Monday, February 26, 2024

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን በሚመሩት ብሔራዊ ጦርና በጄኔራል መሐመድ ሃምዳን ዳጋሎ (ሄሜቲ) በሚታዘዘው ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መካከል የሚካሄደው ውጊያ ዕልቂቱ ወደ አስከፊ ደረጃ እየተሸጋገረ ነው፡፡

ከ5‚000 የሚበልጡ ሰዎች የተገደሉበትና ከስድስት ሚሊዮን ያላነሱ ዜጎችን ያፈናቀለው የሱዳን ጦርነት ትኩረት ተነፍጎታል፡፡ በዩክሬንና በሩሲያ ጦርነት በኋላም በፍልስጤምና እስራኤል ግጭት የተጠመደው ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ፣ ለሱዳን ዕልቂት ተገቢውን ቦታ የሰጠው አይመስልም፡፡

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ሱዳናውያን

በሱዳን እየተባባሰ በቀጠለው ጦርነት ሕፃናትና ሴቶችን ጨምሮ ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከባድ ጉዳት እየገጠማቸው ነው ተብሏል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ሴቶች ለወሲብ ባርነት እየተዳረጉ ነው የሚሉ አሰቃቂ ሪፖርቶች እየወጡ ነው፡፡ አስገድዶ መድፈርን ጨምሮ ሴቶች ለበርካታ ፆታዊ ጥቃቶች ተጋላጭ መሆናቸው እየተነገረም ነው፡፡

በአትባራ ግዛት የዩኒሴፍ ተወካይ የሆኑት አዴል ካዴር እንደተናገሩት፣ አሁን ያለው የሱዳን ቀውስ እ.ኤ.አ. በ2002 በዳርፉር ጦርነት ካጋጠመውም የባሰ ነው ብለዋል፡፡ ተወካይዋ እንደተናገሩት አሁን እየተፈጸመ ያለው በሕፃናትና በሴቶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ከቀደሙት በ550 እጥፍ የበለጠ ነውም ብለዋል፡፡ በጦርነት ጊዜ ሁሌም ሲቪሎች ትልቁን ዋጋ እንደሚከፍሉት ሁሉ በአሁኑ የሱዳን ጦርነትም ዋነኛ ተጎጂዎች ንፁኃን ዜጎች መሆናቸው ተነግሯል፡፡

በሱዳን የቀድሞ የአሜሪካ ምክትል መልዕክተኛ የነበሩት ዴቪድ ሺን (አምባሳደር) የመሣሪያ ማዕቀብ መጣል ለሱዳን ግጭት መፍትሔ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ አሜሪካንን ጨምሮ በርካታ አገሮች በሱዳን ላይ የመሣሪያ ማዕቀብ መጣላቸውን አምባሳደሩ ያወሳሉ፡፡ ይሁን እንጂ በተቃራኒው ለሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች ያልተቋረጠ የመሣሪያ ድጋፍ የሚያቀርቡ አገሮች አሉ ይላሉ፡፡

የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ለፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የመሣሪያ ድጋፍ  ስታደርግ፣ ግብፅ ደግሞ የሱዳን ብሔራዊ ጦርን ታስታጥቃለች ይላሉ፡፡ ለእነዚህ ለተፋላሚዎች መሣሪያ የሚያቀርቡ ኃይሎች በተለይም የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ የመሣሪያ ድጋፏን እንድታቆም ማሳመን የተሻለ ነው ሲሉ ነው ዴቪድ ሺን (አምባሳደር) የተናገሩት፡፡

አሜሪካዊው ዲፕሎማት የአሜሪካ ቁልፍ አጋር የሚባሉ አገሮች በሱዳን ግጭት ጣልቃ መግባታቸውን አይክዱም፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ጠብ ጫሪ አገሮች ለዚህ ችግር ፈጣሪነታቸው ከመቀጣትና ከመወገዝ ይልቅ፣ ይመከሩ የሚል የማይመስል መፍትሔ ነው ሲሰጡ የተደመጡት፡፡ ምዕራባዊያኑ ፖለቲከኞችና መገናኛ ብዙኃን የሱዳን ጦርነት መቀጠል አውሮፓን በስደተኞች ጎርፍ እንዲጥለቀለቅ ያደርጋል የሚለውን ጉዳይ ማንሳትን የመረጡ ይመስላሉ፡፡

በዳርፉር ግዛት የሚንቀሳቀሱ የዓረብ ሚሊሻዎች ዓረብ ባልሆኑ ጎሳዎች ላይ ጥቃት እያደረሱ ነው እየተባለ ነው፡፡ በዳርፉር መዲና ኤልጀኒናና በአካባቢው የማሳሊድ ነዋሪዎች ከባድ ጥቃት እንደደረሰባቸው ተዘግቧል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) በቅርቡ በዚህ ጉዳይ ላይ ጠንካራ መግለጫ አውጥቷል፡፡

በሱዳን የተመድ ዕርዳታ ማስተባበሪያ ተወካይዋ ክሌመንት ንኩዌታ ሳላሚ፣ ‹‹በሱዳን እየደረሰ ያለውን ዕልቂትና ሰቆቃ በአግባቡ የሚገልጽ ቃላት አጥተናል፤›› በማለት ነበር የተናገሩት፡፡ ግድያ፣ ጭፍጨፋ፣ ዕገታ፣ አስገድዶ መድፈር፣ ማፈናቀል፣ ዘር ተኮር ጥቃት፣ ወዘተ በሱዳን ሁሉንም ዓይነት ቀውስ እያየን ነው ብለዋል፡፡

በሱዳን ግማሹ ሕዝብ ማለትም 25 ሚሊዮን ሰዎች መሠረታዊ ሕይወት ማቆያ ዕርዳታ ፈላጊ ሆነዋል፡፡ ጦርነቱ በካርቱምና በዙሪያዋ፣ በምዕራብ (ዳርፉር)፣ እንዲሁም በደቡባዊ ዋና ዋና ከተሞች ቀጥሏል፡፡ ሁለቱም የሱዳን ተፋላሚዎች ብሔራዊ ጦሩም ሆነ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት በመፈጸም ተጠያቂ እየሆኑ ነው፡፡ በተለይ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉና የእሱ አጋር ናቸው የተባሉ ዓረብ ሚሊሻዎች በዳርፉር ከባድ ጭፍጨፋ እያካሄዱ ናቸው እየተባለ ነው፡፡

እ.ኤ.አ. ዲሴምበር 2018 የሱዳን አብዮት ሲቀጣጠል፣ ለ30 ዓመታት አገር የገዙት ኦማር አልበሽር ከሥልጣን ለቀው በሱዳን ዴሞክራሲያዊ ለውጥ እንዲመጣ የሚጠይቁ ዜጎች ለተቃውሞ አደባባይ ወጡ፡፡ በዚህ የዜጎች ለውጥ ጥያቄ መሀል ብቅ ያሉት ጄኔራል አብዱልፈታ አልቡርሃንና ጄኔራል መሐመድ ሃምዳን ደጋሎ (ሄሜቲ) ወታደራዊ ምክር ቤት በመመሥረት ከጊዜያዊ ሲቪል አስተዳደሩ ጋር በጋራ አገር ለማስተዳደር ተስማሙ፡፡ ይሁን እንጂ ሁለቱ ጄኔራሎች ከሲቪል አስተዳደሩ መሪ ከአብዱላ ሃምዶክ ጋር መስማማት እያቃታቸው ሄደ፡፡ ጄኔራል አልቡርሃንና ምክትላቸው ሄሜቲ በጋራ የሲቪል አስተዳደሩን ከሥልጣን ለማውረድ ማሴር ጀመሩ፡፡ ሲቪሉን አብደላ ሃምዶክን ከሥልጣን አስወግደውም ሁለቱ የጦር መኮንኖች በጋራ አገር መምራት ቀጠሉ፡፡

ይሁን እንጂ በሒደት እርስ በርሳቸው መስማማት እያቃታቸው መጣ፡፡ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ትጥቁን ፈትቶ ወደ ብሔራዊ ጦሩ እንዲጠቃለል የቀረበው ውሳኔ በሁለቱ ጄኔራሎች መካከል የቆየውን የሥልጣን የበላይነት የመጨበጥ ፍጥጫ አፈነዳው፡፡ ካለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ጀምሮ በሁለቱ ኃይሎች መካከል ከባድ ጦርነት እየተካሄደ ይገኛል፡፡

አልቡርሃንና ሄሜቲን ለመሸምገል በርካታ ጥረት የተደረገ ቢሆንም እስካሁን ግን አንዱም አልሠራም፡፡ የአፍሪካ ኅብረት፣ የዓረብ ሊግ፣ ኢጋድ፣ አሜሪካ፣ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ግብፅ፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ ብዙ ወገኖች የሰላም ጥሪ ሲያቀርቡ ቢቆዩም ሁለቱ ወገኖች በቀላሉ የሚታረቁ አልሆነም፡፡ ባለፈው ሐምሌ በሁለቱ ወገኖች መካከል መጠነኛ መግባባት የፈጠረ ድርድር ቢጀመርም የሱዳን ጦር ተወካዮች ሒደቱን ጥለው መውጣታቸው አይዘነጋም፡፡ ከሰሞኑ በሳዑዲና በአሜሪካ ጥረት በጅዳ ከተማ ንግግር የተጀመረ ሲሆን የዚህ ንግግር ውጤትም በጉጉት እየተጠበቀ ነው፡፡

ይሁን እንጂ ስለድርድርና ስለሰላም ጥረት እየተነገረ ባለበት የጦርነቱ ግለት መጨመሩ እየተነገረ ይገኛል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተደረጉ ከባድ ውጊያዎች የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ሙሉ ለሙሉ የዳርፉር ግዛትን በቁጥጥሩ ሥር አውሏል ተብሏል፡፡ በካርቱምም ቢሆን የበላይነቱን እየወሰደ መሆኑ ተነግሯል፡፡ የሱዳን ብሔራዊ ጦር ከፊል ካርቱምን ጨምሮ ሰሜናዊ የሱዳን ክፍልን ይዞ መቀጠሉ የተነገረ ሲሆን፣ ዋና መቀመጫውን ከካርቱም በመንቀል ወደ ፖርት ሱዳን ከተማ ማዛወሩ ታውቋል፡፡

የሱዳን ቀውስ ቀስ በቀስ የሊቢያን ዓይነት መልክ እየያዘ እንደመጣ አንዳንድ ተንታኞች በመናገር ላይ ናቸው፡፡ በሊቢያ ትሪፖሊ መቀመጫውን ባደረገው ዓለም አቀፍ ዕውቅና ባለው አስተዳደርና በቤንጋዜ ጠንካራ ኃይል በገነቡት በጄኔራል ሀፍታር መካከል ረጅም ዓመታት የዘለቀ ደም አፋሳሽ ግጭት ሲካሄድ መቆየቱ አይዘነጋም፡፡ ሊቢያን ለሁለት የከፈለው የሁለቱ ጎራ ጦርነት ደግሞ ቱርክ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ፣ ግብፅና ሌሎችም የውጭ ኃይሎች ጎራ ለይተው እንዲሠለፉ ያደረገ ዓለም አቀፍ ቀውስ ሆኗል፡፡

በሱዳንም ይህን መሰል ቀውስ ሊከሰት እንደሚችል የሚገምቱ ወገኖች፣ ሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች በሰላም ችግሩን ካልቋጩት ሱዳን ለሁለት እንደምትከፈል እየተናገሩ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በሱዳን ተፋላሚዎች ሁኔታ አደራዳሪዎች ጭምር ተስፋ እየቆረጡ መምጣታቸው ነው የተነገረው፡፡

በጥቅምት ወር የአፍሪካ ኅብረትና ኢጋድ በሳዑዲ ዓረቢያና በአሜሪካ አነሳሽነት የተጀመረውን ሁለቱን ኃይሎች የማግባባት ጥረትን ማገዝ ጀምረው ነበር፡፡ በብዙ ጥረት ሁለቱ ኃይሎች እ.ኤ.አ. ኖቬምበር 7 የሰብዓዊ ዕርዳታ ያለገደብ እንዲንቀሳቀስ ለማድረግ መስማማታቸው ይፋ መደረጉ ይታወሳል፡፡

በሁለቱ ወገኖች መካከል አንፃራዊ መቀራረብ ስለመፈጠሩ መዘገብ ጀምሮም ነበር፡፡ በቀጣዩ ድርድር ወደተኩስ አቁም ስምምነት እንደሚሸጋገሩ ከፍተኛ ተስፋም ተጥሎ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ከሰሞኑ ተጀመረ የተባለው የጅዳ ንግግር ያለ ስምምነት መበተኑ እየተነገረ ነው፡፡

ሁለቱ ኃይሎች በዋናነት የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ከያዛቸው የሱዳን ግዛቶች፣ በተለይም ከካርቱምና ከዋና ዋና ከተሞች ለቆ ይውጣ በሚለው ጉዳይ ልዩነታቸው መስፋቱ ተነግሯል፡፡ በዚህ የተነሳ አደራዳሪዎቹ ንግግሩ ፈቅ ሊል አይችልም ብለው እንዳቋረጡት እየተነገረ ነው፡፡ ሱዳን ትሪብዩን የተሰኘው የዜና ምንጭ ውስጥ አዋቂዎች ነገሩኝ ብሎ እንደዘገበው፣ አደራዳሪዎቹ ለጊዜው የንግግር ሒደቱ እንዲቋረጥ አድርገዋል፡፡

ባለፈው ወር በኒውዮርክ ተካሂዶ በነበረው የአፍሪካ ኅብረትና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰባተኛው ዓመታዊ ጉባዔ ላይ፣ ከአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ከሙሳ ፋቂ ማህማት ጋር በጋራ ሆነው የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬስ ስለሱዳን ጉዳይ መግለጫ ሰጥተው ነበር፡፡

ጉተሬስ በዚህ መግለጫቸው፣ ‹‹በሱዳን የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ ከመጣ ጊዜ ጀምሮ፣ የተባበሩት መንግሥታትም ሆነ የአፍሪካ ኅብረት ሽግግሩ የሰመረ እንዲሆን ብዙ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ የሱዳን የጦር መሪዎች ግን ወደ ጦርነት መግባት ነው የመረጡት፡፡ በውጭ ኃይሎች የገንዘብና የመሣሪያ ድጋፍ እስካሁን ጦርነቱን መቀጠል መርጠዋል፡፡ ይሁን እንጂ የእነርሱ የሰላም እምቢተኝነት ሳይሆን ለሱዳን ቀውስ የአፍሪካ ኅብረትና የተባበሩት መንግሥታት ናቸው ተጠያቂ ሲደረጉ የሚታየው›› በማለት ነበር ሁለቱ ተፋላሚዎችና ደጋፊዎቻቸውን የወቀሱት፡፡

በኢትዮጵያ የሚኖሩት ሱዳናዊው የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች ተንታኝ በሽር ናስር ግን ለሰላም ጊዜው አለመርፈዱን ነው የሚናገሩት፡፡ ‹‹ሰላሙ መምጣት ያለበት ከራሳቸው ከተፋላሚዎቹ ነው፡፡ የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት የሚፈይደው ነገር የለም፡፡ ተከታታይ ንግግሮች በመካከላቸው መቀጠሉን አውቃለሁ፡፡ እነዚህ ንግግሮች ምን ዓይነት ውጤት ይዘው እንደሚመጡ ራሳቸው በይፋ እስኪገልጹ መጠበቅ የሚሻል ይመስለኛል፡፡ ፈጥኖ ደራሽ የሚባለው ኃይል የሚሊሻ ጦር ነው፡፡ መደበኛው የሱዳን ጦር ሸሸ፣ ተሸንፎ መቀመጫውን ወደ ፖርት ሱዳን ከተማ አዛወረ ይባላል፡፡ ይሁን እንጂ የሱዳን ብሔራዊ ጦር አሁንም ቢሆን ውጤታማ ውጊያ እያካሄደ ነው፡፡ የሚሊሻ ኃይሉ በውጊያ መግፋቱ የትም እንደማያደርሰው የሚታወቅ ነው፤›› በማለት ነበር ሱዳናዊው ስለአገራቸው ወቅታዊ ሁኔታ የገለጹት፡፡

ሱዳን ልክ እንደ ሊቢያ በሁለቱ የጦር አበጋዞች ውጊያ የመከፈል ዕጣ አይገጥማትም ወይ ተብለው የተጠየቁት ሱዳናዊው በሽር ናስር፣ ‹‹በፍፁም አይሆንም፣ የሱዳን ሁኔታ ከሊቢያው በጣም የተለየ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ከዚህ ይልቅ ድርድሩ የት እንደሚደርስ ካዩ በኋላ ሁኔታው ወደየት እንደሚያመራ መተንተን እንደሚመርጡ በመጠቆም ነበር ሐሳባቸውን የደመደሙት፡፡

ከሰሞኑ አድማሱና ግለቱ እየተቀየረ የመጣው የሱዳን ጦርነት እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ጎረቤት አገሮች ማሳሰቡ የሚጠበቅ ነው፡፡ እስካሁን በይፋ የኢትዮጵያ መንግሥት በዚህ ጉዳይ ይፋ ያደረገው መረጃ የለም፡፡

በጦርነቱ ሥጋት የተነሳዘ ከካርቱም ወደ ገዳሪፍ ጽሕፈት ቤቱን ያዘወረው በሱዳን የኢትዮጵያ ኤምባሲ በኦፊሴላዊ የፌስቡክ ገጹ ላይ፣ ‹‹የአዲስ ፓስፖርት ጥያቄ ያቀረባችሁ ዜጎች ገዳሪፍ ቀርባችሁ ፓስፖርታችሁን ውሰዱ›› ከሚል አጭር ማስታወቂያ በዘለለ ከሰሞኑ በሱዳን ስላለው ሁኔታ የሰጠው መረጃ የለም፡፡

ከሱዳን ጋር የሚጎራበተው የመተማ አካባቢ አስተዳደርም ቢሆን ከሰሞኑ ሁኔታ ጋር ተያይዞ የተለየ ቀጣናዊ የፀጥታ ሥጋት እንደሌለ ነው ያረጋገጠው፡፡ በመተማ ዮሐንስ ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዜናና ኅትመት ክፍል ቡድን መሪ አቶ ስጦታው ጫኔ በድንበር አካባቢ በሱዳን ጦርነት የመጣ የተለየ ችግር አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡

‹‹ከሁለት ቀን ቀደም ብሎ በግለሰቦች መካከል ድንበር ላይ ግጭት ተፈጥሮ ነበር፡፡ ሰው ታገተብን ብለው የተወሰኑ ሰዎች ከሱዳን ተነስተው በድንበር በኩል ግጭት አንስተው ነበር፡፡ ጉዳዩ የድንበር ኬላው ለተወሰነ ጊዜ እንዲዘጋ ቢያደርግም ነገር ግን ወዲያውኑ በተወሰደ ዕርምጃ በመግባባት ለችግሩ እልባት ተሰጥቷል፡፡ ድንበሩም መልሶ ተከፍቷል፤›› በማለት በአካባቢው ከዚህ የተለየ ሁኔታ አለመከሰቱን አመልክተዋል፡፡

‹‹ወደ መተማና አካባቢው ተጨማሪ ብዙ ስደተኛ ከሱዳን ሊመጣ ይችላል የሚለው ግምት ከፍተኛ ነው፤›› ሲሉ የገለጹት አቶ ስጦታው፣ እስካሁን እየገቡ ላሉት ስደተኞች ከዓለም አቀፍ የስደተኞች ተቋማትና ዕርዳታ ለጋሾች ጋር በመተባበር አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡ ከዚህ ውጪ ግን መተማና አካባቢው ሰላማዊ ቀጣና ሆኖ መቀጠሉን ነው የገለጹት፡፡

የሱዳን ጦርነት እስካሁን ከስደተኞች ድንበር መሻገር በዘለለ በጎረቤት አገሮች ላይ የተለየ ቀውስ የፈጠረበት ሁኔታ አለመታየቱ ይነገራል፡፡ ይሁን እንጂ ጦርነቱ እንደ ግብፅ፣ ሳዑዲ ዓረቢያና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስን የመሳሰሉ ቀጣናዊ ፍላጎት ያላቸው የውጭ ኃይሎች የተሠለፉበት መሆኑን በመጥቀስ፣ በዚሁ ከቀጠለ ቀጣናዊ ይዘት ሊላበስ እንደሚችል እንዳንዶች እየገመቱ ነው፡፡

በሱዳን ረጅም ዓመት የኖሩት አቶ ተስፉ የሺወንድም ሱዳን ልትበትን እንደምትችል ይገምታሉ፡፡ ‹‹ሰሜናዊውን የሱዳን ክፍል ግብፅ ትይዘዋለች፡፡ የግብፆች የረጅም ጊዜ ዓላማም ይኼው ነው፡፡ ግብፆቹ ከብሔራዊ ጦሩ ጄኔራል አልቡርሃን ጎን ተሠልፈው ፈጥኖ ደራሹን ኃይል ለማጥቃት በሚል የሱዳን መሠረተ ልማት አውታሮችን በአየር እየደበደቡ ነው፡፡ የሱዳን ጦር ይባላል እንጂ ግብፆቹ ናቸው በጦርነቱ የአየር ድብደባ እያደረጉ ያሉት፤›› ይላሉ፡፡

ሱዳኖች እርስ በርስ በሚያደርጉት ውጊያ ዝለው አገሪቱ ብትፈራርስና ብትበተን፣ ግብፆቹ ጥቅማቸውን በተሻለ እንደሚያስጠብቁ እንደሚያምኑ ነው የሱዳን ጉዳይ አዋቂው የሚናገሩት፡፡ ‹‹ከዚህ ቀደም ሀለይብ የሚባል ከሱዳን የነጠቁትና የራሳቸው ያደረጉት ግዛት አለ፡፡ አሁን ደግሞ ሱዳን ስትዳከም በሱዳን ላይ ያላቸውን ተፅዕኖ የበለጠ ይጨምራሉ፤›› ሲሉም ይገልጻሉ፡፡ በአንዳንድ የግብፅ ሚዲያዎች ሱዳን የሚባል አገር የለም ድንበራችን እስከ ኢትዮጵያ ነው የሚል ጀብደኛ ትርክት ሲስተጋባ እንደሰሙም ነው ያከሉት፡፡

‹‹አዲስ አበባ ዋሽንግተን አይደለችም፤›› ሲሉ የጠቀሱት አቶ ተስፉ፣ የሱዳን ቀውስ ወደ ኢትዮጵያ ሊመጣ የማይችልበት ዕድል አለመኖሩን ነው የገለጹት፡፡

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ከትናንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ፣ የሱዳን ቀውስ እንዲባባስ አድርገዋል ባላቸው ሦስት የቀድሞ የሱዳን መንግሥት ባለሥልጣናት ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡ ሦስቱ ባለሥልጣናት የሱዳን ቀውስን በማባባስ የቀድሞውን ሥርዓት ወደ ሥልጣን እንዲመጣ እያሴሩ ነው የሚል ክስም ተለጥፎባቸዋል፡፡ አሜሪካ በእነዚህ ሰዎች ላይ ማዕቀብን የጨመሩ ዕርምጃዎች እንደምትወስድ ነው ያስታወቀችው፡፡

የሱዳን ሰላም መስፈን ከምንም በላይ እንዳስጨነቃት የገለጸችው አሜሪካ ሦስት ሰዎችን መርጣ በማዕቀብ ከምትቀጣ የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎችን የሚያስታጥቁና የሚረዱ አገሮች ላይ ዕርምጃ ብትወስድ፣ ለሱዳን ቀውስ የተሻለ መፍትሔ ሊሆን ይችል እንደነበር ታዛቢዎች ይናገራሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -