Sunday, February 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየኪነ ጥበብ ባለሙያዎችን ‹‹ኑልኝ›› ያለው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባህል ማዕከል

የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችን ‹‹ኑልኝ›› ያለው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባህል ማዕከል

ቀን:

ጥበበኞች ተሰባስበው ስለአገራቸው ወግና ባህል በጋራ ተነጋግረውበታል፡፡ ስለቴአትር በስፋት ተምረው አስተምረውበታል፡፡ የብሔር ብሔረሰቦች ቱባ የሙዚቃ ሥራዎች ሳይበረዙ ሳይከለሱ ከነ መዓዛቸው ተከሽነው እንዲቀርቡ በቀድሞ ስሙ የአፄ ኃይለ ሥላሴ የባህል ማዕከል የአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባህል ማዕከል ዘመን የማይሽረው መሠረትን አስቀምጦ አልፏል።

ባህል ማዕከሉ ለድምፃውያን፣ ለዜማ አቀናባሪዎች እንዲሁም ለኦርኬስትራ መመሥረት ምክንያት እንደሆነም ይነገርለታል።

በአዲስ አበባ ባህል ማዕከል ውስጥ የሠዓሊና ገጣሚ ገብረ ክርስቶስ ደስታና ሌሎች በማዕከሉ ያለፉ የታላላቅ ሠዓሊያን የሥዕል ሥራዎች ይገኛሉ ።

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ከ1950ዎቹ ጀምሮ ለሙዚቃ፣ ለሥዕል በአጠቃላይ ለኪነ ጥበብ ሥራዎች ጉልህ ድርሻ አለው። ታዲያ ይህ ታላላቅ የኪነ ጥበብ ፈርጦችን ያፈራው የአዲስ አበባ ባህል ማዕከል   የተቀዛቀዘ የሚመስለውን የኪነ ጥበብ ሥራ እንደገና ለማቀጣጠል ከመድረኩ የራቁ አንጋፋና ወጣት የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችን ‹‹መድረኩ ለእናንተ ክፍት ነው፣ ኑ፣ የግጥም ሥራዎቻችሁን አቅርቡ፣ ሥዕላችሁንም ሳሉ የመድረክ ላይ ሙዚቃዎቻችሁንም አጠናቅሩ፣ ማዕከሉ ለኢትዮጵያ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በሙሉ እስካሁን ከነበረው በበለጠ በሩን ከፍቶ እየጠበቃችሁ ነው›› በማለት ኅዳር 13 ቀን 2016 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ ሰርከስ ማኅበር ጋር በመሆን ታላቅ የኪነ ጥበብ ምሽት አድርጓል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስመጥር እንዲሆን ካደረጉት ተቋማት መካከል ፈር ቀዳጁ የአዲስ አበባ ባህል ማዕከል ነው ሲሉ የተናገሩት የባህል ማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር ተስፋዬ እሸቱ ናቸው።

ባህል ማዕከሉ ለኢትዮጵያ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ የኪነ ጥበብ አድባር በመሆን ያገለገለና እያገለገለ የሚገኝ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፣ በባህል ማዕከሉ ገብቶ ያልዘፈነ፣ ያልጻፈ ያልተወነ የኪነ ጥበብ ባለሙያ መጥቀስ ያስቸግራል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ባህል ማዕከል ‹‹የጋሽ ፀጋዬ ገብረመድህን፣ የጋሽ አባተ መኩሪያ፣ የጋሽ ስብሃት ገብረ እግዚአብሔር፣ የጋሽ ዮሐንስ አድማሱ፣ የጋሽ መንግሥቱ ለማ ቤት ነበር›› በማለት የብዙዎች መፍለቂያ እንደነበር አስታውሰዋል።

‹‹ማዕከሉ ከመቼውም በላይ የራሱን አሻራ ለማሳረፍ ቤቱን ወለል አድርጎ እየጠበቃችሁ ነው ደራሲያን ኑ፣ ድርሰታችሁን አቅርቡ፣ ፀሐፊያንም ፃፉ፣ አዘጋጆችም ቴአትራችሁን አዘጋጁ፣ መለማመጃ አጥታችሁ በየቦታው ያላችሁ የኪነ ጥበብ አፍቃሪያንና አማተር ተዋንያን እባካችሁ ኑ ማዕከሉ ከመቼውም በላይ ክፍት ነው›› በማለት ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

ዛሬ ረቡዕ 19 ቀን 2016 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ ባለው ፕሮግራም በየሳምንቱ የሚቀርበው መደበኛ የኪነ ጥበብ ምሽት በደማቅ ሁኔታ እንደሚጀምር ተናግረው፣ የኪነ ጥበብ አፍቃሪዎች እንዲገኙ ጋብዘዋል። 

በየሳምንቱ ማክሰኞ፣ ሐሙስና ቅዳሜ ፊልምና ልዩ ልዩ የኪነ ጥበብ ሥራዎች የሚታዩ ሲሆን፣ በየወሩ ደግሞ በታዩ ፊልሞች ላይ ውይይትና አስተያየት ይደረግባቸዋል።

በየሳምንቱ አንጋፋ የኪነ ጥበብ ሰዎች እንደሚጋብዙ፣ ‹‹የአንድ ግጥም የአንድ ወግ እንግዳ›› በሚል አርቲስቶች ሥራቸውን እንደሚያቀርቡ በዛሬው ዕለትም ‹‹የአንድ ግጥም የአንድ ወግ እንግዳ›› በሚለው የተጋበዘችው አርቲስት ገነት ንጋቱ እንደሆነች ተስፋዬ (ረዳት ፕሮፌሰር) ገልጸዋል፡፡

 በሌላ በኩል በቀጣይ ሁለት ወር የመጀመሪያ የተባለ ፌስቲቫል እንደሚካሄድ የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፣ በዚህም ከሰላሳ በላይ ባሉ የዩኒቨርሲቲ ባህል ማዕከላት የሚገኙ ተማሪዎች በአንድነት ሆነው የየራሳቸውን ሥራ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተሰባስበው ያቀርባሉ ብለዋል።

የአዲስ አበባ የተማሪዎችና የአስተዳደር ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አብዱራዝቅ መሃመድ (ዶ/ር) በመድረኩ ባደረጉት ንግግር፣ በኢትዮጵያ መደበኛ የባህል ፖሊሲ ከመርቀቁ በፊት አገራዊ ውክልና ያለው ተቋም እንደሆነ መስክረዋል፡፡

ፈር ያለው የቋንቋ ፖሊሲ ከመታሰቡ በፊት የቋንቋዎች እኩልነት ሲቀነቀንበት የነበረ፣ የሐሳብ እኩልነትና ነፃነት እምብርት ከመሆኑ ባሻገር፣ መልክ ያለው የኪነ ጥበብ እንቅስቃሴ ከመስፋፋቱ በፊት ተፅዕኖ ፈጣሪ ጠቢባን ያፈራ የባህል ማዕከል ነው ብለዋል፡፡

አገራዊ እሴቶችን ከፍ የሚያደርጉ የትውልድን አካዳሚያዊና ሥነ ምግባራዊ ሰብዕና የሚያድሱና የአገር ፍቅር ስሜትን የሚያላብሱ፣ ልዩነትን በወል እሴቶች የሚያስተሳስሩ፣ እያዝናኑ የሚያስተምሩ አገራዊ ግጥሞች፣ መዝሙሮች፣ ሙዚቃዎችና ቴአትሮች ሲቀርብበት ቆይቷል ያሉት አብዱል አዛቅ (ዶ/ር) አሁንም አድማሱን በማስፋት በመላው አገሪቱ ተደራሽ ለመሆን እየሠራ እንደሚገኝ አክለዋል፡፡

በሌላ በኩል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባህል ማዕከልና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሰርከስ ማኅበር ጥምረት መካከል በጋራ መሥራት የሚያስችል ውል የተደረገ ሲሆን፣ በስምምነታቸው ውስጥ 11 ዋና ዋና ነጥቦች መካተታቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሰርከስ ማኅበር ፕሬዚዳንት አርቲስት ተክሉ አሻገር ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያን የሰርከስ ማዕከል ለማድረግ እንዲሁም የተለያዩ ሲምፖዚየሞችንና ፌስቲቫሎችን በማዘጋጀት ለታዳሚያን ማቅረብ የሚሉት ነጥቦችም ይገኙበታል ብለዋል፡፡

በዚሁ የኪነ ጥበብ ምሽት አንጋፋና ስመጥር የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የተገኙ ሲሆን፣ የተለያዩ ግጥሞችን አቅርበዋል፡፡

ከዚህ ባሻገር በተለያዩ አገሮች እየዞሩ አገራቸውን በሰርከስ የሚያስተዋውቁ ወጣቶች ልዩ ልዩ ትርዒቶችን ያሳዩ ሲሆን፣ በቀጣይም ከአዲስ አበባ የባህል ማዕከል ጋር በመሆን የተለያዩ ሥራዎቻቸውን እንደሚያቀርቡ ተነግሯል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...