Monday, February 26, 2024

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ ነዋሪዋ ወጣት፣ ባለፈው ሳምንት ለሦስት ቀናት መታሰሯን ትናገራለች፡፡ አምስት የሚሆኑ የፀጥታ አባላት የጀበና ቡና የምትሸጥበት ቦታ መጥተው ማክሰኞ አመሻሽ ግድም እንደወሰዷትም ትናገራለች፡፡ በተለምዶ ሦስተኛ ፖሊስ ጣቢያ የሚባለው እስር ቤት እንዳቆዩዋትም ትገልጻለች፡፡

ስልኳን ተቀብለው የመክፈቻ ሚስጥር ኮዷን እንድትሰጣቸው በማድረግ በመልዕክት መላኪያና በማኅበራዊ ሚዲያዎች የምትለዋወጣቸውን መልዕክቶችን ጨምሮ፣ የምትገናኛቸውን ሰዎች ማንነትና አጠቃላይ የስልኳን መረጃዎች እንደበረበሩትም ትናገራለች፡፡

‹‹በታላቁ ሩጫ አንቺና ጓደኞችሽ ተቃውሞ ስታሰሙ ነበር?›› የሚል ተደጋጋሚ ጥያቄ እንደቀረበላትም ገልጻለች፡፡ በተለይ እሷ ጓደኞቿን ሰብስባና አደራጅታ በሩጫው ላይ ለተቃውሞ ማሰማቷን በመግለጽ እንደከሰሷትም ተናግራለች፡፡ ቡና በጀበና አፍልቶ ከመሸጥና በአካባቢው ካሉ ደንበኞቿና የዕድሜ እኩዮቿ ጋር ተግባብቶና ተሳስቆ ከማሳለፍ ባለፈ፣ የከረረ የፖለቲካ ወሬ እንኳ አውርታ እንደማታውቅ ነው ወጣቷ የገለጸችው፡፡ በታላቁ ሩጫ ዝግጅት ላይም ቢሆን እንደ ማንኛውም ሰው በሩጫ ተሳታፊ እንደነበረች ነው የተናገረችው፡፡ እሷ የተለየ ጥፋት መፈጸሟን ባትቀበለውም፣ ይሁን እንጂ በሩጫው ላይ በጭፈራና በዝማሬ ተቃውሞ ካሰሙ ተሳታፊዎች አንዷ ነበርሽበት ተብላ በፀጥታ ኃይሎች መከሰሷን ገልጻለች፡፡

ይህች ወጣት በታላቁ ሩጫ መዘዝ ከታሰሩት አንዷ እንጂ ሌሎች ብዙዎች መያዛቸውን ተናግራለች፡፡ በታላቁ ሩጫ ላይ ተቃውሞ ያሰሙ ናቸው በሚል ከተለያዩ የአዲስ አበባ ሠፈሮች ከተያዙ ወጣቶች ጋር አብራ መታሰሯንም አክላለች፡፡

ከሰሞኑ በታላቁ ሩጫ ላይ የተስተጋቡ የተሳታፊዎች ተቃውሞዎች የማኅበራዊ ትስስር ገጾች መነጋገሪያ ጉዳይ ሆነው ነው የሰነበቱት፡፡ በሩጫው ዕለት ተሳታፊዎች ያሰሟቸው የተቃውሞ መልክ ያላቸው ዝማሬዎችና ጭፈራዎች በቪዲዮ ተቀድተው መሠራጨታቸው የብዙዎችን ትኩረት ስበዋል፡፡

ለመንግሥት የወገኑ አንዳንድ የማኅበራዊ ሚዲያ ጦማሪዎች መንግሥት በታላቁ ሩጫ ላይ ስድብና ትችት ያሰሙ የነበሩ ሰዎችን ይዞ ለሕግ ተጠያቂ እንዲያደርግ ሲቀሰቅሱ ነበር፡፡ በመንግሥት ላይ በተቃውሞ ስም ዘለፋ የፈጸሙ የአዲስ አበባ ወጣቶች ተለቃቅመው መያዝ እንዳለባቸው የጠየቁ የመንግሥት ደጋፊ ነን ያሉ ሰዎች በርካታ ነበሩ፡፡ መንግሥት ይህን ጉትጎታና ግፊት ተከትሎ እንደሆነ ተቃውሞ ያሰሙ ያላቸውን ወገኖችን ማሰሩ ግን አልተረጋገጠም፡፡

ይህን በሚመለከት አስተያየት የተጠየቁት የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ምክትል ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ፣ ‹‹ሩጫው በሰላም መጠናቀቁን ከገለጽን እኮ ቆየን፤›› ሲሉ ነበር ምላሽ የሰጡት፡፡

በሩጫው ላይ ‹‹ፋኖዎች እየመጡ ነው›› የሚለውን መልዕክት አንዳንዶች በጭፈራና በዝማሬ ማስተላለፋቸው፣ በመንግሥት ወገንና በደጋፊዎቹ የተወደደ አይመስልም፡፡ ብዙ ተከታይ ያላቸው የማኅበራዊ ገጽ ጦማሪያን ‹‹እነዚህን ወጣቶች አስሮ መግረፍ ነው፤›› የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በአንድ ወቅት በኢትዮጵያ ታሪክ ‹‹ለመጀመርያ ጊዜ ዴሞክራሲን የማይፈራ መንግሥት ሥልጣን ይዟል፤›› ብለው በመናገር የሚታወሱት አንጋፋው የኦሮሞ ፖለቲከኛ አቶ ሌንጮ ለታ ከሰሞኑ ግን፣ ‹‹የአዲስ አበባ ሕዝብ የአማራ ፋኖ ነፃ ያወጣናል ብሎ ተስፋ የሚያደርግ ነው፤›› ሲሉ በሩጫው መድረክ ላይ የታየውን የተቃውሞ ትዕይንት ተቃውመውታል፡፡

መንግሥት በይፋ በሩጫው ላይ የታየውን ተቃውሞ ሲያወግዝ አልታየም፡፡ ተቃውሞ ባሰሙ ሰዎች ላይ ዕርምጃ መውሰዱንም አልገለጸም፡፡ ይሁን እንጂ ደጋፊዎቹ ተቃውመዋል በተባሉ ሰዎች ላይ ዕርምጃ እንዲወስድ ሰፊ ጉትጎታ ነበር ሲያደርጉ የታዩት፡፡

ይህ ሁኔታ ደግሞ በኢትዮጵያ ያለውን የመቃወምና የመደገፍ ነፃነት ሁኔታ ጥያቄ እንዲነሳበት እያደረገ ይገኛል፡፡ በሌሎች አገሮች በየስታዲየሞቹና በየስፖርት ማዘውተሪያዎች ከአገራዊ ጉዳዮች እስከ ዓለም አቀፍ አጀንዳዎች የተቃውሞ ድምፅ ሲስተጋባባቸው መታየቱ የተለመደ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዓረብ አገሮች ስታዲየሞች የፍልስጤም ጉዳይ ጭምር ተቃውሞ ሲስተጋባበት እንደሚታይ የሚጠቅሱ አንዳንድ ወገኖች፣ በኢትዮጵያም በታላቁ ሩጫ መድረክ ላይ ተቃውሞ ቢሰማ ኃጢያቱ ምንድነው ሲሉ ይናገራሉ፡፡

የሕግ ባለሙያው አቶ አበባው አበበ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በየትም ቢሆን ሰዎች በአንድ ላይ በተሰባሰቡ ጊዜ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ የሰብዓዊ መብት ወይም የዴሞክራሲ ጥያቄ ይዘት ያላቸው ማስተጋባታቸው የተለመደ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ‹‹እኛ አገር እንደ እንግዳ ነገር ጉዳዩ ቢቆጠርም ይህ በየትም አገር የተለመደ ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹በ1983 የወጣ ሰላማዊ ሠልፍ የማድረግና የፖለቲካ ስብሰባ የማድረግ አዋጅ አለ፡፡ የሰዎቹን ዓላማን ከዚህ አዋጅ አንፃር እንየው፡፡ የዝግጅቱ ማለትም የታላቁ ሩጫ ዓላማ ስፖርታዊና አገራዊ ገጽታን መገንቢያ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ሰዎች እንደ ኮምፒዩተር ለአንድ ዓይነት አገልግሎት ተብለን የተገነባን ሳንሆን፣ የተለያየ አመለካከት ይዘን የተፈጠርን መሆናችን ሊረሳ አይገባም፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ አሁን በቀውስ ውስጥ ነው ያለችው፡፡ በተለያዩ ጦርነት በሚካሄድባቸው አካባቢዎች ጋር ካሉ ሰዎች ጋር ቁርኝት ወይም ትስስር ያላቸው ሰዎችም በዚህ ዝግጅት ላይ እንደሚሳተፉ መረሳት የለበትም፡፡ በዚህ አጋጣሚ እነዚህ ሰዎች ጦርነቱን ባለመደገፍ፣ ጦርነቱን በማነወር ሐሳባቸውን ከመግለጽ በተጨማሪ አሸናፊና ተሸናፊ እንዳለ አድርገው የመፎከር ዓይነት ስሜት ቢያንፀባርቁ የሚጠበቅ ነው፤›› በማለት የሕግ ባለሙያው አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

በዚህ የተነሳ የሕግ ጥሰት ፈጽማችኋል ተብለው ቢጠረጠሩ ምንም ኃጢያት እንደሌለውና ሕግን እንደ መጣስም እንደማይቆጠር የሚናገሩት አቶ አበባው፣ አንድ ሰው በሕግ ወንጀለኝነቱ እስካልተረጋገጠ ድረስ ወንጀለኛ ሊባል እንደማይችል ሕጉ እንደሚያደርግ ነው የጠቀሱት፡፡

‹‹ሆኖም የጥቆማ ሥርዓታችን፣ ተጠርጣሪን የምንለይበት አካሄዳችን፣ ወደ ሕግ አግባብ የምናመጣበት ሁኔታና ለፍርድ የምናቀርብበት ሒደት ሕግን የተከተለ ሳይሆን የግለሰቦችን አመለካከት ማዕከል ያደረገ አንዳንዴም ቂም በቀልን መሠረት ያደረገ ሲሆን ይታያል፤›› የሚሉት የሕግ ባለሙያው ከዚህ ቀደም እንደነበረው የፖለቲካ ቀውሶችን ተንተርሶ ትግሬ፣ አማራ፣ ኦሮሞ ወይም የሌላ ወገን ወንጀለኛ ነው ወደ የሚል የጅምላ ፍረጃ ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

የዛሬ አምስት ዓመት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ለውጥ መምጣቱን ተከትሎ፣ ኢትዮጵያ በዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብቶች አያያዝ በርካታ መሻሻሎችን ማሳየቱ በዓለም ዙሪያ አድናቆትን አትርፎ እንደነበር ይታወሳል፡፡

በጊዜው ሚዲያዎች በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ መፈቀዱ፣ ጋዜጠኞችና ማኅበራዊ አንቂዎች፣ እንዲሁም የሲቪል ማኅበራት በነፃነት ይንቀሳቀሱ መባሉ በአገሪቱ አዲስ የነፃነት ተስፋ ያሳደረ ነበር፡፡ በውጭ የቆዩ፣ በሽብር የተከሰሱና ፀረ ልማታዊ ዴሞክራሲ ተብለው ሲወገዙ የቆዩ ኃይሎች ሰላማዊ በሆነ መንገድ በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ መፈቀዱ ከረዥም ጊዜ በኋላ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ተስፋ ደግሞ እንዲያብብ ያደረገ አጋጣሚ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ ይህ በዴሞክራሲና በሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ላይ የታየው መሻሻል በሒደት እየከሰመ መምጣቱ ይነገራል፡፡ በአገሪቱ እየተፈጠሩ ያሉ ተከታታይ ግጭቶች ለይዞታው መባባስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ይነገራል፡፡ በጊዜ ሒደት መንግሥት ወደ ሥልጣን ሲመጣ የነበረው ተቃውሞን የመታገስ ሆደ ሰፊነት መቀነሱም ሌላኛው መሠረታዊ ችግር መሆኑ ይነገራል፡፡

ከታላቁ ሩጫ ጋር በተያያዘ ተቃውሞ ያነሱ ሰዎች አንዳንዶቹ የዩቲዩብ ገበያን ዓላማ አድርገው ትኩረት የሚስብ እንቅስቃሴ ለመፍጠር በሚል ተቃውሞ ሊቀሰቅሱ እንደሚችሉ ግምት መኖሩን የሕግ ባለሙያው አቶ አበባው ይናገራሉ፡፡ ዝግጅቱ ተቃውሞ ማሰሚያ መድረክ ሳይሆን ስፖርታዊ ውድድር በመሆኑ በዚህ መድረክ ተቃውሞ ማሰማቱ ተቀባይነት የሚያሳጣ ሊሆን እንደሚችልም ያወሳሉ፡፡

‹‹ሆኖም እነዚህ ሰዎች ተቃውሞ አሰሙ፡፡ አሁን በሕገ መንግሥት አግባብ ስናየው እነዚህ ሰዎች ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን አይደለም ወይ የገለጹት? መንግሥትን ከመቃወም ይልቅ እየደገፉ አጨብጭበውና አሞግሰው ቢሆን ኖሮስ እነዚህ ሰዎች ይታሰሩ ከማለት ይልቅ አይሸለሙም ነበር ወይ?›› ሲሉ በተለያየ መንገድ አጋጣሚው እንዲፈተሽ የጠየቁት አቶ አበባው፣ በዚህ ጉዳይ ላይ በኢትዮጵያ አሻሚ አረዳዶችና አካሄዶች እንደሚስተዋሉ ገልጸዋል፡፡

ተቃውሞ አሰምተዋል ተብለው በተያዙ ሰዎች ላይ የተመሠረቱ ክሶች ከባድ ቅጣት የሚያስወስኑ ከባድ ወንጀሎች እንደሆኑ የሕግ ባለሙያው አክለዋል፡፡ ሕገ መንግሥት በኃይል መናድ፣ እንዲሁም ሽብር ለመፈጸም መንቀሳቀስ የሚሉ ወንጀሎችን ጨምሮ በትንሹ ከ14 ዓመት እሥራት በላይ የሚያስቀጡ የወንጀል ጭብጦች ሲቀርቡ መመልከታቸውን ነው የተናገሩት፡፡ ‹‹እየመጡ ነው ብለዋል፣ ያኛውን ወገን በመደገፍ ጨፍረዋል እንዲሁም አሞግሰዋል፡፡ ነገር ግን ይህ በሽብር ወንጀል ነው መታየት ያለበት ወይስ ሐሳብን በመግለጽ ነፃነት አዋጅ መበየን ያለበት የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ሕገ መንግሥትን በኃይል ከመናድ ጋር ተደምሮ ለምን ይታያል የሚለውም ሌላ ጥያቄ ነው፤›› በማለት የተናገሩት ባለሙያው፣ እሳቸው ያዩዋቸው አንድ ሁለት ደብዳቤዎች ከበድ ከበድ ያሉ የዋስትና መብት የማያሰጡ እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡  

ከሰሞኑ ‹‹አክሰስ ናው›› ባወጣው ሪፖርት ኢትዮጵያን በኢንተርኔት መዝጋትና በሚዲያ ነፃነት መገደብ ከሷታል፡፡ በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. ከ2016 ወዲህ 26 ጊዜ ኢንተርኔት የመዘጋት አጋጣሚ መፈጠሩን የሚገልጸው ሪፖርቱ፣ ይህም ዴሞክራሲያዊ መብቶችን አደጋ ላይ እንደጣለ ያትታል፡፡ አገሪቱ በተደጋጋሚ ኢንተርኔት ወደ መዝጋት የገባችው ግጭቶችን ተከትሎ መሆኑን ሪፖርቱ ያትታል፡፡ የትግራይ ክልል ጦርነት ብቻ ሳይሆን አሁንም የመብረድ አዝማሚያ ያላሳየው የአማራ ክልል ግጭት ለኢንተርኔት መዘጋት በምክንያትነት ተጠቅሰዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2023 ብቻ የኢትዮጵያ መንግሥት ሦስት ጊዜ ያህል ኢንተርኔት መዝጋቱንም ነው ይህ ሪፖርት ያስታወቀው፡፡

መላው የኢንተርኔት አገልግሎትን በተወሰኑ አካባቢዎች ወይም በአገር ደረጃ መዝጋትን መንግሥት በተደጋጋሚ እንደሚከተል ሪፖርቱ ይጠቅሳል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የማኅበራዊ ትስስር ገጽ መተግበሪያዎችን በተናጠል የመዝጋት አማራጭን እንደሚጠቀም ይገልጻል፡፡ እንደ ዩቲዩብ፣ ፌስቡክ፣ ቴሌግራም፣ ዋትስአፕና ቲክቶክ ያሉ የማኅበራዊ ትስስር መተግበሪያዎች በተናጠል ወይም በጅምላ የሚዘጉበት ዕድል በኢትዮጵያ በርካታ መሆኑን ሪፖርቱ ያብራራል፡፡

ከዚህ ጋር አያይዞ በኢትዮጵያ እየተፈጸሙ ናቸው ስላላቸው የመብት ጥሰቶች ሪፖርቱ ይዘረዝራል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ቢሮ በአማራ ክልል ከሐምሌ ጀምሮ በቀጠለው ግጭት 183 ንፁኃን ሰዎች ለሞት መዳረጋቸውን እንዳረጋገጠ ይገልጻል፡፡ በዚሁ ክልል ከ1‚000 በላይ ሰዎች መታሰራቸውንም ይጠቅሳል፡፡

‹‹በእኛ አገር አንዳንዴ የጥበብ ሥራዎች ራሱ እንደ ወንጀል ሲቆጠሩ ይታያል፤›› በማለት የሚናገሩት የሕግ ባለሙያው አቶ አበባው ግን፣ በታላቁ ሩጫ ተቃውሞ ያሰሙ ሰዎች ድርጊት በሕገ መንግሥት ጥሰት፣ በሽብርተኝነት ወይም በአመፅ መቀስቀስ የሚያስጠይቅ ነው ወይ የሚለው በጥልቅ መታየት እንደሚኖርበት አሳስበዋል፡፡

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29 ላይ፣ ‹‹የአመለካከትና ሐሳብን በነፃ የመያዝና የመግለጽ መብት›› ተብሎ የሠፈረውን ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ የአክሰስ ናው ሪፖርት ያነሳዋል፡፡ ይህ ማንኛውም ሰው ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት የመሰለውን አመለካከት የማራመድ፣ አስተያየት የመስጠት፣ እንዲሁም የመቃወም መብት እንዳለው የሚያረጋግጥ ድንጋጌ ዓለም አቀፍ የሕግ መሠረት ያለው ስለመሆኑ ያስገነዝባል፡፡

ኢትዮጵያ በ1966 የተፈረመውን (International Covenant on Civil & Political Rights ICCPR) ‹‹ዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን›› የተባለውን ድንጋጌ መፈረሟና እንደ ራሷ ሕግ አድርጋ መቀበሏን ሪፖርቱ ያወሳል፡፡

ይህ ሕግ የደነገገው፣ ‹‹የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሠልፍ የማድረግ ነፃነትና አቤቱታ የማቅረብ መብት›› ደግሞ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 30 ተካቶ መቅረቡን ያመለክታሉ፡፡ ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች በተጨማሪ በአኅጉራዊው የአፍሪካ የሰዎችና የሕዝቦች መብቶች ቻርተር ላይ የተደነገጉ፣ ከሐሳብና ከተቃውሞ ነፃነት ጋር የተያያዙ ድንጋጌዎችን የተቀበለች አገር መሆኗንም ነው ሪፖርቱ ያሰመረበት፡፡

በኢትዮጵያ ተቃውሞ የማቅረብ ነፃነትም ሆነ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ከሕገ መንግሥቱ ጀምሮ የሕግ ማዕቀፍ ያለው ጉዳይ ቢሆንም፣ ዜጎች ይህን መብታቸውን ለመጠቀም በሚጥሩ ወቅት ግን ብዙ ዓይነት ችግር እንደሚገጥማቸው ነው የተለያዩ ሪፖርቶች የሚጠቁሙት፡፡ ከፖለቲካ ለውጡ ወዲህ እነዚህን መብቶች የመጠቀሙ ነፃነት እየሰፋ እንደሚሄድ ብዙ ቢገመትም፣ በሒደት ክልከላ የበዛበት የመንግሥት ዕርምጃ ነው በቦታው የተተካው ይባላል፡፡

‹‹በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ ዘጠኝ ላይ ኢትዮጵያ ያፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ሕጎች የኢትዮጵያ ሕግ አካል እንደሆኑ ተደንግጓል፡፡ ይህንን ሕገ መንግሥት የሚቃረኑ አዋጆች፣ ደንቦች፣ መመርያዎችም ሆኑ የየትኛውም ባለሥልጣን ውሳኔና አስተያየት ተቃባይነት የለውም ተብሎ ተደንግጓል፡፡ በሕገ መንግሥቱ የተሰጠን ሐሳብን የመግለጽ መብት በመጠቀሙ አንድ ሰው ወንጀለኛ የሚባል ከሆነ በዚህ ድንጋጌ መሠረት ሕገወጥ ነው ማለት ነው፤›› በማለት አቶ አበባው ያስረዳሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -