ከኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ ሦስተኛው ክፍል ወጣት ወይም ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 29 ክልል ውስጥ የሚገኙ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በአፍሪካም ቢሆን አብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል ተምሮ ያልጨረሰ፣ በሥራም ያልተሰማራ አፍላ ወጣት ነው፡፡
ለአኅጉሪቷ ሀብት ከሆኑት ወጣቶች ባሻገር አፍሪካ በውስጧ የከበሩ ማዕድናት፣ ነዳጅና የተለያዩ የተፈጥሮ ፀጋዎችን የታደለች ብትሆንም፣ በየጊዜው በሚፈጠሩ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውሶች ዕድገቷን ገትተውታል፡፡ በአፍሪካ ብሎም በኢትዮጵያ በምግብ ራስን ከመቻል ጀምሮ ሌሎች ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ፍላጎቶችን ማሟላትም ፈተና ሆኗል፡፡
እንደ ምክንያት ተደርገው ከሚጠቀሱት መካከል ደግሞ የወጣቶችን ዕውቀትና ጉልበት በአግባቡ አለመጠቀም ይገኝበታል፡፡ በርካታ ወጣቶች መሥራትና መለወጥ እየፈለጉ፣ ነገር ግን ፍላጎታቸውንና አመለካከታቸውን እንዲሁም ተስፋቸውን የሚረዳቸው በማጣት ብቻ በድህነት ጎዳና ላይ ሆነው ይታያሉ፡፡
አፍሪካውያን ወጣቶች ፍላጎታቸው ምን ይሆን? ተስፋቸውስ?
ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሰሃራ በታች በሚገኙ ሰባት የአፍሪካ አገሮች ውስጥ በሚገኙ ወጣቶች ዙሪያ የተደረገውና ኅዳር 6 ቀን 2016 ዓ.ም. ለውይይት የቀረበው ‹‹አፍሪካ ዩዝ አስፓይሬሽን ኤንድ ሬዚሊየንስ ሪሰርች ፕሮጀክት፤›› እንደሚያመለክተው፣ በሰባቱ አገሮች የሚገኙ ወጣቶች ችግራቸው፣ አመለካከታቸውና ተስፋቸው ተቀራራቢ እንደሆነ አመላክቷል፡፡
ጥናቱ በኢትዮጵያ፣ በጋና፣ በኬንያ፣ በናይጄሪያ፣ በሩዋንዳ፣ በሴኔጋልና በዑጋንዳ ያሉ ወጣቶችን ያካተተ ሲሆን፣ የጥናቱ ዋና ዓላማም በተለይ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከተከሰተ ጀምሮ በወጣቶቹ ላይ ያሳደረው አንድምታና በአሁኑ ወቅትም ወጣቶች በፖለቲካውና በማኅበራዊ፣ እንዲሁም በኢኮኖሚው ያላቸውን ተሳትፎ ለመዳሰስ እንደሆነ የተናገሩት የፕሮጀክቱ ኦፊሰር ሚስተር ጆሊ ኦቲኖ ናቸው፡፡
ፕሮጀክታቸው ባደረገው ጥናት አብዛኛው ወጣቶች በቂ ሥራ እንደሌላቸውና ህልማቸውን ለማሳካት ሳይችሉ ስለመቅረታቸው መመልከት እንደቻሉ የተናገሩት ሚስተር ኦቲኖ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የአፍሪካ ወጣቶች የሥራ ዕድሉ ቢገጥማቸው መሥራትና መለወጥ እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ባሉ ወጣቶች ተመሳሳይ ጥናት የተደረገ ሲሆን፣ ጥናቱ በሰባት ክልሎችና በ38 ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ 1‚810 ወጣቶች ቃለ መጠይቅ ተደርጎላቸዋል፡፡ አብዛኞቹ ወጣቶች ሠርተው መለወጥን የሚሹ በማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚፈልጉም የጥናቱ አቅራቢ ኪያ ገዛኸኝ ተናግረዋል፡፡
በጥናቱ ወጣቶች የሚፈልጉትንና የሚያስቡትን ለመሆን የሚያደርጉት ጥረት ሳይሳካ እንደሚቀር፣ ህልማቸውና ተስፋቸው ግን ሠርተው መለወጥ እንደሆነ ጥናቱን ጠቅሰው አክለዋል፡፡
በደፈናው ወጣቶች ሥራ አይወዱም፣ ስንፍና ያጠቃቸዋል፣ በአቋራጭ መለወጥን ይፈልጋሉ የሚለው የቆየ አመለካከት ፈፅሞ የተሳሳተ እንደሆነ፣ ወጣቱ ከዚህ ይልቅ ለአገሬ እሠራለሁ ዕድሉን ካገኘሁ የማላደርገው የለም የሚል እንደሆነና በወጣቶች ላይ ያለውን አመለካከት መቀየር እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡
ስለጥናቱ አስፈላጊነትና ወጣቶችን አቅጣጫ ለማስያዝ መነሻ ሐሳብ እንደሚሆን የተናገሩት የፕሮጀክቱ ዋና መሪ አዳምነሽ ቦጋለ (ዶ/ር)፣ ጥናቱ የአፍሪካ ብሎም የኢትዮጵያ ወጣቶች ምን ይፈልጋሉ ሕይወታቸውስ ምን ይመስላል? ወዴትስ እያመሩ ነው? ምንስ ቢደረግላቸው ይበጃቸዋል? የሚሉትን ድምፆች ከራሳቸው አንደበት በመስማት መፍትሔ እንዲፈለግላቸውና እንደ አስፈላጊነቱ የልማት ፖሊሲዎችና አቅጣጫዎች እንዲቀመጡ የሚያግዝ እንደሚሆን ተናግረዋል።
በሌላ በኩል ወጣቶች የሚፈልጉትን ሕይወት ለመምራት፣ ከመማርና ከማወቅ በዘለለ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያላቸው ማኅበራዊ ተቀባይነት ምንድን ነው? የሚለውን ለመዳሰስ ሞክሯል ብለዋል፡፡
የጥናቱ ትልቁና አስደሳች ውጤት፣ ወጣቱ ሰነፍ ሥራን አምርሮ የሚጠላ፣ ሱሰኛና ቸልተኛ የሚለውን የቆየ አመለካከት፣ እንደሚባለው እንዳልሆነ በጥናቱ ማረጋገጣቸው መሆኑን አዳምነሽ (ዶ/ር) ጠቁመዋል፡፡
ከዚህ በተቃራኒ ወጣቱ ሠርቶ ራሱንም ሆነ አገሩን መጥቀም የሚፈልግ፣ አሁን ካለበት የኑሮ ሁኔታ የመውጣት ትልቅ ተስፋ እንዳለው የተመላከተ ሲሆን፣ በዕውቀትም ቢሆን ነገሮች ከተመቻቹለት ትልቅ ተስፋ እንዳላቸው ከጥናቱ በመነሳት አብራርተዋል።