Sunday, February 25, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ኢትዮጵያን ከግጭት ቀጣናነት ማላቀቅ የግድ ነው!

ፍሬ አልባ ፖለቲካዊ ልዩነቶች ወደ ግጭት እያመሩ ለአገርና ለሕዝብ የማያባራ መከራ ሲያቀባብሉ፣ ከትናንት ስህተቶች ለመማር ፈቃደኛ ያልሆኑ ፖለቲከኞችና ተከታዮቻቸው በእሳት ላይ ቤንዚን እያርከፈከፉ ጠማማ ጉዞአቸውን ሲቀጥሉ፣ አንተም ተው አንቺም ተው የሚሉ ገላጋዮች ወደ ጎን እየተገፉ ጥጋቸውን እንዲይዙ ሲደረጉ፣ የአገሪቱ ዕጣ ፈንታ ከብሩህ ተስፋ ይልቅ ጨፍጋጋ ገጽታ ሲላበስና የአሁኑም ሆነ የመጪው ትውልድ መፃኢ ዕድል የአቅጣጫ መጠቆሚያ እንደጠፋበት መርከብ ግራ ተጋብቶ ሲዋልል ዝምታን መስበር የግድ ነው፡፡ በከባድ መሣሪያ የተጋዘ ውጊያ በሚካሄድባቸው አካባቢዎች የሰቆቃ ደምፅ የሚያሰሙ ወገኖች እሪታ በተደጋጋሚ ሲያስተጋባ፣ ሁሉም ተፋላሚ ወገኖችም ሆኑ መላው የአገሪቱ ሕዝብ ለሰላማዊ መፍትሔ የበኩላቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከአንድ ግጭት ወደ ሌላው እንደ ቀልድ የሚገባበት የጥፋት መንገድ በፍጥነት ካልቆመ፣ ነገ ተነገ ወዲያ የአገርን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት የማስጠበቅ ታሪካዊ ተልዕኮ ከፍተኛ ችግር እንደሚገጥመው ጥርጥር የለውም፡፡ በእርስ በርስ ሽኩቻ ሳቢያ ዙሪያ ገባው ሰላም ሲያጣ፣ ላደፈጡ ታሪካዊ ጠላቶች በቀላሉ ዒላማ መሆን ይከተላል፡፡

ባለፈው ሳምንት የአገር መከላከያ ሚኒስትሩ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለውጭ ጉዳይና ለሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የተቋሙን የሩብ ዓመት አፈጻጻም ሪፖርት ሲያቀርቡ፣ ካነሷቸው መሠረታዊ ጉዳዮች አንደኛው የመከላከያ ሠራዊቱን ሥምሪት የሚመለከተው ይገኝበታል፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች የፀጥታ ችግሮች መስፋፋት ዘላቂና ቀጣይነት ያለው አቅም ለመገንባት እንቅፋት መፍጠሩን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ አመራሮች ሕዝባቸውን በማስተባበር አካባቢያቸውን ከሽፍቶች ማፅዳት ባለመቻላቸው፣ የሠራዊቱ ግዳጅ አፈጻጸም እንዲሰፋና የክልል መንግሥታት መዋቅር ሥራን ሸፍኖ እንዲሠራ መገደዱን አስረድተው ነበር፡፡ የመከላከያ ሠራዊት ተልዕኮ ሌባ፣ ሽፍታና ወንበዴ ማፅዳት አለመሆኑንና ሚሊሻ ወይም ከዚያ ካለፈ ፌዴራል ፖሊስ የት ሊሰማሩ ነው ብለው፣ በየመንደሩ ያለውን የሌባ እንቅስቃሴ መከላከያ መጥቶ ያፅዳ የሚል ፍላጎት እየሰፋ ከሄደ፣ ሠራዊቱ ሥራውን ማከናወን አይችልም ብለውም ነበር። የመከላከያ ሠራዊት ተልዕኮ የአገር ሉዓላዊነት ማስጠበቅ፣ ወደፊት ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን መመከትና ማስቀረት እንደሆነ ገልጸው በየመንደሩ ሌባ ማሳደድ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡

ከዚህ ገለጻና ማብራሪያ እንደምንገነዘበው የአገር መከላከያ ሠራዊት አቅሙን ከመቼውም ጊዜ በተሻለ በማሳደግ፣ ለበለጠ አገራዊ ተልዕኮ መዘጋጀት እንዳለበት ነው፡፡ በተጨማሪም በየክልሉ የሚገኙ የአስተዳደርና የፖለቲካ ተሿሚዎች ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት፣ ከአቅም በላይ የሆኑና ለግጭት የሚዳርጉ ድርጊቶችን ማስወገድ፣ እንዲሁም ችግር በሚያጋጥምበት ጊዜ የራሳቸውን የፀጥታ ኃይል በአግባቡ ማሰማራት እንዳለባቸውም ጠቋሚ ነው፡፡ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በሕጋዊና በፖለቲካዊ ወይም እንደ ክልሎቹ ነባራዊ ሁኔታ በአገር ሽማግሌዎች መፍታት እየተቻለ፣ ለትልቁም ሆነ ለትንሹ ችግር የአገር መከላከያ ሠራዊት እንዲገባላቸው ማድረግም አይገባቸውም ነበር፡፡ የአገር መከላከያ ሠራዊት ዋና ኃላፊነት የአገርን ዳር ድንበር ማስከበር በመሆኑ፣ ክልሎችም ሆኑ ከእነሱ በታች ያሉ መዋቅሮች ችግሮች በሰላማዊ መንገድ የሚፈቱበት መንገድ ላይ ቢያተኩሩ ኖሮ እንዲህ ዓይነቱ ማሳሰቢያ ለፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ አይቀርብም ነበር የሚል እምነት አለ፡፡ ኢትዮጵያን በታላቁ የህዳሴ ግድብም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚፈታተኗት ጠላቶች መኖራቸው እየታወቀ፣ ውስጣዊ ችግርን በሠለጠነ መንገድ አለመፍታት ዋጋ ያስከፍላል፡፡

ሰሞኑን በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ሕዝባዊ ውይይቶች ሲካሄዱ ነበር፡፡ በተለይ በላሊበላ ከተማ በተደረገ የውይይት መድረክ ላይ የተንፀባረቁ የሕዝብ አስተያየቶችን፣ የክልሉ መንግሥትም ሆነ የፌዴራል መንግሥት አፅንኦት ሊሰጧቸው ይገባል፡፡ ከሕዝብ አስተያየቶቹ ለመረዳት እንደተቻለው የአካባቢው ነዋሪዎች ሰላም በእጅጉ ናፍቋቸዋል፡፡ የላሊበላ ከተማም ሆነ አካባቢው የበርካታ ታሪካዊ ቅርሶች መገኛ በመሆኑ በከባድ መሣሪያ የተጋዘ ጦርነት ብቻ ሳይሆን፣ በምንም ዓይነት ሁኔታ ውጊያ መካሄድ እንደሌለበት ሲነገር ነበር፡፡ ከባድ መሣሪያ ሲተኮስ በላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ንዝረቱ ይሰማ እንደነበርም ተወስቷል፣ በገለልተኛ ወገኖች ባይጣራም ጉዳት ደርሷል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ በዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡት አብያተ ክርስቲያናት ብቻ ሳይሆኑ፣ በአካባቢው የሚኖሩ ወገኖችም ጉዳት እንዳይደርስባቸው ከባድ ጥንቃቄ መደረግ አለበት፡፡ ከነዋሪዎቹ አንደበት እንደተሰማው ለተፈጠረው ችግር ዋናው መፍትሔ፣ ተቀራርቦ መነጋገርና ዕርቅ መፍጠር የሚለው ተጠቃሽ ነው፡፡ በተቃርኖ ጎራዎች ተሠልፈው ችግር ከሚያባብሱ የሩቅ አትራፊዎች ይልቅ፣ በጦርነት ወላፈን ውስጥ ሆነው የሚጮሁ ወገኖች ድምፅ ይደመጥ፡፡

የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ የሚያስገነዝበው በሁሉም አካባቢዎች ያሉ ግጭቶችና መቆራቆሶች በፍጥነት እንዲቆሙ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ መንግሥት ከማንም የበለጠ ኃላፊነት አለበት፡፡ የፌዴራል መንግሥት መቀመጫ ከሆነችው አዲስ አበባ ከተማ በአምስቱም በሮች ተወጥቶ በሰላም መግባት የማይቻልበት ሁኔታ ላይ ተሁኖ፣ ልማትንም ሆነ ዕድገትን ማስገኘት ቀርቶ ማለም አይቻልም፡፡ በሁሉም አካባቢዎች ቅሬታም ሆነ ተቃውሞ ያላቸውን ወገኖች፣ በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ ወደ ንግግርና ድርድር መድረክ መጋበዝ ይገባል፡፡ አኩራፊዎች በበዙ ቁጥር የውጭ ኃይሎች ሳይቀሩ እጃቸውን አስረዝመው እያስገቡ፣ የእርስ በርስ ግጭቱንም ሆነ ጦርነቱን የበለጠ በማስረዘም አገርን ያዳክማሉ፡፡ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ጊዜያት በነበሩ መንግሥታት ላይ ያመፁ ወገኖችን ሶማሊያ፣ ሱዳን፣ ኤርትራም ሆነች ሌሎች ሲያስጠልሉ ነበር፡፡ ራቅ ያሉት ደግሞ በገንዘብ፣ በሥልጠና፣ በመሣሪያና በሎጂስቲክስ ሲደግፉ ይታወቃሉ፡፡ ኢትዮጵያ ከድህነት መንጥቀው ሊያወጧት የሚችሉ የተለያዩ ትውልድ አባላትን ከመገበሯም በላይ፣ ከፍተኛ መጠን ያለው ሀብት የጦርነት እሳት ውስጥ ማግዳለች፡፡ ይኼ የጥፋት ጉዞ አይበቃም ወይ?

የኢትዮጵያን ስም ዘወትር ከግጭት፣ ከድርቅ፣ ከመፈናቀልና ከረሃብ ጋር ተያይዞ መስማት በእጅጉ ልብ ይሰብራል፡፡ በታሪኳ አንድም ጊዜ የሌሎችን ሳትፈልግ ወረራ እየተፈጸመባት ተገዳ ስትዋጋ የኖረች አገር፣ አሁንም ስሟ ከግጭት ወይም ከጦርነት ጋር በተደጋጋሚ አብሮ ሲነሳ ያስደነግጣል፡፡ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በውጭ ኃይሎች ግፊት በፕሪቶሪያ ስምምነት ቢገታም፣ ውሎ ሳያድር በአማራ ክልል መጠነ ሰፊ ግጭት ተቀስቅሶ የዜጎች ሞትና የንብረት ውድመት ሲሰማ ያሳዝናል፡፡ በኦሮሚያ ክልልም ተመሳሳይ ነገር ሲኖር ተስፋ ያስቆርጣል፡፡ ከ120 ሚሊዮን ሕዝብ ውስጥ ሩብ ያህሉ የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ እየተለመነለት፣ አብዛኛው ሕዝብ የኑሮ ውድነቱን መቋቋም ተስኖት የመከራ ቀንበር ተጭኖበትና ከሰላም ይልቅ የግጭት ዜናዎች በስፋት ሲሠራጩ መጪው ጊዜ ቢያስፈራ አይገርምም፡፡ በዚህ ሁሉ አስፈሪ ሁኔታ ውስጥ የቀይ ባህር ጂኦ ፖለቲካ ተሳታፊነት ጥያቄ ተነስቶ፣ በውጭ መገናኛ ብዙኃንና በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ኢትዮጵያ ለወረራ እየተዘጋጀች ነው የሚሉ ዘገባዎች በብዛት ሲደመጡ ግራ ያጋባል፡፡ ይህን ጊዜ ነው እንግዲህ ኢትዮጵያን ከግጭት ቀጣናነት ማላቀቅ የግድ የሚለው!   

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...

ሕወሓት በትግራይ ጦርነት ወቅት በፌዴራል መንግሥት ተይዘው ከነበሩት አባላቱ መካከል ሁለቱን አሰናበተ

በሕወሓት አባላት ላይ የዓቃቤ ሕግ ምስክር የነበሩት ወ/ሮ ኬሪያ...

የኤሌክትሪክ ኃይል ለታንዛኒያ ለመሸጥ የሚያስችል ስምምነት ለመፈጸም የመንግሥት ውሳኔ እየተጠበቀ ነው

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለታንዛኒያ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ለማከናወን የሚያስችለውን...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሰብዓዊ ቀውሶችን ማስቆም ተቀዳሚ ተግባር ይሁን!

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተወክለው ከመጡ ሰዎች ጋር ያደረጉት ውይይት፣ በአማራ ክልልም ሆነ በሌሎች ሥፍራዎች የሚካሄዱ ግጭቶች ምን...

የበራሪው የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ጄኔራል ለገሠ ተፈራ ቅርሶችን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተረከበ

በቀድሞው የኢትዮጵያ መንግሥት (1967-1983) ዘመን የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ሜዳይ የየካቲት 1966 1ኛ ደረጃ ኒሻን ተሸላሚ የነበሩ የአየር ኃይል ጀት አብራሪው የብርጋዴር ጄኔራል ለገሠ ተፈራ...

የዜጎች በነፃነት የመንቀሳቀስ መብት ዘላቂ መፍትሔ ይበጅለት!

ሰሞኑን በአዲስ አበባ የተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ በተጠናቀቀ ማግሥት፣ መንግሥት ልዩ ትኩረት የሚሹ በርካታ ጉዳዮች እየጠበቁት ነው፡፡ ከእነዚህ በርካታ ጉዳዮች መካከል በዋናነት የሚጠቀሰው...