Monday, February 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበርካታ የኢዜማ አመራሮች መልቀቂያ ማስገባታቸው ተነገረ

በርካታ የኢዜማ አመራሮች መልቀቂያ ማስገባታቸው ተነገረ

ቀን:

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ፓርቲ ሦስት አመራሮች ለፓርቲው የመልቀቂያ ደብዳቤ ማስገባታቸው ተነገረ፡፡ ፓርቲው ባለው ሁለት ዓይነት መዋቅር ማለትም በትይዩ ካቢኔና በሥራ አስፈጻሚ ውስጥ ሲሳተፉ የቆዩ የፓርቲው አመራሮች መልቀቂያውን ማስገባታቸው ታውቋል፡፡

መልቀቂያውን ካስገቡት መካከል ባንትይገኝ ታምራት (ዶ/ር) አንዱ ሲሆኑ፣ በድርጅቱ መሪ በብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) በሚመራው ትይዩ ካቢኔ ውስጥ የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ትይዩ ካቢኔ ተጠሪ ሆነው ሲሠሩ መቆየታቸው ታውቋል፡፡

መምህር ወንደወሰን ተሾመ የተባሉ በድርጅቱ ሊቀመንበር በሚመራው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውስጥ አባል የነበሩ አባልም መልቀቂያ እንዳስገቡ የተነገረ ሲሆን፣ ለጊዜው ስማቸውን ማወቅ ያልተቻለ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚሠሩ አንድ የፓርቲው አመራርም በተመሳሳይ መልቀቂያ ማስገባታቸው ታውቋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ኢዜማን ለመልቀቅ ምን እንዳነሳሳቸው የተጠየቁት ባንትይገኝ (ዶ/ር)፣ በድርጅቱ ውስጥ እየባሰ የመጣው ድርጅታዊ አሠራሮችን የመጣስ አዝማሚያ መሠረታዊ ችግር እንደሆነ አንስተዋል፡፡ ድርጅቱን ለመልቀቅ ከወሰኑ እንደቆዩ የጠቀሱት ባንትይገኝ (ዶ/ር) ዓርብ ኅዳር 21 ቀን 2016 ዓ.ም. በይፋ መልቀቂያ እንዳስገቡ ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡

‹‹ከኢዴፓ ጀምሮ አብሮኝ ይሠራ የነበረውና በኢዜማ ሥራ አስፈጻሚ ውስጥ ሲሳተፍ የቆየው መምህር ወንደወሰን ተሾመም መልቀቂየ ማስገባቱን አረጋግጫለሁ›› ያሉት ባንትይገኝ (ዶ/ር)፣ በአንድ ሳምንት ጊዜ እርሳቸውን ጨምሮ ሦስት ሰዎች መልቀቂያ ማስገባታቸውን ተናግረዋል፡፡

ፓርቲው መጋቢት 2015 ላይ የአመራሮች ምርጫ ማካሄዱን ተከትሎ፣ በየጊዜው ከድርጅቱ ራሳቸውን የሚያገሉ አመራሮችና አባላት ቁጥራቸው መጨመሩ ሲዘገብ ቆይቷል፡፡

በ2015 ዓ.ም. መጨረሻ ወራት ላይ አቶ የሺዋስ አሰፋ፣ ሀብታሙ ኪታባ፣ ዳንኤል ሺበሺ፣ ናንሲ ውድነህ፣ ጂአልጋው ጀመረ፣ ተክሌ በቀለና ኑሪ ሙደሲር የተባሉ የፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባላት ራሳቸውን ከፓርቲው ማግለላቸውን ይፋ አድርገው ነበር፡፡ በተጠቀሰው ጊዜ ተጨማሪ 41 አባላት ከኢዜማ መልቀቃቸው ተገልጾም እንደነበር አይዘነጋም፡፡

ሰኔ ወር ላይ ደግሞ ወደ 250 በየደረጃው ያሉ ተጨማሪ የኢዜማ አመራሮች ለቀቁ የሚለው ጉዳይ ይፋ ሆኖ ነበር፡፡

ከኢዜማ የሚለቁት እነዚህ አባላት ፓርቲው ዓላማውን መሳቱን በተደጋጋሚ በቅሬታ ሲያነሱም ይደመጣል፡፡ አሁን ላይ መልቀቂያ ያስገቡት ባንትይገኝም (ዶ/ር) ይህንኑ ደግመው የተናገሩ ሲሆን፣ አንድ ግለሰብ የድርጅቱን አሠራሮች እንደፈለገ የሚጥስበት ሁኔታ መፈጠሩን አንስተዋል፡፡

‹‹ትይዩ ካቢኔ ይባል የነበረውን ልክ እንደ መንግሥት ሚኒስትሮች ምክር ቤት የተዋቀረውን ካቢኔ፣ የፓርቲው መሪ አፍርሰው ከ21 ወደ ሰባት ቁጥሩ ባነሰ ክላስተር ተክተውታል›› ሲሉ ቅሬታ አቅርበዋል፡፡ የፓርቲው መሪ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) ይህን ዕርምጃ የወሰዱበትን መነሻ ምክንያት ጨምሮ በፓርቲው እንቅስቃሴ መዳከም ጉዳይ ውይይት እንዲካሄድ ቢጠየቁም፣ በተለያዩ ምክንያቶች ለውይይት ጥሪው ምላሽ አለመስጠታቸውንም አንስተዋል፡፡

‹‹ብልፅግና አይነካ የሚል አቋም ወደመያዝ ፓርቲው አጋድሏል፤›› ሲሉ የሚከሱት ባንትይገኝ፣ ከመንግሥት ጋር ተባብሮ መሥራት በሚል በጠቅላላ ጉባዔ የተላለፈውን ውሳኔ ፍጹም በጣሰ መንገድ የፓርቲው መሪና የመንግሥት ሹመት ያገኙ አባላት የመንግሥት መገልገያ እንደሆኑም ተችተዋል፡፡

በሌላ በኩል የፓርቲው ከፍተኛ አመራር ጫኔ ከበደ (ዶ/ር) በእሥር መሰቃየታቸው ሳያንስ፣ የታሰሩበት ጉዳይ ወንጀልነቱ ሳይረጋገጥ ዕርምጃውን መደገፉ ፍጹም ያልተገባ እንደሆነ አንስተዋል፡፡ ልክ እንደ መንግሥት አንዳንድ የፖለቲካ ኃይሎችን መፈረጁ፣ ከመንግሥት ጎን ቆሞ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን መደገፉና በተለይም በአማራ ክልል የሚካሄደውን ዘመቻ መደገፉ ለመልቀቅ እንደገፋፋቸው ነው አክለው የገለጹት፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...