Sunday, February 25, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በኤክሳይስ ታክስ አተገባበር መፍትሔ ላላገኙ ተሽከርካሪዎች እንደገና ጨረታ መውጣቱ ቅሬታ አስነሳ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • የጉምሩክ ኮሚሽን ሁሉንም ጋዊ መንገዶች ተከትሎ ጨረታውን ማውጣቱን አስታውቋል

በ2012 ዓ.ም. የወጣው የኤክሳይስ ታክስ ተግባራዊ በሚደረግበት ወቅት ውዝግብ አስነስተው ከነበሩት 297 ተሽከርካሪዎች ውስጥ አብዛኞቹ በጉምሩክ ኮሚሽን እንደገና ለጨረታ በመቅረባቸው፣ በተሽከርካሪዎቹ ባለቤቶች ላይ ቅሬታ ፈጠረ፡፡

የጉምሩክ ኮሚሽን የአዲስ አበባ ቃሊቲና አዳማ ጉምሩክ ቅርንጫፎች ባወጧቸው ማስታወቂያዎች መሠረት የቃሊቲ ቅርንጫፍ 46 ተሽከርካሪዎችን ለኅዳር 20 ቀን 2016 ዓ.ም.፣ የአዳማ ቅርንጫፍ ደግሞ 165 ተሽከርካሪዎችን ለኅዳር 18 ቀን 2016 ዓ.ም. ለማጫረት ቀጠሮ ይዘዋል፡፡

በየካቲት ወር 2012 ዓ.ም. ተግባራዊ የሆነው የኤክሳይስ ታክስ ባገለገሉ ተሽከርካሪዎች ላይ ከፍተኛ ታክስ የሚጥል ሲሆን፣ አዋጁ ከመፅደቁ በፊት የባንክ ፈቃድ አውጥተው የማስመጣት ሒደት ጀምረው ለነበሩት ግን የስድስት ወራት ጊዜ ሰጥቶ የማስመጣት ሒደቱን እንዲጨርሱ ደንግጎ ነበር፡፡

ሆኖም ነሐሴ 5 ቀን 2012 ዓ.ም. የስድስት ወራቱ የጊዜ ገደብ ሲጠናቀቅ በቀናት ልዩነት ወደ አገር ውስጥ የገቡት ተሽከርካሪዎች ጉዳይ ለሦስት ዓመታት ውዝግብ ፈጥሮ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡

በወቅቱ የኮቪድ ወረርሽኝ ተከስቶ ስለነበረና በዓለም ላይ የነበረው የትራንስፖርት ሥርዓት ችግር ውስጥ ገብቶ ስለነበር ተሽከርካሪዎቻቸው በቀናት ልዩነት አርፍደው ወደ ኢትዮጵያ እንደገቡ የሚገልጹት፣ የኢትዮ ተሽከርካሪ አስመጪዎች ማኅበር አባላት መፍትሔ ፍለጋ በተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርጉም ሊሳካላቸው እንዳልቻለ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ተሽከርካሪዎቹ ተወርሰውባቸው መፍትሔ ሲያፈላልጉ ከቆዩት መካከል በርካታ ከስደት ተመላሾች ሲገኙ፣ ከእነዚህ ውስጥ 25 ያህል ሴት የስደት ተመላሾች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ያስገቡት አቤቱታ መልስ በማግኘቱ እንዲመለሰላቸው ተፈቅዷል፡፡ ሆኖም ከተፈቀደላቸው ውስጥ የሁለት ግለሰቦችና የሌሎች 23 ተጨማሪ የስደት ተመላሾች ያስመጧቸው ተሽከርካሪዎች እንዳልተመለሱላቸው አስረድተዋል፡፡

ሁለቱ የጉምሩክ ኮሚሽን ቅርንጫፎች ባወጧቸው ጨረታዎች በአጠቃላይ 211 ተሽከርካሪዎች የቀረቡ ሲሆን፣ እንደ ዓይነታቸው ከዝቅተኛው 347 ሺሕ ብር እስከ ከፍተኛው 13 ሚሊዮን ብር ድረስ የመነሻ ዋጋ አላቸው፡፡

ኮሚሽኑ ከዚህ በፊት 23 ተሽከርካሪዎችን በጨረታ ሸጦ የነበረ ሲሆን፣ 37 ተሽከርካሪዎችን ደግሞ ለተለያዩ የመንግሥት ቢሮዎች ሰጥቶ ነበር፡፡ አሁን በእጁ ያሉትን ተሽከርካሪዎች ለመሸጥ ከዚህ በፊት የተለያዩ ሙከራዎችን አድርጎ፣ አስመጪዎቹና የስደት ተመላሾቹ የተለያዩ ተፅዕኖዎችን በመፍጠራቸው በአንድ ጊዜ ብቻ 23 ተሽከርካሪዎችን መሸጡ ታውቋል፡፡

አስመጪዎቹና ተመላሾቹ በጉምሩክ ኮሚሽን፣ በገንዘብ ሚኒስቴር፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ በሚኒስትሮች ምክር ቤትና በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቢሮ መካከል ቢመላለሱና መፍትሔ ቢጠይቁም ምንም ሊሳካላቸው እንዳልቻለ፣ የአስመጪዎቹ ማኅበር አባላት ቅሬታቸውን አስምተዋል፡፡ የቀሩት ሁሉም ተሽከርካሪዎቻቸው ለጨረታ መቅረባቸው እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል፡፡

ባለፈው ዓመት አጋማሽ 23 ተሽከርካሪዎች በጨረታ መሸጣቸውንና 37 ተሽከርካሪዎች ለመንግሥት ቢሮዎች በመሰጠታቸው ምክንያት የገንዘብ ሚኒስቴር የመጨረሻ መፍትሔ እንዲሰጣቸው የጠየቁት ባለንብረቶች፣ የገንዘብ ሚኒስቴር ለመፍትሔ ብሎ ያቀረባቸውን ሐሳቦች የሚኒስትሮች ምክር ቤት እንዲያፀድቅለት ጠይቆ ነበር፡፡

በሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ተፈርሞ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት የተላከው የመፍትሔ ሐሳብ የተጠየቀበት ደብዳቤ መጋቢት 25 ቀን 2015 ዓ.ም. ነበር የተጻፈው።

ለመፍትሔም አቅርቦት የነበረው ከተሸጡት 23 ተሽከርካሪዎች ከተገኘው 23.6 ሚሊዮን ብር ውስጥ በቀድሞ ኤክሳይስ ታክስ ሊከፈል የሚገባው ቀረጥና ታክስ ተቀናሽ ተደርጎ ቀሪው እንዲመለስላቸው፣ ለመንግሥት የተሰጡትን 37 ተሽከርካሪዎች በሚመለከት ደግሞ 21.9 ሚሊዮን ብር ለአስመጪዎቹ እንዲከፈላቸው ነበር፡፡

ሦስተኛ የመፍትሔ ሐሳብ የቀረበው ደግሞ ኮሚሽኑ በእጁ ያሉትን ተሽከርካሪዎች በሚመለከት ሲሆን፣ ለእነሱም ‹‹አስመጪዎቹ በቀድሞው የኤክሳይስ ታክስ አዋጅና በሌሎችም ሕጎች መሠረት ሊከፈል የሚገባውን ቀረጥና ታክስ ከፍለው ተሽከርካሪዎቹን እንዲረከቡ›› የሚል ነው፡፡

ሪፖርተር ጨረታውን ያወጣው የጉምሩክ ኮሚሽን ኃላፊዎችን ለማነጋገር ተደጋጋሚ ጥረት አድርጎ የነበረ ሲሆን፣ ዋና ኮሚሽነሩ አቶ ደበሌ ቃበታ በላኩት የስልክ ጽሑፍ መልዕክት እንደገለጹት ተቋማቸው በተሰጠው የሕግ አግባብ መሠረት ሁሉንም ዕርምጃዎች ወስዷል፡፡ ከዚህ የበለጠ ተጨማሪ ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች