Thursday, December 7, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ወደ ኢንዱስሪው የሚቀላቀሉበት የ‹‹ሲድስ ፎር ዘ ፊውቸር›› ሥልጠና

የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ወደ ኢንዱስሪው የሚቀላቀሉበት የ‹‹ሲድስ ፎር ዘ ፊውቸር›› ሥልጠና

ቀን:

ከዩኒቨርሲቲ ጨርሰው የሚወጡ ተማሪዎች በኢንዱስትሪ ውስጥ የሚገጥማቸውን የክህሎት ክፍተት ለመሙላት የተቀረፀው የሁዋዌ ሲድስ ፎር ዘፊውቸር ሥልጠና፣ ተማሪዎች የኢንዱስትሪ ዕውቀት ይዘው እንዲወጡ እያስቻለ መሆኑን ትምህርት ሚኒስቴር ይገልጻል።

የሁዋዌ ሲድስ ፎር ዘ ፊውቸር 2023 የሥልጠና ፕሮግራም፣ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የሚከናወን ሲሆን፣ ዘንድሮም ከ14 ዩኒቨርሲቲዎች ለተውጣጡ 106 ተማሪዎች ሥልጠናው ተሰጥቷል።

የሥልጠናው የመዝጊያ ፕሮግራም ኅዳር 4 ቀን 2016 ዓ.ም. የተካሄደ ሲሆን፣ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ደኤታ አቶ ንጉሡ ጥላሁን፣ የሁዋዌን ሲድስ ፎር ዘ ፊውቸር ሥልጠና የመሳሰሉ ቴክኖሎጂን ይዘው የሚመጡ ከፍተኛ አበርክቶ ያላቸው ዓለም አቀፍ ተቋማትን፣ ተቋማቸው በመጋበዝና ምቹ ሁኔታ በመፍጠር በኢትዮጵያ ሥልጠና እንዲስፋፋ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡

ተማሪዎቹ በሥልጠና ወቅት ያቀረቧቸውን የፈጠራ ሐሳቦች በማስታወስም፣ የተሠሩ ፕሮጀክቶች መሬት መንካትና መደገፍ እንዳለባቸው አክለዋል፡፡

የግሉ ዘርፍ በሚሠራቸው ሥራዎች ውስጥ የሚኒስቴራቸው ሚና ተመራቂዎች ወደ ሥራ በሚሰማሩበት ጊዜ የሚገጥሟቸውን ፈተናዎች እንዲያልፉ መደገፍና ማገዝ እንደሆነ ጠቁመው፣ ሠልጣኞች በቢዝነስ ሲሠማሩ፣ በዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ ዋነኛ ሞተር ሲሆኑ፣ ሲያሠለጥኑ፣ በተፈጠረው ገበያም ተጠቃሚ ሲሆኑ ከሁዋዌ ወይም ከግለሰቦች ጋር ሲሠሩ፣ ወደፊት ኢንተርፕራይዝ መሥርተው ሲንቀሳቀሱ ተገቢውንና አስፈላጊውን ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑንም ገልጸዋል።

በትምህርት ሚኒስቴር የአይሲቲና ዲጂታል ትምህርት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዘለዓለም አሰፋ (ዶ/ር)፣ ተማሪዎች በክፍል ውስጥ ከሚወስዷቸው ትምህርቶች በተጨማሪ ለኢንዱስትሪ የሚጠቀም ክህሎት ይዘው መውጣት እንዳለባቸው፣ ለዚህም  ከኢንዱስትሪዎች ጋር እየሠሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የአይሲቲ አካዳሚዎች መከፈት አንዱ ምክንያትም ለኢንዱስትሪ የሚያስፈልጉ ክህሎቶችን ለተማሪዎች ለማላበስ መሆኑን አክለዋል፡፡

ሁዋዌን ጨምሮ ከሌሎች በቴክኖሎጂ ታዋቂ ከሆኑ ድርጅቶች ጋር በመሆን የአይሲቲ አካዴሚ መክፈታቸውን፣ ይህም በመደበኛ ትምህርት የማይገኙ ትምህርቶች ከአይቲ ኢንዱስትሪዎች ጋር በመሆን በአጫጭር ኮርሶች እንዲያገኙ እንደሚያስችል፣  በተግባርም ያገኙት ተሞክሮ እንደሚያሳየውም እንደ ሲድስ ፎር ዘ ፊውቸር ያሉ ሥልጠናዎች ተማሪዎች የኢንዱስትሪ ዕውቀት ይዘው እንዲወጡ ማስቻሉን ጠቁመዋል፡፡

መሰል ክህሎቶችን ይዘው የወጡ ተማሪዎችም የሥራ ዕድል እንዲያገኙ ለሥራ ፈጠራ እየተጠቀሙበት መሆኑን አክለዋል።

ሁዋዌ ሲድስ ፎር ዘ ፊውቸር ላለፉት በርካታ ዓመታት ሲካሄድ የነበረ ሲሆን፣ ቻይና ሄደው ክህሎቶችን እንዲያዳብሩ ሲደረግ መቆየቱን፣ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ በኋላ ጉዞው ሲቋረጥ የተጀመረው የበይነመረብ (ቨርቹዋል) ሥልጠና የሠልጣኞችን ቁጥር ለመጨመር እንዳስቻለም ገልጸዋል፡፡

 የዚህ ሥልጠና ትልቁ ጥቅም ወደ ኢንዱስትሪው ለመቀላቀልም ሆነ ሥራ ለመፍጠር የሚያስችል የቴክኖሎጂ ነባራዊ ክህሎትን ለመያዝ እንደሆነ ዘላለም (ዶ/ር) ገልጸው፣ ሥልጠናዎቹ ለአራተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት የሚያስፈልጉና ለ5ጂ ደግሞ ቀድመው እንዲዘጋጁ እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡

የሁዋዌ ሰብ ሪጅናል የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ሚስተር ዣንግ ቦወን ኩባንያው ተሰጥኦዎችን ለማዳበር የሚያደርገው አስተዋፅዖ ቀጣይነት እንዳለው ገልጸው፣ ‹‹ሲድስ ፎር ዘ ፊውቸር ሁዋዌ›› ለወጣቱ ትውልድ ከሚያቀርባቸው በርካታ የሥልጠና ፕሮግራሞች መካከል አንዱ ነው ብለዋል።

በሥልጠናው የሳይበር ደኅንነት የተካተተ መሆኑን፣ የቴክኖሎጂ ፈጠራንና ትብብርን እንደሚያደርግም አመላክተዋል።

ኢትዮጵያዊው ወጣት የአይሲቲ ሥራ ፈጣሪ፣ የሃሁ ጆብስ እና የምናብ አይሲቲ ሶሉሽንስ መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ቃለአብ መዝገቡ፣ ለሠልጣኞች በዘርፉ ያላቸውን ልምድ አካፍለዋል። ክህሎት ያገኙት ከዩኒቨርሲቲ በተጨማሪ ከውጭ ከሚመጡ እንደ ሁዋዌ ባሉ ተቋማት መሆኑን፣ ተጨማሪ ሥልጠናዎችን መውሰድ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

የዘንድሮው የሲድስ ፎር ዘ ፊውቸር 2023 መርሐ ግብር ከ13 የመንግሥትና አንድ የግል ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ 120 ተማሪዎች የተሳተፉበት ነው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 106 ማለትም 32 ሴት እና 74 ወንድ ተማሪዎች ሥልጠናውን አጠናቀቅውና ፈተናውን አልፈው ሠርተፍኬት ወስደዋል። 34 ተማሪዎች በዋናዎቹ የሥልጠናው ኮርሶች በዲጂታል ፓወር፣ በክላውድ ኮምፒዩቲንግ፣ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስና በ5ጂ 100 በመቶ ውጤት አግኝተዋል።

ተማሪዎቹ በ12 ቡድን ተመድበው የቴክፎርጉድ ፕሮጀክቶቻቸውን በማቅረብ የተወዳደሩ ሲሆን፣ በእዚህም ከአምስት ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ሦስት ቡድኖች ለዓለም አቀፍ ውድድር አልፈዋል። በውድድሩ አሸናፊ የሚሆኑት የ100,000 ዶላር ሽልማት ያገኛሉ፡፡

የቴክ ፎር ጉድ ውድድር የሚያተኩረው፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ግቦች በሚደግፏቸው ፈጠራዎች ላይ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...