Monday, February 26, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የ267.7 ሚሊዮን ብር ኪሳራ ያስተናገደው አኃዱ ባንክ 300 ሚሊዮን ብር ለማትረፍ ግብ ጥሏል

ተዛማጅ ፅሁፎች

የባንክ ኢንዱስትሪውን ዘግይተው ከተቀላቀሉት መካከል አንዱ የሆነው አኃዱ ባንክ፣ በ2015 የሒሳብ ዓመት የሥራ አፈጻጸሙ 267.7 ሚሊዮን ብር ኪሳራ ቢያጋጥመውም፣ ዘንድሮ ኪሳራውን ለማካካስ ጠንክሮ እንደሚሠራ አስታወቀ፡፡

ባንኩ በ2015 የሒሳብ ዓመት የሥራ አፈጻጸሙ ከፍተኛ እመርታ ማስመዝገቡን የሚገልጹት  የባንኩ የሥራ ኃላፊዎች፣ አዲስ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ያወጣው ከፍተኛ ወጪ ላጋጠመው ኪሳራ ምክንያት መሆኑን ይጠቅሳሉ። እንዲህ ያለው ሁኔታም ተፈጥሯዊና ተጠባቂ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ 

ባንኩ ወደ ሥራ የገባበት ወቅት ከመሆኑ አኳያ የባንኩን መሠረት ለማጠናከር ከፍተኛ ወጪ ማውጣቱን፣ ይህንን ተግባር አጠናቆ በትክክል ወደ ሥራ ከገባ የስድስት ወራት ዕድሜ ብቻ የያዘ ከመሆኑ አኳያ፣ በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ ኪሳራ እንዳጋጠመው ገልጸዋል፡፡ 

የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ሰፊዓለም ሊበን ለሪፖርተር እንደገለጹትም፣ ባንኩ አስተማማኝ መሠረት የጣለ በመሆኑ የበጀት ዓመቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ወደ ትርፍ እየተሸጋገረ ነው፡፡ ባንኩ በዘንድሮው የ2016 ሒሳብ ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ወደ ትርፋማነት መሸጋገሩን የሚያረጋግጥ የሥራ አፈጻጸም ማስመዝገቡን፣ ይህም ባንኩ በጠንካራ መሠረት ላይ መሆኑን እንደሚያረጋግጥ ገልጸዋል።

ባንኩ በ2016 የሒሳብ ዓመት ከ250 እስከ 300 ሚሊዮን ብር ትርፍ ለማግኘት አቅዶ እየሠራ ሲሆን፣ በመጀመሪያው የሩብ ዓመትም ያስመዘገበው ትርፍ በዓመቱ ውስጥ ያቀደው ትርፍ እንደሚሳካ ያመላከተ መሆኑን ጠቁመዋል። 

በማሳያነትም ባንኩ በሰኔ ወር 2015 ዓ.ም. ላይ 672.6 ሚሊዮን ብር የነበረው የባንኩ የተከፈለ ካፒታል፣ በ2016 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት መጨረሻ ላይ 900 ሚሊዮን ብር መድረሱን አመልክተዋል። የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑም በ2015 ዓ.ም. ከነበረበት ሁለት ቢሊዮን ብር ወደ 3.02 ቢሊዮን ብር መድረሱ፣ ባንኩ በተያዘው የሒሳብ ዓመት ያቀደውን ለማሳካት እንደሚችል አመላካች እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ በ2015 ሒሳብ ዓመት ላይ 201 ሺሕ የነበረው የባንኩ ገንዘብ አስቀማጮች ብዛት፣ በ2016 የሒሳብ ዓመት የመጀመሪያው ሦስት ወራት ውስጥ ከ400 ሺሕ በላይ መድረሱን የጠቀሱት ፕሬዝዳንቱ፣ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት 23 ሚሊዮን ዶላር የነበረው የውጭ ምንዛሪ ግኝቱም፣ በዘንድሮው ሩብ ዓመት ከ70 ሚሊዮን ዶላር በላይ መድረሱን ገልጸዋል። በመሆኑም ባንኩ ካጋጠመው ኪሳራ ወጥቶ በ2016 የሒሳብ ዓመት እስከ 300 ሚሊዮን ብር የሚደረስ ትርፍ ለማግኘት እንደሚችል፣ የሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸሙም ዕቅዱ እንደሚሳካ ጠቋሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ 

የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ አንተነህ ሰብስቤ በበኩላቸው ለባንኩ ባለአክሲዮኖች ባቀረቡት ዓመታዊ ሪፖርት፣ ባንኩ በ2015 የሒሳብ ዓመት የተለያዩ ተግዳሮቶች እንደነበሩበት ገልጸዋል፡፡ የአገሪቱ ማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታ መዛባትና እንዲሁም ማኅበራዊና ፖለቲካዊ አለመረጋጋት በባንኩ ዘርፍ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማስከተላቸውን ጠቅሰዋል፡፡

የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እየፈተኑ ያሉ የውስጥ ተግዳሮቶች፣ በዋናነትም የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ ቀጣይነት ያለው ከፍተኛ የዋጋ ንረት፣ ሥራ አጥነትና የበጀት ጉድለት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣት፣ መንግሥት ጥብቅ የፊሲካልና የገንዘብ የፖሊሲ ዕርምጃዎችን እንዲወስድ ማስገደዱ፣ በባንክ ኢንዱስትሪው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳላቸው አስረድተዋል። ለአብነትም መንግሥት በባንኮች ላይ የጣለው አስገዳጅ የግምጃ ቤት ቦንድ ግዥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መልኩ በባንክ ሥራ ላይ ተፅዕኖ እንዳለው ተናግረዋል።

‹‹በሒሳብ ዓመቱ ብዙ ተግዳሮቶች ቢያጋጥሙንም ባንኩን ጠንካራ መሠረት ላይ ማቆም ችለናል፤›› ያሉት የቦርድ ሊቀመንበሩ፣ ባንኩ ሥራ በጀመረበት የመጀመሪያ ዓመት በተለያዩ ዘርፎች አመርቂ ስኬቶችን እንዳስመዘገበ ገልጸዋል፡፡

ባንኩ በ2015 የሒሳብ ዓመት አስመዝግቧቸዋል ካሉት ዋና ዋና ተግባራት መካከል አንዱ፣ ወደ ሥራ በገባ በአንድ ዓመት እንቅስቃሴው ብቻ ከ201 ሺሕ በላይ ደንበኞችን በማፍራት፣ ከሁለት ቢሊዮን ብር ባለይ ተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰባ መቻሉን ነው። በተጨማሪም ለተለያዩ የሥራ ዘርፎች ከ924.7 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር ማቅረቡን ያመለከቱት የቦርድ ሊቀመንበሩ፣ በሒሳብ ዓመቱ ያቀረበው ብድርም በዋናነት ለባንኩ ተጨማሪ ሀብት ሊያመነጩ ለሚችሉና የባንኩን ተልዕኮ ያስፈጽማሉ ተብለው ለታመነባቸው ዘርፎች መዋሉን ገልጸዋል።

ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ ከሰጠው ጠቅላላ ብድር ውስጥ የአገር ውስጥ ንግድ 36 በመቶ ድርሻ ሲይዝ፣ ለወጪና ለንግድ የተሰጠው ደግሞ 32.7 በመቶ ድርሻ አለው፡፡ ቀሪው ለግንባታ በአምራች ኢንዱስትሪ የግለሰብ ብድርና ለሌሎች ዘርፎች የተሰጠ ነው፡፡ ባንኩ የተበላሸ የብድር መጠን 0.01 በመቶ ብቻ መሆኑንም በመጥቀስ 99.9 በመቶ ጤናማ ብድር መሆኑንም ጠቅሷል፡፡ 

አኃዱ ባንክ በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ የተከፈለ ካፒታል መጠን 672.3 ሚሊዮን ብር መሆኑን ለማወቅ የተቻለ ሲሆን፣ ይህ የተከፈለ የካፒታል መጠን አኃዱ ባንክን ዝቅተኛ ካፒታል ካላቸው የግል ባንኮች መካከል አንዱ ያደርገዋል፡፡ 

የባንኩ ሪፖርትም ይህንኑ የጠቀሰ ሲሆን፣ የተከፈለ ካፒታል ብሔራዊ ባንኩ ካስቀመጠው ባንኮች ሊያሟሉ ይገባል ብሎ ካስቀመጠው ዝቅተኛ የአምስት ቢሊዮን ካፒታል አንፃር በጣም ዝቅተኛ የሚባል ነው፡፡ ባንኩ የተቀመጠውን ዝቅተኛ የካፒታል መጠን እ.ኤ.አ. እስከ 2028 ድረስ የማሟላት ግዴታ አለበት፡፡ ይህንን ግዴታውን ለመወጣት በቀሪዎቹ ሦስት ዓመታት ካፒታሉን ለማሳደግ እየተሠራ መሆኑን የገለጹት አቶ ሰፊዓለም፣ በዚህ ዓመት የተከፈለ ካፒታሉን እስከ ሁለት ቢሊዮን ብር ለማድረስ እየተሠራ ሲሆን፣ በ2016 በመጀመሪያው ሩብ ዓመትም የተከፈለ ካፒታሉ 1.3 ቢሊዮን ብር ሊደርስ መቻሉ፣ የሚፈለገውን አምስት ቢሊዮን ብር ካፒታል የብሔራዊ ባንክ ባስቀመጠው የጊዜ ገደብ ለማሰባሰብ የሚቻል ስለመሆኑ ያሳያል ብለዋል፡፡ 

ባንኩ በአዲሱ የሒሳብ ዓመት ተጠባቂ የሚባሉ ተግዳሮቶችን ተቋቁሞ አትራፊ ለመሆኑ እርግጠኛ የሆኑት ፕሬዚዳንቱ፣ በአንፃሩ ግን ትልቅ ተግዳሮት ሊሆንብን ይችላል ብለው የጠቀሱት፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የ14 በመቶ የብድር ገደብ ነው፡፡ ፕሬዚዳንቱ እንደ አኃዱ ባንክ ያሉ ባንኮች አሁን ላይ እንደ ዋና ችግር የገጠማቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የባንኮች የብድር ምጣኔ ከ14 በመቶ መብለጥ የለበትም የሚለው ውሳኔ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ይህ መመርያ አነስተኛ የሚባሉ ባንኮችን በከፍተኛ ሁኔታ የሚጎዳ ነው፡፡ እነዚህ ባንኮች ይሰጡ የነበረው ብድር አነስተኛ ስለነበር በ14 በመቶ ብቻ ብድር አሳድጉ ቢባሉ ምንም ዓይነት ተጨማሪ ብድር ሊሰጡ አይችሉም፡፡ ከአንድ ቢሊዮን ብር በታች ብድር የነበራቸው ባንኮች 14 በመቶ የብድር ዕድገት ምንም ነገር ሊለውጡ አይችሉም፡፡ ስለዚህ ይህ መመርያ አንዱና ትልቁ ችግር ስለሚሆን ይህ እንዲስተካከል ጥያቄ ቀርቦ መልሱን እየተጠባባቁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር በአማራ ክልል ያሉ ቅርንጫፎች አብዛኛዎቹ እየሠሩ ባይሆንም፣ ባንኩ አሁን ባለው አቋሙ ግን ለበጀት ዓመቱ ያቀደውን ሁሉ ለማሳደግ እየሠራ ያለውን ሥራ ማረጋገጫ ይሆናል ብለዋል፡፡ 

አኃዱ ባንክ በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች የከፍተኛውን ቅርጫፎች 75 ያደረሰ መሆኑ ታውቋል፡፡ አኃዱ ባንክ ከኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ያገኘው ሰኔ 2 ቀን 2014 ዓ.ም. ሲሆን፣ በይፋ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት የተጀመረው ሐምሌ 2 ቀን 2014 ዓ.ም. ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች