Monday, February 26, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ በግሉ ኢንሹራንስ ዘርፍ ሁለተኛውን የገበያ ድርሻ ለመያዝ ያስቻለውን ውጤት ማስመዝገቡን ገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ የባንኮች የጥሬ ገንዘብ እጥረት፣ የመለዋወጫ ዕቃዎች ዋጋ መናርና ሌሎች የወጪዎች መጨመር የኩባንያውን የፋይናንስ አቅም በእጅጉ የፈተነው ቢሆንም በ2015 የሒሳብ ዓመት የኩባንያውን የገበያ ድርሻ በማሳደግ ለባለአክሲዮኖቹ ከፍተኛ የትርፍ ድርሻ ማስገኘት የቻለበትን አፈጻጸም ማስመዝገቡን ገለጸ፡፡ 

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ ባለፈው ቅዳሜ ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ባቀረበው የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት በተጠናቀቀው የ2015 ሒሳብ ዓመት ውጤታማ አፈጻጸም ያሳየበት የመሆኑን ያህል የተለያዩ ችግሮችም ያጋጠሙበት እንደነበር ጠቅሷል፡፡ 

የባንኩ ሪፖርት ዋና ዋና ችግሮች ብሎ ከዘረዘራቸው መካከል በኢኮኖሚው ውስጥ የተከሰተው ከፍተኛ የዋጋ ንረት በተሽከርካሪ የመለዋወጫ ዕቃዎች ዋጋ ላይም ጎልቶ መታየቱ በዋናነት ተጠቅሷል።

ከዚህም ሌላ ‹‹የቢሮ ኪራይ ዋጋ መጨመር፣ በአገር ውስጥ ያሉ ባንኮች የጥሬ ገንዘብ እጥረት (Liquidity) ችግርና ሌሎች የሥራ ወጪዎች መጨመር የኩባንያውን የፋይናንስ አቅም በእጅጉ ፈትነዋል፤›› ብሏል፡፡ እንደ ተግዳሮት የተነሳው ሌላው ጉዳይ ኩባንያው ከሚያስገነባው የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ጋር በተያያዘ ያጋጠመው የውጭ ምንዛሪ እጥረትና በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋለው የፀጥታ ችግር የኩባንያውን ሥራ እንቅስቃሴ ላይ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ተጽዕኖ ማሳደሩን ይገልጻል።

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ እንዲህ ያሉ ችግሮች ያጋጠሙት ቢሆንም የ2015 የሒሳብ ዓመት አፈጻጸሙ ከቀዳሚዎቹ ዓመታት የተሻለ አፈጻጸም ያሳየበትና የኩባንያውንም የገበያ ድርሻ ያሳደገበት እንደነበረ የኩባንያው የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር ወ/ሮ መሪማ ጪብሳ ባቀረቡት ሪፖርት ገልጸዋል፡፡ ኩባንያው በሒሳብ ዓመቱ 1.7 ቢሊዮን ብር የዓረቦን ገቢ መሰብሰብ መቻሉን የገለጹት የቦርድ ሊቀመንበሯ፣ ይህም በኢንዱስትሪው ያለውን የገበያ ድርሻ በማሳደግ ከግል ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ሁለተኛውን ከፍተኛ የገበያ ድርሻ እንዲይዝ አስችሎታል ብለዋል፡፡

በሒሳብ ዓመቱ ያሰባሰበው የዓረቦን መጠን ከቀዳሚው ዓመት በ74 በመቶ ዕድገት ያሳየ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ ከጠቅላላ የዓረቦን ገቢ ውስጥ የሕይወት የኢንሹራንስ ዘርፍ የተገኘው ድርሻ 47 ሚሊዮን ብር ሲሆን ይህም ከቀዳሚው ዓመት የ143 በመቶ ብልጫ እንዳለው ታውቋል፡፡ በሒሳብ ዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ አገልግሎት መስጠት ከጀመረበት ከወለድ ነጻ የኢንሹራንስ አገልግሎት (ታካፉል) ደግሞ 29 ሚሊዮን ብር ማሰባሰብ መቻሉም በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡

ከኩባንያው ዓመታዊ ሪፖርት መረዳት እንደተቻለው በሒሳብ ዓመቱ ሕይወት ነክ ካልሆነው የኢንሹራንስ ዘርፍ አሰባስባለሁ ብሎ ያቀደው 1.27 ቢሊዮን ብር ሲሆን አፈጻጸሙ ከዕቅዱ 126 በመቶ ብልጫ በማሳየት እንዲሁም ከቀዳሚው ዓመት ደግሞ የ74 በመቶ በማደግ 1.6 ቢሊዮን ብር ዓረቦን መሰብሰብ መቻሉን ነው፡፡ 

በሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍም ለማሰባሰብ አቅዶ የነበረው 38.3 ሚሊዮን ብር እንደነበር የሚያመለክተው ሪፖርቱ አፈጻጸሙ 123 በመቶ ሆኗል፡፡ ይህ የዓረቦን ገቢ ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነፃፀር 143 በመቶ ብልጫ እንዳለው ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡ 

በሒሳብ ዓመቱ ለኩባንያው የቀረበው የካሳ ክፍያ ጥያቄ 376 ሚሊዮን ብር ሲሆን በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ የከፈለው የካሳ ክፍያ ግን 396 ሚሊዮን ብር ሆኗል፡፡ ለሕይወት ኢንሹራንስ የተከፈለው ካሳ ክፍያ ደግሞ 26.9 ሚሊዮን ብር ነው፡፡

የካሳ ክፍያው ከጥያቄው በላይ የሆነው በተንጠልጣይ ሲተላለፉ የቆዩና መጠባበቂያ ሲያዝላቸው የቆዩ የካሳ ጥያቄዎች በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት በመከፈላቸው ምክንያት መሆኑ ተገልጿል፡፡ 

ኩባንያው በሒሳብ ዓመቱ ወጪ ካደረገው የካሳ ክፍያ በተጨማሪ በሒደት ላይ ላሉ የካሳ ክፍያ ጥያቄዎች 734 ሚሊዮን ብር መጠባበቂያ መያዙንም አስታውቋል፡፡ በቀዳሚው ዓመት በተመሳሳይ ወቅት ተይዞ የነበረው መጠባበቂያ 662 ሚሊዮን ብር መሆኑን ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡

ከዚህም ሌላ ኩባንያው የማክሮ ኢንሹራንስ ጨምሮ ሕይወት ነክ ካልሆነው የኢንሹራንስ ዘርፍ ከተሰበሰበው 1.6 ቢሊዮን ብር ዓረቦን ውስጥ ለጠለፋ መድን ሰጪዎች 594 ሚሊዮን ብር የከፈለ ሲሆን ይህም ከተሰበሰበው ዓረቦን ውስጥ 37 በመቶ ድርሻ እንዳለው የቦርድ ሊቀመንበሯ በሪፖርታቸው ጠቅሰዋል፡፡ 

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ በተለያዩ የንግድ ድርጅቶች ውስጥ ያለው የአክሲዮን ድርሻና ሌሎች ኢንቨስትመንቶቹ መጠን 1.9 ቢሊዮን ብር መድረሱንም ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡ ከዚህ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የያዘው ኩባንያው ዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ግንባታ ነው ተብሏል፡፡ እስካሁን ለዚህ የሕንፃ ግንባታ 841 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል፡፡ 

ከዚህም ሌላ 769 ሚሊዮን ብር በጊዜ የተገደበ የባንክ ተቀማጭ ያለው ሲሆን ፣ በተለያዩ የንግድ ድርጅቶች ውስጥ ያለው የአክሲዮን ድርሻ ደግሞ 322 ሚሊዮን ብር መድረሱ ታውቋል፡፡ ከኢንሹራንስ ዘርፍ ውጪ ያለው አጠቃላይ ኢንቨስትመንቱ ከቀዳሚው ዓመት አንፃር ሲታይ 44 በመቶ ማደጉንም ሪፖርቱ ይጠቁማል። በአጠቃላይ፣ ኩባንያው በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ ጠቅላላ የሀብት መጠኑ በ48 በመቶ ጨምሮ 3.78 ቢሊዮን ብር መድረሱን ሪፖርቱ ያመለክታል።

እንዲህ ካለው እንቅስቃሴው ኩባንያው በሒሳብ ዓመቱ 333.9 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታውቋል፡፡ በቀዳሚው ዓመት ያገኘው የተጣራ ትርፍ 189.54 ሚሊዮን ብር እንደነበር ሪፖርቱ ያሳያል፡፡ ከሒሳብ ዓመቱ ትርፍ አብዛኛው የተገኘ ከቀጥታ የኢንሹራንስ ዘርፍ ሥራ መሆኑን የቦርድ ሊቀመንበሯ ተናግረዋል፡፡ 

አያይዘውም በዚህ አፈጻጸሙ ከግል ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ከፍተኛ የሚባለውን የትርፍ ድርሻ ክፍፍል ለባለአክሲዮኖቹ ማስገኘቱን ተናግረዋል። በዚህም መሠረት አንድ ሺሕ ብር ዋጋ ያለው የኩባንያው አንድ አክሲዮን 430 ብር ትርፍ ማግኘት የቻለ ሲሆን፣ ይህም ዓምና ከነበረው 350 ብር ጋር ሲነፃፀር በ29 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን ጠቅሰዋል፡፡ 

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ ሜክሲኮ አደባባይ አካባቢ እያስገነባ የሚገኘው ባለ 33 ወለል ሕንፃ ለማጠናቀቅ ከስድስት ቢሊዮን ብር በላይ የሚያስፈልገው መሆኑን ገልጿል፡፡

በቅዳሜው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የቀረበው የዳይሬክተሮች ቦርድ ሪፖርት እንደሚያመለክተው የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ግንባታ ቦርዱ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠቱ አመርቂ የሚባል ውጤት ሊመዘገብ መቻሉን ጠቅሷል፡፡ 

አያይዞም በአሁኑ ወቅት የሕንፃው ከምድር በታች የግንባታ ሥራ የተጠናቀቀ ሲሆን ከመሬት በላይ በፖሊየሙ የሕንፃ አቅጣጫ በኩል ሦስተኛው ፎቅ (ወለል) በመገንባት ይገኛል፡፡ ሆኖም እስካሁን ያለው የሕንፃ ግንባታ ሥራ 1.2 ቢሊዮን ብር ኩባንያው በራሱ አቅም ኢንቨስት ያደረገበት ሲሆን ቀሪው የግንባታ ሥራ አሁን ባለው ዋጋ መሠረት ስድስት ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልገው ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡ 

ከኩባንያው መረጃ መረዳት እንደሚቻለው የዋና መሥሪያ ቤቱ ሕንፃ ግንባታ ሲጀመር ይህንን ያህል ወጪ ያወጣል ተብሎ ያልተገመተ ቢሆንም ከግንባታ ኮንትራት ውል በኋላ የተፈጠረው የዋጋ ንረት የሕንፃ ግንባታ ወጪው እንዲጨምር አስገድዷል፡፡ 

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ በኢንዲስትሪ ውስጥ ከ15 ዓመት በላይ የዘለቀ ሲሆን ከሕይወት ኢንሹራንስና ሕይወት ነክ ካልሆነው ኢንሹራንስ ሽፋን ባሻገር የማክሮ ኢንሹራንስ በመስጠት ከሚጠቀሱት ሦስት ኩባንያዎች መካከል አንዱ ሲሆን በተጠናቀቀው ዓመትም የታካፉል ኢንሹራንስ ጀምሯል፡፡ 

ከስምንት በላይ ኩባንያዎች ውስጥ የአክሲዮን ባለድርሻ ሲሆን ከእነዚህ መካከል በኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ ውስጥ ከ140 ሚሊዮን ብር በላይ፣ በኦሮሚያ ባንክ ውስጥ ደግሞ ከ121 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው አክሲዮኖች ባለቤት ሲሆን በአጠቃላይ በተለያዩ ኩባንያዎች ውስጥ ከ329.9 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው አክሲዮኖች ባለቤትም ነው፡፡ 

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ የታካፉል ካፒታሉን በ28 በመቶ በማሳደግ 870 ሚሊዮን ብር አድርሷል፡፡ አዲስ አበባን ጨምሮ በክልል ከተሞች ያሉት ቅርንጫፎች 56 ሲሆኑ በቅርቡም በአሶሳ፣ ጋምቤላ፣ ጅግጅጋ፣ ዶዶላና ሰመራ አምስት ቅርንጫፎችን እንደሚከፍት አስታውቋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች