖለቲካ ምሁሩ በለጠ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ የባህር በር አልባ የሆነችበትን አጋጣሚ ከታሪካዊ ዳራው በመነሳት በሰፊው ፈትሸዋል፡፡ ኢትዮጵያን ከቀይ ባህር ቀጣና ለመነጠል ሆን ብሎ በቀጠናው አገሮች ሲሠራበት የቆየ ቀጣናዊ የጂኦፖለቲካ አሻጥርን በሰፊው የተመለከቱት ምሁሩ፣ ይህ ሴራ አሁንም ስለመቀጠሉ ሞግተዋል፡፡ ኢትዮጵያ በቅርብ ጊዜ የባህር በር እንዲኖራት ያላትን ፍላጎት ይፋ አድርጋለች ያሉት ምሁሩ፣ ይህ ግን በቀጣናው አገሮች ዘንድ ፍራቻና ጥርጣሬ መፍጠሩን አመልክተዋል፡፡

ሳዑዲ ዓረቢያዎች ከጀመሩት ኢትዮጵያን ገለል ካደረገው የቀይ ባህር ፎረም ከሚባል ማኅበር ጀምሮ፣ ከዓረብ ኤምሬቶች ጋር እስከገቡበት ቀጣናዊ የበላይነት የመያዝ ሽኩቻ ድረስ የፈተሹት ምሁሩ፣ በዓለም ጂኦፖለቲካ ለመምጣት እያንጃበበ እስካለው የቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት ድባብ የኃይል ውጥረት ድረስ፣ ብዙ ጉዳዮችን ምሁሩ ተመልክተዋል፡፡ የባህር በር ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ ሊሳካ ይችልበታል ስለሚሉት ጉዳይ ሲያነሱ፣ የውስጥ ሽኩቻና ተጋላጭነትን በመቅረፍ፣ ውስጣዊ ጥንካሬን የመፍጠር፣ እንዲሁም ቀጣናዊ ተሰሚነትን የማሳደግ አስፈላጊነትን አስምረውበታል፡፡

‹‹ኢትዮጵያ ፈረንጆቹ (the genie is now out of the box) እንደሚሉት፣ ኢትዮጵያ የባህር በር እንደሚያስፈልጋት ይፋ አድርጋለች፡፡ ይህ የባህር በር ፍላጎት ግን ሌላውን በተለይም የገረቤት አገሮችን ሥጋት ውስጥ በማይከት መንገድ መቅረብ አለበት፤›› ሲሉ ሐሳብ ሰጥተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ቀጣናዊ፣ አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የጂኦፖለቲካ ሁኔታዎችን ለመጠቀም ብዙ ሥራ መሥራት እንዳለባት የመከሩት ምሁሩ፣ ለባህር በር ጥያቄ ወታደራዊ አማራጭ መጠቀም ግን ፈጽሞ ሊታሰብ እንደማይገባው አሳስበዋል፡፡ በአገር ቤት በቂ ችግርና ቀውስ የተሸከመችው አገሪቱ ለባህር በር ጥያቄ ከጎረቤት አገሮች ጋር ወደ ግጭት ብትገባ የማትወጣው ቀውስ ውስጥ ልትወድቅ እንደምትችል ነው ያሳሰቡት፡፡

ሌላኛው ጥናት አቅራቢ ማቲዎስ (ዶ/ር) በበኩላቸው ኢትዮጵያ በቀጣናዋ ለወደብ አገልግሎቶች ያላትን የባህር በር አማራጮች አዋጪነት በሰፊው ፈትሸዋል፡፡ በኢትዮጵያ ዙሪያ ባሉ አገሮች አሥር የወደብ አማራጮች እንዳሉ የጠቆሙት ምሁሩ፣ ባላቸው ርቀትና ቅርበት፣ በአገልግሎት ምቹነትና ቅልጥፍና፣ በዋጋና በሌላም ሎጂስቲካዊ መመዘኛዎችን መጠቀም እንደሚያዋጣ በሰፊው ተመልክተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከእነዚህ አማራጮች መካከል ያዋጣኛል የምትለውን የባህር በር ባለቤት ከሆኑ አገሮች ጋር በትብብርና በጋራ አልምታ መጠቀም እንደምትችል ያመለከቱት ምሁሩ፣ ከዚህ አለፍ ሲልም ለረዥም ዓመታት በሚዘልቅ ኪራይና በሌሎችም ሰላማዊ መንገዶች ፍላጎቷን ማሳካት እንደምትችል ጠቁመዋል፡፡

የሎጂስቲክስ ምሁሩ ማቲዎስ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በስትራቴጂክ ዕቅዶቿና ፖሊሲዎቿ ጭምር የባህር በርና የወደብ አማራጭ ጉዳይን ማካተት መጀመሯ ትልቅ ለውጥ መሆኑን አንስተዋል፡፡ ከዚህ ከፍ ባለ ሁኔታ ግን ለዘርፉ ተቋማዊ ቅርጽ የማበጀት አስፈላጊነትን ያነሱ ሲሆን ‹‹የወደብ ባለሥልጣን የመሳሰሉ ተቋማት ቢኖሩን›› ሲሉ ሐሳብ ሰንዝረዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ያላት ፍላጎትን ተመልክቶ ‹‹የእኛን ተጠቀሙ›› የሚል ሳቢ ጥያቄ ከራሳቸው ከጎረቤት አገሮች ሊመጣ እንደሚችልም ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ የባህር በርና የወደብ አማራጭ ፍላጎቷን ለማሳካት ቀጣናዊና አኅጉራዊ ዕድሎችን መጠቀም እንዳለባት አሳስበዋል፡፡

ዓለም አቀፋዊ ሕጎችን በማጥናት የሚታወቁት ዲፕሎማቱ ኢብራሂም (አምባሳደር) በበኩላቸው ዓለም አቀፍ ሕግ የዲፕሎማሲ ውጤት መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከጎረቤትም ሆነ ከቀጣናው አገሮች ጋር በባህር በርና በወደብ አጠቃቀም ጉዳዮች የምታደርጋቸው ስምምነቶችም የዓለም አቀፍ ሕግ አካል መሆናቸውን ነው የጠቀሱት፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የፈረመቻቸውንና አባል የሆነችባቸውን ዓለም አፍ የሕግ ማዕቀፎች በዝርዝር በመመልከት አዋጪና ዘላቂ የሆኑ መንገዶችን ልትጠቀም እንደምትችል አሳይተዋል፡፡ በዚህ ረገድ ምርጥ ተሞክሮ ነው ያሉትን የሌሎች አገሮችን የወደብና የባህር በር ስምምነቶች በማንሳት ኢትዮጵያ ከአነዚህ የተሻለውን መውሰድ እንደምትችል ነው የጠቆሙት፡፡

በጥናት መድረኩ ላይ ለኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄን በማስመለስ ታሪካዊ ድል ያስመዘገቡ ያለፈው ትውልድ ምርጥ ተሞክሮ ታሪካዊ ድል እንደነበር በጉልህ ተነስቷል፡፡ በሰላማዊ መንገድ ኤርትራን በፌዴሬሽን ከኢትዮጵያ ጋር በማስተሳሰር የባህር በር ጥያቄን የመለሰ ትውልድ ያፈራችው ኢትዮጵያ፣ ይህን ታሪካዊ ስኬት ማስቀጠል የሚችል ተተኪ ትውልድ ማፍራት ባለመቻሏ የባህር በር አልባ ሀገር ሆና እንደቀረች ነው ጎልቶ የተነሳው፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን አሁን ላይ የባህር በርና ወደብን በተመለከተ ግብታዊ አስተያየቶች ሲሰጡ እንደሚሰማ ያነሱ አንዳንድ ተወያዮች፣ ይህ ያልተጠናና ጥንቃቄ የጎደለው አካሄድም፣ ሰላም የናፈቃትን አገር ከጎረቤቶቿ ጋር ችግር ውስጥ እንዳይካተት አስጠንቅቀዋል፡፡           

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ ሲኒመር ትሬዲንግ...

የባህር በር በቀጣናዊ ተዛምዶ ውስጥ

በበቀለ ሹሜ መግቢያ በ2010 ዓ.ም. መጋቢት ማለቂያን ይዞ ዓብይ አህመድ በጠቅላይ...

ሥጋት ያስቀራል ተብሎ የሚታሰበው የጫኝና አውራጅ መመርያ

በአዲስ አበባ ከተማ በሕገወጥ መልኩ በመደራጀት ማኅበረሰቡ ላይ እንግልትና...

ማወቅ ወይስ አለማወቅ – ድፍረት ወይስ ፍርኃት?

በአሰፋ አደፍርስ ወገኖቼ ፈርተንም ደፍረንም የትም አንደርስምና ለአገራችን ሰላምና ክብር...