Monday, February 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ከጨረታ በስተጀርባ ያሉ ድርድሮችን ለማስቀረት ጥረት እያደረግን ነው›› ሱሌማን ደደፎ (አምባሳደር)፣ የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ (የቀድሞ ሜቴክ) ዋና ሥራ አስፈጻሚ

ሱሌማን ደደፎ (አምባሳደር) በተባበሩት ዓረብ ኤሜሬትስ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ፣ ከጥር 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የቦርድ ሰብሳቢ አብረሃም በላይ (ዶ/ር) በተፈረመ ደብዳቤ፣ የዋና ሥራ አስፈጻሚነት ሹመት ማግኘታቸው ይታወሳል፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከኮተቤ የመምህራን ማሠልጠኛ ኮሌጅ በውጭ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ አግኝተዋል፡፡ በተጨማሪም ከአምስተርዳም ዩኒቨርሲቲ በኢንተርናሽናል ቢዝነስ ማስተርስ አግኝተዋል፡፡ ለአራት ዓመታት በናይጄሪያ የኢትዮጵያ አምባሳደር፣ ለአምስት ዓመታት ያህል በጂቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር፣ እንዲሁም በተባበሩት ዓረብ ኤሜሬትስ አምባሳደር ሆነው ሠርተዋል፡፡ የቀድሞው የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ለሁለት ከተከፈለ በኋላ የተቋቋመውን የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ በዋና ሥራ አስፈጻሚነት እየመሩት ነው፡፡ ስለግሩፑ አመሠራረት፣ የቀድሞው ሜቴክ ያከናወናቸውንና የገጠሙትን ችግሮች በተመለከተ ሰላማዊት መንገሻ ከእሳቸው ጋር ያደረገችው ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ተሰናድቷል፡፡

ሪፖርተር፡- ሜቴክ ለሁለት ከተከፈለ በኋላ አብዛኞቹን ብድሮች የዕዳ ሀብት አስተዳደር እንዲወስደው ተደርጎ በመንግሥት ካፒታል ተመድቦላችኋል፡፡ ተቋሙተቋቋመለት ዓላማ መሠረት በሚገባ እንዲሠራ ቢፈለግም በሚፈለገው ደረጃ ለውጥ አልመጣም ይባላል፡፡ ለውጥ መምጣት ያልቻለው ለምንድነው? መጥቷል ካላችሁ ምን ዓይነት ለውጥ ተገኝቷል?

አምባሳደር ሱሌማን፡- እንደሚታወቀው እኔ የምመራው ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ቀድሞ ሜቴክ ተብሎ ከሚጠራው ውስጥ የወጣ ነው፡፡ ሜቴክ በአወቃቀር በርካታ ኢንዱስትሪዎችን በሥሩ ይዞ ለመከላከያ ሠራዊት ጥቅም የሚሰጡ ምርቶችን እንዲያመርት ታስቦ የተቋቋመ ትልቅ ኢንዱስትሪ ነው፡፡ ሲቋቋም የተመሠረተበት ዓላማ መጥፎ አልነበረም፡፡ በወቅቱ ሜቴክ ሲቋቋም የነበረው ምኞት ትክክል ነበር፡፡ በርካታ አገሮችም በእንዲህ ዓይነት ተቋማት የኢንዱስትሪ ዘርፉን ማሳደግ ችለዋል፡፡ በወቅቱ ሞዴል የተደረጉ አገሮችም አሉ፡፡ ይሁን እንጂ ሜቴክ ተቋቁሞ የልማት ሥራዎችን ከማከናወን ይልቅ በአገሪቱ ላይ ከፍተኛ ጥፋት አድርሷል፡፡ ምናልባት ለሕወሓት መውደቅ አንዱ ምክንያት ይህ ሊሆን ይችላል ብዬ አስባለሁ፡፡ ሜቴክ የልማት ተቋም ሳይሆን የጥፋትና የዘረፋ ተቋም ሆኖ ነው ያገለገለው፡፡ በዚህ የተነሳ የመንግሥት ለውጥ ሲመጣ አዲሱ መንግሥት በፍጥነት በአገሪቱ ላይ ሲደርስ የነበረውን ጉዳት ለማስቆም ዕርምጃ መውሰድ ነበረበት፡፡  

በሜቴክ አማካይነት የህዳሴ ግድብ ትልቅ ችግር ውስጥ ሊወድቅ ሲል ፈጣን ዕርምጃ ተወስዷል፡፡ የግድቡ ግንባታ ከፍተኛ ወንጀልና ጥፋት ተሠርቶበታል፡፡ የህዳሴ ግድብ ከታሰበለት ጊዜ በላይ እንዳይሄድና እንዲጓተት ተደርጎ ነበር፡፡ ለአንድ ህዳሴ ፕሮጀክት ከሦስት በላይ የህዳሴ ግድቦች ሊገነቡበት የሚችል ገንዘብ ወጪ ተደርጎበታል፡፡ በአራት ዓመታት መጠናቀቅ የነበረበት ሥራ እስከ 12 ዓመታት ፈጅቷል፡፡ በዚያ ወቅት በአራት ቢሊዮን ዶላር ይገነባል የተባለ ፕሮጀክት አሁን ከፍተኛ ወጪ እያስወጣ ነው፡፡ ሜቴክ የአገሪቱን ገንዘብ ሲበዘብዝ ስለነበር አዲሱ መንግሥት ቶሎ ማስቆም ነበረበት፡፡ በዚህም መሠረት ለሁለት መክፈል አስፈላጊ ሆኗል፡፡ እንደ አዲስ ሲደራጅ ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕና መከላከያ በሚል ከተከፈለ በኋላ፣ ግሩፑ የመከላከያ ምርቶች ያልሆኑትን ብቻ እንዲያመርት ተደርጓል፡፡ ግሩፑ ሲደራጅ ዘጠኝ ኢንዱስትሪዎች በሥሩ አሉ፡፡ እነዚህን ዘጠኝ ኢንዱስትሪዎች ከእነ ፋብሪካዎቻቸው እያስተዳደርን ነው፡፡ አሁን ያለበትን አቋም በመለወጥ የልማት ኃይል እንዲሆንና የኢንዱስትሪ ሴክተሩን እንዲመራ፣ ገበያ በማረጋጋት ውስጥ ቁልፍ ሚና እንዲጫወት፣ ከውጭ የሚገቡትን አገር ውስጥ ለማምረት በማሰብ ግሩፑ ከተመሠረተ አምስት ዓመታት ሆኖታል፡፡

በእነዚህ አምስት ዓመት ትልቁን ሥራ ሲሠራ የነበረው፣ እንዲሁም መልሶ የማቋቋምና የማደራጀት ሥራ ስለነበር በሚፈለገው ደረጃ ምርት አላመረተም፡፡ አሁንም ድረስ እየተከናወነ ያለው ሀብትና ዕዳውን የመለየት፣ ያጠፋውንና ያለማውን የመለየትና በሕግ የሚገዛውን ከሕግ በታች ሆኖ እንደ ማንኛውም አገራዊ ተቋም ማድረግ ነው፡፡ ጎን ለጎን ተቋሙ በበጀት የሚተዳደር ስላልሆነ ሠርቶ መተዳደር እንዲችል ከማምረት በተጨማሪ፣ የምርምርና የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡ ለዚህ ምርታማነት እንዲያመች መዋቅሩን ማስተካከልና የሰው ኃይሉን መልሶ ማደራጀት ያስፈልጋል፡፡ ግሩፑ አዲስ መዋቅር እንዲኖረው በውጭ አገር ባለሙያ ተጠንቶ አዲስ በተሠራው መዋቅር መሠረት የሰው ኃይል እንደ አዲስ ለመመደብ እየተሠራ ነው፡፡ ኢንዱስትሪዎቹ ውስጥ በጣም ከፍተኛ  የሆነ የሰው ኃይል ታጭቋል፡፡ አሁን ሠራተኞችን በመቀነስ በባለሙያ እንዲመራ ለማድረግ የሰው ኃይል ድልድል እየተሠራ ነው፡፡ ሜቴክ በነበረበት ጊዜ ከአሥር ሺሕ በላይ ሠራተኞች ነበሩት፣ በጣም ብዙ ናቸው፡፡ በድጋሚ እንዲቋቋም ሲደረግ በግሩፑ ውስጥ አምስት ሺሕ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ የቀሩት ወደ መከላከያ ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ሄደዋል፡፡ አሁን ግሩፑ ውስጥ ያሉት አምስት ሺሕ ቢሆኑም ተቋሙ ሊሸከመው ከሚችለው በላይ የሰው ኃይል አለ፡፡ በአዲሱ የመዋቅር ጥናት መሠረትም በባለሙያ ብቻ ስለሚመራ፣ ሦስት ሺሕ ያህል ሠራተኞች ብቻ ይዞ የመቀጠል ሐሳብ አለው፡፡

ሪፖርተር፡- ከነበረበት ኪሳራ መውጣት ያልቻለው ለምንድነው?

አምባሳደር ሱሌማን፡- ግሩፑ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከኪሳራ አልወጣም ነበር፡፡ በኪሳራ ውስጥ ሆኖ ነበር ሲሠራ የቆየው፡፡ በቂ ምርት አልነበረውም፡፡ ኢንዱስትሪዎቹም ማምረት የሚችሉትን ያህል ቀርቶ አነስተኛ ምርትም አላመረቱም ነበር፡፡ የማምረቻ ግብዓት ስላልነበር ማምረት አልቻሉም፡፡ ካለፈው ዓመት አጋማሽ ጀምሮ የተወሰነ ማንሰራራት ጀምረው፣ አብዛኞቹ ኢንዱስትሪዎች ትርፍ እንኳን ባይባልም ከኪሳራ መውጣት ችለዋል፡፡ በዚህ መሠረት ዘንድሮ በከፍተኛ መጠን ለማምረት አቅደናል፡፡ ጠቅላላ ምርቱ እስከ ዛሬ ተቋሙ ከሚያመርተው በላይ ብዙ ሲሆን፣ በአቅሙ ልክ እንዲያመርት እየተደረገ ነው፡፡ የሜቴክ አቅም ትልቅ ነው፡፡ የሕዝብ ሀብት ስለሆነ በሚገባው ልክ ተደራጅቶ በአቅሙ ልክ መሥራት አለበት፡፡ ይህን ተቋም የሚወዳደር የግል ተቋም የለም፡፡ ድርጅቱ ውስጥ ያለው ሀብት በጣም ትልቅ ነው፡፡ ይህንን ሀብት ወደ ምርት መቀየር አስፈላጊ ነው፡፡ ዘንድሮ 15 ቢሊዮን ብር የሚያወጣ ምርት ለማምረት አቅደናል፡፡ በጣም የተጋነነ ዕቅድ እንደሆነ እናውቃለን፡፡ የሜቴክ ትልቁ ምርት እስከ ሁለት ቢሊዮን ብር ድረስ ነበር፣ ይሳካል ብለን እናስባለን፡፡ ግን ማምረት የሚችለውን ያህል ካላመረተ መቀጠል አይችልም፡፡

ዕቅዳችንን ለማሳካት የውጭ ምንዛሪ እጥረት ፈተና ሊሆንብን ይችላል፡፡ ኢንዱስትሪው ሙሉ በሙሉ የማምረቻ ሒደቱ የተመሠረተው ከውጭ በሚገቡ ዕቃዎች ላይ ነው፡፡ ማንኛውም ማሽነሪ፣ የማምረቻ ጥሬ ዕቃና የመሳሰሉት ግብዓቶች በሙሉ ከውጭ የሚገቡ ሲሆን፣ በአገር ውስጥ ጥሬ ዕቃ በመጠቀም ምርት የሚያመርቱ ሦስት የብረት ኢንዱስትሪዎች ብቻ ናቸው፡፡ ሌሎቹ ስድስት ኢንዱስትሪዎች ሙሉ በሙሉ ከውጭ የሚገባ ጥሬ ዕቃ የሚያስፈልጋቸው ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ላለፉት ሁለት ዓመታት ምንም ዓይነት ምርት ማምረት አልቻሉም፡፡ ግብዓቶቹ የውጭ ምንዛሪ ስለሚፈልጉ በተደጋጋሚ ብንጠይቅም ማግኘት አልቻልንም፡፡ መንግሥት እንደ መድኃኒት፣ ማዳበሪያ፣ መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች፣ እንደ ነዳጅና ስንዴ ግዥ ላይ አተኩሯል፡፡ በመጨረሻም የሰፕላይ ክሬዲት ኤልሲ በመክፈት ለመጠቀም እየሞከርን ቢሆንም፣ እሱም ቢሆን ብዙ ውጣ ውረድ ስላለው እስካሁን አልተፈቀደልንም፡፡ የቀድሞ ንብረቶችን ከየቦታው በመሰብሰብና ቁርጥራጭ ብረቶችን በመሰብሰብ በድጋሚ ጥቅም ላይ እንዲውሉ በማድረግ እየሠራን ነው፡፡ የቢሾፍቱና የአዳማ ግብርና ማሽነሪ ኢንዱስትሪዎች በአገር ውስጥ ቁርጥራጭ እየሠሩ ነው፡፡ ግን በዚህ መቀጠል የለበትም፡፡

ኢትዮጵያ የራሷ የሆነ አውቶቡስ፣ መኪና፣ ትራክተር ማምረት አለባት፡፡ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ግማሽ ሚሊዮን ያህል ትራክተር እንኳን የለም፡፡ የተሻለ የግብርና ኮምባይነር የላትም፡፡ ኢትዮጵያ ራሷ ማምረት ካልቻለች በግዥ ትራክተር ግብርናን ማዘመን አይቻልም፡፡ ለመኪና መሥሪያ ምንም ዓይነት ግብዓት አይመረትም፡፡ ጎማ ብቻ ነው የሚመረተው፡፡ እዚህ ላይ አንድ ያስታወስኩት ነገር ሜቴክ መቀሌ የኢንጂን ፋብሪካ አቋቁሞ እንደነበር ነው፡፡ ትንሽ ማምረት እንደጀመረ በተፈጠረው የወቅቱ ሁኔታ አማካይነት መቀጠል አልቻለም፡፡ አሁንም ተመሳሳይ አዳዲስ ድርጅቶችን በኢትዮጵያ ለመጀመር የተማረ የሰው ኃይልም ሆነ ገንዘብ የለንም፡፡ ያደጉ አገሮች ልምድም የተመለከትን እንደሆነ ሙሉ የመኪና ዕቃዎችን አያመርቱም፡፡ ነገር ግን ከፍተኛ ወጪ የሚያስወጡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ያመርታሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት መቀሌ የተጀመረው ምርት መቀጠል እንዳለበት ወይም አዋጭ መሆኑ ከታወቀ እሱን ለማስቀጠል፣ ካልሆነ ደግሞ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ውስጥ አዲስ የኢንጂን ፋብሪካ ለመገንባት የሚያስችል ጥናት እየተሠራ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የተለያዩ የኢንዱስትሪ ዘርፎች ስላሉት በውጤታማነት ማሳካት ያልተቻለው አመራሮች ሁሉንም እንቅስቃሴ መቆጣጠር ስላልቻሉ ነው በሚለው ይስማማሉ?  አመራሩን ለማስተካከል ምን እየተሠራ ነው?

አምባሳደር ሱሌማን፡- ድርጅቱ ሠራተኞችን የሚያሠለጥንበት ማዕከል አለው፡፡ ከአዳማና ከአዲስ አበባ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ትስስር ለመፍጠር ጥረት እያደረግን ነው፡፡ ምርምሮች ወደ ተግባር የሚለወጡበትና ተማሪዎች ብቁ እንዲሆኑ ሥልጠና የሚያገኙበት መንገድ እየተፈጠረ ነው፡፡ ቀድሞ የነበሩ የድርጅቱ አመራሮች የዝርፊያ ሥልት አሁንም ድረስ በተለያየ መንገድ እየቀጠለ ስለሆነ ከኪሳራ እንዳይላቀቅ ማነቆ ሆነውብናል፡፡ በቅርቡ ይፋ የተደረገው የፓወር ኢኪዩፕመንት ማምረቻ ፋብሪካ ስምንት አመራሮች ከብረት ስርቆት ጋር በተገናኘ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ሌሎች አመራሮችንም ቀስ በቀስ ተጠያቂ እናደርጋለን፡፡ ብቃት ያላቸው አመራሮችንና ባለሙያዎችን በመመደብ ለውጥ ለማምጣት እየሠራን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሜቴክ ለሁለት ከተከፈለ በኋላ እስካሁን ያልተፈታው ችግር የሪቬራናኢምፔሪያል ሆቴሎች ውዝግብ ነበር፡፡ ችግሩ አሁን ምን ላይ ይገኛል?

አምባሳደር ሱሌማን፡- ግሩፑ ከመፈጠሩ በፊት ሜቴክ በጣም ብዙ ጥፋት እንደሠራ ነግሬሻለሁ፡፡ ተቋሙ በሕግ የሚመራ አልነበረም ካልኩባቸው ምክንያቶች አንዱ የሆቴሎች ግዥ ነው፡፡ የኢምፔሪያል ሆቴል ግዥ በሜቴክ በኩል ተፈጽሟል፡፡ ሜቴክ ግዥውን የፈጸመው ከሆቴሉ ባለቤት ሳይሆን ከደላላ ነበር፡፡ የሆቴሉ ባለቤት ስሙን ሳያዘዋውር ለደላለው ቢሸጠውም፣ ደላላው መሀል ላይ ኮሚሽን ለማግኘት ስም ሳይዘዋወር ለሜቴክ ሸጦታል፡፡ በወቅቱ የነበሩት የሜቴክ ኃላፊዎች በስማቸው ላልዞረ ቤት ስድስት ሚሊዮን ዶላር አየር ላይ ከፍለው ገዝተው ነበር፡፡ የአገር ውስጥ ማንኛውም ግዥ በውጭ ምንዛሪ ሆኖም አያውቅም፡፡ የባለቤትነት ማረጋገጫ ሳይወስዱ የሆቴል ርክክብ ተደረገ፡፡ ሆቴሉ በግሩፑ ሥር ቢሆንም ይዞታው በቀድሞ ባለቤቱ ነው፡፡ እስካሁን በእንጥልጥል ቀርቶ በሕግ ሕደት ላይ ይገኛል፡፡ ጉዳዩ በጣም ውስብስብ ስለሆነ የፍትሕ ሚኒስቴር ጣልቃ በመግባት ክትትል እያደረገ ነው፡፡ ከባለቤቱ ጋር በሜቴክ በኩል ምንም ቅራኔ የለም፡፡ ደላላውና የቀድሞ የሜቴክ ኃላፊዎች በአየር ላይ የበሉት ገንዘብ ስለሆነ ተበልቶ ቀርቷል፡፡ ኢምፔሪያል ሆቴል አሁን በግሩፑ ሥር ቢሆንም የይዞታ ማረጋገጫ ሳያገኝ ቀርቷል፡፡ ሪቬራ ሆቴል የተለያዩ ክርክሮች የነበሩበት ቢሆንም አሁን በስማችን አዙረነዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በሜቴክ ላይ ኦዲት እየተደረገ ነው ተብሎ ነበር፡፡ ኦዲቱ ተሠርቶ ተጠናቀቀ? ምን ያህል ኪሳራ ተገኘ?

አምበሳደር ሱሌማን፡- የሒሳብ ምርመራ አገልግሎት ኮርፖሬሽን ባደረገው የኦዲት ምርመራ 65 ቢሊዮን ብር የት እንደገባ አይታወቅም፡፡ ሜቴክ ከተመሠረተ ከ2002 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 2012 ዓ.ም. ድረስ የነበረውን የሒሳብ ኦዲት ከተሠራ በኋላ ከፍተኛ ኪሳራ ተገኝቷል፡፡ ሪፖርቱን መሠረት በማድረግ መንግሥት እንዲሽረው (Writeoff) ጠይቀን፣ በኦዲቱ የተገኘው የኪሳራ ገንዘብ በዕዳ እንዳይመዘገብ መንግሥት ሽሮታል፡፡ በኦዲት የተገኘው ገንዘብ ምንም ሥራ ላይ ያልዋለ፣ በወቅቱ የነበሩ አመራሮች ተከፋፍለው የወሰዱት በመሆኑ አገሪቱ የአንድ ህዳሴ ግድብ መሥሪያ ብር ተዘርፋለች፡፡ ሜቴክ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ያለው አጠቃላይ ኦዲት እየተደረገ ነው፡፡ ከ2012 ዓ.ም. በኋላ ያለው በሒደት ላይ ነው፡፡ በኦዲት ሪፖርት ግኝት መሠረት ከኪሳራው በተጨማሪ፣ በሀብት ደረጃ የተመዘገቡት እንዲሸጡ በማድረግ ለግሩፑ ገቢ እያደረግን ነው፡፡ ፈፅሞ አስፈላጊነት ያልነበራቸው አምስት ቤቶች አሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ያለ አገልግሎት ባዶዋቸውን ስለሚገኙ ወደ ገንዘብ ለመቀየር በቅርቡ ለሽያጭ እናቀርባቸዋለን፡፡

ሪፖርተር፡- የኤሌክትሪክናኢንዱስትሪ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በኢትዮጵያ በጣም ተፈላጊ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ግሩፑ ይህን ለማሟላት ምን እየሠራ ነው? ቢሾፍቱና ሀይቴክ ቴክኖሎጂ ኪሳራ ውስጥ የገቡት ለምንድነው?

አምባሳደር ሱሌማን፡- ሁለቱ ብቻ ሳይሆኑ ሁሉም ኢንዱስትሪዎች እያመረቱ አይደሉም፡፡ በግብዓት እጥረትና በውጭ ምንዛሪ እጥረት ለሁለት ዓመታት ምንም አልተመረተም፡፡ ሀይቴክ ግብዓት ቢኖረው ሁሉንም የቴክኖሎጂ ውጤቶች ቲቪ፣ ኮምፒዩተር፣ ሞባይል፣ ካሽ ሬጂስተር ይሠራል፡፡ በ2016 ዓ.ም. ያለፉት ሦስት ወራት የተሽከርካሪዎች፣ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ምርቶች፣ የእርሻ መሣሪያዎች፣ የኤሌክትሪክና የኤሌክትሮኒክስ ዋና ዋና ምርቶች፣ ብረታ ብረት፣ መለዋወጫዎች፣ የፋብሪኬሽንና የፕላስቲክ ምርቶች በማምረት 89 ሚሊዮን ብር አግኝተናል፡፡ ከቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ውጪ ሌሎች ስምንት ኢንዱስትሪዎች ትርፋማ ናቸው፡፡ የውጭ ምንዛሪ ችግር ሲቃለል ተፅዕኖውን ሊያቃልሉ የሚችሉ ተግባራትን ማከናወንና ምርታማነት ለማሻሻል እየሠራን ነው፡፡ ከኪሳራ መውጣታችን በራሱ ለእኛ መነሳሻ ነው፡፡ ትልቅ የትራክተር ፋብሪካ የመክፈት ዕቅድ አለን፡፡ በመጀመሪያ ከውጭ በማስገባት ደረጃ በደረጃ ደግሞ የትራክተር ግብዓቶች በአገር ውስጥ መመረት የሚችሉበት መንገድ ይፈጠራል፡፡ የትራክተር ፋብሪካው ሙሉ በሙሉ ሥራ እንዲጀምርና የተወሰኑ ትራክተሮች እንዲመረቱ በዚህ ዓመት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ እየተሠራ ነው፡፡ ዋይቲኦ ከተባለ ኩባንያ 2,000 ትራክተሮችና ትልቅ ፋብሪካ አንድ ላይ እንዲያቀርብልን እየተነጋገርን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የሚያስፈልጋችሁ የውጭ ምንዛሪ መጠን ምን ያህል ነው?

አምባሳደር ሱሌማን፡- ለእኛ 350 ሚሊዮን ዶላር በቂ ነበር፡፡ ለኢንዱስትሪዎቻችን ማስፋፊያ የጠየቅነው የውጭ ምንዛሪ አንድ ትልቅ ሌባ ካለው ገንዘብ ያነሰ ነው፡፡ እኛ ትልቅ ሆኖብን ማምረት አልቻልንም፡፡ መንግሥት ሊረዳን ይፈልጋል፡፡ አቅም እንደሌለው ስለሚታወቅ በሁለት ዓመት የሚከፈል የዱቤ አገልግሎት ተጠቀሙ ቢልም፣ የዱቤ ሽያጭ የሚያደርጉ ድርጅቶችን እየፈለግን ነው፡፡ በዚያ ምክንያት እስካሁን የሰፕላይ ክሬዲት ኤልሲ አልተፈቀደልንም፡፡

ሪፖርተር፡- አስረክቡ የተባላችኋቸው ፕሮጀክቶች ምን ላይ ደረሱ? ህዳሴ ግድብና ያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ ያሉ ንብረቶችን በተመለከተ ምን እየሠራችሁ ነው?

አምባሳደር ሱሌማን፡- የሁለቱንም ጉዳይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተነጋገርን እንገኛለን፡፡ የህዳሴ ግድብን በተመለከተ የእኛ ንብረት የሆነውን ለመውሰድ ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ጋር ንግግር ጀምረናል፡፡ የያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ ከመጀመሪያም የሜቴክ አልነበረም፡፡ ሙሉ በሙሉ ሀብቱ የኬሚካል ኮርፖሬሽን ነው፡፡ ሜቴክ የድለላ ሥራ ለመሥራት ሥራውን ከወሰደ በኋላ፣ የኮንስትራክሽን ሥራውን ለተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን ኩባንያ በመስጠት ምንም ሥራ ሳይሠራ ጥሎ ወጥቶ ነበር፡፡ በመንግሥት ውሳኔ መሠረት ከራሳችን ዕቃዎች በስተቀር ያለውን ሙሉ በሙሉ ባለበት ሁኔታ እንዲያስረከክብ ተደርጓል፣ እኛም አስረክበናል፡፡ የያዩ ማዳበሪያ ፕሮጀክትን በወቅቱ ጉልበት ተጠቅመው የዘረፋ ሥልት እያበጁ ነበር የወሰዱት፡፡ ሜቴክም ከወሰደ በኋላ ለመዝረፍ የሚያመቸውን ኮንትራክተር በማስገባት፣ በውሸት የፍርድ ቤት ውሳኔዎች በመጠቀም ዝርፊያ እንዲፈጸምበት ተደርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- ሜቴክ ያለ ጨረታ ብዙ ፕሮጀክት ይወስድ ነበር፡፡ አሁንም ይህ አሠራር ይቀጥላል?

አምባሳደር ሱሌማን፡- የለም አይቀጥልም፡፡ አንዱ የሪፎርም አካል በሕግ መገዛት ነው፡፡ ጨረታ ከለየለት ሙስና የፀዳ ነው ብለሽ አታስቢ፡፡ እንዲያውም የማጭበርበሪያ መንገድ ነው፡፡ በተቻለ መጠን በአዲሱ አደረጃጀት በጨረታ ግዥ ለመፈጸምና ፕሮጀክት ያለ ጨረታ እንዳይወስድ ይደረጋል፡፡ ጨረታ ከተካሄደ ስርቆት የለም ተብሎ አይታሰብም፡፡ ከጨረታ በስተጀርባ ያሉ ድርድሮችን ለማስቀረት ጥረት እያደረግን ነው፡፡ በዝቅተኛ ዋጋ የጨረታ አሸናፊ ከሚኖር በጥራት የተሻለ እንዲሆን እየተሠራ ነው፡፡ አገራችን ይህንን ፈታኝ ወቅት ታልፈዋለች፡፡ ካለንበት ከባድ ችግር ለመውጣት ከሚረዱ አንዱ ኢኮኖሚ ነው፡፡ ኢኮኖሚን ለማሳደግ የኢንዱስትሪዎች ሚና በጣም ወሳኝ ነው፡፡ ኢንዱስትሪዎች በየራሳቸው የሚጠበቅባቸውን ከተወጡ ኢኮኖሚው ይረጋጋል፡፡ የኢኮኖሚ ቀውስ ያልተረጋጋ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ይፈጥራል፡፡ ኢንዱስትሪው ኢኮኖሚውን የማሳደግ ብቃት ሲኖረው አገር ታድጋለች፡፡ ግሩፑ ይህንን ጊዜ ለማለፍ በተሻለ የሰው ኃይል በመደራጀት ብቁ ሆኖ ይወጣል የሚል ተስፋ አለኝ፡፡ ኢትዮጵያ የጥንት ታሪክ ያላትና ረዥም ዓመት ያስቆጠረች በሚል ብቻ መኖር አያዋጣም፡፡ በአለም ላይ በኢኮኖሚ የመጨረሻዎቹ ደረጃ ላይ ነው የምትገኘው፡፡ አሁንም ድረስ ከውጭ የሚመጣ ዕርዳታ ተመፅዋች ሕዝብ ያለባት አገር ናት፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የዋጋ ንረቱን ለማርገብ የተተገበረው የገንዘብ ፖሊሲ ውጤታማ ነው ለማለት ያስቸግራል›› አቶ አሰግድ ገብረ ማርያም፣ የፋይናንስ ባለሙያና አማካሪ

የዓለም ኢኮኖሚ በተለያዩ ተግዳሮቶች እየተፈተነ ነው፡፡ በተለይ የዋጋ ንረት መጠኑ ይለያይ እንጂ፣ የእያንዳንዱን አገር በር አንኳኩቷል፡፡ መንግሥታት ይህንን ችግር ለማርገብ የተለያዩ የፖሊሲ ዕርምጃዎችን እየወሰዱ...

‹‹በአመራሮቻችን የተነሳ የፓርቲያችን ህልውና ጥያቄ ውስጥ ገብቷል›› አቶ አበባው ደሳለው፣ የአብን አባልና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በአማራ ከተመሠረቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአመዛኙ የተሻለ ሕዝባዊ ድጋፍ ያገኘ፣ ከሦስት ዓመታት በፊት በአገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ተወዳዳሪ...

‹‹የግሉን ዘርፍ በመዋቅር መለያየት የነበሩ ችግሮችን ከማባባስ ውጪ መፍትሔ አያመጣም›› አቶ ሺበሺ ቤተማርያም፣ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ

አቶ ሺበሺ ቤተማርያም በኢኮኖሚክስ፣ በኢኮኖሚ ፖሊሲና ዕቅድ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በማግኘት ለ36 ዓመታት የዘለቀ የሥራ ልምድ እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ በዕቅድና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር፣ በዓለም አቀፍ...