በያሬድ ነጋሽ
‹‹ሻምፒዮን ለመሆን መጀመሪያ መስመሩን ከማቋረጥ የበለጠ ጥረት ይጠይቃል። ለፍትሐዊ ጨዋታ (Fair Play) ቅድሚያ የሚሰጥ ሻምፒዮንነት ለስፖርት የውበት ባህሪን ከመስጠት በተጨማሪ ከአሸናፊነት በላይ ነው። ሻምፒዮን በፍትሐዊ ጨዋታ መንፈስ ራሱን ያዘጋጀ ነው፤›› ጄንኖ ካሙቲ፣ የዓለም አቀፍ የፍትሐዊ ጨዋታ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት።
ከላይ ጠቅለል ተደርጎ የተቀመጠው ፍትሐዊ የስፖርታዊ ውድድር መንፈስን (Fair Play) ሲነሳ በተለይም በእግር ኳስ ውድድር፣ በበርካታ በስፖርት ወዳጆች ህሊና ቀድሞ የሚከሰተው በውድድር ሥፍራዎች የሚደርሱ ጉዳቶችን ችላ በማለት ውድድሩ እንዲቀጥል በመደረጉ ሳቢያ የሰው ሕይወት መጥፋቱን ተከትሎ ተጨዋቾች በፈቃደኝነት ለጉዳቱ ቅድሚያ እንዲሰጡ፣ ካልሆነም የጨዋታው ዳኛ አስገድዶ ጨዋታውን እንዲያቋርጠው የተደረገበትን አሠራር ሲሆን (Fair Play) ከዚህ በዘለለ ከታች የተጠቀሱትን የማይሻሩ ጽንሰ ሐሳቦችን ያነገበ ነው።
ክብር ፡- ለእያንዳንዱ ተወዳዳሪ የተጻፉና ያልተጻፉ ሕጎችን የማክበር ግዴታ አለበት። ፍትሐዊ ጨዋታ ለተጋጣሚዎች፣ ለተጨዋቾች፣ ለዳኞችና ለደጋፊዎች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታያለንን ክብርን ይጠይቃል፡፡
ጓደኝነት፡- የሜዳ ላይ ፉክክር ጓደኝነትን አያጠፋም። በተቃራኒው ወዳጅነት ከትልቅ ፉክክር ሊመነጭ ይችላል፡፡
የቡድን መንፈስ፡- ግለሰቦች በራሳቸው ጠንካራ ሊሆኑ ይችላሉ። ነገር ግን ከዚያ በላይ በኅብረት በጣም ጠንካራ ናቸው። የድል ጊዜን ከቡድን ጋር መጋራት የመጨረሻው ደስታ ነው፡፡
እኩልነት፡- በእኩልነት መወዳደር በስፖርት ውስጥ አስፈላጊ ነው። አለበለዚያ አፈጻጸሙ በትክክል ሊለካ አይችልም፡፡
ከዶፒንግ ነፃ ስፖርት፡- አደንዛዥ ዕፅ ወይም ዶፒንግ በመውሰድ አለመታለል ማለት ነው። ይህን የሚያደርግ ማንኛውም ሰው ጨዋታውንና ታዳጊዎችን ያበላሻል፡፡
ታማኝነት፡- ታማኝ መሆንና ጠንካራ የሞራል መርሆዎች መከተል ለፍትሐዊ ጨዋታ አስፈላጊ ናቸው። እውነተኛ ሻምፒዮን ለመሆን ካሰቡ ስፖርትን በጥሩ የሥነ ምግባር ማዕቀፍ ውስጥ መከወን በጣም አስፈላጊ ነው፡፡
አንድነት፡- እርስ በርስ መደጋገፍ፣ ስሜትን፣ ዓላማዎችንና ሕልሞችን መለዋወጥ አስፈላጊ ነው። የጋራ መደጋገፍ በሜዳም ሆነ ከሜዳ ውጪ የጋራ ስኬትን ያመጣል፡፡
መቻቻል፡- የማትስማሙበትን ባህሪ ወይም ውሳኔ ለመቀበል ራስን መግዛትን ያዳብራል፡፡
እንክብካቤ፡- እውነተኛ ሻምፒዮናዎች ለሌሎች እንክብካቤ ሳይደረግበት የተገኘ ድል ደስታ እንደማያስገኝ ስለሚያውቁ አንዳቸው ለአንዳቸው ይጨነቃሉ፡፡ የሚሉና ሌሎች መርህዎችን አካቶ አሁን ያለንበት ወቅት ድረስ ደርሷል። ይህንን ተከትሎ በውድድር ወቅት በልዩ ሁኔታ ፍትሐዊ የስፖርታዊ ውድድር መንፈስን (Fair Play) ለሚተገብሩ ስፖርተኞች ዓለም አቀፍ ሽልማቶችንም የማበርከት ልማዱም አለ።
ወደ እግር ኳሱ መድረክ ስንመጣ ፊፋ አርዓያ ይሆናሉ ያላቸውን ክስተቶች እየተከታተለ ከ1987 ዓ.ም. ጀምሮ ለበርካቶች ሽልማቱን በማበርከት ላይ ይገኛል።እግር ኳስ ሜዳ ውስጥ በጉዳት ምክንያት ምላሱ ታጥፎ መተንፈስ የቸገረውን ተጨዋች ምላሱን እንዳይውጥ በመርዳት ሕይወት መታደጉ የሚወሳው የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጨዋች በኃይሉ አሰፋ ቱሳ ከፊፋ ቀርቶ፣ ከአገራችን የስፖርት አስተዳደር አርዓያ ለሚሆን ተግባሩ ሽልማት ባይበረከትለትም በ2013 ዓ.ም. የካቲት ወር አዳማ ከነማ ከወላይታ ድቻ ጋር ባደረገው ጨዋታ ወቅት የአዳማው ግብ ጠባቂ ታሪክ ጌትነት ከራሱ ቡድን ተጫዋች አሚር ነስሩ ጋር ተጋጭቶ ምላሱ ታጥፎ መተንፈስ ባቃተው ወቅት ሆስፒታል ደርሶ ጤንነቱ የመስተካከሉን ዜና የሰሙ የስፖርት ቤተሰቦች፣ ‹‹በኃይሉ አሰፋ ቱሳ ቢኖር ሆስፒታል ድረስ አይሄድም ነበር…›› በማለት በኃይሉን ከሽልማት በላይ የሆነ መልካም ስም እንደቸሩት እናስታውሳለን።
የሲድኒ የእግር ኳስ ክለብ ግብ ጠባቂ ዳኒ ቩኮቪች በእግር ኳስ ሜዳው ላይ የሚበር ወፍ በኳሱ ተመትቶ በወደቀበት ወቅት የዳኛውን ትኩረት ወደ ክስተቱ በመሳብ ጨዋታውን እንዲያቆም አስገድዶ የተጎዳውን ወፍ አስፈላጊውን ሕክምና ወደሚያገኝበት አስተማማኝ ቦታ በመውሰዱ፣ ፍትሐዊ የውድድር መንፈስ (Fair Play) ሰፋ ያለ ጽንሰ ሐሳብ እንዳለው ያስመሰከረበትና የእንስሳት ተሟጋቾችን ምሥጋና ያተረፈበት ነበር።
ሌላው እ.ኤ.አ. በ2003 በዴንማርክና በኢራን መካከል በተደረገው ዓለም አቀፍ ጨዋታ ወቅት አንድ ኢራናዊ ተጫዋች ከደጋፊ የሰማው የፊሽካ ድምፅ ከዳኛ የመጣ መስሎት ኳሱን በራሱ የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ በእጁ ማንሳቱን የተመለከተው ዳኛ የፍፁም ቅጣት ምት ከመስጠት ባይቦዝንም፣ የዴንማርኩ አማካይ ሞርተን ዊግሆርስት ከአሠልጣኙ ሞርተን ኦልሰን ጋር በኢራኑ ተጫዋች የስህተቱ ምንጭ ላይ ፈጣን ውይይት ካደረገ በኋላ፣ ፍፁም ቅጣት ምቱን ከጎል በስተቀኝ በኩል ወደ ውጭ እንዲወጣ አድርጎ በመምታት የዳኛው ውሳኔው ተገቢ እንዳልሆነ አሳየ።
የኢራናውያን ተጫዋቾች ለዊዬጎርስትን ለጨዋነቱ አጨበጨቡለት። ነገሩን የሚያስደንቅ የሚያደርገው የዊግሆርስት ቡድን ዴንማርክ በጨዋታው 1 ለ 0 መሸነፏ ሲሆን፣ ለዊግሆርስት በአስደናቂው ክስተት ባደረገው ደፋር ስፖርታዊ ጨዋነት ውሳኔ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ልዩ ሽልማትን አበርክቶለታል። የእዚህ ዴንማርካዊ ካፒቴን ድርጊት፣ ‹‹ሰው በተደናገረበት ገጠመኝ ተጠቅሜ ትርፍ አላጋብስም። ሰዎች በተደናገሩበት ሁኔታ ውስጥ ከሚገኝ ትርፍ ይልቅ ኪሳራ ይሻለኛል፤›› የሚል ትርጉም ከማንገቡ ጋር ተያይዞ፣ ‹‹በእግር ኳስ ሜዳ ላይ ታላላቅ ቅዱሳት መጻሕፍት ተይዘው ለዓለም ሕዝብ ስብከት የተሰበከበት ነበር፤›› ሊባል ያስችለዋል።
የፍትሐዊ የጨዋታ መንፈስ (Fair Play) “Global Problems as a Top Priority” የሚል ሐሳብን ተሸክሞ የተመለከትንበትን ስፖርታዊ ክስተት እናስከትላለን። ከሰባት ዓመት በፊት የፓሪሱ ሴንት ዠርሜይን አጥቂ ዝላታን ኢብራሂሞቪች በካየን ላይ በሁለተኛው ደቂቃ ጎል ካስቆጠረው በኋላ ደስታውን ለመግለጽ ማሊያውን በማውለቁ ባገኘው ቢጫ ካርድ ሳቢያ፣ ቀድሞ ካያቸው ቢጫ ካርዶች ጋር ተደምሮ በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ከሞናኮ ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ በዕገዳ ምክንያት እንዲያልፈውቢያደርገውም፣ በወቅቱ ማሊያውን ለማውለቅ ምክንያት የሆነውና በሰውነቱ ላይ የተነቀሰው ጊዜያዊ ንቅሳት ትልቅ መልዕክትን ለዓለም ያጋራበት ነበር። ‹‹ቅዳሜ ማሊያ ሳወልቅ… ንቅሳቴ በዓለም ዙሪያ በረሃብ የሚሰቃዩ 50 የእውነተኛ ሰዎች ስም የያዘ ነበር። ንቅሳቱ ጊዜያዊ ስለሆነ ይጠፋል። ግን ሰዎቹ አሁንም እዚያ አሉ። በዓለም ዙሪያ 805 ሚሊዮን ሰዎች በረሃብ እየተሰቃዩ ይገኛሉ። የዓለም ምግብ ፕሮግራምን ለመርዳት እንድትነሳሱ እፈልጋለሁ፤›› ብሏል ዝላታን በድረ ገጹ። የዝላታንን ሐሳብ የተመለከተ፣ ‹‹ዛሬ በየዘርፉ ያሉ ታዋቂ የአገራችን ሰዎች በሽልማት ፕሮግራሞችና በቃለ መጠይቅ ወቅት ባልተገባ መንገድ አነጋጋሪ የሚሆኑ አለባበሶችን ከመምረጥ ይልቅ፣ በአገራችን ትኩረት የተነፈጋቸው ዘርፈ ብዙ ችግሮችን የማስተጋቢያ መድረክ በማድረግ ትኩረት እንዲያገኙ ሊያደርጉ አይገባም?›› በሚል መጠየቁ አይቀሬ ይሆናል።
ወደ ቀደመ ነገራችን ስንመለስ፣ እግር ኳስ 22 ሰዎች አንዲት ቅሪላ ከበው ከወዲያ ወዲህ የሚያለፉበት የስፖርት ዘርፍ ብቻ ሳይሆን፣ ከላይ በተመለከትነው የሥነ ምግባር ደንብ ላይ ተንተርሶ አያሌ ዓለም አቀፍ አጀንዳዎች የሚተላለፉበት ዓይነተኛ መስክ ነው፡፡
በቅርብ ጊዜ በጋዜጠኛ ሰኢድ ኪያር የሚቀነቀነው “እግር ኳስ ያለ በረኛ” የሚል አስተሳሰብ ኢትዮጵያዊ ፍልስፍና ሆኖ ብቅ ብሎ ተመለከትን። ‹‹በረኛም ጎል ድረስ ደርሶ ግብ ሊያስቆጥር የሚችል ተጫዋች ነው፤›› ይለዋል ሰኢድ ነገሩን ሲያብራራልን (በ2015 ዓ.ም. ሰይፉ በኢቢኤስ ላይ እንግዳ ሆኖ ከተናገረው)። ይህንን የእግር ኳስ ፍልስፍና ለመጀመሪያ ጊዜ የተመለከትነው በ2010 ዓ.ም. በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 የወጣት ማዕከል ሜዳ ላይ በተካሄደ እግር ኳስ ውድድር ላይ ነበር (ሰኢድ ከዚህ ቀደም ሌላ ሥፍራ አሳይቶት ሊሆን ይችላል። ከዚህ ጊዜ በኋላ ግን በተለያዩ የክልል ከተማዎች ሳይቀር ለተግባራዊነቱ ተንቀሷል)፡፡
ዕለቱ ቅዳሜ ጠዋት ነበር፡፡ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ አባል የነበረበትና በዊኒ ዓለምአየሁ የተመሠረተው ደብርዓባይ የእግር ኳስ ቡድን፣ ጋዜጠኛ ሰኢድ ኪያር ይዞት ከመጣው ቡድን ጋር የጨዋታ ቀጠሮ አለው፡፡ የደብርዓባይ ቡድን ለሜዳው ቅርብ በሆኑ ልጆች የተዋቀረ በመሆኑ ትጥቁን አሰናድቶ እንግዳውን ቡድን መጠባበቅ ጀመረ፡፡ አረፋፍዶ ወደ ሜዳው የደረሰው የሰኢድ ኪያር ቡድን አዲስ ድባብን በሜዳው ላይ አረበበ፡፡ ይዞት የመጣው የአጨዋወት ሥልት ባይታወቅም፣ ራሱ ሰኢድ ኪያርን ጨምሮ የቀድሞ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች የሆኑትን ትልቁን አንዋርና ዋበላ (ነፍስ ይማር)፣ ከቅርቦቹ መሀል ደግሞ መሱድ መሐመድ ዓይነት ክፍያ ተከፍሎ በትልልቅ መድረኮች ላይ እንመለከታቸው የነበሩ ልጆች፣ ከከፍታ ሥፍራቸው ወርደው የመንደር ሜዳ ድረስ ለጨዋታ መምጣታቸው ሜዳው አካባቢ ውሎዋቸውን ላደረጉ በርካታ ተስፈኛ ጨቅላ እግር ኳስ ተጫዋቾች ጠቀሜታው በእጅጉ የላቀ በመሆኑ አፅንኦት የሚቸረውና በሌሎች መስክ ያሉ ፕሮፌሽናሎችም እንዲህ ታች ወርደው ማኅበረሰቡን ቢገናኙት አገራዊ ጠቀሜታው እንደሚያይል የብዙዎች እምነት ሆነ፡፡
ተጋጣሚው የጨዋታውን ጅምር የሚያበስረውን ፊሽካ በመጠባበቅ ላይ ሳለ ግን፣ ‹‹አንጋፋና ወጣት እግር ኳስ ተጫዋቾች ወደ መንደር ወርደው አማተር ውድድር ላይ ለመሳተፉ መምጣታቸው ለታዳጊዎች ዓይነተኛ ጠቀሜታ አለው፤›› በሚል የተቸረው አድናቆት ላይ ውኃ የሚቸልስ ክስተት ተፈጠረ። ይኼውም ጋዜጠኛ ሰኢድ ኪያር ይዞት የመጣው ቡድን ያለ በረኛ እንደሚጫወት፣ ወይም በረኛው ከተቀሩት ተጫዋቾች ጋር ተቀላቅሎ ኳስ እንደሚጫወትና ጎላቸው ባዶውን እንደሚሆን ተነገረ (በረኛ ልገልብጥልህና ጆተኒ ግጠመኝ ዓይነት)፡፡
ፊሽካው ተነፍቶ ከተጀመረ በኋላ ጨዋታው መልኩን አጣ፡፡ በእግር ኳስ ጨዋታ እንዲኖር የሚፈለገው ጨዋነት፣ ጓደኝነትና ወንድማማችነት ድራሹ ጠፋ፡፡ ፀያፍ ስድብ በረከተ፡፡ የደብርዓባይ እግር ኳስ ቡድን አባላት እግር ኳስን በቅጡ ለመጫወት አቅሙ የነበራቸው ቢሆኑም፣ ይህ ቀርቶ በከፍተኛ ቁጣ “ኳሱን ካጣህ እግሩን” በሚል የቴኳንዶ ስብስብ አባላት መስለው ጨዋታውን 4 ለ 0 አሸንፈው አጠናቀቁ፡፡
ጨዋታው እንዳለቀ ሁሉም የደብርዓባይ ቡድን አባላት የተመካከሩ ይመስል ወደ ጋዜጠኛ ሰኢድ ኪያር በመምጣት፣ “እኛም ማልያ ለብሰናል!” የሚል ንግግር ተናግረው ሜዳውን ለቀው ወጡ፡፡ እግር ኳስን ያለ በረኛ አቀንቃኙ ቡድንም ጨዋታውን በሚመለከት በአያሌ ደጋፊዎች እየተንጓጠጠ ወደ መጣበት ተመለሰ፡፡
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የደብርዓባይ እግር ኳስ ቡድን አባላት ለቁርስ በተሰባሰቡበት ወቅት፣ የጨዋታውን መንፈስ ስለቀየረውና ወንድማማችነቱን ስላጠፋው ክስተት መወያየት ጀመሩ፡፡
የደብርዓባይ የእግር ኳስ ቡድን የቀድሞ እግር ኳስ አሠልጣኝ በነበሩትና በሕይወት ጫና ምክንያት ከስፖርት በራቁት አቶ ከበደ (ከአየር ጤና አካባቢ ተነስተው በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ሚና ባላቸው እግር ኳስ ተጫዋቾች ላይ የእኚህ አሠልጣኝ አሻራ የላቀ ነበር) የሚሠለጥን፣ በወቅቱ እግር ኳስን ከሙያተኛ ባልተናነሰ መልኩ ተጫውተው ያደጉና ዕድል በማጣታቸው እንጂ በዘርፉ የበኩላቸውን አበርክተው ማለፉ ይቻላቸው የነበሩ እንደ ዮሴፍ አካሉ፣ ማሙሽ ለማ፣ ቴዎድሮስ ውስኑና ሌሎችም ልጆች ያካተተ በመሆኑ የዕለቱን ጨዋታ ለመገምገም ከበቂ በላይ የሆነ ስብስብ ነበር፡፡
የመጀመሪያው የውይይት ነጥብ የጋዜጠኛ ሰኢድ ‹‹‘ቡድናቸው ይዞት በመጣው አዲስ የእግር ኳስ ፍልስፍናና የተጫዋቾች ዕውቅና ላይ የተቀሰቀሰ የተቃራኒ ቡድን የቅናት መንፈስ የጨዋታውን ዓውድ ቀይሮ ሥርዓት አልበኝነት አነገሠ’ ብለው ሊያስቡ ይችሉ ይሆናል፤›› የሚል ጥርጣሬ ተነሳ። ይህንን አስበው ከሆነም ተጨማሪ ስህተት ውስጥ ሊጥላቸው እንደሚችል የሚያስታውስ ዓለም አቀፍ እግር ኳሳዊ የታሪክ ክስተት ለአብነት ተነሳ፡፡
ሉዊስ ናኒ እ.ኤ.አ. ሐምሌ 2007 ዓ.ም. (2007 እና 2008 የውድድር ዓመት) በአሌክስ ፈርጉሰን ይሠለጥን የነበረውን ማንቸስተር ዩናይትድ ከተቀላቀለ በኋላ፣ በአንድ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ላይ በተቃራኒ ሜዳ በቀኝ ኮርነር አቅራቢያ፣ በወቅቱ በዕድሜ ለጋ የነበረው ይህ ፖርቹጋላዊ በግንባሩ ለአምስት ሰከንድ ያህል እያንጠባጠበ በተጋጣሚ ተከላካዮች መሀል ለማለፍ ይሞክራል፡፡ የተጋጣሚ ተጨዋቾች ሉዊስ ናኒን ጨዋታው እስኪጠናቀቅ ድረስ አካሉን ለመጉዳት ያደርጉት የነበረው ጥረትን ለተመለከተ፣ ‹‹ፖርቹጋላዊው ከባድ አደጋ ሳይደርስበት ጨዋታውን መጨረሱ ዕድለኛ የሚያስብለው ነው፤›› ማለቱ አይቀርም፡፡ “Disrespectful Moment in the Football History” በሚል ዩቲዩብ ላይ ቢፈልጉ፣ ለተጋጣሚ ክብር የነፈጉ በርካታ ድርጊቶችና የተቃራኒ ቡድን ተጫዋቾች ምላሽ ምን እንደነበር መመልከት ይቻላል።
ሉዊስ ናኒ ነገሩን የተረዳበት መንገድ ግን፣ ባሳየው የላቀ ክህሎት የቼልሲ ተጨዋቾች ንዴትና ቅናት አድሮባቸው ሊጎዱት እንደፈለጉ ነበር፡፡ ነገር ግን ናኒ ሁኔታውን በግልጽ ለመረዳት ሩቅ መሄድ አላስፈለገውም፡፡ አንጋፋ የቡድን አጋሩ የሆኑት ጊግስና ፖል ስኮልስ በቴስታ ሊያንጠባጥብ የሞከረበት መንገድ መደበኛ ባልሆነ (Freestyle) ወይም በልምምድ ሥፍራ ዓይነት ቦታዎች የሚደረግ በመሆኑ፣ ለተጋጣሚ ክብር የሚነፍግና የቼልሲ ቡድን ተጫዋቾች ቁጣ ከዚህ የመነጨ መሆኑን ጠቅሰው እንዲታረም መክረውት ነበር፡፡
የማንቸስተር ዩናይትድ አንጋፋዎቹ ተጫዋቾች ምክርና የደብርዓባይ እግር ኳስ ቡድን ተጫዋቾች ለጋዜጠኛ ሰኢድ ኪያር፣ “እኛም ማልያ ለብሰናል” በሚል የገለጹበት መንገድ ትርጓሜያቸው አንድ ነበር፡፡ ‹‹መደበኛ ያልሆነ ነገር በመደበኛ እግር ኳስ ውስጥ ማምጣት ለተቃራኒ ቡድን አሠልጣኝ፣ ደጋፊና ተጫዋቾች ክብር ይነፍጋል፡፡ ክብር ሲጎድል ጓደኝነት፣ ወንድማማችነት፣ ወዳጅነት የተሰኙ የ(Fair Play) ሕግጋቶች ይጓደላሉ። ይህ ሲጓደል ደግሞ እግር ኳስ ዓለም አቀፍ ጠቀሜታ ያላቸው ማኅበረሰባዊ አጀንዳዎ የሚተላለፉበት መሆኑ ቀርቶ፣ ሊያዩት የሚጠየፉት የዋልጌዎች መናኸሪያ ይሆናል (በፕሮፌሽናልም ይሁን በመንደር ደረጃ ባለ ውድድር)። ጋዜጠኛው ይህንን ቢዘነጋውም፣ ትልቁ አንዋርን ያከሉ አንጋፋ ተጫዋቾች፣ ይህንን ጽንሰ ሐሳብ የሳተ ፍልስፍና ባለመኮነናቸው ቅሬታ ያጭራል የሚሉ ሐሳቦች የውይይቱ አካል ሆኑ።
እግር ኳስ ውስጥ ኖሮ ጨዋታውን ከነፍሱ ያዋሀደ የትኛውም አካል ወደ ሕዝብ ይዞታ ባይመጣም እንኳን፣ “እግር ኳሱ እንዲህ ቢሆን” ብሎ የሚያስበው የራሱ ፍልስፍና ይኖረዋል፣ አብነት እናንሳ።
በዚሁ ደብርዓባይ የእግር ኳስ ቡድን ውስጥ አባል የሆነው ዳንኤል ጥበቡና ሌሎች ጓደኞቹ፣ ‹‹ውጤቱ ቀደም ብሎ የሚታወቅ እግር ኳስ›› የሚል ልዩ የእግር ኳስ ፍልስፍና ነበራቸው። ይኼውም ከፊት ባሉት የጨዋታ ደቂቃዎች የሚሆነው የሚታወቅና ከሙዚቃ ጋር የተቀነባበረ ዓይነት ነበር፡፡
ዝርዝር ሐሳቡ በእግር ኳስ ታይሚንግ ከሙዚቃ ሪትም ጋር እኩል በጊዜ ቤት መሠላት የሚችል መሆኑን፣ በእግር ኳስ ፔስ ማለት በሙዚቃው ቴምፖ ከሚሉት ጋር አቻ እንደሆነ፣ ከአንድ ተጫዋች የተሸማ ኳስ በተሳካ ሁኔታ ለሌላኛው ጓደኛው ሲደርስ የጊዜ ቤት ሥሌቱ በሙዚቃ ኖታ ድርደራ ላይ ሙሉ ባር መሆን እንደሚችል ከግንዛቤ በማስገባት፣ የአምስት ደቂቃ ተስማሚ ሙዚቃ ተደርሶ እግር ኳስ ተጫዋቾች በከሮግራፊ ተሰናድተውበት ሊጫወቱበት እንደሚቻልና “ደብ” በሚባል የሙዚቃ ሥልት መስማት የተሳናቸው ሰዎች በትልልቅ ስፒከሮች ሙዚቃው ሰውነታቸውን እንዲነዝር በማድረግ እንዲደንሱ እንደተቻለ ሁሉ፣ በሙዚቃ በተቀነባበረ እግር ኳስ ዓይነ ሥውራን ከእግር ኳስ ምቱ ጋር የተጣጣመ የሙዚቃ ድምፆችን ወደጆሯቸው እንዲደርስ በማድረግ እግር ኳስን ማጣጣም የሚችሉበትን መንገድ ማመቻቸት እንደሚቻል እነ ዳንኤል ያምናሉ፡፡
ይኼም ቢሆን በሰነድ ደረጃ ተዘጋጅቶ ለተግባራዊነቱ አያሌ ጥናትና ምርምር የሚፈልግ ጽንሰ ሐሳብ ቢሆንም ታዲያ፣ ይህንን ፍልስፍና የራሱን ዘዬ ሊቀይሱለት የሚገባ አማራጭ የእግር ኳስ መንገድ ሊሆን እንደሚችል ሲያበክሩ እንጂ ‹‹በመደበኛ እግር ኳስ ውስጥ ይዘነው ካልመጣን›› የሚል ውርርድ ውስጥ ሲገቡ አላየናቸውም። የመጀመሪያው ውይይት በዚህ ተጠናቀቀ። በቁርስ ሰዓቱ በሁለተኝነት የተነሳው የውይይት አጀንዳ፣ “እግር ኳስ ያለ በረኛ” የሚለው ፍልስፍና ኢትዮጵያዊ አበርክቶ ሆና ለዓለም እንዲተዋወቅ ጋዜጠኛው ምን ማድረግ አለበት የሚል ነበር፡፡
- ይኼ ፍልስፍና ወደ ሕዝብ ከመምጣቱ በፊት በመጀመሪያ ከስፖርት ሳይንስ ሊቃውንት ጋር በመቀናጀት፣ ጥናታዊ ሰነድ በማዘጋጀት፣ ሰነዱን በተዘጋ ስቴዲየም ውስጥ መሬት ላይ መውረድና ጉድለቱ በጉልህ መፈተሽ ነበረበት (ጋዜጠኛ ሰኢድ ይህንን ያደረገ አይመስልም)፡፡ ለምሳሌ አንዱ ቡድን ብቻ በረኛ ከማይኖረው (ጆተኒ በረኛ ልገልብጥልህና ግጠመኝ እንዳይሆን፣ በዚህም ሳቢያ “ለተጋጣሚ ክብር” የተሰኘውን የነፃ ጨዋታ ሕግ ጥሶ፣ ግልፍተኝነትን የሚቀሰቅስና በሜዳ ላይ ሥርዓት አልበኝነት የሚያነግስ በመሆኑ)፣ ሁለቱም ቡድን በረኛ ባይኖራቸውና ፍልስፍናው ከመደበኛው ውድድር ወጥቶ “በረኛ የሌለበት የእግር ኳስ ዓይነት” ተብሎ ቢጠራ፡፡
- የራሱ ሕጎች ቢረቁለት ለምሳሌ በረኛ ከሌለ በተገኘው ቦታ ኳስ እየተመታ ጨዋታው የጎል ጎተራነቱ እንዳይበዛ፣ “ፍፁም ቅጣት ምት ውስጥ ሳይገባ ማግባት አይቻልም” የሚሉና ሌሎች የራሱ ሕጎች ቢረቁለት ተገቢ ነው፡፡ ምክንያቱን ይኼ ቡድን ከአሥር ጎል በላይ ተቆጥሮበት የተሸነፈባቸው ጨዋታዎች እንዳሉም መመልከታችን፣ ችግሩ ከየትም ቦታ ኳስ ተመቶ ጎል የሚቆጠርበት ከመሆኑ የመነጨ እንደሆነ በግልጽ መናገር ይቻላል (ጋዜጠኛ ሰኢድ በሰይፉ በኢቢኤስ ፕሮግራም ላይ በነበረው ቃለ መጠይቅ ወቅት፣ ‹‹ለተጋጣሚ ፋታ በማሳጣትና ኳስን በመቆጣጠር ጎል እንዳይቆጠርብን ማድረግ ይቻላል›› በሚል የገለጸው ሐሳብ አይደለም፣ ሙያቸው እግር ኳስ መጫወት ከሆኑት ፕሮፌሽናሎች ጋር ይቅርና ከመንደር ተጨዋቾች ደረጃ ቢሆን እንኳን የሚሳካ እንዳልሆነ ያበክረዋል)፡፡
በተረፈ በጥናትና በቤተ ሙከራ ላይ የተመሠረተ ማስተካከያ ተደርጎበት ወደ ተግባር ቢገባበት፣ ኢትዮጵያዊ የሆነ አዲስ የእግር ኳስ ፍልስፍና ለዓለም ልናበረክትበት የምንችልበት አጋጣሚ ዝግ እንዳልሆነ በማውሳትና መሠረታዊ ነገር ቢስትም እንኳን፣ አስተሳሰቡን ላፈለቀው አዕምሮ አድናቆት በመቸር ከጨዋታ መልስ የነበረው የቁርስ ሥነ ሥርዓት ተጠናቋል።
ሰላም!
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡