- አንዳንድ ድንጋጌዎች ከሕገ መንግሥቱና ቤተሰብ ሕጉ ጋር ይጋጫሉ ተብሏል
ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ረቂቅ አዋጅ፣ የጉዳዩ ዋና ተዋናይ የሆኑት አርሶና አርብቶ አደሮች ሳይመክሩበት በምሁራን ውይይት ብቻ እንዳይፀድቅ ጥያቄ ቀረበ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኅዳር 6 ቀን 2016 ዓ.ም. ባካሄደው 2ኛ ዓመት 5ኛ መደበኛ ስብሰባ፣ በረቂቅ አዋጁ ላይ ተወያይቶ ለዝርዝር ዕይታ ለግብርና ጉዳዮች በተባባሪነት ለሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቶታል።
የምክር ቤት አባላቱ የገጠር መሬት ባለ ይዞታ አርሶ አደሮች ሆኖ ሳለ፣ በምሁራን ብቻ የዳበረ ረቂቅ ሕግ መቅረቡ ጉዳዩን ባለቤት እንዳያሳጣው ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
አወቀ አምዛየ (ዶ/ር) የተባሉ የምክር ቤት አባል በኢትዮጵያ ታሪክ የተነሱ ሕዝባዊ ንቅናቄዎች መነሻቸው መሬት መሆኑን አስታውቀው፣ ይህ ረቂቅ ሕግ መሬታቸው መንገድና እንዴት ይደራጅ የሚለውን አርሶና አርብቶ አደሮች ሳይመክሩበት የቀረበ ነው ብለዋል፡፡
የምክር ቤቱ አባል የሆኑት ዲና ሙፍቲ (አምባሳደር) በበኩላቸው፣ የሚመለከታቸው አካላት በጉዳዩ ላይ በግልጽ ካልተወያዩበት ላልተፈለገ አመፅ ሊጋብዝ እንደሚችል አስረድተዋል፡፡
በተመሳሳይ ሌሎች የምክር ቤት አባላትም መሬት ለአርሶና አርብቶ አደሮች ውድ ሀብትና የሕይወት መሠረታቸው መሆኑን ጠቅሰው፣ ከእነሱ ጋር ውይይት ሳይደረግ ወደ ሥራ ከገባ ማኅበራዊ ምስቅልቅል ሊያመጣ እንደሚችል አስተያየት ሰንዝረዋል።
በረቂቅ አዋጁ ላይ ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄዎችን ሊያጭሩ የሚችሉ ጉዳዮች የተነሱ ሲሆን፣ በተለይም አንድ ግለሰብ ከሁለት በላይ ሚስቶች ሲኖሩት ስለሚፈጸሙ የመሬት ውሎች፣ መሬትን አስይዞ ስለመበደርና ብድር ያልመለሰ ባለይዞታ ላይ ሊወሰድ ስለሚችል ዕርምጃ ጥያቄ ቀርቧል።
የምክር ቤት አባላት ለአብነት በረቂቁ እንደተቀመጠው አንድ ባለይዞታ ይዞታውን ለራሱ ወይም ለሦስተኛ ወገን ዋስትና አስይዞ ብድር ማግኘት እንደሚችል መደንገጉን፣ ይሁን እንጂ ይዞታውን አስይዞ ብድር የወሰደ ግለሰብ ብድሩን ሳይከፍል ሲቀር አበዳሪው መሬቱን ልሽጥ ብሎ ቢነሳ፣ በሕገ መንግሥቱ መሬት አይሸጥም አይለወጥም የሚለውን ድንጋጌ የሚጥስ መሆኑ ጥያቄ አስነስቷል፡፡
በረቂቅ አዋጁ አንድ ባለይዞታ መሬቱን አስይዞ የተበደረውን ገንዘብ መመለስ ባይችል ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ በማሰብ፣ አበዳሪው በመሬቱ የሚጠቀምበት የጊዜ ጣሪያ ከአሥር ዓመታት መብለጥ እንደሌለበት ተደንግጓል።
በፓርላማው ሕገ መንግሥታዊ ጉዳይ ያስነሳል ተብሎ ጥያቄ የተነሳበት ሌላኛው ጉዳይ ከአንድ በላይ ሚስቶች በሚኖሩበት ጊዜ፣ በመሬቱ ለመጠቀም ሲባል የሴቶችን መብት በሚያስጠብቅ መንገድ ምዝገባ መደረግ እንዳለበት የተቀመጠው ድንጋጌ ነው።
በረቂቁ እንደተብራራው ከዚህ ሕግ መውጣት በኋላ አንድ ሰው ከአንድ በላይ ጋብቻ የሚመሠርት ከሆነ፣ ከመጀመሪያ ሚስቱ ጋር ያለው ጋብቻ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ያላቸውን መሬት ክፍፍል ለማድረግ የመሬቱ መረጃ እንደ ድርሻቸው ወቅታዊ መደረግ አለበት ይላል፡፡
ይሁን እንጂ የምክር ቤት አባላት ይህ ከአንድ በላይ በሚል የሠፈረው ድንጋጌ ከሕገ መንግሥቱ፣ ከቤተሰብ ሕጉና ከሌሎች ሕጎች ጋር የሚጋጭና በትዳር ውስጥ ሌላ ችግር እንዳይፈጥር ሥጋታቸውን ገልጸዋል።