Sunday, February 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ሥሌትና ስሜት

በኅዳር ሁለተኛ ሳምንት ከጎተራ ወደ ሜክሲኮ ልንጓዝ ነው። በሙሉ ልብስ ዘንጠው የደስ ደስ ገጽታ የሚያሳዩን አዛውንት የጋቢናውን በር እየከፈቱ ወጣቱን ሾፌር፣ ‹‹እስኪ ወዲህ ጠጋ በል ዓይንህን ልየው፡፡ ዘንድሮ እኮ መሪ የሚጭብጥን ጠጋ አድርገን ካላየነው ችግር መከተሉ አይቀሬ ነው። ታዲያ መንበሩን የጨበጡትን የሚያካትት መስሎህ ደግሞ ነገር እንዳታመጣብኝ በዚህ ማለዳ…›› እያሉ ሲቀልዱ ሰማናቸው። ሾፌሩ የምራቸውን መስሎት ዓይኑን ሊያስመረምር ከአንገቱ ሰገግ አለ። ‹‹ወይድ እባክህ የዓይን ሐኪም አደረገኝ እንዴ በአንድ ጊዜ?›› ሲሉ ፌስታል ይዛ የምትከተላቸው ኮረዳ ትስቃለች። ‹‹እኔ መቼ ይኼን ብሌንህን አልኩህ? ሰው ዓይኑ ያለው ልቡ ላይ ነው። ሳይንስ የሚቀናህ ከሆነ ደግሞ አዕምሮ በለው፣ ያው ነው የስም ለውጥ ነው። ከስም ለዋጭ፣ ከአውቆ አበድ፣ ከአታላይ ቀስቃሽና ከሴረኛ አገራችንን ፈጣሪ ይጠብቃት…›› በማለት እጆቻቸውን ወደ ሰማይ ዘረጉ፣ በቆሙበት ጸሎታቸውንም አጉተመተሙ። ‹‹የዚህን ሾፌር ልብ አንተ ምራ። የአፉን ሳይሆን የልቡን አንተ መርምረህ ቀና ሆኖ እንዲነዳ ዕርዳው…›› ብለው ከጨረሱ በኋላ ተሳፈሩ። አፍታ ሳይቆይ ታክሲያችንም ሞላ። መልካም ጅማሮ ነው!

‹‹አያ ሞኛ ሞኝ ሰው ጥበብ የጎደለው፣ እህል ያከማቻል ስንቅ እየመሰለው…›› ይላል በገና ደርዳሪው ከወደ ታክሲው ቴፕ። ወያላው ደግሞ፣ ‹‹ወይ ስምንተኛው ሺሕ የገና ፆም ሳይጀመር አንተ አሁን ፆም ልታስጀምረን ነው እንዴ? ምናለበት ማስመሰሉን ትተህ ዓለማዊ ዘፈን ብትከፍትልን?›› እያለ ሾፌሩን ይለክፈዋል። ሾፌራችን ግን፣ ‹‹ግድ የለም ፆም ይድረስና እኔና አንተ እንገናኛለን…›› እያለ ይዝታል። ‹‹ጉድ ነው የዘንድሮ ሰው የሠፈረበት ጋኔን እንኳን በአርባ ቀን በዓመት ሙሉ ፆምና ጸሎትም የሚለቀው አይመስልም። እንዲያው ብቻ ለይምሰል ካጨበጨቡት ሲያጨበጭብ፣ ከሰከሩት ሲሳከር፣ ከካዱት ሲወዳጅና ከክፉ እየተቃቀፈ መኖር ሲችልበት…›› ትላለች ከሾፌሩ ጀርባ የተቀመጠች ጥርሰ ፍንጭት። በዚህ መሀል አጠገቧ ወዳለሁት ዘወር ብላ፣ ‹‹ለምን ዝም ትላለህ? እምቢም አንድ ነው፣ እሺም አንድ ነው። ልክ ነሽ፣ ተሳስተሻል ማለትም የአባት ነው። ዝምታው ምንድነው?›› ስትለኝ ደንግጬ ዓያታለሁ። ጥያቄው አዕምሮዬ ውስጥ እየተጉላላ ጆሮዬ ላይ ንግግሯ ይደውላል። ‘ዝምታው ምንድነው?’ እንጃ!

‹‹እሱን አብረን የዝምታን አባት እንጠይቀዋለን። እስከዚያው ወንድማችንን ለቀቅ አድርጊው…›› ብሎ ከጀርባችን ሙሉ ልብስ የለበሰ ጎልማሳ ተሳፋሪ አጉረመረመ። ታክሲ ውስጥ ነው ፀብ ውስጥ ነው የገባሁት እያልኩ ስወዛገብ፣ ‹‹ማን ነው ደግሞ የዝምታ አባት?›› ብላ ጎልማሳውን ጠየቀችው። ‹‹እሱ!›› አላት ወደ ታክሲያችን ጣራ እየጠቆመ። መላው ተሳፋሪ ወደ ጥቆማው ሲያንጋጥጥ ብርሃን የሚተፋ የልብ ቅርፅ በእጁ የታቀፈ የፈጣሪ ምሥል ተለጥፏል። ከጎንና ከጎኑ የቢዮንሴና የጄዚ ምሥሎች ያጅቡታል። ‹‹ወይ ዘንድሮ፣ መድኃኔዓለምን ነው የዝምታ አባት የሚለው? እውነት እሱ ዝም ቢል ኖሮ ድሆችና የእውነት ተሟጋቾች ከምደረ ገጽ አንጠፋም ነበር?›› ብላ ሦስተኛ ወንበር ላይ የተሰየመች ወይዘሮ በቁጣ ትናገራለች። አጠገቧ ወደ ተቀመጠው ወጣት ዞራ መልስ ስትሻ ጆሮው ላይ ‘ኢርፎን’ ሰክቶ ሲወዛወዝ አልሰማትም። ‹‹ኔትወርክ ሳይኖር ስለፈልፍ ዝም አላችሁ?›› ብላ መጨረሻ ወንበር ወደ ተቀመጡት ዞራ ብትጠይቅ ሁሉም ፈገግ እያሉ አንዴ እሷን አንዴ ልጁን አፈራርቀው አዩ። የበገናው ዜማ ቀጥሎ፣ ‹‹የቀድሞ ሰው ስህተት በፆም ቀን ዓሳን መብላት፣ የአሁን ዘመን ሰው አያውቅ መላ በጦም ሽሮ ነው የሚበላ…›› ሲል እየሰማን እንሰመጣለን። ይሻላል!

ታክሲያችን ረጅሙን ጉዞ ተያይዛዋለች። ‹‹እንካ እሱን ሒሳብ እንዳትቀበለው…›› መጨረሻ ወንበር የተቀመጠ ፀጉረ ጨብራራ ከጎልማሳው አጠገብ ወደ ተሰየመው ይጠቁማል። የተጠቆመው ተሳፋሪ ዞሮ የምሥጋና አፀፋውን በአስገምጋሚ ድምፅ ሲመልስ ታክሲያችን የሚሳይል ማስወንጨፊያ ጣቢያ መሰለች። ጆሮውን በ‘ኢርፎን’ ደፍኖ የተቀመጠው አውልቆ፣ ‹‹ኧረ ፍሬንድ ‘ታይታኒክ’ ላይ አልተሳፈርንም እኮ? ከዚህ ስትወርድ ሲኦል ደጃፍ ላይ እንድትገኝ መጥሪያ ተልኮልሃል እንዴ? ጆሮአችንን እንፈልገዋለን…›› ብሎ መልሶ ጆሮውን ደፈነ። ከባለ አስገምጋሚው ድምፅ ተሳፋሪ ይልቅ በዚህኛው ተገርመን ጥቂት ስንተያይ እንደቆየን፣ ‹‹ከመንግሥት ተቃዋሚዎች የአንዳቸው አባል ይሆናል ተውት። ዘንድሮ በሰው ቁስል እንጨት እየሰደዱ ሳይሰሙ ሳያዩ እንደ ጋጋሪ ቆስቋሽ ያልበላቸውን የሚያኩት ብሰውብናል…›› ብላ አንዲት ሰልካካ ቀይ ድንገት ፖለቲካውን ስታመጣው፣ ‹‹እንዴት ነው ነገሩ አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ከምሽት የቲቪ ዜና በተጨማሪ ታክሲ ውስጥም አሉ እንዴ?” አለ ጎልማሳው። ‹‹አንተና ቢጤዎችህ መንደር ውስጥ ከምታመነዥጉት ከንቱ ወሬ ቢያንስ የእነሱ ይሻላል…›› ሲል የጆሮ ታንቡራችንን ያርገበገበው ተሳፋሪ፣ ‹‹እንደ አሮጌ ሸክላ ከምታንቋርሩብን በላይ ያሰለቸን ነገር የለም…›› ብሎ ጎልማሳው መለሰ። ደርቢ በሉት!

መንገዳችን  እየተጋመሰ ነው። ሾፌራችን በበገና ቅኝት ተመስጦ ከራሱ ጋር  ጥሞና ይዟል። ‹‹ልጆቼ ከግራም ከቀኝም የነገር ሰበዝ እየመዘዛችሁ ስትጫወቱ ደስ ይላል፡፡ ነገር ግን ጨዋታው ለዛና ፈገግታ ይኑረው እንጂ በነገር አትናጀሱ…›› እስካሁን ድምፃቸው ያልተሰማ አንዲት እናት ማሳሰቢያ ጣል አደረጉ። ትንሽ ቆየት ብለው ደግሞ፣ ‹‹ወይ አዲስ አበባ ወይ አራዳ ሆይ፣ መንደሮች ፈራርሰው በሕንፃ ማጌጡ ውበት ሆነሽ ወይ? እኔ እኮ አልገባኝ ያለ ነገር ቢኖር አዲስ አበባ እነዚያን የጥንቶቹን መንደሮቿን ይዘታቸውን ጠብቆ ማዘመን ይሻላል፣ ወይስ ውበትና ቅጥ በሌላቸው የኩረጃ ጉራማይሌ ሕንፃዎች የአኒሜሽን ብሎክ ማስመሰል…›› አሉ ሻሻቸውን እያስተካከሉ። ‹‹እኚህ እናትማ በሚገባ የተማሩና የተመራመሩ ቢሆኑ እንጂ፣ እንዲያው ያለ ምክንያት አስገራሚ ንፅፅር አላመጡም…›› ትላለች አንዷ ከጥግ። ‹‹ምንድነው የሚሉት ሴትዮዋ? ከተማ የሚያምረው በዘመናዊ ሕንፃዎች እንጂ በአረጁ ጉረኖዎች ነው እንዴ? አሁን ገና በብልፅግናችን ላይ መጡ…›› ስትል አጠገቤ ያለችው፣ ‹‹አይ ሰው እንዲያው ግን የሃይማኖታችን፣ የፖለቲካችንና የልማዳችን ድምዳሜ ሁሉ ከጥቅማችን ውጪ ከሆነ ስህተት ነው ማለት ነው?›› ሌላዋ ከመሀል ወንበር መጨረሻ ወንበር ወደ ተሰየሙት ዞራ በለሆሳስ ጠየቀች። ነገሩ ደርቷል!

‹‹ቢሆን ነዋ፣ ባይሆንማ በድጋፍና በተቃውሞ መሀል አማካዩን የመፍትሔ መንገድ ለመፈለግ መጠመድ በተገባን ነበር። ባለመታደል ጽንፍና ጽንፍ ይዘን በብሔር፣ በእምነትና በጥቅም ተቧድነንና ተሳስረን እንደ ደመኛ ጠላት እየተሻኮትን ፍረጃ ለመለጣጠፍ እሽቅድምድም ከያዝን እኮ በጣም ቆየን…›› አለ ጎልማሳው። እኚያ እናት ግን፣ ‹‹ልጆቼ ወግ ጀምረን በሥርዓት መነጋገር ሲገባን ለምን ይሆን በተቀደደልን ቦይ ውስጥ ብቻ እየፈሰስን ከንቱ ነገሮች ላይ የምናተኩረው፡፡ እኔ ዘመናዊነትን ከጥንቱ ጋር ብናዋህድ ያምራል የሚል ይዘት ያለው ሐሳብ ሳቀርብ፣ ድጋፍና ተቃውሞ ለመቁጠር አስቤ አይደለም፡፡ ነገር ግን በአዲስ አበባም ሆነ በመላ አገራችን ጉዳይ ሐሳብ ተነስቶ ስንነጋገር ትኩረታችን መሆን ያለበት የጋራ ጉዳያችን እንጂ ታሳቢ የሚደረጉ ጥቅሞች ከሆኑ ዋጋም አይኖረንም፡፡ አንዴ ምን ሆነ መሰላችሁ ሰውየው በምሽት ሞቅ ብሎት እየተንገዳገደ ሲሄድ ሌሎች ሁለት ሞቅ ያላቸው ሰዎች ሲጨቃጨቁ ደረሰ፡፡ ከሰዎቹ አንዱ ለሰውየው አንድ ጥያቄ አቀረቡት፡፡ እጁን ወደ ሰማዩ አመልክቶ በኮከቦች የተከበበችውን ደማቅ ጨረቃ እያሳየው ‹ምን እንደሆነች ነግረህ ገላግለን› አለው፡፡ ሰውየውም ‹እኔ ሠፈሬ እዚህ ስላልሆነ ምን እንደሆነች አላውቅም› አላቸው፡፡ እኛም እንዲህ እየሆንን ነው…›› ብለው ሲስቁ እየመረረንም ቢሆን ሳቅን፡፡ ወቸ ጉድ!

ጉዟችን ሊገባደድ ነው። ሾፌራችን የነፍሱን ጥያቄ መልሶ መጨረስ ያቃተው መሰለ በገናውን አቋርጦ፣ ‹‹ሳስጠራው ከርሜ ስሜን በጀግንነት፣ ምን ሰበረው ቅስሜን አንቺን ያገኘሁ ዕለት…›› የሚለውን ዜማ ሲከፍት ከትከት ብሎ የሚስቅ ሰው ድምፅ ተሰማ፡፡ ወዲያው ቀጥሎም፣ ‹‹‹ዕብድ ቢጨምት እስከ ስድስት ሰዓት ነው› ሲሉ አይገባኝም ነበር፡፡ አሁን ግን በደንብ ተገለጸልኝ…›› እያለ ባለ ሳቁ ሲያስከትል፣ ‹‹ዓለም ላይ ስንኖር ነፍሳችንም ሥጋችንም የሚፈልጉት ምግብ አለ፡፡ የእኛ ዋና ተግባር ሁለቱንም ማመጣጠን ነው…›› ብሎ ጎልማሳው ተናገረ፡፡ ‹‹ጎበዝ በፈለገን መንገድ እየተረጎምን እኮ ነው ነገራችን ሁሉ ማሰሪያ አልባ ሆኖ ለያዥ ለገናዥ ያስቸገርነው…›› ብላ ያቺ ተንኳሽ ዘው ስትል፣ ‹‹ምነው እህቴ እንኳን እኛ በድምፃችን ፓርላማ የገቡትም እኮ ትርጉም ላይ ተቸግረው አይደል እንዴ ወይ ሕገ መንግሥቱ ወይ በእሱ መርህ ላይ ተመሥርተው የወጡ ሕጎች ሥራ ላይ መዋል ያቃታቸው…›› ብሎ መለሰላት፡፡ የሁለቱ ምልልስ አልጥም ያላቸው እኚያ እናት፣ ‹‹አይ እናንተ ልጆች በሥሌትና በስሜት መሀል ያለው ፖለቲካ ሳይገባችሁ ነው እንዴ አንዱን ከአንዱ እያማታችሁ፣ ወግና ደርዝ ያለው ነገር ሳንነጋገር መንገዳችን የሚያልቀው…›› እያሉ ሲብሰለሰሉ ወያላው ‹‹መጨረሻ!›› ብሎ አስወርዶ ወደ ጉዳዮቻችን አሰናበተን፡፡ መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት