Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የበዳይና የተበዳይ ችሎት!

ሰላም! ሰላም! ‹‹የጊዜ እንጂ የሰው ጀግና የለውም›› ይባል ነበር አሉ፡፡ ጊዜ ይህንን ያህል ክብር ሲያገኝ እኛ ለምን እንረክሳለን? ግራ ይገባኛል፡፡ የጊዜ ነገር ሲነሳ ብዙ የሚባሉ ጉዳዮች አሉ፡፡ ጊዜን የመሰለ ዳኛ እያለ እንዴት አይባልም፡፡ አገርኛ ጉዳዮቻችን ከመብዛታቸው የተነሳ የቱን ጥዬ የቱን እንደማነሳ ሳስበው ደርሶ እንደ ወፈፌ ብቻዬን ያስቀባጥረኛል፡፡ የአገራችን ሰው በአንድ በኩል የኑሮ ውድነቱ ናላውን እያዞረው፣ በሌላ በኩል ሰላም አጥቶ ግራ ተጋብቶ እየቀባጠረ ‹‹የአማኑኤል ምሩቅ›› ቢመስል ምን ይገርማል? ‹‹ይገርማል እኮ ባሻዬ ጊዜው እንዴት ይሮጣል?›› ብላቸው በቀደም ከቤተ ክርስቲያን ሲመለሱ፣ ‹‹ከሥጋ እስከ ነፍስ ያለውን ነው? ወይስ እንደ ንፋስ የሚጋልበውን ጊዜ ማለትህ ነው?›› ብለው አዞሩብኝ። ‹‹ሥጋና ነፍስ ይሁን ጊዜና ንፋስ ምን አገናኛቸው?›› ብላቸው፣ በሃይማኖታዊ ምልከታ የሚባለውን በአጭሩ አብራሩልኝ። እኔ በደላላ ጭንቅላቴ ረቀቅ ያለው ምልከታ ባይገባኝም እናንተ ግን ትረዳላችሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ‹‹የአባትህ አነጋገር አደነጋገረኝ እኮ…›› ብዬ ምሁሩን ልጃቸውን ባዋየው፣ ‹‹የሃይማኖት አስተምህሮን ለመረዳት ቀረብ ብሎ መማር ነዋ…›› ብሎ የባሰ አስደነገጠኝ። አንዳንዴ ሳስበው ስንቱን ዕውቀት በውስጣቸው አምቀው የኖሩ ወገኖች ፅናት ይገርመኛል፡፡ ፅናቱን ይስጠን እንጂ ስንት ያልተነገረ ዕውቀት አለ መሰላችሁ? ኧረ ብዙ ነው ወገኖቼ!

‹ሁሌም እንደ ልብ መሆን የለም› የሚባለው አባባል እኮ አሁን አሁን ለአንዳንዶቻችን ‘መቼም የፈለጉትን መሆን የለም’ ወደሚለው የተሸጋገረ መሰለኝ። መቼም የትውልዱ ዘመን ሁሉ የሽግግር ነው። የሀብት ሽግግር ላይ የነበሩት ዘመን አበቃ ማለት ነው? ለነገሩ ሙሉ ለሙሉ እንዲያ ብሎ መደምደም ባይቻልም፣ በየቦታው የመሸጉ የሥቃይ ፊታውራሪዎችና ዘራፊዎች ጉዳይ ምኑን ተነካና? ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ግን፣ ‹‹ገና ያልተነገሩ ጉዶች ወይ ጨርቃችንን አስጥለው ያሳብዱናል፣ አሊያም አገር አስጥለው ያስኮበልሉናል…›› እያለ ብቻውን ሲስቅ ዕብደት የጀማመረው መስሎኝ በድንጋጤ ክው አልኩ፡፡ ይገርማችኋል በአንድ ወቅት አኗኗራችንን በማስመልከት አንድ የተሠራ ጥናት በሬዲዮ ሳዳምጥ ነበር። በተለይ የኑሮአችን ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ ምን ዓይነት መልክ እንደያዘ ይተነትናል፡፡ በእውነቱ በጣም አስደንጋጭና ግራ አጋቢ ነገር ሰማሁ። አብዛኛው ሰው በሰጠው አስተያየት በቀን ሦስቴ ምግብ ማግኘት ቀርቶ አንዴ በልቶ ውሎ ማደር በጣም ከባድ እንደሆነ ሲነገር ያስደነግጣል። በዚህ በኩል ፈረንጆቹ የተበደሩትን ዕዳ መክፈል አልቻሉም እያሉ ያሙናል፡፡ እኛ ደግሞ በዕድገት እየተተኮስን ነን ብለን አውርተን አፍታም ሳንቆይ፣ የዕርዳታ ምግብ በመቋረጡ ምክንያት በርካታ ሚሊዮኖች ሕይወታቸው አደጋ ላይ ነው እያልን በመሀል ወፈፍ ያደርገናል፡፡ ለይቶልናል ማለት ነው!

መቼም ጨዋታ ነው አትቀየሙኝም። ይኼውላችሁ ሐበሻ የሚታማው ውስጡ አምቆ በያዘው ገመናው ብቻ ነው ይባላል። ካላመናችሁ በየግላችሁ ለሐሜት የምትፈጁዋቸውን ማገዶዎች ብዛት አስቡና መልሱን ድረሱበት። ‘የለም ሐበሻ የሚታማው በስንፍናው ነው’ የምትሉ ወደ እናንተ ሐሳብ ስለምመጣ ተረጋጉ። አሁን ልብ ብላችሁ ብታስቡት የእረፍትና የሥራ ቀን አዋዋላችን ሲታይ ለብዙዎቻችን ተመሳሳይ ነው፡፡ የሚሠራውና ሥራ አጡ ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ይህንን ስል ግን በዘረፋ ንፋስ አመጣሽ ሀብት አካብተው በውስኪ ሲራጩ ውለው የሚያድሩትን እንደማይመለከት ልብ ይባልልኝ፡፡ የታሰሩ ጥቅል ገንዘቦችን እንደ ፈንዲሻ እየበተኑ ሲጫጫሱ የሚያነጉ ወንበዴዎችን ማለቴ ነው፡፡ ቆይ እስቲ ሰሞኑን ውስኪ ቤቶችና ጮማ መቁረጫዎች ከመጠን በላይ ሙሉ ናቸው የሚባለው እውነት ነው? አንድ ወዳጄ እንደነገረኝ ‘አስረሽ ምቺው’ የሚባልባቸው ከመቃሚያ እስከ መጨፈሪያ ጢም እንዳሉ መሆናቸው የዕድገቱ ማሳያ ሆኗል ነው የሚባለው፡፡ ኢኮኖሚስቶቻችን ዝም አትበሉ እንጂ!

 አንዱ የሆነ ጊዜ በቀጥታ የሬዲዮ ውይይት ላይ ሊሳተፍ ደውሎ፣ ‹‹እኔ…”››አለ። ‹‹…እኔ ከወዲሁ ያስጨነቀኝ የዋጋ ጭማሪ ሳይሆን የሥጋው ጥራት ጉዳይ ነው…›› ሲል ሰምቼው ባሻዬን ትክ ብዬ ሳያቸው፣ ‹‹ልክ እንደ ሥጋው ለነፍሳችን አብዝተን ብንጨነቅ የት እንደርስ ነበር?›› ብለው አቀረቀሩ። ባሻዬ ደግሞ በትንሽ በትልቁ ማቀርቀር ይወዳሉ። ምናልባት እኔ በዕድሜ ስለማንሳቸው ይሆናል ጉድ ሰምቼና ሁሉ ነገራችንን ታዝቤ ቀና የምለው? እንዲያውም አንዳንዴ ራሳቸው ባሻዬ፣ ‹‹ሆድህን ሰፋ አድርገው…›› ይሉኛል። እኔ ደግሞ ቀጥታ ተርጉሜ፣ ‹‹ከዚህ በላይ?›› እላለሁ። ከዚህ በላይ ካሰፋነውማ ሌላ ሦስት ሺሕ ዘመን ሆድና ሆድ ተኮር ዕሳቤዎች እንደ ነገሡብን፣ እንዳስጨነቁንና እንዳሳሰቡን እንቀረራለን በቃ። በአዕምሮ የምንሰፋበት ጊዜ ስለሚናፍቀኝ እኮ ነው በዚህ ዘመን እነ ሆድ አምላኩን የምኮንነው። ‹ማዘን ያለብን ለተራበው ሳይሆን ለጠገበው ነው…› እየተባልን አድገን አገሩን የዘረፋና የጭካኔ አምባ ማድረጋችን እያቃጠለኝ ብዙ ነገሮችን አስብና እተዋለሁ፡፡  የአገር ሀብት ተዘርፎ መተው አለ እንዴ ጎበዝ!

እናላችሁ እንዲህ የባጥ የቆጡን ስሰማና ሳይ በመሀል በመሀል አንድ ገጽ የፈጀው የማንጠግቦሽ አስቤዛ ዝርዝር ትዝ እያለኝ ልቤ ድንግጥ እያለ ተቸገርኩ። ገበያው እንደምታዩት ነው። በጠዋትና በማታ መካከል ገበያው የሰማይና የምድር ያህል ልዩነት ያለው ጭማሪ ነው የሚገጥመን። ‹‹ሰውን ማመን ገዝቶ ነው? ሸጦ ነው?›› ስለው፣ ‹‹አንተ ደላላ ሆነህ ያላወቅከውን እኔ እንዴት አውቃለሁ?›› የሚለኝ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ነው። አንድ ያልገባው ነገር ምን መሰላችሁ? ምናልባት መንግሥት ራሱ ተናግሮት ሲያበቃ ለራሱ ያልገባው፣ ደላላ ያልሆነ በከተማው ላይ ቢፈለግ አለመኖሩን ነው። እዚህ ጋ አባባሌን አዛብታችሁ እንዳትረዱብኝ ደላላ ሁለት ትርጉም አለው። አንድ ፈላጊና ተፈላጊን ከመሀል ሆኖ ማገናኘት። ሁለት አባብሎና አዘናግቶ ገደል መክተት። ስም በመለጠፍ መቼም አንታማም፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ያስቀመጥናቸውን ሕገወጥ ደላላ ብለን አውግዘናል። ‹እኛ አላልንም መንግሥት ነው…› ትሉ ይሆናል እኮ በልባችሁ። ለነገሩ አገሩን የደላላ መጫወቻ ያደረገው ራሱ መንግሥት እኮ ነው፡፡ የመንግሥት ባለሥልጣን ኮሚሽን ሲበላ ነበር እኮ ነው የተባልነው፣ ግልጽ መሰለኝ፡፡ በውጭ አገር ግዥ ሳይቀር ኮሚሽን እንደ ደላላ የሚቀረጥፉ የመንግሥት ሹማምንት አሉ እኮ፡፡ አሁንስ ገባችሁ? ካልገባችሁ ዓቃቤ ሕግን ጠይቁ!

 የጀመርኩትን ልጨርስላችሁና ሌላውን በሌላ ጨዋታ ልመለስበት። ‹‹የዋጋ ንረት›› ብሎ ነገር የሮኬት ሳይንስ ሆኖብኛል እያልኳችሁ ነበር። አዎ ከሰሞኑ ሽቀላ እኔም ወግ ይድረሰኝ ብዬ በግ ተራ ሄጄ ላቱንና ደንደሱን መትሬ አንድ መለስተኛ በግ መርጬ፣ ‹‹ስንት ነው?›› ስለው ሻጩን፣ ‹‹ተጽፎበታል እኮ…›› ብሎ ወደ ሆዱ ጠቆመኝ። አዙሬ ሳየው ‹25 በመቶ ቅናሽ› ይላል። ‹‹ምን ማለት ነው?›› ብዬ ስጠይቀው ሻጩ ምን ቢለኝ ጥሩ ነው? ‹‹ከአምናው የኅዳር ወር የበግ ዋጋ ጋር ሲነፃፀር 25 በመቶ ጭማሪ ማለት ነው…›› አለኛ። አምና ለገዛሁት በግ ሦስት ሺሕ ብር ከፍዬ ነበር። አሁን ግን አሥር ሺሕ ብር ክፈል ነው ያለኝ፡፡ እውነት እውነት እላችኋለሁ እንዲህ ያለ ጉድ በደላላነት ታሪኬ አላውቅም። የ25 በመቶ ቅናሽ ተብሎ ከሦስት እጥፍ በላይ የተጠየቅኩበትን የበግ ዋጋ ሳስብ፣ ከውስጤ እንደ እሬት የመረረ ነገር ነበር በአፌ የመጣው፡፡ እኔ መቼም ሲፈጥረኝ ቀጥተኛ ስለሆንኩ፣ ‹‹ብትፈልግ ጥብስ፣ ዱለት ወይም ቅቅል አድርገህ ብላው…›› ብዬ በንዴት ትቼው ሄድኩ፡፡ በቃ!

 የውድ ባለቤቴን ማንጠግቦሽን ጥያቄ ለማሟላት አንድ ቪላ ጆሮውን አስመትቼ ሳበቃ፣ ኮሚሽኔን ለመቀበል ቀለበት መንገድ ዳር ከደንበኛዬ ጋር ተቀጣጠርኩ። አሁን እስኪ ካልጠፋ ቦታ ሰው ቀለበት መንገድ ዳር ይቀጣጠራል? አንዳንድ ሰዎች ቀለበታቸው ውስጥ አልገባ ስንላቸው ቀለበት  መንገድ  ዳር ይቀጥሩናል። ግርግሩ ደርቷል። ክንፍ ላይ የመደብነው መንገድ የአማካይነቱን ሥፍራ ወስዶ ከተማ መሀል ለመሀል ተዘርግቶ ፀሐይ የሚሞቅ ዘንዶ መስሏል። ‹ቀለበት መንገድ መዝለል ክልክል ነው› ብሎ መለጠፍ ከተከለከለ ቆየ መሰለኝ። ኮሚሽኔን የሚያቀብለኝ ሰው ሲቆይብኝ መንገድ መንገዱን እያየሁ አንድ ነገር ማሰብ ጀመርኩ። ዘንድሮ ምን የማይታሰብ አለ? ይኼኔ አንዱ አልፎ ሂያጅ አጠገቤ መጥቶ ቆመና አላፊ አግዳሚውን እየቃኘ፣ ‹‹እየው ያንን…›› ብሎ ጠቆመኝ። አንድ ልጅ እግር በግ ተሸክሞ ቀለበት መንገድ ያቋርጣል። ‹‹እስኪ አሁን ያ ሲኖትራክ ቢዳምጠው ለማንኛቸው ልናዝን ነው?›› እያለ አንገቱን ሲያወዛውዝ እኔ ማዶ አያለሁ። አምጠው ወልደው አንድ ጎልማሳ የሚያደርሱ እናት ቦርሳቸውን እንዳነገቱ ከዘርፋፋው ቀሚሳቸው ጋር እየታገሉ የመንገዱን አጥሮች ይዘላሉ። ከዓይን ይሰውረን!

በሉ እንሰነባበት። ኮሚሽኔን ተቀብዬ ያንን የምባዝንለትን በግ ሌላ ቦታ ተንከራትቼ በውድ ዋጋ ገዛሁና ቤት ላደርስ አሸክሜ ተጣደፍኩ። ቤት ስንደርስ ተሸካሚው ግራ ገባው። ‹‹እዚህ ነው ሠፈርዎ?›› አለኝ። ‹‹አዎ…›› አልኩት። ‹‹ይኼ ነው ቤትዎ?›› አለኝ መልሶ። ‹‹ምነው?›› አልኩት። አንዳች ነገር የተጠራጠረ መሰለ። መንደሬም ኑሮዬም እንደ ማንኛውም ተራ ሰው መሆኑን ዓይቶ በግ የመግዛት አቅሜን ሲገምተው ለካ ግራ ገብቶት ኖሯል። ‹‹በል እንካ…›› ብዬ 50 ብር ስሰጠው፣ ‹‹ከሁለት መቶ ብር በታችማ አያዋጣም…›› አለኝና አረፈው። ‹‹ትቀበላለህ አትቀበልም?›› ስለው፣ ‹‹ዋጋዬን ተናግሬያለሁ ካልከፈሉ እጠቁማለሁ…›› አይለኝ መሰላችሁ? መጣቻ የእኔዋ ማንጠግቦሽ እሳት ለብሳ እሳት ጎርሳ። ‹‹ምን ብለህ ነው የምትጠቁመው አንተ? በዓመት አንዴ  ሥጋ በሉ ብለህ ነው ለመንደርተኛው ላይ የምትጠቁመው? የእኔ አንበርብር ምንተስኖት ላይ ታች ብሎ ለፍቶ ላቡን ጠብ አድርጎ ኑሮውን በጥበብ የሚኖር አርዓያ ባሌ ነው። ከጠቆምክ ሰርቆና አምታቶ ከአገር ከሕዝብ ቀምቶ አውሮፓና አሜሪካ ገንዘቡን የሚያሸሸውን ጠቁም። እኛ መርከብ ወይም አውሮፕላን የሸጥን ወይም የህዳሴ ግድቡን በጀት የዘረፍን መሰለህ እንዴ? የእኛ ግልገል በግ መግዛት ገረመህ? አሉልህ እኮ ተነግሮ የማያልቅ የሕዝብ ዕንባ ያፈሰሱልህ…›› ስትለው ላብ አጠመቀው። እኔን ላብ ያጥምቀኝ? ፍርድ ቤት ተከሶ የቀረበ መሰለ እኮ!

በእሱ ቤት እንግዲህ ‘መኒ ላውንድሪ’ ሊያጋልጥ ጫፍ ደርሶ ነበር። ሐሜትና ትችቱን ባለምደውና ልብ ባልገዛ ኖሮ በለፋሁበት ገንዘቤ ሳቢያ ጣቢያ አድሬ ነበር። መቼስ የማይለመድ የለም ለመድነው። ክፉንም ደጉንም ማለቴ ነው ታዲያ። እንዲያው ስታስቡት ስንቱ ነው አሁን በባዶ ቤት ገንዘቡንና ንብረቱን በጉቦ አሟጦ፣ በፍትሕ ዕጦት ለፈሪሳውያን ባደላ ችሎት ፊት ቆሞ ተረትቶና ንብረቱን ተነጥቆ ቆሎ ያረረበት? ስንቱ ያለ ቤትና ያለ ትዳር ቀረ? ስንቱ ተበላ? ስንቱ አበደ? ስንቱ ወደቀ? ስንቱ ከሰረ? ‹‹ለሰላሳ ዲናር ሊያጣ ነፍስ ይማር…›› ያለው ዘፋኙ እውነት ነው። ታዲያ ይሁዳ ዋጋውን እስኪያገኝ እስኪ እኛ አጠገባችን ያሉትን አግኝተው ያጡትን፣ ስቀው ያዘኑትን እያሰብን እንረዳዳ። አይመስላችሁም? በእርግጥም ሞቆ የቀዘቀዘባቸው ስንት ይሆኑ? ስንቶቹ ይሆኑ በሥነ ልቦና ጉዳት ተሰብረው የቀሩ?  ግና በዳይና ተበዳይ በፍትሕ ችሎት መዳኘታቸው አይቀርም፡፡ ግፍ የፈጸመም ለፍርድ መቅረቡ አይቀሬ መሆኑን ሳስብ፣ ‹ለሁሉም ጊዜውን ይጠብቅለታል…› ያለው አንጋፋ ድምፃዊ ምን ታይቶት ነበር አሰኘኝ፡፡ ጊዜው ይራቅ እንጂ ለአንዳንዱ እንደ ራዕይ ይታየዋል፡፡  መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት