Monday, February 26, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች ውስጥ ሲሚንቶ በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው፡፡ ምርቱን በተገቢው መንገድ ለገበያ ከማቅረብ ጋር የተያያዙ በርካታ ችግሮች ገበያው ላይ ሲፈጠሩ የነበሩት ጫናዎች በራሱ ለሲሚንቶ እጥረት እንደ አንድ ምክንያት የሚወሰድ ነው፡፡ ዋነኛ ችግሩ ግን በአገሪቱ የሚመረተው ሲሚንቶ ከፍላጎቱ ጋር ሊጣጣም ሳይችል መቅረቱ ነው፡፡ ይህም  አጠቃላይ የሲሚንቶ ገበያን ከማበለሻሸቱም በላይ እጅግ በተጋነነ ዋጋ እንዲሸጥ ምክንያት ሆኗል፡፡ ያልተረጋጋው የሲሚንቶ ገበያ ለብዙ ፕሮጀክቶች መስተጓጎልና ወጪ መናር ትልቁን ድርሻ እንደሚይዝ በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎችና ኮንትራክተሮች ይናገራሉ፡፡

የሲሚንቶ ፍላጎትንና አሁን እየተመረተ ያለውን መጠን የሚያመላክቱ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በፍላጎትና በአቅራቦት መካከል ያለው ልዩነት ሰፊ ሆኖ መቀጠሉ ኢኮኖሚው ላይ እያሳደረ ያለው ተፅዕኖ መቀጠሉን ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች አጠቃላይ እያመረቱት ያለው ምርት ከስምንት ሚሊዮን ኩንታል የሚበልጥ አይደለም፡፡ ፍላጎቱ ደግሞ ከዚህ ሁለትና ሦስት እጅ የሚልቅ በመሆኑ ሰፊ የሆነ ልዩነት እንዳለ የሚያመላክት ነው፡፡

የኮንስትራክሽን ዘርፍ ዋነኛ ግብዓት የሆነውን ይህንን ምርት በበቂ ሁኔታ ለማምረት ከባድ ቢሆንም ለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ ይህንን የሲሚንቶ እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የወራት ዕድሜ ብቻ እንደቀረው አሳውቋል፡፡

የኢትዮጵያ የሲሚንቶ ገበያን ከማረጋጋት በላይ አሁን ያለውን የሲሚንቶ አቅርቦት በ50 በመቶ ለማሳደግ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ መድረሱን ያስታወቀው ለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ በኢትዮጵያ ኢስት አፍሪካ ሆልዲንግና በቻይናው ዌስት ኢንተርናሽናል ሆልዲንግ ኩባንያ ጥምረት የተቋቋመ ነው፡፡ ባለፈው እሑድ ኅዳር 16 ቀን 2016 ዓ.ም. እንደተገለጸው ግዙፉ ሲሚንቶ ፋብሪካ አጠቃላይ ግንባታው ተጠናቅቆ ከአራት ወራት በኋላ ሥራ ይጀምራል፡፡ ከአዲስ አበባ ከ150 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን አንሳሮ ወረዳ ለሚ ከተማ ውስጥ በለሚ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ውስጥ የተገነባው ይህ ሲሚንቶ ፋብሪካ ዋነኛ የሥራ የተባለውን የማሽነሪ ተከላ ማጠናቀቁን አስታውቋልና ሥራው የሚጠናቀቀው ቀደም ተይዞለት ከነበረው የጊዜ ገደብ በፊት እንደሚሆን ተገልጿል፡፡  

ከ600 ሚሊዮን ዶላር በላይ በጀት የተያዘለት ግዙፉ የለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካ ወደ ሥራ ሲገባ በዓመት አምስት ሚሊዮን ቶን ሲሚንቶ ማምረት የሚችል ሲሆን፣ ይህ የማምረት አቅሙ ደግሞ በአፍሪካ ትልቁ የሲሚንቶ ፋብሪካ የሚያደርገው መሆኑን የኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ ፕሬዚዳንት አቶ አበባው ታደለ ገልጸዋል፡፡

የዌስት ኢንተርናሽናል ሆልዲንግ ፕሬዚዳንት ሚስተር ዋንግፋይ ፋብሪካውን አቅም በተመለከተ የሰጡት መረጃም ይህንን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ በአፍሪካ በምርት መጠኑ ከፍተኛ የሆነውን ፋብሪካ መገንባት መቻላቸው ለኩባንያቸው ትልቅ ስኬት ስለመሆኑም ጠቅሰዋል፡፡ በአፍሪካ ደረጃ ለሚ ናሽናል የሲሚንቶ ፋብሪካ ሊያመርት የሚችለውን ያህል ሲሚንቶ የሚያመርት አለመኖሩን ሚስተር ዋንግ ተናግረዋል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጡ የተጠየቁት የለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ ፕሮጀክት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አበባየው በቀለ (ኢንጂነር)፣ ፋብሪካው ከአፍሪካ ትልቁ ነው የተባለው ተጨባጭ መረጃ ነው ይላሉ፡፡ የሲሚንቶ ፋብሪካ የሚለካው በቀን በሚመርተው የአሊንከር መጠን ነው፡፡ አሊንከር ዋና የሲሚንቶ ኮምፖናንት ነው፡፡ ስለዚህ የእኛ ሲሚንቶ ፋብሪካ በቀን 10 ሺሕ ቶን አሊንከር የሚያመርት በመሆኑ ይህ የአሊንከር መጠን ወደ ሲሚንቶ ሲቀየር 15 ሺሕ ቶን ሲሚንቶ ወይም 150 ሺሕ ኩንታል ሲሚንቶ በቀን ያመረታል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በአሁኑ ወቅት በዚህን ያህል ደረጃ የሚያመርት ፋብሪካ በአፍሪካ የሌለ በመሆኑ የለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ግዙፉ አፍሪካ ሲሚንቶ ፋብሪካ ያደርገዋል በማለት ፋብሪካው ያለውን የማምረት አቅም ገልጸዋል፡፡

የለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ የምርት መጠን በዚህን ያህል ደረጃ የሚገለጽ በመሆኑም የአገሪቱን የሲሚንቶ ፍላጎት 50 በመቶ እንደሚሸፍን አቶ አበባው ገልጸዋል፡፡ የአገሪቱን የሲሚንቶ ምርት ገበያ በ50 በመቶ ይጨምራል የተባለውም የድሬዳዋ የሚገኘው አዲሱ የናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ ያቀርባል ተብሎ ከሚጠበቀው ሦስት ሚሊዮን ኩንታልና የለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ የሚያመርተው አምስት ኩንታል ጋር ሲደመር በናሽናል ሲሚንቶ በኩል ብቻ 8 ሚሊዮን ኩንታል በዓመት ለገበያ የሚቀርብ በመሆኑ ነው ተብሏል፡፡ 

የለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ በግዝፈቱና በምርት መጠኑ ከፍተኛነት ብቻ ሳይሆን በኢትዮጰያ የግል ዘርፍ እንዲህ ባለ ጥምረት በፍጥነት ተገንብቶ ወደ ሥራ የሚገባ ፕሮጀክት መሆኑም ልዩ ያደርገዋል ተብሏል፡፡

ፕሮጀክቱ በአጭር ጊዜ መጠናቀቅ ያለውን ጠቀሜታ በመረዳት የኮንስትራክሽን ግንባታ ሥራው የተረከበው የቻይና ሲኖማ ኮንስትራክሽን ጋር ውይይት በማድረግ ግንባታው በ15 ወራት እንዲጠናቀቅና በማርች 2024 ፋብሪካውን ወደ ሥራ ለመግባት በሚያስችልበት ፍጥነት እየተሠራ በመሆኑ ለግንባታው የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ መድረስ መቻሉንም አቶ አበባው ገልጸዋል፡፡

የፕሮጀክቱ መጠናቀቅ በኮንስትራክሽን ዘርፉ ላይ የሚያሳርፈው አዎንታዊ ተፅዕኖ ከፍተኛ በመሆኑ በሁሉም ባለድርሻ አካላት የላቀ ግምት የተሰጠው እንደሆነ ያስታወሱት አቶ ብዙአየሁ፣ በአፍሪካ ትልቁ ባለ አንድ መስመር (Signal Line) ሲሚንቶ ፋብሪካ ያደርገዋል ብለዋል፡፡ አጠቃላይ የፋብሪካው ይዘትና ለባሀብቶቹም ሆነ ለአገር ለአዳዲስ ኢንቨስትመንት መስህብ በመሆን የሚረዳ መሆኑንና በአጭር ጊዜና በፍጥነት በመጠናቀቅ ከሚመዝገቡ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ እንደሚሆንም አመልክተዋል፡፡ እንደ አቶ አበባው ገለጻ፣ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት የተስፋ ብርሃን ከመሆኑም በላይ ለአካባቢው የሚሰጠው ሰፊ ዕድገት ለእኛ የላቀ ክብር እንደሚያጎናፅፈን አምናለሁም በማለት የፕሮጀክቱን ጠቀሜታ አብራርተዋል፡፡

‹‹ግንባታው አንድ ብሎ ሥራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ዛሬ አሥራ አንደኛ ወሩን ይዟል፤›› ያሉት የፕሮጀክቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ በበኩላቸው፣ በኢትዮጵያ በዚህን ያህል ፍጥነት የሚያልቅ ፕሮጀክት ካለመኖሩ አንፃር የፕሮጀክቱ ግንባታ ሒደት በምሳሌነት ሊጠቀስ የሚችል መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ፕሮጀክቱትን 15 ወሮች ለማጠናቀቅ አዲስ ፕላን ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ የተገባበትን ዋና ምክንያት ሲያብራሩም፣ ከጥቂት ወራት በፊት ፕሮጅቱን የጎበኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር)፣ ይህንን ፕሮጀክት በ15 ወራት ማጠናቀቅ አለባችሁ በማለት መመርያ በመሰጠቱ ነው፡፡

‹‹እኛም በአሥራ ስምንት ወራት ለማጠናቀቅ የጀመርነውን ሥራ በ15 ወራት ለማጠናቀቅ ዕቅዳችንን ከልሰን በመሥራታችን አሁን ያለበት ደረጃ ላይ መድረስ ተችሏል፤›› ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የሲቪል ሥራውን ሙሉ ለሙሉ በማጠናቀቃቸው ዋና ዋና የሚባሉ የፋብሪካው አካሎቻችን ተከላ በመጠናቀቃቸው፣ በቀሪዎቹ አራት ወራት ውስጥ የማጠናቀቂያ ሥራ አልቆ ለምርቃት እንደሚበቃም እርግጠኛ ናቸው፡፡ ፕሮጀክቶችን እንዲህ ባለ ፍጥነት ማጠናቀቅ ብዙ ትርጉም እንዳለው ያመላከቱት አበባው (ኢንጂነር)፣ በኢትዮጵያ በፋይናንስ እጥረት፣ በማኔጅመንት ችግርንና በተለያዩ ምክንያቶች የፕሮጀክቶች ሥራ የሚዘጉ መሆኑን አስታውሰው፣ ኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ ይህንን ፕሮጀክት ለመተግበር የቻይናውን ኩባንያ በጆይንት ቬንቸር ማስገባቱ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ይህም ዌስት ኢንተርናሽናል ለፋብሪከው ግብዓት የሚሆኑ የውጭ ምንዛሪ የሚጠይቁ ግብዓቶችን ሁሉ በራሱ ወጪ በፍጥነት እየሠራ በመምጣቱ ግንባታውን ሊያፋጥነው ችሏል ብለዋል፡፡

እንዲህ ያሉ ግንባታዎች ሲታሰቡ የውጭ ምንዛሪ የሚቀርቡ የውጭ ኩባንያዎችን ማጣመር ምን ያህል አዋጭ እንደሆነ ይህ ፕሮጅት ምስክር እንደሚሆንም አቶ አበባው (ኢንጂነር) አብራርተዋል፡፡ የፕሮጀክቱ በዚህ ፍጥነት እዚህ ደረጃ ላይ ሊደርስ የቻለበት ሌላው ምክንያት ተብሎ በአቶ አበባው የተጠቀሰው ደግሞ በሚኒስቴር ደረጃ በአገሪቱ ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ የፕሮጀክቶችን ሁኔታ ዕለት በዕለት የሚከታተልና አስፈላጊውን ዕገዛ የሚሰጥ የሚኒስትሮች ኮሚቴ በመንግሥት፣ በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተቋቁሞ እየደገፈን በመሆኑ ነው ይላሉ፡፡

ለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ የተለያዩ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ፕሮጅቱን በመጎብኘት አስፈላጊውን ድጋፍ ለመስጠት በመቻላቸው ለፕሮጀክቱ ፍጥነት አስተዋጽኦ ነበረውም ተብሏል፡፡ የክልሉ መንግሥትም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ድጋፍ መስጠቱ፣  እንዲሁም የአካባቢው ኅብረተሰብና የፀጥታ ኃይሉ ያደረገው ርብርብ ለፕሮጀክቱ ዕውን መሆን ታላቅ አስተዋጽኦ ነበረው ተብሏል፡፡ የለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ ዕውን መሆን የሲሚንቶ ገበያን ከማረጋጋት ሌላ ሌሎች በርካታ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎች እንዳሉትም ተገልጿል፡፡ አበባው (ኢንጂነር) እንደገለጹትም፣ በተለይ የለሚ አካባቢን በብዙ መንገድ የሚለውጥ መሆኑን ተጠቅሷል፡፡ በምሳሌነት ከጠቀሱት መካከል፣ ወደ እዚህ ፋብሪካ የተጠቀሰው 500 እስከ 600 ከባድ ተሽከርካሪዎች በየዕለቱ ምልልስ የሚያደርጉ በመሆኑ ሲሆን፣ ይህ በአካባቢው የንግድ እንቅስቃሴን በከፍተኛ ሁኔታ ሊለውጥ መቻሉ ነው፡፡

ከዚህም ሌላ ፋብሪካው ከ10 ሺሕ በላይ ዜጎችን የሚቀጥር መሆኑም ሌላው ኢኮኖሚዊ ጠቀሜታውን ያሳያል ተብሏል፡፡ በግንባታ ወቅትም ከሦስት ሺሕ በላይ ሠራተኞች ተቀጥረው እየሠሩ ነው፡፡ በዚህ ፕሮጀክት የቻይናውያን ባለሙያዎች ተሳትፎ ከፍተኛ ሲሆን፣ እስካሁን ድረስ 1,200 የሚሆኑ የቻይና ባለሙያዎች በዚህ ፕሮጀክት ላይ ተሳታፊ እንደነበሩ ለማሳወቅ ተችሏል፡፡  

በለሚ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ውስጥ ከሚገነቡ ግዙፍ ኩባንያዎች መካከል የሲሚንቶ ፋብሪካው ትልቁ ነው፡፡ በዚህ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከሲሚንቶ ፋብሪካው ሌላ የተገጣጣሚ ቤቶች ፋብሪካው ማምረት ጀምሯል፡፡ የጂፕሰም ፋብሪካው የሲቪል ሥራው እየተጠናቀቀ ነው፡፡ የአሉሚኒየምና የመስታወት ፋብሪካውም ወደ ግንባታ እንደገባ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ታውቋል፡፡ በዚህ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የሚገነቡት የተለያዩ ኢንዱትሪዎች፣ በአጠቃላይ ከ1.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ የሚጠይቁ ስለመሆኑ መገለጹ አይዘነጋም፡፡ የሲሚንቶ ፋብሪካው እህት ኩባንያ የሚሆነውና በድሬዳዋ ግንባታ ላይ የሚኘው አዲሱ የናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካም ከ350 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ የሚጠይቅ ነው፡፡ የእነዚህ ፋብሪካዎች መጠናቀቅ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቅ እንደሚሆንም ከተደረገው ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ ኩባንያናና ዌስት ኢንተርናሽናል ሆልዲንግ በጆይት ቬንቸር የሚገነባ የለሚ ኢንዱስትሪያል ፓርን በኢትዮጵያ ወገን ዋነኛ ተጨማሪ የሆነው ኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንቶች ላይ በመሳተፍ የሚታወቅ ነው፡፡  ዌስት ኢንተርናሽናል ሆልዲንግ ደግሞ መሠረቱን ሆንግ ኮንላ ያደረገ የቻይና የግል ኩባንያ ሲሆን በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶችን  በማንቀሳቀስ የሚታወቅ ነው፡፡

በተርንኪ ፕሮጀክቱን በመገንባት ላይ የሚገኘው የቻይና መንግሥት የኮንስትራሽን ኩባንያ የሆነው ሲኖማ ደግሞ ከዚህ ፕሮጀክት ሌላ በኢትዮጵያ ውስጥ በተገነቡ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች ውስጥ የተሳተፈ ሲሆን፣ በተመሳሳይ ሥራ በሌሎች አገሮች ውስጥ በመሥራት ላይ የሚገኝ ነው፡፡   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች