Sunday, February 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊ የኤችአይቪ/ኤድስ የሥርጭት ምጣኔ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ ተገለጸ

 የኤችአይቪ/ኤድስ የሥርጭት ምጣኔ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ ተገለጸ

ቀን:

ወጣቶችን ጨምሮ ለበሽታው ተጋላጭ ተብለው በተለዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ላይ እየታየ ያለው የኤችአይቪ/ኤድስ የሥርጭት ምጣኔ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ ተነገረ፡፡

የኤችአይቪ/ኤድስ ሥርጭት በቀን ሠራተኞች፣ በሴተኛ አዳሪዎች፣ በረጅም ርቀት አሽከርካሪዎች፣ በአደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚዎች ላይ ያለው የሥርጭት ምጣኔ በጣም ከፍተኛ መሆኑን በጤና ሚኒስቴር የኤችአይቪ/ኤድስና ቫይራል ሄፒታይተስ የመከላከልና የመቆጣጠር መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፈቃዱ ያደታ አስረድተዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ36ኛ እንዲሁም በኢትዮጵያ ለ35ኛ ጊዜ ‹‹የማኅበረሰብ መሪነት ለላቀ ኤችአይቪ መከላከል›› በሚል መሪ ቃል ዓርብ ኅዳር 21 ቀን 2016 ዓ.ም. የኤችአይቪ/ኤድስ ቀን ሲከበር ለጋዜጠኞች ማብራሪያ የሰጡት አቶ ፈቃዱ፣ የኤችአይቪ ሥርጭት በኢትዮጵያ ከአንድ ፐርሰንት በታች ዝቅ ቢልም የሥርጭት ምጣኔው ከክልል ወደ ክልል የተለያየ ነው ብለዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ከፍተኛ ሥርጭት ካለባቸው ክልሎች መካከል ጋምቤላ ክልል የመጀመሪያው ሆኖ 3.69 በመቶ፣ አዲስ አበባ ከተማ 3.17 በመቶ፣ እንዲሁም ሐረሪ ክልልና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ሦስት በመቶ የሥርጭት ምጣኔ እንዳላቸው፣ ሶማሌ ክልል ዝቅተኛ የቫይረስ ሥርጭት መኖሩን ተናግረዋል፡፡

እንደ የሥርጭት መጠኑ የተለያዩ የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራዎች ያስፈልጋሉ ያሉት አቶ ፈቃዱ፣ የቁሳቁስ፣ የሙያ፣ የአጋር ድርጅቶችና የኅብረተሰቡ ድጋፍና ተሳትፎ ካልተጨመረ ከአሁኑ ወቅት በበለጠ ሊጠቁ የሚችሉ ክልሎች እደሚኖሩ አስታውቀዋል፡፡

በግጭት ምክንያት የሚፈናቀሉ ማኅበረሰቦችና የተለያዩ የማኅበራዊና የኢኮኖሚያዊ ችግሮች ያሉባቸው ሰዎች ለበሽታው የበለጠ ተጋላጭ እንደሆኑ ያብራሩት ሥራ አስፈጻሚው፣ የኤችአይቪ/ኤድስ መድኃኒት እጥረት አለ ተብሎ ለተነሳላቸው ጥያቄ፣ ‹‹አገሪቱ የመድኃኒት ማምረት አቅም ላይ ባለመድረሷ ከውጭ ታስገባለች፡፡ በዚህም ግዥ ለመፈጸም የሚወስደውን የተራዘመ ጊዜ ጨምሮ በርካታ ችግሮች ቢኖሩም በጤና ተቋም ደረጃ ምንም ዓይነት እጥረት አላጋጠመም ብለዋል፡፡

ማኅበረሰቡ ኤችአይቪ/ኤድስ የመቆጣጠርና የመከላከል ሥራዎች ላይ የላቀ አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ጥሪያቸውን ያስተላለፉት የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ ናቸው፡፡

የበሽታው ሥርጭት ቀደም ሲል ከነበረበት በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱን የተናገሩት ሚኒስትሯ፣ እ.ኤ.አ. በ2030 የማኅበረሰቡ የጤና ችግር የሆነውን ኤችአይቪ/ኤድስን ሥጋት ወደ የማይሆንበት ደረጃ ለማድረስ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች በመደረግ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በአገር ደረጃ የሥጋት ቀጣና ተብለው የተለዩ አካባቢዎች መኖራቸውን እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ ካሉት 121 ወረዳዎች 48 ወረዳዎች በትኩረት የሚሠራባቸው እንደሆነ የተናገሩት፣ የአዲስ አበባ ከተማ ጤና ቢሮ የኤችአይቪ/ኤድስ ዘርፈ ብዙ ማስተግበሪያ ዳይሬክተር ሲስተር ፈለቀች አንዳርጌ ናቸው፡፡

ለበሽታው ይበልጥ ተጋላች ናቸው ተብለው የተለዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች መኖራቸውን የገለጹት ሲስተር ፈለቀች አፍላ ወጣቶች፣ የትዳር አጋራቸውን የፈቱና የሞቱባቸው፣ እንዲሁም ሴተኛ አዳሪዎች በማለት የተለዩ መሆናቸውንና ለእነዚህ አካባቢዎች ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡

በአጠቃላይ በአገር አቀፍ ደረጃ በሽታው ወረርሽኝ የማይሆንበት ደረጃ መድረሱን ተናግረው፣ ነገር ግን ከቦታ ወደ ቦታ የበሽታው ሥርጭት የተለያየ ነው ብለዋል፡፡ በአዲስ አበባ የሥርጭት ምጣኔው 3.4 በመቶ መሆኑንና ባለፈው አንድ ዓመት ብቻ 489 ሰዎች በበሽታው መያዛቸውን አክለዋል፡፡

የመዘናጋት ሁኔታዎች በሰፊው እየተስተዋሉ ነው ያሉት ሲስተር ፈለቀች፣ ሞት በመቀነሱ ምክንያት ኤችአይቪ/ኤድስ የለም የሚሉ ሰዎች ተበራክተዋል ብለዋል፡፡ በተለይ ከ20 እስከ 25 ዓመት ዕድሜ ክልል ያሉ ወጣቶች ‹‹ሞት የለም›› በማለት የመዘናጋት ሁኔታዎች እያሳዩ ነው ብለው፣ በአጠቃላይ በአገር አቀፍ ደረጃ የኤችአይቪ/ኤድስ የሥርጭት ምጣኔ 0.91 በመቶ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በዚህ ሥሌትም ከ610‚350 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ኤችአይቪ/ኤድስ በደማቸው እንደሚገኝና ከእነዚህ ውስጥም 8‚257 ያህሉ አዲስ የተያዙ፣ እንዲሁም ከ11 ሺሕ በላይ ሰዎች ደግሞ በየዓመቱ በአገር ደረጃ እንደሚሞቱ አረጋግጠዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...