Sunday, February 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊዓለም አቀፍ ትኩረት የተሰጠው የምርመራ ጋዜጠኝነት

ዓለም አቀፍ ትኩረት የተሰጠው የምርመራ ጋዜጠኝነት

ቀን:

የምርመራ ጋዜጠኝነት/ዘገባ ከሌሎች የዘገባ ዓይነቶች ይለያል፡፡ ከዜጎች ወይም ማንኛውም መረጃው እንዲነገርና እንዲተላለፍ ከሚፈልግ አካል የሚለቀቅ ወይም በፍጥነት ተሠርቶ የሚሠራጭ ‹‹Leak Information›› ዓይነት ዘገባ አይደለም፡፡ የምርመራ ጋዜጠኝነት በወንጀል ወይም በሙስና ላይ ብቻ የሚሠራ ዘገባም አይደለም፡፡ የምርመራ ጋዜጠኝነት ስለጤና፣ ስለትምህርት፣ ስለሰብዓዊ መበት፣ ስለድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች፣ ስለስደት፣ ስለኢንቨስትመንት፣ በሥልጣን ስለመባለግ፣ ስለምርጫ፣ ስለስፖርት፣ ወዘተ. ሊሆን ይችላል፡፡ በዋናነት የምርመራ ጋዜጠኝነት ከሌሎች የዘገባ ሥራዎች የሚለይበት ምክንያት ለዘገባ የሚሆኑ ግብዓቶች ጥልቅና ለየት ያለ ምርመራ የሚፈልጉና እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ድረስ ዋጋ ሊያስከፍሉ የሚችሉ መሆናቸው ነው፡፡

ዓለም አቀፍ ትኩረት የተሰጠው የምርመራ ጋዜጠኝነት | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
በ19ኛው የአፍሪካ የምርመራ ጋዜጠኝነት ጉባዔ ላይ የተሳተፉ ጋዜጠኞች በከፊል

የምርመራ ጋዜጠኝነት የተጀመረው፣ የምርመራ ዘገባ አባት እየተባለ በሚጠራው እንግሊዛዊው ዊሊያም ቶማስ ስቲይድ እንደነበር የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ ስቲይድ፣ እ.ኤ.አ. ከ1849 እስከ 1912 ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆኑ ይነገርለት የነበው የ‹‹ዘ ፖል ሞል ጋዜት›› አዘጋጅ ነበር፡፡

በቪክቶሪያ ዘመን አነጋጋሪ የነበውና ዘ ፖል ሞል ጋዜጣ ያተመው ‹‹The maiden Tribute of modern Babylon›› የምርመራ ዘገባው፣ በለንደን ከተማ የ13 ዓመት ታዳጊዎች በቤተሰቦቻቸው አስገዳጅነት ሴተኛ አዳሪ እንዲሆኑ እንደሚገደዱ ያጋለጠ ነበር፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የስቲይድ የምርመራ ዘገባ ከፍተኛ ወንጀልን ያጋለጠ ስለነበር፣ የአገሪቱ ፓርላማ የወንጀል ሕግ እንዲሻሻል፣ ለሴቶችና ልጃገረዶች ልዩ ጥበቃ እንዲደረግላቸውና እንዳይጨቆኑ ክልከላ የሚጥሉ ድንጋጌዎች በአገሪቱ የወንጀል ሕግ ውስጥ እንዲካተት በመደረጉ የ‹‹ስቲይድ ሕግ› ተብሎ እንዲጠራ መደረጉንም መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡

ምንም እንኳን የምርመራ ጋዜጠኝነት ወይም ዘገባ ከተጀመረ ከ170 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ቢሆንም፣ አሁንም ብዙ መሥራትን የሚጠይቅና በፍላጎትና በልዩ ችሎታ የሚሠራ የጋዜጠኝነት ሙያ ሆኖ ቀጥሏል፡፡

እንግሊዛዊው ስቲይድ የጀመረው የምርመራ ጋዜጠኝነት በዕውቀትና ቴክኖሎጂ ታግዞ በተለይ የተሻለ ግንዛቤ ባላቸውና ባደጉ አገሮች በተሻለ ሁኔታ እየተሠራበት ቢሆንም፣ አሁንም የጋዜጠኞችን ቁርጠኝነትና የሕይወት መስዋዕትነት የመጠየቁ ጉዳይ ቀጥሏል፡፡

ይህ የምርመራ ጋዜጠኝነት/ዘገባ ሥራ በተለይ በአፍሪካና በሌሎችም አኅጉራት በሚገኙ ታዳጊ አገሮች ውስጥ ከፍ ያለ መስዋዕትነትን የሚጠይቅ፣ አስፈሪና አስቸጋሪ ሥራ መሆኑን በሥራው ተሠማርተው የሚገኙ ጋዜጠኞች ህያው ምስክር ናቸው፡፡

ዓለም አቀፍ ትኩረት የተሰጠው የምርመራ ጋዜጠኝነት | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
በ13ኛው ዓለም አቀፍ የምርመራ ጋዜጠኝነት ጉባዔ ላይ የግሎባል ሻይኒንግ ላይት ሽልማትን ያሸነፉ ጋዜጠኞች

 

የምርመራ ዘገባን ተባብሮና ተናቦ በጥምረት ለመሥራት፣ አኅጉር አቀፍ ጥምረት (Africa investigation Journalism Network) እና ዓለም አቀፍ የምርመራ ዘገባ ጥምረት መድረክ (Global Investigative journalism Network) አስፈላጊነት ግድ ይላል፡፡

በመሆኑም አኅጉር አቀፍ የምርመራ ዘገባ ጥምረት (Africa investigative Network – AIJN) ዋና መሥሪያ ቤቱን በደቡብ አፍሪካ ጆሀንስበርግ አድርጎ፣ በአፍሪካ አገሮች የሚገኙ የምርመራ ዘገባ ጋዜጠኞች፣ ድንበር ተሻጋሪ የምርመራ ሥራዎችን በትብብር እንዲሠሩ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

ጥምረቱ የአፍሪካ አኅጉር ጋዘጠኞች ተገቢ መረጃ፣ ቴክኖሎጂ፣ ምርምር፣ ፈጠራና የተለያዩ ለዘገባ የሚያገለግሉ ቁሳቁሶችንና የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠናዎችን እንዲያገኙና የምርመራ ሥራዎቻቸው በድንበር የታጠሩ እንዳይሆኑ፣ በሚፈጥሩት ጥምረትና ትብብር በጋራ የሚሠሩበት ሁኔታ እንዲፈጠር ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው፡፡

በመሆኑም የአፍሪካ ጋዜጠኞች ስለአኅጉራቸውና ዓለም አቀፍ የምርመራ ዘገባዎች አሠራር፣ ስለምርመራ ጋዜጠኝነት/ዘገባና ድንበር ተሻጋሪ ሥራዎች እንዴት  በትብብር መሥራት እንዳለባቸው የሚመክሩበት፣ ሐሳብ የሚለዋወጡበት፣ የሥራ ሙያ ክህሎት ልምዳቸውን የሚያዳብሩበትና የሚመካከሩበት፣ በጉምቱው ጋዜጠኛ፣ አርታዒ፣ የዩኒቨርሲቲ መምህርና ደራሲ ፕሮፌሰር አንተን ሀርበር አማካይነት የተጀመረውንና 19ኛው የ‹‹Africa Investigative Journalism Conference-AIJC23›› ጉባዔ  በደቡብ አፍሪካ ጆሀንስበርግ ከተማ በዊትዋተርስራንድ (WITWATERSRAND-WITS) ዩኒቨርሲተ ከኅዳር 10 እስከ 12 ቀን 2016 ዓ.ም. አካሄዷል፡፡

ከተመሠረተ 101 ዓመታትን ባስቆጠረው ዊትስ ዩኒቨርሲቲ የተካሄደው 19ኛው የአፍሪካ የምርመራ ጋዜጠኝነት ጉባዔ (AIJC-23) ላይ ከ40 በላይ የአፍሪካ አገሮች 350 የምርመራ ጋዜጠኞች የተሳተፉበትና ከ80 በላይ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይትና የልምድ ልውውጥ የተደረገበት ነበር፡፡

ዓለም አቀፍ ትኩረት የተሰጠው የምርመራ ጋዜጠኝነት | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

ከ40 ዓመታት በላይ በኅትመት ጋዜጠኛነት፣ በአርታዒነት፣ በተለያዩ ጋዜጦችና መጽሔቶች ላይ ዓምደኛ፣ በሬዲዮና በቴሌቪዥን አርታዒነት የሠሩትና ሁለት መጻሕፍት ማሳተማቸውን የሚናገሩት ፕሮፌሰር አንተን ሀርበር፣ የ65 ዓመት አዛውንትና ጉምቱ ጋዜጠኛ ሲሆኑ፣ በመጠናቀቅ ላይ ባለው የአውሮፓውያን ዓመት መገባደጃ የተካሄደው የአፍሪካ የምርመራ ጋዜጠኝነት ጉባዔ (AIJC-23) የመጨረሻቸው በመሆኑ ለሌላ ተተኪ አስረክበው ተሰናብተዋል፡፡

የምርመራ ጋዜጠኝነት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተቋቋመ ከ170 ዓመታት በላይ ዕድሜ እንዳስቆጠረ የሚነገር ቢሆንም፣ አፍሪካ በራሷ ልጆች የሚመራና የሚመራመር የምርመራ ዘገባ ተቋም ስለሚያስፈልጋት፣ የአፍሪካ የምርመራ ዘገባ ጥምረት (AIJN) መቋቋሙ ትልቅ እመርታ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

‹‹ዓላማችን ብዙ ነው፡፡ ቀዳሚው ዓላማ ትብብርና ጥምረት መፍጠር ቢሆንም፣ በምንፈጥረው ጥምረት የአፍሪካ አገሮችና ሕዝቦችን፣ ከሙስናና ከሕገወጥ ስደት፣ ከድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች፣ ከፆታ ጥቃት፣ ከጤናና ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዙ ወንጀሎች ዙሪያ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት፣ የአፍሪካን ጋዜጠኞች ሥራን ከፍ ማድረግ፣ ዕውቅና መስጠትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ትኩረት እንዲሰጠው ማድረግ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የምርመራ ጋዜጠኝነት የአፍሪካ መሪዎች ላይ ተፅዕኖ በመፍጠር ለሕዝባቸው ታማኝ አገልጋይ እንዲሆኑ፣ አኅጉሪቱ እንድትበለፅግና ተጠያቂነት እንዲሠፍን ማድረግና የተሠሩ መልካም ሥራዎችም ዕውቅና እንዲያገኙ ማስቻል ተቀዳሚ ሚናው ነው፡፡ ሆኖም ተግዳሮቶቹ ብዙ ናቸው፡፡ ዋነኛው ተግዳሮት ደግሞ ሀብት መሆኑንም ፕሮፌሰር አንተን ሀርበር ተናግረዋል፡፡

ጥሩ የምርመራ ሥራ ለመሥራትና የጋዜጠኞችን ደኅንነት ለማስጠበቅ ሀብት ተግዳሮት መሆኑን አፅንኦት ሰጥተውታል፡፡

የአፍሪካ አገሮች ጋዜጠኞችን ባለፉት 19 ዓመታት በተካሄዱ ጉባዔዎች ለማጣመር ያደረጉት ጥረት ከፍተኛ ውጤት ማግኘቱ ትልቅ ስኬት መሆኑን ተናግረው፣ በተለይ በ19ኛው ጉባዔ የተነሱ አዳዲስ ሐሳቦችና ጥምረቶች የበለጠ አስደሳች መሆናቸውን አክለዋል፡፡

ከዌስትጌት ሾፒንግ ሞል የሽብር ተግባር እስከ ሶማሊያ ጦርነት ከ20 ዓመታት በላይ የተለያዩ የምርመራ ዘገባዎችን በመሥራት የሚታወቀው ኬንያዊው ጋዜጠኛ ቶም ኦዱላ፣ በ19ኛው በAIJC-23 ጉባዔ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀውን ሽልማት አሸናፊ ሆኗል፡፡

ዓለም አቀፍ ትኩረት የተሰጠው የምርመራ ጋዜጠኝነት | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የፎዮ (Fojo) ሚዲያ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ከርሰቲ ፎርስበርግ

 

ቶም ኦዱላ በ19ኛው AIJC-23 ጉባዔ ላይ አሸናፊ የሆነበት የምርመራ ዘገባ፣ በአገሩ ኬንያ በሚገኙ ሁለት ግዙፍ የሻይ ቅጠል ማምረት ኢንቨስመንት ሥራ በተሰማሩ ድርጅቶች ውስጥ የሚሠሩ ሴት የጉልበት ሠራተኞች ላይ፣ ከአሥር ዓመታት በላይ ሲፈጸም የነበረን የወሲብ ጥቃትና የጉልበት ብዝበዛን ያጋለጠበት ዘገባ ነው፡፡ ጋዜጠኛ ቶም ኦዱላ ‹‹Sex for work- The true cost of our tea›› በሚል በሠራው የምርመራ ዘገባ የክብር ሽልማት ሊያገኝ ችሏል፡፡

እ.ኤ.አ. በ1886 በተመሠረተችውና ‹‹የወርቅ ምድር›› በመባል በምትታወቀው የደቡብ አፍሪካ ትልቋ ከተማ ጆሀንስበርግ፣ ለሦስት ቀናት በተደረገው የአፍሪካ የምርመራ ጋዜጠኝነት ጉባዔ ላይ የሪፖርተር፣ የኢትዮጵያ ኢንሳይደርና የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋዜጠኞች በፎዬ ሚዲያ ኢንስቲትዩት (Fojo)ና አይኤምኤስ (IMS) አማካይነት ተጋብዘው ጉባዔውን ታድመዋል፡፡

በ19ኛው በአፍሪካ የምርመራ ጋዜጠንነት ጉባዔ (AIJC-23) የምርመራ ዘገባዎቻቸውን ለውድድር ያቀረቡ 200 ጋዜጠኞች ቢሆንም፣ የተቀመጡትን መስፈርቶች አሟልተው ለመጨረሻው ዙር ከቀረቡት 20 የምርመራ ጋዜጠኞች፣ጋዜጠኛ ቶም ኦዱላ አሸናፊ ሆኗል፡፡ 

ሌላው የምርመራ ጋዜጠኞች ጥምረት ፈጥረው በትብብር እንዲሠሩና የጋዜጠኝነት ሙያ ዓለም አቀፍ ይሁንታ እንዲያገኝ እየሠራ የሚገኘውና ከተመሠረተ 22 ዓመታትን ያስቆጠረው ዓለም አቀፍ የምርመራ ጋዜጠኝነት/ ዘገባ ጥምረት (Global investigative Journalism Net Work) ሲሆን፣ እሱም 13ኛ ጠቅላላ ጉባዔውን ከመስከረም 8 እስከ 11 ቀን 2016 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. ከሴፕቴምበር 19 እስከ 22 ቀን 2023) በስዊድን ጎተንበርግ ከተማ አካሂዷል፡፡

ዓለም አቀፍ የምርመራ ጋዜጠኛነት ጥምረት ማኅበር ዋና መሥሪያ ቤቱን በአሜሪካ አድርጎ የመሠረተ ቢሆንም፣ በመላው ዓለም የሚገኙ የምርመራ ጋዜጠኞች ተሰባስበው ዓለም አቀፍ የምርመራ ጋዜጠኞች ጉባዔ (GIJC) ለማድረግ በአካል የተገናኙት እ.ኤ.አ. በ2001 እና 2003 በዴንማርክ በኮፐንሀገን ከተማ ነው፡፡

የስብሰባው ዋና አስፈላጊነት የምርመራ ዘገባን በመላው ዓለም ለማስፋፋትና ጋዜጠኞች በየሁለት ዓመቱ በአካል ተገናኝተው ያላቸውን ዕውቀትና የአሠራር ጥበብ፣ አዳዲስ ሃሳቦችን ለመቀያየር፣ ድንበር ዘለል ዘገባዎችን ጥምረት በመፍጠር መረጃ ተቀባብለው የሚዘግቡበት መረብ መዘርጋት፣ መረጃዎችን ለመለዋወጥ፣ ልምድ ለመለዋወጥና ዕውቀት ለማስፋት፣ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን ለማግኘትና ሙያውን ማሳደጊያ መንገዶችን ለማዘጋጀት በማለም ነው፡፡

ከስቶክሆልም ቀጥላ የስዊድን ሁለተኛዋና ዋና የወደብ ንግድ በሚካሄድባት ጎተንበርግ ከተማ በተደረገው ዓለም አቀፍ የምርመራ ጋዜጠኞች ጉባዔ፣ ከኢትዮጵያ የሪፖርተር፣ የኢትዮጵያ ኢንሳይደርና የሲፍተር (Sifter) ኒውስ ሌተር (Online Media) ዘጋቢዎችን ጨምሮ ከ134 አገሮች 2,138 ጋዜጠኞች ጉባዔውን ተካፍለዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞችን ጨምሮ ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ጋዜጠኞችን ስፖንሰር በማድረግ፣ በዓለም አቀፍ የምርመራ ጋዜጠኝነት ስብሰባ ላይ እንዲሳተፉ ያደረገው ፎጆ ሚዲያ ኢንስቲቲዩት (Fojo) ነው፡፡

‹‹በተለይ እ.ኤ.አ. ከ2019 ጀምሮ በዓለም ውስጥ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ የማይኔማ መፈንቅለ መንግሥት፣ ሩሲያ ዩክሬንን መውረር፣ አደገኛነቱና አሰቃቂነቱ እየጨመረ የመጣው የአየር ንብረት ለውጥና ሌሎችም ተለዋዋጭና ያልታሰቡ ክስተቶች ዓለምን ቢፈታተኗትም፣ ዓለም አቀፍ የምርመራ ጋዜጠኞች ይህንን ችግር በመጋፈጥ፣ ባለሥልጣናትንና ተገቢ ያልሆኑ አሠራሮችን የሚተገብሩ ኩባንያዎችን በመከታተልና በማጋለጥ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ቆይተዋል፤›› በማለት የፎዬ ሚዲያ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ክርስቲ ፎርስበርግ ስብሰባውን በንግግር ሲከፍቱ ተናግረዋል፡፡

በጎተንበርግ የተደረገውን 13ኛውን ዓለም አቀፍ የምርመራ ጋዜጠኞች ጉባዔ ካዘጋጁት ሦስት ተቋማት አንዱ የሆነው ፎዮ (Fojo) የሚዲያ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬከተር፣ በስብሰባው 2000 ጋዜጠኞች እንደሚገኙ እምነት የነበራቸው ቢሆንም፣ ከጠበቁት በላይ 2,138 ጋዜጠኞች መሳተፋቸው አስደሳች ከመሆኑም በተጨማሪ፣ የጋዜጠኞች ድንበር ተሻጋሪ ትብብር መጨመሩንና ዓለም አቀፍ ችግሮችን በቀላሉ ለመድረስ ከሚያስችል ደረጃ መድረሱን አመላካች መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ጎተንበርግና 13ኛው ዓለም አቀፍ የምርመራ ጋዜጠኝነት ጉባዔ አጀማመርና ፍጻሜ

ከመስከረም 8 ቀን እስከ 11 ቀን 2016 ዓ.ም. (ሴፕቴምበር 19 እስከ 22 ቀን 2023) የተካሄደው (GIJC-23) ጉባዔ አጀማመሩና አፈጻጸሙ እጅግ አስደሳች ነበር፡፡ ሁሉም የስብሰባው ተካፋይ ጋዜጠኞች ከ134 አገሮች የተሰባሰቡ ቢሆኑም፣ መልካቸው፣ ቁመታቸውና አለባበሳቸው የተለያየ ሆኖ ልዩ ውበት ከመፍጠሩ በስተቀር፣ የነበረው መስተጋበር የአንድ ቤት ልጆች አስመስሏቸው ነበር፡፡ ሁሉም ታዳሚዎች በአንድ የመሰብሰቢያ አዳራሽ የተገኙት የስብሰባው መክፈቻና መዝጊያ ላይ ብቻ የነበረ ሲሆን፣ በአንድ አዳራሽ ውስጥ አንድ ላይ ሆነው ሲታዩ እጅግ በጣም የተጠቀሰውን ያህል ብዛት ያላቸው አይመስሉም፡፡

ሦስት እያንዳንዳቸው 25 ወለል ያላቸው ሕንፃዎችን በአንድ መሠረት አጣምሮ የያዘው ጎታዬ ታወር ሌግዠሪ ሆቴል፣ በሥሩ ባሉ ተገጣጣሚ የስብሰባ አዳራሾች ሁሉንም ታዳሚ ያለ ምንም መጨናነቅ ያስተናገደ ሲሆን፣ ታዳሚው ለሻይ ዕረፍት ወይም ምሳ ሰዓት ተሰባስቦ ከመታየቱ በስተቀር፣ ስብሰባው ሲጠናቀቅ የት እንደገባ ሳይታወቅ ሁሉም ከዓይን ይሠውራል፡፡ ጫጫታም ሆነ ግርግር ሳይኖር ሁሉም እንቅስቃሴ በሥርዓት የተሞላ ነበር፡፡

በዓለም አቀፍ የምርመራ ዘገባ ጋዜጠኞች ጉባዔ (GIJC-23) ላይ ከ84 አገሮች 419 የምርመራ ዘጋቢዎች ሥራዎቻቸውን ለውድድር አቅርበዋል፡፡

በ2023 ዓለም አቀፍ የምርመራ ዘገባ ጋዜጠኞች ጉባዔ፣ የአንፀባራቂ ብርሃን ሽልማት ‹‹Global Shining Light Award››ን ሕገወጥ የማዕድን ሥራን በሚመለከት የቬንዩዜላ ጋዜጠኛ፣ ሥርዓት ተበጅቶለት ስለሚፈጸም ሕገወጥ አመፅና ዘረፋን በሚመለከት የናይጀሪያ ጋዜጠኛ፣ ፖሊስ በዜጎች ላይ የሚያደርሰውን ሕገወጥ ድብደባ በሚመለከት የደቡብ አፍሪካ ጋዜጠኛ፣ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ አትራፊ ሥራን በሚመለከት የሰሜን ሜቆዶኒያ ጋዜጠኞች በሠሩት የምርመራ ዘገባ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡

ከግሎባል ሻይኒንግ ላይት አዋርድ በተጨማሪ፣ ስለሚስጥር እስር ቤቶች፣ ስለጅምላ መቃብር የምርመራ ዘገባ የሠሩ ጋዜጠኞችም ‹‹ሠርተፊኬት ኦፍ ኤክሰለንስ›› ተሸልመዋል፡፡

በዓለም አቀፍ የምርመራ ዘገባ ጋዜጠኝነት ጉባዔ (GIJC-23) የተሸለሙት በአነስተኛና በመካከለኛ የሚዲያ ተቋማት የሚሠሩ ጋዜጠኞችና ፍሪላንሰርስ ጭምር ኛቸው፡፡

ለጋዜጠኞቹ ሽልማቱን የሰጡት ተሰናባቹ የዓለም አቀፍ የምርመራ ዘገባ ጋዜጠኝነት ጥምረት (GIJCN) ዋና ዳይሬክተር የነበሩትና በዕለቱ በኤሚሊያ ስትራክ የተተኩት ሚስተር ዴቬድ ኢ. ካፕላን ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...