Sunday, February 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የሕልም እንጀራ!

ሰላም! ሰላም! በሰሜን፣ በደቡብ፣ በምሥራቅና በምዕራብ ኢትዮጵያ ውስጥ የምትኖሩና በተለያዩ አገሮች የምትገኙ ወገኖቼ በሙሉ፡፡ ‹‹ሰላም ጤና ይስጥልኝ እንደምን አላችሁ ወገን ዘመዶቼ…›› ይል እንደነበረው ድምፀ መረዋው መልካሙ ተበጀ፣ የእኔም ሰላምታ ባላችሁበት ቦታ ሁሉ ይድረሳችሁ። ይብዛም ይነስም አንፃራዊ ሰላም በመኖሩ እኮ ነው በሳምንት አንዴም ቢሆን ተገናኝተን ወጋችንን የምንሰልቀው። ሰላም ሲጠፋማ እንዴት እንደምንሆን የምናውቀው እኛ ነን፡፡ ለዚህ እኮ ነው ሰላም ለሚባለው ውድ ቃል ትልቅ ሥፍራ መስጠት ያለብን። ‹‹ቃል ይተክላል፣ ቃል ይነቅላል›› እንዲሉ ሰላም ለሚባለው ቃል የምንሰጠው ትኩረት ከበድ ይበል እላለሁ፡፡ ‹‹ቀድሞ ነገር እኛ ኢትዮጵያውያን በእርስ በርስ መስተጋብራችን ውስጥ ችግር ነበረብን እንዴ? ከውጭ በተውሶ የመጡ የፖለቲካ ሽኩቻዎች ውስጣችን ገብተው እስኪያምሱንና አገራችንንም መከራ እስኪከቱ ድረስ እኮ ሰላማችን የተጠበቀ ነበር…›› በማለት አዛውንቱ ባሻዬን ይህችን ከደላላ ጭንቅላቴ የፈለቀች ሐሳብ ባዋያቸው፣ ‹‹ይህ የአገሩ ሰው ሁሉ በየተገኘበት መድረክ በፀፀት የሚያነሳው ሐሳብ እንዴት ይጠፋሃል?›› ብለው ተቀኙብኝ። የእሳቸውን ቅኔ ወርቅና ብር ለመፈልቀቅ ብነሳ የጎጆዬ ቋጠሮ ስላለብኝ ኅብረ ቃሉም ይኼ ነው ሳልል ወደ ድለላ ሽቀላዬ ሮጥኩ። ሽሽት በሉት!

ከሽቀላዬ ፋታ ሳገኝ ደግሞ ተመልሼ እዚያው የአገር ጉዳይ ውስጥ ዘው ከማለት የበለጠ የሚይዘኝ ነገር አላገኝም። ለመሆኑ የአገር ጉዳይ ሲነሳ እነ ‹‹ፖለቲካን በሩቁ›› ሁሉንም ነገር እያጣጣሉብን በአሳቻ መንገድ የሚቀየሱብን ለምንድነው? ‹‹ሳስበው… ሳስበው…›› አለች ማንጠግቦሽ በዝግታ አቦል ቡና እየቀዳች። ‹‹ሳስበው… ሳስበው… ከአገር ጉዳይ ራሳቸውን ራቅ አድርገው በግራ አሳይተው በቀኝ የሚታጠፉብን የግላቸውን ሀብት ለማካባት ስለሚሯሯጡ ሳይሆን አይቀርም። ለምን ብትለኝ እነሱ የአገርን ጉዳይ ‹ፖለቲካና ኮረንቲ› እያሉ እየሸሹ፣ የአገር ሀብትን ለመቦጥቦጥ ግን ማንም አይቀድማቸውም፡፡ ፖለቲከኞቹም ፖለቲካቸውን አትንካ እንጂ አገርን እንደ ጎድን አጥንት ብትግጥ ደንታቸውም አይደለም…›› ስለትለኝ ደነገጥኩ፡፡ ‹‹እንጃ ብቻ ዘንድሮማ የብር ማሽን አስገብተው ሲያትሙ የሚውሉ በዝተው ነው መሰል፣ የአንድ አፓርታማ ቤት ዋጋ እስከ 30 ሚሊዮን ብር መድረሱን ስትሰማ ያሳብዳል…›› ስትለኝ አዕምሮዬን በአገላለጿ ሰቅዛ ያዘችው። እኔም ቆያይቼ ሳስበው ድንጋይ ዳቦ ሲሆን የታየው እዚህች ምድር ላይ ብቻ ይመስለኛል። አንዱ ደላላ ወዳጄ ደግሞ የዘመኑን ባለገንዘቦች የሚገልጽበት መንገድ ግርም ይለኛል፡፡ ‹‹የአሁኖቹማ እንደ ቅጠል ከዛፍ ላይ የሚሸመጥጡ ነው የሚመስሉት…›› ሲለኝ ወጥቶ፣ ወርዶና ላብን ጠብ አድርጎ ማግኘት የኦሪት ዘመን ታሪክ እየመሰለኝ ተቸገርኩ፡፡ እናንተስ!

ታዲያላችሁ በዚህና በመሳሰሉ ጉዳዮች እያደር ጫና እየፈጠረብኝ ከሰዎች ጋር በቀላሉ መግባባት ላይ ተፅዕኖ ፈጠረብኝ። ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹አንተ ምን ሆነው ነው በቀላሉ ከሰዎች ጋር መግባባት ያቃተህ?›› እያለ ይጨቀጭቀኛል። ‹‹በማያግባባ ነገር በቀላሉም ሆነ በከባዱ መግባባት ብሎ ነገር ምንድነው? ኧረ ተውኝ እስኪ። ኢትዮጵያዊ ሲባል የማውቀው አንድም ፀረ ሌብነትና አስመሳይነት መሆኑን ነበር። አሁን ግን እንደምታየው ብዙኃኑ ሕዝብ በየቀኑ ቁልቁል እየተምዘገዘገ፣ ምንነቱና ምንጩ የማይታወቅ ሀብት የሚያካብቱ እንደ አሜባ እየተባዙልህ ነው፡፡ በቀደም ዕለት የሰሞኑ የጉንፋን ወረርሽኝ አስፈርቶኝ ስኒፕ የሚባለውን የቫይረስ መከላከያ ለመግዛት አንድ ፋርማሲ ጎራ አልኩ፡፡ እዚህ ዘመናዊ ፋርማሲ ስገባ የመጀመሪያዬ ስለነበር በያዛቸው መድኃኒቶችና ተጓዳኝ ዕቃዎች ብዛትና በስፋቱ እየተደነቅኩ ፋርማሲስቱን ስኒፕ ስጠኝ አልኩት፡፡ ፋርማሲስቱም ሒሳብ እንድከፍል ወደ ዘመናዊው የገንዘብ መቀበያ አመለከተኝ፡፡ ለአንዲት ‹ስትሪፕ› ስኒፕ 160 ብር ክፈል ስባል ደነገጥኩ፡፡ ካቻምና 20 ብር፣ አምና 40 ብር የነበረው ዘንድሮ እዚህ ደረሰ…›› ብዬው በንዴት ብው ስል ሳቀብኝ፡፡ እኔ ግን ዕንባዬ ነበር የመጣው!

ምሁሩ የባሻዬ ልጅ አስደንጋጩን የኑሮ ውድነት በሁሉም የምግብ ምርቶችና ሌሎች ግብዓቶች ላይ እያደረሰ ያለውን የዋጋ ንረት አስረድቶኝ፣ ለጥቂት ወራት የሥነ ልቦና ሳይንስ ሥልጠና ውሰድ አለና ተመዘገበልኝ። በስተርጅና ተማሪ ቤት ብዬ ሳጉረመርም ባሻዬ ሰምተው፣ ‹‹ምናለበት በሆነልኝና እኔም በተማርኩ። ከሊቅ እስከ ደቂቅ ተምታቶበት ሲያምታታኝ፣ ከራሴ መታረቂያ የሚሆን ዕውቀት በገበየሁ…›› እያሉ አደፋፈሩኝ። ለጊዜው እጄ ላይ የነበረ አንድ ቪላ ነበረና እሱን ጆሮውን እስክል ብቻ ታገስኩ። የቤቱ ባለቤቶች የጠሩትን 60 ሚሊዮን ብር በማግሥቱ አፍርሰው የለም 75 ሚሊዮን ብር ነው ያልንህ ሲሉኝ፣ ከአንድም ሦስት ውድ ደንበኞቼ ‹ደላላ አይወለድብሽ› እያሉ አገሬን ረገሟት። ቱግ ብዬ ሄጄ ባለቤቶቹን ማማከርና ዋጋ ማጣራት ያለ ነው። ‹‹ያልጠራችሁትን ጠራን ብላችሁ ሊገዙ ያሰፈሰፉ ደንበኞቼ እኔ ላይ ፈረዱ…›› ብላቸው፣ ‹‹ጆሮህን ተመርመር፣ መታከሚያ ከሌለህ እናሳክምሃለን…›› ብለው አላገጡብኝ፡፡ አሁን እኔ እንዴት ብዬ ነው ከእነዚህ ሰዎች ጋር በቀላሉ የምግባባው? ገንዘብ ያ ወዳጄ ደላላ እንዳለው ከዛፍ ላይ ቢሸመጠጥ እንጂ፣ እንዴት በአንድ አዳር የ15 ሚሊዮን ብር ልዩነት ይፈጠራል እያልኩ ግራ እንደተጋባሁ ተከዝኩ፡፡ ሲያንሰኝ ነው!

ወሰንኩላችኋ እኔ አንበርብር የምንተስኖት ልጅ። ኑሮና ፖለቲካው (ማለቴ ኑሮና ብልኃቱ) አልሰምር ብሎኝ እንጂ ድሮም እኮ ኮከብ ተማሪ ነበርኩ። ምን ዋጋ አለው? ይህች ዓለም እንኳን ለተራዎቹ ኮከቦች ለአጥቢያዎቹም አትመችም። የቀለም ቀንድ ከመሆናችን በፊት ቀንዳችንን እያለ የሚያስጎነብሰን መከራ የዋዛ አይደለም ጎበዝ። ቢሆንም ሞኝነት አልፎበታል ብዬ ቢረፍድም ሳይሆን ቢመሽም ይነጋል ብዬ፣ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ያስመዘገበኝን የአጭር ጊዜ የሳይኮሎጂ ሥልጠና ጀመርኩ። ‹አጀማመሩን ቻሉበት እንጂ አጨራረሱ ለራሱ ይጨነቃል› ብሏል አሉ ቶማስ ኤዲሰን የሚባል ሳይንቲስት። ልብ አድርጉ የጠቀስኩት ስም ሳይኮሎጂኛ ዘዴ በመጠቀም ሥልጠናዬን ስተገብር ነው። ደግሞ በኋላ ነፍሱ ካረፈች ሰው ጋር እንዳታጣሉኝ። ለማንኛውም እኔም ሲሉ ሰምቼ የፈረንጅ ሳይንቲስት ስም አነሳሁባችሁ እንጂ፣ እኛም እኮ እሳት የላሱ አሰላሳዮች እንደነበሩን መቼም አትስቱትም፡፡ ለማንኛውም የታሪክ ድርሳናትን የማገላበጥ ልምድ ብናካብት በርካታ የታሪክ ማርሽ ቀያሪዎች ነበሩን፡፡ ዋ ጊዜ!

ምን ነበር የምናወራው? አዎ ባሌ ትምህርት ቤት ገባ ብላ ደግሞ ማንጠግቦሽ ምሳ ቋጥራ፣ አዲስ ኮሮጆ ገዝታ፣ አንድ ባለስኩዌርና አራት ባለመስመር ደብተሮች ገዝታ በጀርባ የሚታዘል ቦርሳ ጨምራ አንግተው አለችኝ። ‹‹ምነው ማንጠግቦሽ እንደ ዘመኑ ተማሪዎች ይህንን ሁሉ ተሸክሜ ስሄድ ሰው ምን ይላል? የዘመኑ ተማሪ በየካፌውና በየሬስቶራንቱ ቁርስ፣ ምሳ፣ እራቱን ጥስቅ አርጎ እየበላ እኔ የምሳ ዕቃ ስሸከም የምን ጉድ ነው? ምነው መሳቂያ ባታደርጊኝ?›› ብዬ ተቆጥቼ ባዶ እጄን እየተቆናጠርኩ ወደ መማሪያዬ ሄጄ ከአስተማሪዋ ሃያ ደቂቃ ቀድሜ ክላስ ተገኘሁ። መምህርትና ተማሪዎች ከመምጣታቸው በፊት ግን ከቤት አወጣጤን አስታወስኩና ሆዴ ባባ፡፡ ባለቤቴ ማንጠግቦሽ ውድ ባሏ ትምህርት ቤት መግባቱ አስደስቷት ያንን ሁሉ ድርጅትና ዝግጅት ስታደርግ፣ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት ግን ምን ነክቶት ነው እንደ ዘመኑ ጎረምሳ እንዲያ ያደረገው ብዬ ሳስብ እልህ መሆኑ ገባኝ፡፡ ሰዎች ቪአይፒ ውስጥ አንድ ኪሎ ሥጋ በሦስት ሺሕ ብር እየበሉና በርካታ ሺሕ ብሮች ከፍለው ውስኪ የሚያወራርዱት እየሠሩ ሳይሆን፣ በአቋራጭ ዝርፊያ የመሆኑ ሚስጥር የአዕምሮ ጓዳው ውስጥ እየተግተለተለ መሆኑን ስረዳ ማንጠግቦሽ ዘንድ ደውዬ ከልቤ ይቅርታ ጠየቅኩ፣ ይቅርም ተባልኩ፡፡ ይቅር እንባባል!

አጀማመሩን እንጂ አጨራረሱን አትጨነቁበት ያልኩትን እያስታወሳችሁ ታዲያ። ማለቴ የቶማስ ኤዲሰንን ጥቅስ ማለቴ ነው። እናም የመሀሉን ላጫውታችሁ። መቼም ምቀኛ ከሩቅ አይመጣም አይደል? በሥነ ልቦና ሳይንስ እያሸነፈ ገቢውን ሊያሳድግ እኛን ሊበልጠን ነው ብለው ነው መሰል ደላላ ባልንጀሮቼ አሳልፈው የማይሰጡኝን ሥራ ሁሉ እየደወሉ ይነግሩኝ ጀመር። አርፌ መማር አልቻልኩም። ሳሳድደው የማላገኘው ሽያጭና ኪራይ ሁሉ ተግተልትሎ መጣ። ‹‹ሶሪ ከሥራ ቦታ ነው…›› እያልኩ አስተማሪዋን ጠቅሼ ‹‹መጣሁ፣ በዚያ አድርገው፣ ለእነዚያ አትንገራቸው…›› እያልኩ ክንፍ አውጥቼ እበራለሁ። መቼም የዕውቀት መጥፎ የለውም። ሥልጠናው ከሰጠኝ ዕገዛ አንዱ ዘዴ ፈጣሪነት ነው። ታዲያላችሁ አንዱን ለፋብሪካ የሚሆን ቦታ አጋዝቼው ሳበቃ መልሶ ደውሎ ሌላ ትዕዛዝ ይጨምራል፡፡ አንዱን ጨረስኩ ስል ሌላው ይደረባል፡፡ ኮሚሽኑም በላይ በላዩ እየተጨመረ ነው፡፡ በቀደም ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኑሮ ውድነቱ ምክንያት የገቢ አለማደግ ውጤት ነው ያሉት ትዝ ሲለኝ፣ ገቢያችን እንዲጨምር ደግሞ መንግሥት መሀል ላይ የተዘረጉ መሰናክሎችን ቢያስወግድ እያልኩ ተመኘሁ፡፡ ምኞት አይከለከል!

ያው እንዳልኳችሁ ልብ ገዝቻለሁ አሉ በዘመኑ አኗኗር ዘይቤ፡፡ አንድ ሠፈራችን ውስጥ ጫት ሲያመነዥክና ትምባሆ ሲያቦን የሚውል፣ ነገሩ ሁሉ እንዳሰበው ያልሆነለት ህንዳዊ አለ። እሱን የተወሰነ ኮሚሽን እንደማስብለት ነገርኩትና ያዘዝኩትን ብቻ እንዲፈጽም ጠየቅኩት። እንዴት ተግባባችሁ ስትሉ ሰማሁ ልበል? በአማርኛ ነዋ፡፡ ዘንድሮ እኮ ዕድሜ ለልማት አጋሮቻችን ፍልሰት ቻይናና ህንድ ቤተኛ ሆነው መስሎኝ። እንዴት ያለ ነገር ነው እናንተ፡፡ ኋላ እሺ ሲለኝ የክት የምለው አንድ ወዳጄ ለሠርጉ ከጣሊያን ድረስ ገዝቶ ያመጣልኝን ሱፍ አልብሼ፣ ጥርሱን በከሰል የለ በኮልጌት ልቡ እስኪጠፋ አስፈግፍጌ፣ ከአንድ ቢሮክራሲ ካስቸገረው ባለፋብሪካ ደንበኛዬ ጋር አድርጌ ፈቃድ መጠየቂያ ቢሮ ላኩዋቸው። ‹‹የአገሬ ልጅ የምሠራው ከህንዶች ጋር ነው። እሱ የሚሠራበት ካምፓኒ ዓለም አቀፋዊና ግዙፍ ነው…›› ምናምን ብሎ ቀባጠረ፡፡ ህንዳዊው መንደርተኛዬም ‹‹የስ… የስ…›› አለና በግሩም መስተንግዶ ተፈቀደላቸው። ሙሉ ልብሴን ለማስወለቅ ያየሁትን አበሳ ግን እኔ ነኝ የማውቀው። ግብግብ በሉት!

እንሰነባበት መሰል። ከዚህም ከዚያም ሥራ ተንዛዛ ብያችሁ የለ? ኪሴ በደንብ ዘጭ ብሎ ሲሞላ ደግሞ ትምህርቱ ሰለቸኝ። ምን ሆኜ ነው ከፈጣሪ በቀር አውቆ የሚጨርሰው የሌለን የልቦና ሐሳብ የማጠናው እያልኩ ለማቋረጥ ሰበብ መፈለግ ጀመርኩ። ‹አንድ ቀን› የሚሏት የለችም? የአንዱ መጀመሪያ የሌላው መቋጫ ሆና የምትከሰት? አዎ አንድ ቀን ወጣቷ አስተማሪያችን አያውቁም ይሁን፣ ምን ያመጣሉ ይሁን አላውቅም የሌለ ነገር መቀባጠር ጀመረች። ‹‹ለምሳሌ…›› አለች ከየት እንደተንደረደች ሳናውቅ። ‹‹…ለምሳሌ ወላጆቹ በልጅነቱ ሲፋቱ ያየ ልጅ ያለ ጥርጥር እሱም አግብቶ መፍታቱ አይቀርም…›› ብላ አረፈችው። ‹‹እንዴ… እንዴ… እኛ እኮ በጥናትና ምርምር የታገዘ ሳይንሳዊ ገለጻ እንጂ፣ ከየትም ለሚቃረም ሐተታማ አነቃቂዎቻችን ምን አጎደሉብን?›› ብሎ አንዱ ነገር ጀመረ። ሲከስትባት ነው እንጂ ሰውዬው ከሦስት እንስቶች ጋር አጠገቤ ተቀምጦ ‹ቻት› ሲያደርግ ዓይቼዋለሁ። በእሱ ቤት ያልታየ ነው የመሰለው፡፡ ነገር ግን እኔ አሁን የባህሪ ለውጥ ስላደረግኩ ልቤ ቢዝነስ ላይ እንጂ የሰው ‹ቻት› ላይ ስለሆነ አለፍኩት፡፡ ማለፍ ይሻላል!

ሌላ ምሳሌ ቀጠለች መምህርት። ‹‹የሚያጨሱ ሰዎች በራስ መተማመን የጎደላቸውና ለማንም ለምንም የማይጠቅሙ ዜጎች ናቸው…›› ብላ መነሻና መድረሻ የሌለው ነገር ተናግራ አረፈችው። ይኼኔ አንዱ እጁን ሳያወጣና ሳያስፈቅድ፣ ‹‹የለም መምህርት አንድ ጥያቄ አለኝ። ዓለማችንን የሚመሩ አሉ የተባሉ ሰዎች እኮ በአብዛኛው አጫሾች ናቸው። ቶማስ ጀፈርሰንና ጆርጅ ዋሽንግተን በአሜሪካ የትምባሆ እርሻ ያስፋፉ ናቸው። ደግሞም የአሜሪካ አብዮት ሙሉ ለሙሉ ማለት ይቻላል የተደጎመው ከሲጋራ ሽያጭ በተገኘ ገቢ ነበር…›› ሲላት ከወዲያ ማዶ የፈለግኩት ሰበብ ተገኘና ሁለተኛ ሳልመለስ ቀረሁ። ኋላ የተለመደችዋ ግሮሰሪያችን እኔና ምሁሩ የባሻዬ ልጅ አንድ አንድ ስንል፣ ‹‹የዘንድሮ አስተማሪ እንዲህ ከአመክንዮ ውጪ የባጥ የቆጡን ማስረጃ እያደረገ የሚያስተምር ከሆነ፣ እውነትም ተማሪውንም ትምህርቱንም በአጭሩ እየቀጨው ነው…›› ብለው በምፀት ፈገግ ብሎ፣ ‹‹አስተማሪው የተማሪውን ቦታ ስለያዘው አይመስልህም? ተናጋሪው አድማጭ አድማጩ ለፍላፊ ሆኖ አገር እያቃጠለ ያለው ለዚህ አይመስልህም? አገልጋዩ ተገልጋይ፣ ተገልጋዩ አገልጋይ ስለሆነ አይመስልህም መልካም ሥነ ምግባርና መልካም አስተዳደር የሕልም እንጀራ የሆኑብን?›› ብሎ መልሱን ራሱ መለሰው። መልካም ሰንበት!    

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት