Sunday, February 25, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የቢጂአይ ኢትዮጵያ የፋብሪካ ሠራተኞች የሥራ ማቆም አድማ አደረጉ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በቢጂአይ ኢትዮጵያ ፋብሪካ ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞች፣ ማክሰኞ ኅዳር 18 ቀን 2016 ዓ.ም. ከማለዳ ጀምሮ እስከ አመሻሽ ድረስ የሥራ ማቆም አድማ በማድረግ ተቃውሞ አሰሙ፡፡

ሠራተኞቹ የሥራ አድማ በማድረግ የተቃወሙት ሜክሲኮ አደባባይ ተግባረ ዕድ ኮሌጅ አጠገብ የሚገኘው የቢጂአይ ፋብሪካ ማሽኖችና የተለያዩ ንብረቶች ሰበታ ከተማ በሚገኘው የሜታ ቢራ ፋብሪካ ሊዘዋወሩ ሲሉ የሰራተኞች የካሳ ክፍያ ሳይፈጸም ንብረቶቹ እንዳይወጡ በሚል ምክንያት የተፈጠረ ተቃውሞ እንደሆነ፣ ሪፖርተር ሜክሲኮ አካባቢ በሚገኘው የቢጂአይ ኢትዮጵያ ዋና መሥሪያ ቤት በመገኘት ለመረዳት ችሏል፡፡

ሚያዝያ 12 ቀን 2014 ዓ.ም. ቢጂአይ ኢትዮጵያ የእንግሊዝ ኩባንያ ዲያጆ ንብረት የሆነውን ሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካን መግዛቱና ከኢትዮጵያ የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን ፈቃድ ማግኘቱ ይታወሳል፡፡

ሠራተኞቹ ተቃውሞ ያሰሙት፣ የፋብሪካው ንብረቶች ከዋናው መሥሪያ ቤት ተነቅለው የሚሄዱት በስምምነቱ መሠረት ከድርጅቱ ያለጊዜያቸው በጡረታ ሲሰናበቱ ድርጅቱ ማግኘት ያለባቸውን ክፍያ መፈጸም የነበረበት ቢሆንም፣ ድርጅቱ ክፍያ ካለመፈጸሙም በላይ ድርጅቱ ወደ ሜታ በሚዘዋወርበት ወቅት የስራ ዝውውር አድርገው መሥራት እየቻሉ በግዴታ ጡረታ እንዲወጡ ስለተነገራቸው እንደሆነ ተቃውሞ ሲያሰሙ የነበሩ ሠራተኞች ተናግረዋል፡፡

ድርጅቱ ላለፈው አንድ ዓመት ሠራተኞች በገዛ ፈቃዳቸው ጡረታ (Early Retirement) እንዲወጡ እያደረገ መሆኑን የተናገሩት ሠራተኞቹ፣ የጥቅማ ጥቅም ክፍያው መስተካከል አለበት ብለዋል፡፡

ሰራተኞቹ እንደሚሉት ከሆነ የቢራ ጠርሙስ መሥሪያ ማሽነሪዎች (bottling) በሕገወጥ መንገድ ወደ ራያ ቢራ ፋብሪካ እንዳዘዋወረ በመግለጽ፣ ቢጂአይ ከራያ ቢራ ጋር ባለው የኪራይ ውል ብቻ ውህደት ሳይፈጥሩ ወደ ራያ ቢራ እንዲዘዋወር እንዳደረጉ ሠራተኞቹ ተናግረዋል፡፡

ሠራተኞቹ ከቢጂአይ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሄርቬ ሚልሃድ ጋር ተገናኝተው እስከሚነጋገሩ ድረስ ወደ ሥራ እንደማይመለሱ የገለጹ ቢሆንም፣ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ለጊዜው ተረጋግተው እንዲሠሩ በኢሜይል መልዕክት መላካቸውን ሠራተኞቹ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ሰበታ የሚገኘው የሜታ አቦ ቢራ ሠራተኞች ትናንት ማለዳ የቢጂአይ የፋብሪካ ንብረቶችን በመንቀል ለመውሰድ በመጡበት ወቅት፣ ሠራተኞቹ የጠየቁት ሕጋዊ ጥቅማ ጥቅም ካልተከፈላቸው በስተቀር ምንም ዓይነት ንብረት ከድርጅቱ አይወጣም በማለት ተቃውሞ በማሰማትና ዕገዳ በማድረግ ንብረቶቹ እንዳይወጡ አድርገዋል፡፡

ቢጂአይ ኢትዮጵያ ከ20 ዓመታት በላይ የጊዮርጊስ ቢራ ምርቶችን የሚያመርተው የፋብሪካው ቅጥር ግቢ ጉድጓድ ውስጥ በሚገኝ የከርሰ ምድር ውኃ መሆኑን፣ የውኃው መጠንም በአካባቢው የተለያዩ ሕንፃዎች በመገንባታቸው መቀነሱን፣ በዚህም ምክንያት የፋብሪካውን ንብረቶች የሜታ ቢራ ፋብሪካ ሠራተኞች ለመውሰድ በመጡበት ወቅት የተደረገ ተቃውሞ ነው ሲሉ ሠራተኞቹ ገልጸዋል፡፡

ሪፖርተር የተመለከተው የዋና ሥራ አስፈጻሚው የኢሜይል መልዕክት የተጻፈው ኅዳር 18 ቀን 2016 ዓ.ም. ከጠዋቱ 4፡23 ሰዓት ሲሆን፣ ለሁሉም የዲፓርትመንት ኃላፊዎች ተልኮላቸዋል፡፡

ዋና ሥራ አስፈጻሚው በኢሜይል መልዕክታቸው የየዲፓርትመንት ኃላፊዎች በሥራቸው የሚገኙ ሠራተኞችን ሰብስበው በማነጋገር፣ ለጊዜው ወደ ሥራ እንዲመለሱ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

በተጨማሪም የሥራ ኃላፊዎቹ ለሠራተኞቹ የድርጅቱን የወደፊት ራዕይ በግልጽ እንዲረዱ ማድረግ እንደሚገባቸው፣ ድርጅቱም አሁን ለውጥ እንደሚያስፈልገው እንዲነግሩ አስታውቀዋል፡፡

በመጨረሻም የሥራ ማቆም አድማ እንዲደረግ ባነሳሱ ግለሰቦች ላይ ዕርምጃ እንደሚወሰድ በኢሜይል መልዕክቱ ተገልጿል፡፡

ሪፖርተር ጉዳዩን በተመለከተ ለቢጂአይ ኢትዮጵያ የሕዝብ ግንኙነትና የኮርፖሬት ኃላፊ አቶ በኃይሉ አየለ፣ እንዲሁም ለዋና ሥራ አስፈጻሚው ሄርቬ ሚልሃድ በመደወልና የጽሑፍ መልዕክት በመላክ መረጃ ለማግኘት ቢሞክርም ምላሽ ማግኘት አልተቻለም፡፡

ቢጂአይ ኩባንያ በ53 አገሮች ፋብሪካዎችን በመትከል ቢራና የአልኮል መጠጦችን የሚያመርት ሲሆን፣ በኢትዮጵያም ለ26 ዓመታት በሥራ ላይ ቆይቷል።

ቢጂአይ ኢትዮጵያ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራን ጨምሮ አምስት የቢራ ፋብሪካዎች በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች አሉት። ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ካስትል፣ ፓናሽ፣ ዘቢዳርና ራያ የተባሉ የቢራና የአልኮል ምርቶቹን ለገበያ በማቅረብም ይታወቃል።

ከግማሽ ክፍለ ዘመን በፊት በመንግሥት ባለቤትነት የተመሠረተው ሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካ፣ ወደ ግል ይዞታ ለማዘዋወር የወጣውን ጨረታ ያሸነፈው ዲያጆ የተባለው የእንግሊዝ ኩባንያ እ.ኤ.አ. በ2012 በ225 ሚሊዮን ዶላር ገዝቶት እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ዲያጆ በመክሰሩና በመንግሥት ግብር ዕዳ ምክንያት መቀጠል ባለመቻሉ፣ ቢጂአይ ኢትዮጵያ ሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካን በመግዛት ሚያዝያ 12 ቀን 2014 ዓ.ም. ፋብሪካውን መረከቡ ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች