Monday, February 26, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የአስተሳሰብና የአስተዳደር ዘይቤ ለውጥ ያስፈልጋል!

ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝቡን በጋራ አስተሳስረው የሚያኖሩ በጣም በርካታ ማኅበራዊ እሴቶች አሉ፡፡ እነዚህ ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገሩ የኖሩ እሴቶች አገር ለማቆም ትልቅ አስተዋፅኦ ነበራቸው፣ ዛሬም ከሚታሰበው በላይ አላቸው፡፡ በአራቱም ማዕዘናት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከሚኮሩባቸውና ለመጪው ትውልድ ጭምር ከሚያስተላልፏቸው መልካም እሴቶቻቸው መካከል በሰላምና በፍቅር አብሮ መኖር፣ የብሔር ወይም የእምነት ገደብ ሳይኖር ተጋብቶ መዋለድ፣ ችግሮች ሲያጋጥሙ በጋራ መፍትሔ መፈለግ፣ ግጭቶች ሲኖሩ በፍጥነት በሽምግልና መፍታትና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህን ምርጥ እሴቶች ይዞ አገርን ማልማትና ሀብታም ማድረግ ይቻላል፡፡ እንደ ዘመኑ ተጨባጭ ሁኔታም መልካም እሴቶችን በመያዝ ማደግ እንደሚቻለው ሁሉ፣ ለድህነትና ለኋላቀርነት መንስዔ የሆኑ ጎጂ ልማዶችን ተባብሮ ማስወገድም አስፈላጊ ነው፡፡ በተለይ የኢትዮጵያን ሕዝብ አንድነትና አብሮነት የሚሸረሽሩ አላስፈላጊ አስተሳሰቦችንና ድርጊቶችን ከማስወገድ በተጨማሪ፣ ለልማትና ለዕድገት ምንም ጥቅም የሌላቸውን የአስተዳደር ዘይቤዎችን መለወጥም ተገቢ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ሕዝብ እርስ በርስ የሚያጋጩ ስሜቶችንና ድርጊቶችን መክላት ብቻ ሳይሆን፣ ከድህነት ውስጥ እንዳይወጣ የሚታገሉትን ጎጂ ልማዶች ማስወገድ ይገባል፡፡

የኢትዮጵያውያንን መስተጋብር ጠብቀው የቆዩ የጋራ ማኅበራዊ እሴቶች እየተሸረሸሩ፣ በግጭቶች ምክንያት ሞት፣ መፈናቀል፣ የሰብዓዊ ክብር መዋረድ፣ ለአካላዊና ለሥነ ልቦናዊ ጥቃት መጋለጥ፣ ንብረትን ማጣትና የመሳሰሉት አገር አጥፊ ችግሮች በዝተዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት የገነቧቸው ታሪካዊ እሴቶቻቸው እየተጣሱ አገራቸው የጦርነትና የውድመት ምሳሌ እየሆነች ነው፡፡ የኢትዮጵያውያን የእርስ በርስ ፍቅርና መተሳሰብ መልካም መስተጋብር እየተናደ፣ በብሔርና በእምነት ልዩነት ስም በሚደረጉ ቅስቀሳዎች ብዙዎች ተጎድተዋል፡፡ ከአገር በላይ የራሳቸውንና የቡድናቸውን ጥቅምና ፍላጎት ብቻ ለማስከበር በሚቅበዘበዙ ራስ ወዳዶችና ይሉኝታ ቢሶች ምክንያት፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች አልቀው በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተፈናቅለው ሜዳ ላይ ተጥለዋል፡፡ ከጦርነት ጥፋት እንጂ ምንም ዓይነት ጥቅም ወይም ትርፍ አይገኝም ተብለው ሲለመኑ የነበሩ ጀብደኞች፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ያንን ሁሉ ፍጅትና ውድመት ካደረሱ በኋላ ሲፀፀቱና ይቅርታ ሲጠይቁ አልታዩም፡፡ የተጎዱት ግን የጀብደኞች ፍላጎትና ጥቅም የማይመለከታቸው ንፁኃን ዜጎች ናቸው፡፡ ከዚያ ጥፋት ግን ዛሬም ለመማር ፈቃደኝነት አይታይም፡፡

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር ለዘመን ተሻጋሪዎቹና ለዕድሜ ጠገቦቹ መልካም ማኅበራዊ እሴቶች ዋጋ ከመስጠት ይልቅ፣ መያዣና መጨበጫ የሌላቸው የውጭ ልምዶችን በመቃረም ካደረሰው ጉዳት ለመታረም የተዘጋጀ አይመስልም፡፡ ለአገር በቀል ዕውቀቶችና የግጭት አፈታት ሥልቶች ትኩረት መስጠት ስለማይፈለግ፣ ፖለቲከኞችና አጃቢዎቻቸው ልዩነቶቻቸውን በሥርዓት ይዘው መነጋገር እንደ ኤቨረስት ተራራ ይከብዳቸዋል፡፡ ምንም ዓይነት ወጪ ሳይኖርባቸው በመላ አገሪቱ የሚገኙ አገር በቀል የግጭት አፈታት ሥልቶች ማግኘት ስለማይፈልጉ፣ ሕዝቡን ከአንድ ጦርነት ወደ ሌላ ጦርነት በፈረቃ እያሸጋገሩ ሕይወቱን ያሳጡታል፡፡ በሕይወት የተረፈውን ከመኖሪያ ቀዬው አፈናቅለው በረሃብ ይቆሉታል፡፡ የውጭ ታዛቢዎችና ለጋሾች ግራ እስኪገባቸው ድረስ የጥፋት አዙሪቱ ይቀጥላል፡፡ ይህንን እጅግ አስመራሪና አሰልቺ የመከራ ቀንበር ሰብሮ በኢትዮጵያ ምድር ዘለቄታዊ ሰላም ማስፈን የሚቻለው፣ የአስተሳሰብ ለውጥ ሲኖርና ከስህተቶች ለመማር ፈቃደኝነት ሲኖር ነው፡፡ የአስተሳሰብ ለውጥ የሚያስፈልገው ነባሮቹን መልካም እሴቶች ለመናድ ሳይሆን፣ በእነሱ ላይ ተመሥርቶ አገርን ከገባችበት ቀውስ ውስጥ መንጥቆ ለማውጣት ነው፡፡

ከግጭቱና ከውድመቱ ባሻገር አልላቀቅ ብሎ ያስቸገረው ሌላው ችግር ቅጥ ያጣው ድህነት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ‹‹ድህነትን ታሪክ እናደርጋለን›› የሚለው መፈክር በተደጋጋሚ ቢስተጋባም፣ ቃልና ተግባር አልጣጣም ብለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከችጋር ጋር መለያየት አልቻለም፡፡ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ በረከቶች የታደለች ድንቅ አገር ብትሆንም፣ እነዚህን ፀጋዎች አልምቶ ከዘግናኙ ድህነት ዛሬም የማይወጡት አቀበት ሆኗል፡፡ ፅኑው ድህነት በመፈክር ብቻ የሚገላገሉት መሆኑ ስለሚታወቅ መንግሥታት በተቀያየሩ ቁጥር የተስፋ ቃላት ቢገቡም፣ ያለውን ችግር የሚመጥኑ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በባለሙያዎች ዕገዛ አውጥቶ ሥራ ላይ ማዋል ባለመቻሉ በማያዋጡ አሠራሮች ተጠምዶ ጊዜ ማካባን ተለምዷል፡፡ ለዘመኑ የሚመጥን ዕውቀት፣ ክህሎት፣ ልምድና ሥነ ምግባር የተጎናፀፉ አመራሮችንና ባለሙያዎችን መጠቀም ባለመፈለጉ ብቃት አልባዎች አንዲት ጋት ማራመድ አልቻሉም፡፡ በሥራ ላይ ያሉትን ተቋማት በቀለም ከማሰማመር ውጪ በብቁ አመራር፣ ባለሙያ፣ ቴክኖሎጂ፣ የሥራ ዲሲፕሊንና የዘመናዊነት ባህሪ በማላበስ ማደራጀት ስላልተቻለ የበፊት ችግሮች አሁንም በስፋት አሉ፡፡ ከድህነት ዕሳቤ ሳይወጣ እንዴት ዕድገት እንደሚገኝ አይታወቅም፡፡

በቅርቡ ይፋ በተደረገ አንድ ጥናት መሠረት ኢትዮጵያ ውስጥ ስድስት ሚሊዮን ያህል ሕፃናት የቀነጨሩ ናቸው ተብሏል፡፡ የመቀንጨር ዋነኛ ምክንያት ደግሞ የተመጣጠነ ምግብ ዕጦት ነው፡፡ በግጭት፣ በድርቅና በሌሎች ችግሮች ምክንያት በርካታ ሚሊዮኖች አስቸኳይ የዕርዳታ እህል ይለመንላቸዋል፡፡ የገጠርም ሆነ የከተማ ነዋሪዎች በከፍተኛ የዋጋ ንረት ምክንያት የኑሮ ውድነትን መቋቋም ተስኗቸዋል፡፡ በትንሹ ከ60 ሚሊዮን ሔክታር በላይ መታረስ የሚችል መሬት ያላት፣ ክረምት ከበጋ ውኃ የማታጣ፣ ተስማሚ የአየር ጠባዮች የተጎናፀፈች፣ በእንስሳት ሀብት ከአፍሪካ አንደኛ፣ ከ120 ሚሊዮን ሕዝብ ውስጥ 70 በመቶ ያህሉ ወጣትና ታዳጊ የሆነባት፣ በበርካታ ማዕድናት የተሞላች፣ በጣም ብዙ የቱሪዝም መስህቦች የታደለች፣ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለመሸጋገር ዕምቅ አቅም እንዳላት የሚነገርላት፣ በዘመን አፈራሽ ቴክኖሎጂዎች ዕገዛ ድህነትን ለመገላገል ተስፋ ያላት አገር ውስጥ በቀን አንዴ ምግብ ማግኘት እንደ ቋጥኝ እየከበደ ነው፡፡ ነገር ግን ዘመኑን የሚዋጅ አስተሳሰብና የአስተዳደር ዘይቤ ቢዳብር ኖሮ ሕዝብ የድህነት መጫወቻ አይሆንም ነበር፡፡

መንግሥት በተለያዩ መስኮች አንፀባራቂ የሆኑ ውጤቶች እያስመዘገበ እንደሆነ ሲገልጽ ይደመጣል፡፡ ከሕዝብ ጋር ተገናኝቶ ሲነጋገር ደግሞ ተገኙ የተባሉ ውጤቶችና መሬት ላይ ያለው ነገር አይገናኙም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ መንግሥታት በተቀያየሩ ቁጥር የአሁኑ ከበፊቱ እንዴት የተሻለ መሆኑን ለማሳየት የሚያደርገውን ጥረት ያህል፣ ለእውነተኛ ለውጥና ዕድገት ቢተጋ ኖሮ በርካታ ውጤታማ ስኬቶችን ማየት ይቻል ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ጉዳዮች ውስጥ ትልቅ ትኩረት የሚሹ ፅኑ ችግሮች አሉ፡፡ የመጀመሪያው የሰላምና የፀጥታ ጉዳይ ነው፡፡ ሰላም በሌለበት ተረጋግቶ መሥራት፣ መማር፣ መንቀሳቀስም ሆነ መኖር አይቻልም፡፡ የሰላም ጉዳይ በአገር በቀል የግጭት አፈታት ሥልቶች እንዲታይ ዕድል ካልተሰጠው በስተቀር፣ የአገር ህልውና ከድጡ ወደ ማጡ እየሆነ የከፋ ችግር መፈጠሩ አይቀሬ ነው፡፡ ሌላው ዋነኛ ጉዳይ ከድህነት አዘቅት ውስጥ እንዴት ይወጣል የሚለው ጭንቀት ነው፡፡ ሰላምን ከማስፈን ጎን ለጎን ዘመኑን የሚመጥን ኢኮኖሚያዊ መፍትሔ እንዲገኝ፣ የዕውቀትና የክህሎት ባለቤቶችን ደግፉን ማለት የመንግሥት ኃላፊነት ነው፡፡ ከዚህ መራር ድህነት ውስጥ መውጣት ካልተቻለ የመከራው ጦስ ለአገር ህልውና ይተርፋል፡፡ ለዚህም ሲባል የአስተሳሰብና የአስተዳደር ዘይቤ ለውጥ ይደረግ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...

ሕወሓት በትግራይ ጦርነት ወቅት በፌዴራል መንግሥት ተይዘው ከነበሩት አባላቱ መካከል ሁለቱን አሰናበተ

በሕወሓት አባላት ላይ የዓቃቤ ሕግ ምስክር የነበሩት ወ/ሮ ኬሪያ...

የኤሌክትሪክ ኃይል ለታንዛኒያ ለመሸጥ የሚያስችል ስምምነት ለመፈጸም የመንግሥት ውሳኔ እየተጠበቀ ነው

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለታንዛኒያ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ለማከናወን የሚያስችለውን...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሰብዓዊ ቀውሶችን ማስቆም ተቀዳሚ ተግባር ይሁን!

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተወክለው ከመጡ ሰዎች ጋር ያደረጉት ውይይት፣ በአማራ ክልልም ሆነ በሌሎች ሥፍራዎች የሚካሄዱ ግጭቶች ምን...

የበራሪው የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ጄኔራል ለገሠ ተፈራ ቅርሶችን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተረከበ

በቀድሞው የኢትዮጵያ መንግሥት (1967-1983) ዘመን የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ሜዳይ የየካቲት 1966 1ኛ ደረጃ ኒሻን ተሸላሚ የነበሩ የአየር ኃይል ጀት አብራሪው የብርጋዴር ጄኔራል ለገሠ ተፈራ...

የዜጎች በነፃነት የመንቀሳቀስ መብት ዘላቂ መፍትሔ ይበጅለት!

ሰሞኑን በአዲስ አበባ የተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ በተጠናቀቀ ማግሥት፣ መንግሥት ልዩ ትኩረት የሚሹ በርካታ ጉዳዮች እየጠበቁት ነው፡፡ ከእነዚህ በርካታ ጉዳዮች መካከል በዋናነት የሚጠቀሰው...