Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

መንግሥት የልኬት መሣሪያዎችን በማዛባት ሸማቹን የሚበዘብዙ ነጋዴዎችን አደብ ያስይዝ!

ሸማቾችና ተገልጋዮች ተጎጂዎች የሚሆኑባቸው የተለያዩ አጋጣሚዎች አሉ፡፡ ተመሳሳይ ሆነው በተመረቱ ዕቃዎች ወይም ምርቶች ይታለላሉ፡፡ ባዕድ ነገሮች ተቀላቅለውባቸው የሚቀርቡ ምርቶችም በርካታ ናቸው፡፡ ሚዛን የሚያነሱ ጠጣር ነገሮችን እንደ ድፍን ምስር ያሉ የእህል ዓይነቶች ላይ ሆነ ብለው በመቀላቀል ለገበያ የሚቀርቡ አሉ፡፡ ከደረጃ በታች የሆኑ ምርቶችን እንደ ኦርጅናል ምርት አስመስለው የሚሸጡ አስመጪዎችና ነጋዴዎች ተበራክተዋል። በዚህም ተመሳስሎ የተመረተ ከደረጃ በታች የሆነ ምርትን ሳያውቁ ወይም ያለ ጥርጣሬ የሚገዙ ሸማችም የዚያኑ ያህል ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ሸማቹ የሚታለልባቸው መንገዶች ብዙ ናቸው፡፡ 

በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ ተንሰራፍተው የቆዩት እንዲህ ያሉ የማጭበርበር ተግባራት ለቁጥጥር የማያመቹበት ሁኔታ አልፎ አልፎ ሊኖር እንደሚችል ቢታመንም፣ እየተቻለ ፈጽሞ ቁጥጥር የማይደረግባቸው ምርቶች መኖራቸው ደግሞ አይካድም። ቁጥጥር እንደሚደረግባቸው የሚታወቁት የልኬት መሳሪያዎች አሁንም ለሸማቹ መፍትሔ አላስገኙም፡፡ የልኬት መሣሪያዎች በዝተዋል፡፡ አንዳንዴ ፈጣሪን ፈርተው ምግባሩም ሃጢያት መሆኑን የተገነዘቡ ካልሆኑ ብዙዎቹ በልኬት መሣሪያዎችን አሳክረው ሸማቹን እየበዘበዙ ነው፡፡ 

‹‹በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የከተማችንን የንግድ መደብሮች ያጥለቀለቁት ዲጂታል የልኬት መሣሪያዎች ትክክለኛነት የብዙ ሸማቾች ጥያቄ ሆነዋል፡፡ 

እነዚህ የልኬት መሣሪያዎች በተለይም በሥጋ ቤቶች ውስጥ ተበራክተው የሚገኙ ሲሆን፣ በእነዚህ የልኬት መሣሪያዎች ተለክቶ አንድና ሁለት ኪሎ ተብሎ እዚያው በሥጋ ቤቱ የሚቀርብ ወይም ወደ ቤት የሚወሰድ ሥጋ በሌላ መለኪያ የመመዘን ዕድል ቢያገኝ ሸማቹች ምን ያህል እየተቀሸቡ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይቻላል። እንደው ሚዛኖቹን ሽቀባ ማለት ይቀናናል እንጂ እውነቱ ከነጋዴዎቹ ስግብግብ ባህሪይ የመነጨ መሆኑ አያጠራጥርም።

እንዴት እንደሚያበጃጁት ለማወቅ ባንችልም አንድ ኪሎ ስለመሆኑ ሲመዘን ያየነው ሥጋም ሆነ ሌላ ምርት በሌላ ሚዛን ሲለካ መጠኑ የተባለውን ያህል ካልሆነ ችግሩ የሚዛኑ ሳይሆን የነጋዴዎቹ ነው።

ከሥጋ ቤት ባሻገር በየነዳጅ ማደያዎቹ የሚገኙ ማሽኖችም በተመሳሳይ ሸማቾችን ለማጭበርበር ጥቅም ላይ እንደሚውሉ ይታወቃል። ብዙ ዕድል የለም እንጂ አሥር ሊትር ተብሎ የሚቀዳልን ነዳጅ ትክክል ስለመሆኑ አለመሆኑ ማረጋገጥ ቢቻል እዚህ አካባቢም ቅሸባ መኖሩን ማረጋገጥ ይቻላል።

እርግጥ ነው የነዳጅ መቅጃ ማሽን እንዲቀዳልን ያዘዝነውን መጠን ሊያሳይን ባይችልም በነዳጅ ታንከራችን ውስጥ በትክክል የገባው ግን ከዚያ በታች ሊሆን ይችላል፡፡ እንዲህ ያለው ተግባር ምግባረ ብልሹ በሆኑ ሠራተኞች ባላቸው ማደያዎች የሚፈጸም ነው፡፡ እንደውም ነዳጅ ግብይት በዲጂታል መንገድ ይሁን ሲባል ይህንን አሠራር ቀድመው ካጉረመረሙ ወይም ከተቃወሙት መካከል እኚሁ ነዳጅ በመቀሸብ የሚታወቁት ምግባረ ብልሹ ሠራተኞች ናቸው፡፡ እንደሰማሁትም አሥር ሊትር ቀዳን ብለው ዘጠኝ ሊትር ሲቀዱ የአንድ ሊትሯን ሒሳብ ወደ ኪስ ለማስገባት አላመቻችም፡፡ በጥሬ ገንዘብ ግብይቱ በሚፈጸምበት ወቅት ግን የተሸጠውን ሒሳብ አስልተው ይወስዳሉ፡፡ የዲጂታል ክፍያ አገልግሎቱ እንዲህ ያለውን ሌብነት ያስቀረ ቢሆንም አሁንም ግን ካለተራ አልፎ ጥሬ ገንዘብ የሚቀበሉ ማደያዎች አካባቢ ይህ ሌብነት አለመቅረቱ ማነጋገሩ አልቀረም፡፡ የማደያ ባለቤቶቹም ቢሆኑ መሣሪያቸው አሳንሶ እንዲቀዳ እያደረጉ ስለሚሆን ችግሩ ተቀርፏል ሊባል አይችልም፡፡ የልኬት መጠሪያውን ያኔም አሁንም ትክክለኛ መንገድ እንዳይቆጥር እያደረጉ አሉ የሚለው መረጃ የሚጣል አይደለምና ሠራተኞችም ይሁኑ ባለቤት ተጎጂው ተገልጋዩ ስለሚሆን እነዚህ መሣሪያዎች ትክክለኛነታቸውን ቶሎ ቶሎ መቆጣጠር ካልተቻለ ችግሩ ቀጣይ ነው፡፡ እንዲህ ምን በርከት ያሉ ማደያዎች በዚህ ፀያፍ ተግባር ላይ መሰማራታቸው ተረጋግጦ ዕርምጃ ታሽገው እንዲያስተካክሉና ሕጋዊ ዕርምጃም እንደሚወሰድባቸው መገለጽን እናስታውቃለን ከዚያ በኋላ ግን በትክክል እየሠሩ ስለመሆኑ ማረጋገጫ የለም፡፡ ሌላም ምሳሌ እንጥቀስ ከሰሞኑ ዳቦ ቤቶች በግራም ምን ያህል መሸጥ እንዳልባቸው ተገልጾላቸዋል፡፡ እስካሁን በነበረው አሠራርም 100 ግራም ብለው የሚሸጡልን ዳቦ መቶ ግራም ስለመሆኑ ማረጋገጫ ባይኖረንም ገዝተን እንጠቀማለን፡፡ አዲስ በሚወጣው ሕግ 70 ግራም ዳቦ 10 ብር እንዲሸጥ ተወስኗል፡፡ ችግሩ እንዲህ ያለውን መመርያ በአግባቡ ስለመተግበሩ አረጋጋጩ ማነው? የልኬት መሳሪያን በመጠቀም የሚሠራው ሸፍጥ በቦታና በንግድ ዘርፍ የሚለያይ ቢሆንም በተለይ እንደ ዳቦ ያሉ ምርቶች በወጣው ሕግ መሠረት ጥብቅ ክትትል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ አሁንም ይህንን ሁሉ ዳቦ ቤት በትክክል ስለመሥራታቸው የመቆጣጠሪያ መንገዱ አለ ተብሎ አይታሰብም፡፡ ስለዚህ ቢያንስ በሕግ ቁጥጥር የሚደረግባቸው ዘርፎች ላይ ያሉ የልኬት መሣሪያዎች ትክክለኛነት የሚረጋገጥበት መንገድ ይኑር ዓመት ተጠብቆ የሚከናወን ከሆነ የሚያመጣው ለውጥ አይኖርም፡፡ 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት