Sunday, February 25, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ ባንኮች የኢኮኖሚ መዋቅር ለውጦችን ማስተናገድ የሚያስችል አቅም እንዲፈጥሩ ተጠየቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አወቃቀርና አደረጃጀት እየተቀየረና የዓለም ኢኮኖሚ ግንኙነት እየተወሳሰበ ስለሚሄድ፣ የኢትዮጵያ ባንኮችም ይህንን ተፈጥሯዊ ክስተት ማስተናገድ የሚችሉበትን አቅም መፍጠር እንደሚገባቸው፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምሕረቱ አሳሰቡ፡፡

አቶ ማሞ ሐሙስ ኅዳር 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የኅብረት ባንክ 25ኛ ዓመት ክብረ በዓል ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት፣ ‹‹የአገራችን ኢኮኖሚ አወቃቀር እየተቀየረና የፋይናንስ ፍላጎቱም እየጨመረ ስለሚሄድ፣ ይህንን ተፈጥሯዊ ሒደትና ክስተት ለማስተናገድ ባንኮች ዝግጁ መሆን ይገባቸዋል፤›› ብለዋል፡፡

የዓለም ኢኮኖሚ ግንኙነትም ቢሆን እየተወሳሰበ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ አወቃቀር እየተለወጠ ስለሚሄድ፣ ከዚህም አንፃር ባንኮች ራሳቸውን ዝግጁ ማድረግ እንደሚኖርባቸው አስገንዝበዋል፡፡

ከወቅታዊ አገራዊ የፋይናንስ ፍላጎትና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ አንፃር በመጪው ጊዜ የሚገጥማቸውን ውስጣዊም ሆነ ውጫዊ ፉክክር ተቋቁመው በአሸናፊነት ለመዝለቅ፣ በቁርጠኝነት መነሳት እንደሚኖርባቸው ገዥው አሳስበዋል፡፡  

የኢትዮጵያ ባንኮች በብድር፣ በቁጠባና በተለያዩ የባንክ መመዘኛዎች በዓመት ከ25 በመቶ በላይ ዕድገት እያሳዩ መምጣታቸውን፣ ነገር ግን ባንኮች ከሌሎች አገሮች ባንኮች ጋር ሲነፃፀሩ ብዙ እንደሚቀራቸው ተናግረዋል፡፡   

‹‹የኢትዮጵያ ባንኮች በካፒታል አቅም፣ በቴክኖሎጂ ልህቀት፣ በአሠራር ቅልጥፍናና በአመራር ክህሎት ገና ብዙ ርቀት መጓዝ ይጠብቃቸዋል፤›› ሲሉ ገዥው የኢትዮጵያን ባንኮች ያሉበትን ደረጃ አመላክተዋል፡፡  

ወቅታዊው የአገሪቱን ኢኮኖሚ በተመለከተ በሰጡት አስተያየትም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለፉት 25 ዓመታት በርካታ ውጣ ውረዶች ቢገጥሙትም፣ ከበርካታ ታዳጊ አገሮች አማካይ ዕድገት ጋር ሲነፃፀር አመርቂና ቀጣይነት ያለው ዕድገት እያስዘመገበ ነው ብለዋል፡፡

‹‹ይህም ቢሆን ግን ከፊታችን ብዙ ሥራ አለ፤›› ያሉት ገዥው፣ በዚህ ረገድም የፋይናንስ ዘርፉ በተለይም ባንኮች የሚጫወቱት ሚና እንደሚኖር ገልጸዋል፡፡ ባንኮች ቁጠባ በማሰባሰብ፣ ለኢንቨስትመንት የሚሆን ሀብት በመመደብ፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂ በማስተዋወቅ፣ አደረጃጀታቸውንና አሠራራቸውን በማዘመን የፋይናንስ አካታችነትና ተደራሽነት እንዲስፋፋ የቁጠባ ባህል እንዲዳብር፣ በአጠቃላይ የማይናቅ ሚና የተጫወቱና እየተጫወቱ መገኘታቸውን አልሸሸጉም፡፡

የአገሪቱ ባንኮች ከባንክ አገልግሎት ተገለው የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወገኖችን ወደ ባንክ መረብ ለማስገባትና የተጀመረውን ሁለተኛው የኢኮኖሚ ሪፎርም ለመደገፍ፣ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ስትራቴጂ ነድፈው መንቀሳቀስ እንደሚገባቸውም አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ አጠቃላይ አገልግሎቱን ለማጎልበት ውስጣዊ አቅሙና አደረጃጀቱ፣ እንዲሁም የአሠራር ሥርዓቱን በማዘመን ከዘመኑ ጋር አብሮ መሄድ ከተቻለም ዘመኑን መቅደም እንዳለበት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክም ከተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት አኳያ የባንኮችን ጤንነት፣ ዕድገትና አስተዋጽኦ ለማጎልበት የሚያደርገውን ጥረት እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡

የዛሬ 25 ዓመት የተመሠረተው ኅብረት ባንክ የፋይናንስ ተደራሽነትና አካታችነት ላይ የራሱን አስተዋጽኦ ስለማበርከቱ ዕውቅና የሰጡት ገዥው፣ ይህም ዛሬ አንጋፋና ስመ ጥር ከሚባሉ ባንኮች መካከል አንዱ ለመሆን እንዳበቃው ተናግረዋል፡፡ 

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኅብረት ባንክ በክብረ በዓሉ ላይ ለአሥር በጎ አድራጎት ድርጅቶች ያበረከተውን ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ በክብር እንግዳው በኩል እንዲሰጥ አድርጓል፡፡ ከዚህም ሌላ የባንኩ አባቶች ተብለው ለተጠቀሱ መሥራቾች፣ የቀድሞ ቦርድ አባላትና ቤተሰቦች፣ እንዲሁም ለቀድሞ ፕሬዚዳንቶች ባንኩ በዕለቱ የክብር እንግዳ አቶ ማሞ አማካይነት ዕውቅና እንዲሰጣቸው ተደርጓል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች