Sunday, February 25, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የመጀመሪያው ፀረ ድሮን ቴክኖሎጂ ሥርዓት በቦሌ ኤርፖርት ሥራ ላይ ዋለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በናርዶስ ዮሴፍ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ከሰሃራ በታች ባሉ አገሮች ብቸኛ የሆነውን የመጀመሪያ ፀረ ድሮን ቴክኖሎጂ ሥርዓት፣ ከዓርብ ኅዳር 14 2016 ዓ.ም. ጀምሮ በቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት በሥራ ላይ አዋለ።

በፈረንሣይ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አገልግሎት ኩባንያ ሲኤስ ግሩፕ ተገጥሞ አገልግሎት ላይ የዋለው ይህ አዲስ የቴክኖሎጂ ሥርዓት፣ በኢትዮጵያ የፈረንሣይ ኤምባሲ የገንዘብ ድጋፍ ተሠርቶ ለኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የተበረከተ ነው። 

የቴክኖሎጂ ሥርዓቱን ግንባታ በተመለከተ ከሁለት ዓመታት በፊት የፈረንሣይ ኩባንያ አገልግሎቱን ለኢትዮጵያ አየር መንገድ የማቅረብ ፍላጎቱን ማሳወቁን፣ የኩባንያው ዋና ሥራ አስኪያጅ ኤሪክ ብላንች በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተናግረዋል። 

የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው፣ ‹‹ለረዥም ጊዜ አውሮፕላኖቻችን በረራ አቋርጠው እስኪያርፉ ወይም በተለያዩ የአውሮፕላን ክፍሎች ላይ የተለያየ መጠን ያለው ጉዳት እያደረሱ የነበሩት ወፎች ብቻ ሆነው የቆዩ ቢሆንም፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ድሮኖችም በኤርፖርቶች አካባቢ እየበዙ መምጣታቸው አንድ ችግር እየሆነ ነው፡፡ ይህም የኩባንያውን ጥያቄ መቀበልን አስፈላጊ አድርጎታል፤›› ብለዋል፡፡ 

ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ያረፈበት አጠቃላይ ሥፍራ 3.6 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሲሆን፣ አሁን በሥራ ላይ የዋለው የፀረ ድሮን አገልግሎት የመቆጣጠሪያ መሣሪያዎች የተገጠሙትና የአገልግሎት ሽፋን የሚሰጡት በአየር መንገዱ ምዕራባዊ ክፍል ብቻ ነው ተብሏል፡፡

ይህም የተደረገው አየር መንገዱ ቦታውን እንዲመርጥ በቅድሚያ ጥያቄ ቀርቦለት፣ በረራዎች የሚበዙበትን ክፍል ለአገልግሎቱ ተደራሽነት በማስቀደሙ እንደሆነ ታውቋል፡፡

የቴክኖሎጂ ሥርዓቱ በራዳር የበረራ ቁጥጥር ወደ አየር መንገዱ ክልል የሚገቡ ድሮኖችን የሚለይ ሲሆን፣ በገጠማቸው ካሜራዎች በቀንም ሆነ በማታ የድሮኖቹን ቦታና ርቀት ትክክለኛ መረጃ በመመልከት በድሮኑና በድሮን ኦፕሬተሩ መካከል ያለውን ግንኙነት የሚያቋርጥበት ሁለት ዓይነት አሠራር እንዳለው ተነግሯል። 

የመጀመሪያው አሠራር ድሮኑ በካሜራ ተለይቶ አውሮፕላኖች ከሚገኙበት ቦታ አንፃር ችግር የመፍጠሩ ሁኔታ ቀላል ነው በሚል ከተወሰነ፣ በድሮኑና በኦፕሬተሩ መካከል ያለውን ኔትወርክ በማቋረጥ ድሮኑ መቅረፅ እንዳይችል ነገር ግን ወደ ኦፕሬተሩ መመለስ እንዲችል የሚፈቅድ ዘዴ ነው። 

ሁለተኛው የቴክኖሎጂው ትግበራ ዘዴ ድሮኑ የገባበት የኤርፖርቱ ክፍል ከአውሮፕላኖቹ ጋር በፍጥነት መገናኘት በሚችልበት አቅጣጫ ከሆነ፣ በድሮኑና በኦፕሬተሩ መካከል ያለውን ግንኙነት የድሮኑን የአቅጣጫ መጠቆሚያና መዘወሪያ (GPS) በማቋረጥ ድሮኑ እንዲወድቅ ማድረግ የሚያስችል ነው። 

የፀረ ድሮን ቴክኖሎጂ ሥርዓቱን አሠራር ከሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን፣ ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትና ከኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ የተውጣጡ ሠራተኞች ሥልጠና ወስደው ሥራውን መረከባቸውን ለማወቅ ተችሏል። 

የመንግሥት ተቋማቱ ሠራተኞች አሁን ሥራ ቢጀምሩም፣ የትኛው የመንግሥት ተቋም የዘርፉን የበላይ ኃላፊነት እንደሚወስድ ግን የተቀመጠ ሕጋዊ አሠራርም ሆነ መመርያ የለም። 

በቴክኖሎጂ ሥርዓቱ የምርቃት ሥነ ሥርዓት የትግበራውን ውጤታማነት ማሳያ በቀረበበት ወቅት የአየር መንገድ ግሩፑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጉዳዩን በተመለከተ ጥያቄ አንስተው የነበረ ሲሆን፣ ኃላፊነቱ በሚመሩት ተቋም ሥር እንደማይካተት ገልጸዋል። 

ቴክኖሎጂውን የገጠመው ኩባንያ ዋና ኃላፊ በበኩላቸው፣ ‹‹ድርጅታችን በዘርፉ ካለው ልምድ አንፃር ሥርዓቱን የማስተዳደር ሒደት በአንድ ተቋም ሥር ቢያዝ የበለጠ ውጤታማ ነው፤›› ብለው፣ ‹‹ይህን ማድረግ ካልተቻለ ግን በአየር ትራፊክ ቁጥጥርና በደኅንነት ዘርፍ ልምድ ያላቸው ሠራተኞች የቴክኖሎጂ ሥርዓቱን የመቆጣጠር ሥራ ቢሰጣቸው ብለን እንመክራለን፤›› ብለዋል፡፡

የቴክኖሎጂ ሥርዓቱ ሙሉ ሙሉ የኤርፖርቱን አየር ክልል ሽፋን እንዲሰጥ ለማድረግ ከኩባንያው በኩል ፍላጎት መኖሩም ተገልጿል።

የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሥርዓቱ ውጤታማነት ከተገመገመና አጥጋቢ ሆኖ ከተገኘ ከወራት በኋላ ሊነሳ የሚችል ሐሳብ መሆኑን ተናግረዋል። 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች