Monday, February 26, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ብሔራዊ ባንክ በሕጋዊና በጥቁር ገበያ መካከል ያለውን የምንዛሪ ተመን ለማጥበብ ማቀዱ ተሰማ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  •  የኢንሹራንስ ዘርፍን የሚቆጣጠር ኤጀንሲ ሊቋቋም ነው

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሕጋዊው የውጭ ምንዛሪ ተመንና በተለምዶ ጥቁር ገበያ በሚባለው የምንዛሪ ተመን መካከል ያለውን ሰፊ ልዩነት በከፍተኛ ደረጃ ለማጥበብ ማቀዱ ተሰማ።

ብሔራዊ ባንክ በሕጋዊውና በጥቁር ገበያው መካከል ያለውን ሰፊ የውጭ ምንዛሪ ተመን ልዩነት በ95 በመቶ ለማጥበብ ዕቅድ መያዙ የታወቀ ቢሆንም፣ ይህ ዕቅድ መቼና እንዴት እንደሚፈጸም ግን የታወቀ ነገር የለም። 

ባንኩ ዕቅድ መያዙ የተሰማውም ኅዳር 19 ቀን 2016 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የብሔራዊ ባንክን የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድና የመጀመርያ ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም በገመገመበት ወቅት ነው።

ብሔራዊ ባንክ ይህንን ዕቅዱን በቋሚ ኮሚቴው የግምገማ መድረክ ላይ በይፋ ባያቀርብም፣ ለቋሚ ኮሚቴው የቀረበውን ሰነድ የተመለከቱ አንድ የምክር ቤቱ አባል ግን ዕቅዱን ከሪፖርቱ ላይ እንደተመለከቱ ጠቅሰው ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

የምክር ቤቱ አባል፣ ‹‹ብሔራዊ ባንክ በሕጋዊው የውጭ ምንዛሪ ተመንና በጥቁር ገበያው መካከል ያለውን ልዩነት በ95 በመቶ የማቀራረብ ዕቅድ ይዟል። ነገር ግን በአሁኑ ወቅት በሕጋዊው የምንዛሪ ተመንና በጥቁር ገበያው መካከል ያለው ልዩነት እጥፍ ነው። ስለዚህ ልዩነቱን በ95 በመቶ ለማጥበብ የተያዘው ዕቅድ በተጨባጭ የሚቻል ነው ወይ? ወይስ ዲቫሉዌሽን ለማድረግ (የብርን የመግዛት አቅም ለማዳከም) አስባችኋል?›› ሲሉ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

የብሔራዊ ባንክ ዋና ገዥ አቶ ማሞ ምሕረቱ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ እንደየ ሁኔታው እየተመዘኑ የሚወሰዱ ዕርምጃዎች ይኖራሉ እንጂ በዚህ ወቅት ይህ ዕርምጃ ይወሰዳል ብሎ ብሔራዊ ባንክ ሊናገር አይችልም የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ዋና ገዥው አክለውም፣ ‹‹የውጭ ምንዛሪ ጉዳይን በተመለከተ ሁሉን ነገር እዚህ መናገር አልችልም። ብሔራዊ ባንክን በሚመለከቱ አንዳንድ ጉዳዮች ላይ የምናደርገው ውይይት ተገቢ ላልሆነ ስፔኩሌሽን (ግምት) የሚያጋልጥ መሆን የለበትም። ገና ጥናት ያልተደረገበት ጉዳይ ላይ ብንወያይም ትርጉም የለውም” ብለዋል። 

“ዋናው ቁልፍ ነገር ዓላማችን ላይ መወያየት ሊሆን ይገባል” ያሉት የብሔራዊ ባንክ ዋና ገዥ፣ የባንኩ ዋና ዓላማ የተረጋጋ የዋጋ ሁኔታና የተረጋጋ የውጭ ምንዛሪ ሥርዓት እንዲኖር ማስቻል መሆኑን ተናግረዋል። 

በአሁኑ ወቅት ሕጋዊው የውጭ ምንዛሪ ተመን 55.5 ብር የደረሰ ሲሆን፣ በጥቁር ገበያው ግን አንድ ዶላር እስከ 110 ብር እየተመነዘረ ይገኛል።

ብሔራዊ ባንክ ከሚከተላቸው የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥልቶች መካከል ዋነኞቹ የብር የመግዛት አቅምን ማዳክም (Devaluation)፣ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ለባንኮች ማቅረብና ከዚሁ ጎን ለጎን ጥቁር ገበያው ላይ ሕጋዊ ዕርምጃ በመውሰድ እንዳያንሰራራ ማድረግ መሆናቸውን የዘርፉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ወስጥ ያለውን የውጭ ምንዛሪ ችግር ለመፍታት ጥቅም ላይ ሊውል የሚችለው መሠረታዊ አማራጭ ዲቫሉዌሽን እንደሆነ፣ ነገር ግን ይህ ዕርምጃ በሚወሰድበት ወቅት መንግሥት በቂ የውጭ ምንዛሪ ክምችትና አቅርቦት ሊኖረው ይገባል ይላሉ። ከእነዚህ አማራጮች ጎን ለጎንም በጥቁር ገበያው ላይ ሕጋዊ ዕርምጃ ሊወሰድ እንደሚችል ጠቁመዋል።

ብሔራዊ ባንክ ለቋሚ ኮሚቴው ካቀረባቸው የ2016 በጀት ዓመት ዕቅዶቹ መካከል ሌላኛው የኢንሹራንስ ዘርፉን የመከታተልና የመቆጣጠር ሥራ ከብሔራዊ ባንክ በማውጣት ራሱን በቻለ ሌላ ተቋም እንዲመራ ማድረግ ነው።

በዚህም መሠረት የኢንሹራንስ ዘርፉን የሚቆጣጠር ኤጀንሲ ለማቋቋም የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ ተረቆ መጠናቀቁንና ኤጀንሲውን የማዋቀር ሥራ መጀመሩንም ተናግረዋል።

በአጭር ጊዜ ውስጥም ኤጀንሲውን ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት በመቀጠልም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚቀርብ ተናገረዋል።

ከዚህ የሕግ ማዕቀፍ በተጨማሪ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን ማቋቋሚያ አዋጅና የባንክ ሥራ አዋጅ ለማሻሻል የተሰናዱ ረቂቅ አዋጆች በተመሳሳይ ለሚኒስትሮች ምክር ቤትና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚቀርቡ ተናግረዋል።

የተረቀቀው አዋጅ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አንፃራዊ ነፃነት ኖሮት እንዲሠራ ለማስቻል ያለመ ሲሆን፣ የባንክ ሥራ አዋጅን ለማሻሻል የተሰናዳው ረቂቅ አዋጅ ደግሞ በዋናነት የባንክ ዘርፉን ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ለማድረግ የሚያስችሉ ድንጋጌዎችን መያዙን አቶ ማሞ አስረድተዋል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች