Sunday, February 25, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ብርሃን ባንክ ባስገኘው ቀጥተኛ የትርፍ ድርሻ ባለአክሲዮኖቹን ይቅርታ ጠየቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ብርሃን ባንክ በ2015 የሒሳብ ዓመት ካገኘው ትርፍ ለባለአክሲዮኖች የደለደለው የትርፍ ድርሻ አነስተኛ በመሆኑ ባለአክሲዮኖችን በይፋ ይቅርታ ጠየቀ። በሒሳብ ዓመቱ የባንኩ አንድ አክሲዮን ያገኘው የትርፍ ድርሻ 6.03 በመቶ ነው።

የባንኩ ጠቅላላ ጉባዔ ሐሙስ ኅዳር 21 ቀን 2016 ዓ.ም. ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ በባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ጉማቸው ኩሴ በሒሳብ ዓመቱ የትርፍ ክፍፍል መጠኑ ማነስ ቦርድ ጠቅላላ ጉባዔውን ይቅርታ ይጠይቃል ብለዋል፡፡ 

ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ ያስመገበው የትርፍ መጠን ከቀዳሚው ዓመት አንፃር ሲታይ መጠነኛ ዕድገት ያለው ቢሆንም ለባለአክሲዮኖች የሚከፋፈለው የገንዘብ መጠን የቀነሰበትንም ምክንያት አስረድተዋል፡፡ 

ብርሃን ባንክ ባስገኘው ቀጥተኛ የትርፍ ድርሻ ባለአክሲዮኖቹን ይቅርታ ጠየቀ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የብርሃን ባንክ ጠቅላላ ጉባዔ በተካሄደበት ወቅት

የቦርድ ሊቀመንበሩ ባቀረቡት ሪፖርት እንደገለጹትም፣ ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ ከታክስ በኋላ 505.6 ሚሊዮን ብር ያተረፈ ሲሆን፣ ይህ የትርፍ መጠንም የ3.7 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን ጠቅሰዋል፡፡ ባንኩ ታክስ ሳይከፍልና በብሔራዊ ባንክ የተጣሉ ሕጋዊ መጠባበቂያዎችን ከትርፉ ላይ ተቀናሽ ሳያደርግ ሊኖር የሚችለው የትርፍ ድርሻ 15.6 በመቶ መሆኑን አስታውቀዋል። ይህም ማለት አንድ ሺሕ ብር ዋጋ ያለው የባንኩ አንድ አክሲዮን ብር 156.2 ትርፍ ሊያገኝ ይችል እንደነበር የቦርድ ሊቀመንበሩ ተናግረዋል።

ነገር ግን ተገቢው የታክሰ ክፍያና በኢትዮጵየ ብሔራዊ መመርያ መሠረት አስፈላጊው ተቀናሽ ከተደረገ በኋላ የአንድ ሺሕ ብር ዋጋ ላለው አንድ አክሲዮን የተደለደለው የትርፍ ድርሻ 6.03 በመቶ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ 

ትርፍ ድርሻው በዚህን ያህል የወረደው በባንኩ ውስጣዊ ችግሮችና ከባንኩ ቁጥጥር ውጭ በሆኑ ምክንያቶች መሆኑን የተናገሩት የቦርድ ሊቀመንበሩ፣ ‹‹የትርፍ ድርሻው ሁላችንም ከጠበቅነው በታች በመሆኑ ቦርዱ በአጠቃላይ ይቅርታ ይጠይቃል፤›› ብለዋል፡፡ 

የትርፍ ድርሻቸው በከፍተኛ ደረጃ በማሽቆልቆሉ የተበሳጩት የባንኩ ባለአክሲዮኖች ግን ነገሩን በይቅርታ የሚታለፍ አይደለም ሲሉ ተቃውሞአቸውን አሰምተዋል።

የትርፍ ድርሻቸው መቀነሱ ብቻ ሳይሆን ባንኩ ለከታታይ ሦስት ዓመታት ያሳየው ደካማ እንቅስቃሴና ሌሎች ችግሮችም በመኖራቸው ቦርዱ በይቅርታ ብቻ መታለፍ የለበትም የሚሉ አስተያየቶችን እንዲሰነዘሩ ገፍቷቸዋል፡፡ 

በጠቅላላ ጉባዔው አስተያየት እንዲሰጡ ዕድል የተሰጣቸው ባለአክሲዮኖች ሁሉ የባንኩን አፈጻጸም ተችተዋል። አስተያየታቸውን ከሰጡት ባለአክሲዮኖች መካከል አንዱ፣ ባለአክሲዮኖች ገንዘባቸውን በባንክ ቢያስቀምጡ ከዚህ የተሻለ የወለድ ክፍያ ማግኘት ይችሉ እንደነበር በመግለጽ በባንኩ የትርፍ ድርሻ መጠን ማዘናቸውን ገልጸዋል። ባንኮች በተቀማጭ ገንዘብ ላይ የሚከፍሉት ዝቅተኛው የወለድ መጠን ሰባት በመቶ መሆኑ ይታወቃል። ይህም ማለት በባንክ የተቀመጠ 100 ብር በዓመቱ ሰባት ብር የወለድ ክፍያ ያገኛል። የብርሃን ባንክ ባለ አክሲዮኖች በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት የተወሰነላቸው የትርፍ ድርሻ 6.03 በመቶ በመሆኑ፣ ባባንኩ አንድ አክሲዮን ውስጥ የሚገኝ እያንዳንዱ መቶ ብር በዓመት ያስገኘው ትርፍ ስድስት ብር ብቻ ነው።

ብርሃን ባንክ የአራት ዓመታት የትርፍ መጠን ከዓመት ዓመት እሽቆለቆለ መምጣቱን የባንኩ መረጃዎች ያሳያሉ። 

ባንኩ በ2012 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት 708 ሚሊዮን ብር ያገኘ ሲሆን፣ በ2013 ደግሞ ከታክስ በፊት 338 ሚሊዮን ብር፣ በ2014 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት 583 ሚሊዮን ብር፣ በ2015 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት 605 ሚሊዮን ብር አትርፏል።

ለትርፍ ክፍፍል ከቀረበው ዝቅተኛ ገንዘብ ባሻገር ግን የባንኩ የ2015 የሒሳብ ዓመት አፈጻጸም በተለያየ መጠን ዕድገት እያሳየ ስለመምጣቱ ከቀረበው ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል፡፡ በሁሉም የባንክ ሥራ አፈጻጸሙ በሒሳብ ዓመቱ ዕድገት የታየበት መሆኑን የባንኩ የሥራ ኃላፊዎች የሚያመላክቱ ሲሆን፣ የባንኩ የተበላሸ ብድር መጠን ለተከታታይ ዓመት ከፍ ማለቱ ለተመዘገው አነስተኛ ትርፍ ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል። 

የባንኩ በብሔራዊ ባንክ ሕግ መሠረት ለእነዚህ የተበላሹ ብድሮቹ በየዓመቱ መጠባበቂያ ለመያዝ በመገደዱ በትርፍ ዕድገቱ ላይ ጉዳት ማስከተሉን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት የባንኩ አጠቃላይ የተበላሸ ብድር መጠን በመቀነሱ በቀጣዮቹ ዓመታት የሚኖረው የትርፍ መጠን ከፍተኛ እንደሚሆን እምነታቸውን ገልጸዋል።

የቦርድ ሊቀመንበሩ፣ ‹‹ጤነኛ ያልሆኑ ብድሮች ምጣኔ በ2014 የሒሳብ ዓመት ከነበረበት 8.5 በመቶ በ2015 የሒሳብ ዓመት ወደ 5.4 በመቶ በመቀነስ መሻሻል አሳይቷል፤›› ብለዋል፡፡

 ባንኩ በ2015 የሒሳብ ዓመት ያሰባሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን 7.8 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህም ከቀዳሚው ዓመት የ30 በመቶ ዕድገት ማስመዝገቡን፣ አጠቀላይ የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ መጠንም ወደ 33.8 ቢሊዮን ብር ከፍ እንዲል ማደርጉንም አቶ ጉማቸው ገልጸዋል፡፡ 

ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ባንኩ የሰጠው ብድር መጠን የ30.3 በመቶ ዕድገት በማሳየት በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ የባንኩ የብድር ክምችቱ 30 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡

በሌላ በኩል እየጨመረ የመጣውን የብድር ክምችትና የተበላሹ የብድሮች መጠን ግምት ውስጥ በማስገባት ሌሎች መጠባበቂያዎችን ጨምሮ ባንኩ 311.1 ሚሊዮን ተጨማሪ መጠባበቂያ በሒሳብ ዓመቱ መያዙን ገልጸዋል፡፡ 

ከውጭ ምንዛሪ ግኝት አንፃርም 170 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱ ተጠቁሟል፡፡ ይህም በቀዳሚው አግኝቶት ከነበረው 128.6 ማሊዮን ብር አንፃር የ14.3 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡

የባንኩ ዓመታም ገቢ በ927.4 ሚሊዮን ብር ወይም በ22.1 በመቶ ጭማሪ በማሳየት 5.1 ቢሊዮን ብር መሆኑን እንዲሁም ዓመታዊ ወጪው ደግሞ በ25 በመቶ በማደግ ጠቅላላ ወጪው 4.5 ቢሊዮን ብር እንደነበር ተጠቅሷል፡፡ 

የባንኩ አጠቃላይ የሀብት መጠንም በቀደመው ዓመት ከነበረበት 33.1 ቢሊዮን ብር ወደ 45 ቢሊዮን ብር ከፍ ያለ ሲሆን ዓመታዊ የሀብት መጠን ዕድገቱ 36.2 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ 

ብርሃን ባንክ የተከፈለ ካፒታል መጠኑ በሒሳብ ዓመቱ ውስጥ ያሳየው ዕድገት 6.1 በመቶ ብቻ እንደሆነ ታውቋል፡፡ ይህ የተከፈለ ካፒታል መጠን ዝቅተኛ ዕድገት ካስመዘገቡ ባንኮች ያደርገዋል፡፡ 

የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር እንደገለጹትም የባንኩ አጠቃላይ ካፒታል መጠን በ12.7 በመቶ ብልጫ አሳይቶ አምስት ቢሊዮን መድረሱን፣ የባንኩ የተከፈለ ካፒታል ግን 6.1 በመቶ ዕድገት በማስመዝገብ 3.4 ቢሊዮን መድረሱን ተናግረዋል፡፡ 

በቅርቡ ሥራቸውን የለቀቁትን የባንኩ ፕሬዚዳንት በተመለከተ የቦርድ ሊቀመንበሩ በሪፖርታቸው ‹‹ባንካችንን በፕሬዚዳንትነት ሲመሩ የነበሩት አቶ ግሩም ፀጋዬ በግል ጉዳይ ፈቃዳቸው ለቀዋል፤›› ብለዋል፡፡ በመሆኑም የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መሥፈርት መሠረት አፈላልጎ ያገኘ ሲሆን አስፈላጊው ቅድመ ሁኔታ ከተሟላ በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሥራቸውን የሚጀምሩ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡ 

ብርሃን ባንክ በ2015 የሒሳብ ዓመት 40 አዳዲስ ቅርንጫፎችን በመክፈት አጠቃላይ የቅርንጫፎቹን ቁጥር 366 አድርሷል፡፡ የቋሚ ሠራተኞቹም ቁጥር 5,998 መድረሱ ታውቋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች