Monday, February 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ባዶ ምኞት!

የዛሬው ጉዞ ከፒያሳ ወደ ሜክሲኮ ነው። እኛም አታካቹን ሠልፍ ይዘናል፡፡ ወገብ ከሚያጎብጠውና ጠብ የሚል ነገር ከማይገኝለት ልፋታችን ቀጥሎ እጅግ አድካሚ ነገር ሠልፍ ነው። ለሁሉም ነገር መሠለፍ ይሰለቻል፡፡ ጥቂቱ ተርፎት በሀብት ላይ ሀብት ሲደራርብ ብዙኃኑ የሚላስ የሚቀመስ ሳይኖረው፣ የደላው ምቾት በዝቶበት ሲጨናነቅ መከረኛው ደግሞ በማጣት ሰቀቀን እየተቀጣ ይኖራል። አንዱን ጥጋብ የሚሠራውን አሳጥቶት ሲያወራጨው፣ ሌላውን የሰላም ዕጦት እንቅልፍ ይነሳዋል፡፡ አንዱ ላቡን ጠብ አድርጎ አገር ሲገነባ ሌላው እያፈረሰ፣ ቀንና ሌሊት እረፍትና እንቅልፍ አጥቶ ኑሮን ለማቃለል የሚለፋው ሳያልፍለት፣ ከሰማይ መና የሚወርድለት ይመስል ሌላው ያለ ምንም ድካም የሀብት ኮረብታ ላይ ሲከመር ሕይወት ጣዕም እያጣች መኖር ያስጠላል፡፡ በንፋስ አመጣሽ ሀብት ዘመናዊ መኪና የሚነዱ ጥቂቶች ሲንቀባረሩ፣ ብዙኃኑ ለፍቶ አዳሪ ግን ታክሲ ማግኘት መከራ ሆኖበት ሠልፍ ላይ ሆኖ ዕድሉን ይረግማል፡፡ የሕይወት ትርጉሙ እየገባን አይደለም የሚሉ መበርከታቸው ይህንን እውነት ይገልጻል፡፡ ማስተባበል አይቻልም!

ለአገር ማሰብ ትቶ ለቡድናዊ የበላይነት ብቻ የሚሮጠውን ከጎዳናው ላይ ቆመው ሲያዩት ያሳቅቃል። ምንም ባልበደለ፣ ከፍጥረቱ በድህነት የሚማቅቀውን ዓይተን ሳንጨርስ፣ አስተዋጽኦ ሳይኖረው ንዋይ ተርፎት በድሎት የሚንፈላሰሰውን ስናይ ጉድ ማለት ብቻ ነው፡፡ ማጣትና ማግኘት የጎዳናው ነባር ታሪክ ተናጋሪዎች ናቸው። ከዚህ ሁሉ በላይ ስሜት የሚያደማ ሀቅ ቢኖር ልጅነት ሲገረጅፍ፣ አበባነት ሲጠወልግ ማየት ነው። ይኼም ቢሆን የራሱ የሆነ ፖለቲካዊ ማብራሪያ አያጣም። ማብራሪያው ሁሉ የፖለቲካ አጥር የሚታከክ ነው። የማጣትም ሆነ የማግኘት፣ የደስታና የሐዘን ስሜቶች ሳይቀሩ ሁሉም መነሻቸው ከዚያ ፖለቲካ አጥር ሥር ነው። አገዛዝ ሲያደቃት በኖረ አገር ጥያቄዎች ሁሉ የፖለቲካ መሆናቸው ምን ይገርማል? ‹‹ጥያቄዎቻችን ከመበርከታቸው የተነሳ ማን ይሆን የሚመልሳቸው?›› የሚል ድምፅ ይሰማል፡፡ ‹‹አገር ለማፍረስ ጦርነት ከመቀስቀስ ይልቅ፣ ዕድገት ላይ ቢተኮር እኮ መልሱ አይቸግርም…›› የሚል ሌላ ድምፅ ይከተላል፡፡ እንዲህ እያልን አንዱ ሌላውን ማብረድ ቢለማመድ መልካም ነው!  

‹‹ታዲያስ እንደ እሱ ያለው ቁምነገር ላይ ሚዛን የሚደፋ ድጋፍ ቢኖረንማ ስንት ነገር አስተካክለን ነበር እስካሁን። ምን ዋጋ አለው ስንት ሥራ እያለ ጥጋብ የነፋቸው እኛ ከሌለንበት ተያይዘን ካልጠፋን ይላሉ እንጂ። በሕዝብ ስም እየቆመሩ ያለ እኛ ማን አለ ሲሉ ደግሞ ይደንቃሉ…›› እያለ አንድ ጎልማሳ አስተያየቱን ያዋጣል። ወያላው በበኩሉ፣ ‹‹ኧረ ተረጋጉ፣ እነሱ የሚያቅበዘብዛቸው እኮ የሚሠሩት ግፍ ነው…›› ይላል። ‹‹ምን እናድርግ ብለህ ነው? ምድረ ሌባ የራሱን አገር ሲዘርፍ ስለምበሽቅ እኮ ነው። ምስኪን ሕዝባችን ወገናቸው እንዳልሆነ ለምንድነው የሚበዘብዙት?›› ሲል የምሩን መናደዱ ታወቀበት። ‹‹ያለኛ ፖለቲከኛ፣ ባለራዕይ፣ ለሕዝብ አሳቢ፣ ዴሞክራት የለም እያሉን ሲመፃደቁ የነበሩ ሌቦች መጨረሻቸው እስር ቤት ካልሆነ ምኑን ኖርነው…›› ብሎ ወያላው ሒሳብ ለሚሰጡት ሰዎች መልስ ማዘጋጀት ጀመረ። ሌላ ማንም ሰው ሊናገር የዳዳው የለም። ቁጣ ብቻ ነው ፊቱ ላይ የሚታየው። ቁጣ ብቻ!

ታክሲያችን እየፈጠነ ነው። ጨዋታችንም ቀስ በቀስ ሥር ሰደደ። ‹‹ወይ አገራችን ተተኮሰች እኮ እናንተዬ?›› ትላለች ሦስተኛ ወንበር ላይ የተቀመጠች ወጣት። ‹‹በምን?›› ይላታል ከአጠገቧ። ‹‹በደስታ ነዋ፣ ሕዝብ አገር አጥፊዎች ዋጋቸውን ያገኛሉ ብሎ ተስፋ ሲያደርግ ነዋ…›› ትለዋለች በየዋህነት ምን ይጠይቀኛል ዓይነት። ‹‹እኔን የሚገርመኝ የነበረው አገር ለዕድገት ስትነሳሳ እያደቡ የሚያደናቅፏት ከየሥርቻው መፈልፈላቸው ነው። የኢትዮጵያ ዕድገት እኮ ድህነትን ደህና ሰንብት ለማለት እንድንቃረብ ነበር፡፡ ምን ያደርጋል ታዲያ አገር ላይ የተነሱ ምቀኞች አስቸገሩ እንጂ…›› ሲል ከመጨረሻ ወንበር አንዱ፣ ‹‹እኛ በሚረባውም በማይረባውም እየተለካከፍን ነው እንጂ ፊታችንን ብናዞርባቸው ጭብጥ አይሞሉም ነበር፡፡ መቶ ሳይሞሉ መቶ ሚሊዮን ሕዝብ እንዲያምሱ የፈቀድንላቸው እኛ መሆናችንን አንርሳ፡፡ አሁንም መዋጮአችንን አጠናክረን ግድባችንን በቶሎ አጠናቀን ፊታችንን ወደ ሌሎች ታላላቅ ፕሮጀክቶች እናዙር…›› ብሎ ንግግሩን ገታ፡፡ እንዲህ ነው እንጂ!

‹‹ስለመዋጮ ተወራ እንዴ?›› ሲል የቀደመው ተናጋሪ፣ ‹‹ያው ነው ከዓባይ ሌላ ቀሪው የኢትዮጵያ ክፍል የልማት ሥራ የለውም ካላልን በስተቀር ድህነት በምን እንደሚመጣብን እናውቃለን አይደል? በዓለም ላይ ያሰቡትን በተግባር ለማሳየት ጊዜ የሚቸግራቸው ስንት ጀግኖች እኮ ነው ያሉን…›› የምትለው ከሾፌሩ ጀርባ ያለች የቀይ ዳማ ናት። ‹‹ራዕይ ሲበዛማ ጥሩ ነው። ራዕይ አስፈጻሚ ሥራ ፈቶ ነገር ሲያበዛ ግን ችግር ነው…›› ብሎ ሳይጨርሰው ጎልማሳው፣ ‹‹ለማንኛውም ለመዋጮ መጨነቅ ድሮ ቀርቷል። ሕዝባችን ገንዘቡ ሥራ ላይ እየዋለ መሆኑን ካወቀ መዋጮውን አጠናክሮ ይቀጥላል…›› ይላል አጠገቧ የተቀመጠ ተሳፋሪ። ‹‹ወይ አገሬ ምንም እንኳ በአንድ ወቅት የሌቦች ሠራዊት ቢዘርፋትም፣ ከሌላው የአፍሪካ አገር ጋር ስትተያይ አሁን በጣም የተሻለ ደረጃ ላይ ናት፡፡ ቢያንስ እዚህ አንድ ፕሮጀክት የወጣበትና የተሠራው ላይመጣጠን ይችል ይሆናል፡፡ ሌላው ዘንድ እኮ ጭራሽ በጀቱ የት እንደገባ ይታወቃል? ናይጄሪያና ኬንያን ያላየ ብዙ ያወራል…›› እያለ ያጉተመትማል፡፡ ‹‹እዚህ የናይጄሪያ ልምድ ሰተት ብሎ እየገባ ምን ያወራል…››ብሎ አንዱ ከጥግ በኩል ተነጫነጨ፡፡ ከማይረቡ ፖለቲከኞች ሕዝባችን ውስጥ ያሉ ምልከታዎች ከበድ ያለ ዋጋ አላቸው፡፡ ዋናው ቁምነገር ጠጋ ብሎ ማዳመጥ ነው፡፡ ይሰማል አይደል!

‹‹በዕድገታችን ላይ ስለተነሱ ምቀኞች ያነሳኸው እውነት ቢሆንም፣ መጀመርያ የራስን ኃላፊነት መወጣት ተገቢ ነው። እውነት እንዲህ ለአገራችን በአንድ ድምፅ መነጋገር ብንጀምር የማንም አገር አጥፊ መቀለጃ አንሆንም ነበር…›› የሚለው ደግሞ ወፍራም ኮስታራ ተሳፋሪ ነው። ማንም መልስ አልሰጠም። አጠገቤ የተቀመጠች መጠጥ ያለች ወይዘሮ፣ ‹‹ክፉ ልምድ…›› ትላለች በሹክሹክታ። ‹‹ሰው በገዛ አገሩ ላይ ጠላት ይሆናል? ግብር ማጭበርበር፣ ኮንትሮባንድ መነገድ፣ ጉቦ መቀባበል፣ በጀት መዝረፍ፣ ስንቱን ላንሳው? በውሸት ትርክት አገር ላይ ማሴር፣ ከሰው እንዳልተወለድን ሰብዓዊ ፍጡራንን መግደልና መዝረፍ እንዴት ያለ እርግማን ነው እናንተዬ?›› ስትል ምሬቷ ጣራ የነካ ይመስል ነበር፡፡ ምሬትማ የሰፊው ሕዝብ ቀለብ ከሆነ ቆየ እኮ!

ወደ መዳረሻችን እየተቃረብን ነው። ሜክሲኮ ቅልጥ ያለ ደማቅ የጎዳና ገበያ ከሆነ ቆይቷል። ‹‹የሚገርመኝ ትናንት የነበረውን ዛሬ ሳጣው፣ ዛሬ ያጣሁትን ነገ ሳገኘው ነው…›› ትላለች አንዷ ወይዘሮ። ‹‹እውነት ለመናገር ይህ ሁሉ የኮንትሮባንድ ልባሽ ገበያውን የሞላው በእነ አጅሬ ሌቦች ምክንያት ነው…›› ብሎ ከመጨረሱ ጎልማሳው፣ ‹‹እውነት ነው፣ አገራችንን የሳልቫጅ ቦንዳ ማራገፊያ አድርገው እኛንም የደሃ ደሃ አደረጉን…›› ብሎ ከመጨረሻ ወንበር አንድ ወጣት ሲናገር ይሰማል። በተስፋ ተሰንቆ የነበረው ጨዋታ በአንድ ጊዜ ተቀይሮ ምሬትና ትችት ለማድመጥ ደቂቃ አልፈጀም። አንዱ ስልኩ እንቢ ብሎት ‘ኔትወርኩ’ን እያማረረ ቴሌን ያሳጣል። አንዷ ደግሞ፣ ‹‹አሁን ከዚህ ምን ያህል ሰዓት ይሆን የታክሲ ወረፋ ጠብቄ ተሳፍሬ የምሄደው?›› እያለች ስትጨነቅ ይሰማል። ጭንቅ ጥብብ!

ወዲያው ከወደ ጋቢና፣ ‹‹በየወሩ የቤት ኪራይ የሚጨምሩብን ለምን ይሆን?›› እያለ በስልክ ያጮሃል። ተንፍሰን ሳንጨርስ የሚያካልበን የችግር አባዜ ጉልበቱን አድሶ በየአቅጣጫው ተሳፋሪውን ሲወጥረው፣ ‹እንዲያው ምን ተሻለን እናንተ? መፍትሔው ሁሉ ጊዜያዊ ነው፣ እሱንም የሚሰማ ሲገኝ። ኧረ እንዴት ልንኖር ይሆን ወደፊት?› ይባባሉ ጀመር ተሳፋሪዎች። ታክሲያችን ጠርዝ ይዛ ስትቆምና ወያላው፣ ‹‹መጨረሻ!›› ብሎ ሲያወርደን አንዲት ወጣት ተሳፋሪ፣ ‹‹አሁንማ የችግሩን ዋነኛ ሰንኮፍ ነቃቅለን ጥለን አገራችንን የሰላም፣ የደስታና የፍቅር ማድረጊያ ጊዜያችን ተቃርቧል፡፡ የክፋት ዘመንን ልንሻገር ነው…›› ስትል ትሰማለች። ‹‹ምኞትሽ መልካም ቢሆንም እንዲህ በቀላሉ ሰላምና ደስታ የምናገኝ አይመስልም፡፡ ከምኞት በተጨማሪ ልፋትና ድካም ይጠይቃል፡፡ ባዶ ምኞት ፋይዳ የለውም…›› እያለ ተለያየን፡፡ መልካም ጉዞ! 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት