Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናብሔራዊ ባንክ የሪፖርተር ዘገባ የተሳሳተ ነው ብሎ ያቀረበው ቅሬታና የዝግጅት ክፍሉ ምላሽ

ብሔራዊ ባንክ የሪፖርተር ዘገባ የተሳሳተ ነው ብሎ ያቀረበው ቅሬታና የዝግጅት ክፍሉ ምላሽ

ቀን:

በኅዳር 23 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም ‹‹ብሔራዊ ባንክ በሕጋዊውና በጥቁር ገበያው መካከል ያለውን የምንዛሪ ተመን ልዩነት ለማጥበብ ማቀዱ ተሰማ›› በሚል ርዕስ የወጣውን ዘገባ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ሪፖርተርን የማይወክሉ ቃላትን በመጠቀም ዘገባው ሐሰተኛ መሆኑን የሚገልጽ መረጃ ማሠራጨቱን የዝግጅት ክፍላችን ተመልክቶታል። ይሁን እንጂ ብሔራዊ ባንኩ በዘገባው ላይ ያለውን ቅሬታ በቀጥታ ለዝግጅት ክፍላችን ያላደረሰ በመሆኑና በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ላሠራጨው መረጃ ምላሽ መስጠት ተገቢ ሆኖ ስላላገኘነው ዝምታ መርጠን ነበር።

ነገር ግን ብሔራዊ ባንክ ዘገባው በወጣ በሦስተኛው ቀን፣ ማለትም ማክሰኞ ኅዳር 25 ቀን 2016 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ፣ ሪፖርተር ባለፈው ሳምንት እሑድ ያወጣው (ከላይ የተጠቀሰው) ዘገባ ሐሰተኛ መሆኑን ጠቅሶ ዘገባው በወጣበት የፊት ገጽ ላይ ማረሚያ እንድናወጣ ጠይቆናል። ብሔራዊ ባንክ ለሪፖርተር ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል የላከው ደብዳቤ ሙሉ ይዘት የሚከተለው ነው። 

ለሚዲያ ኤንድ ኮሙዩኒኬሽን ሴንተር (ኤም...) አዲስ አበባ

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ጉዳዩ፡እርማት/ማስተካከያ እንዲደረግ ስለመጠየቅ

ድርጅታችሁ በአማርኛ እያዘጋጀ በሚያሳትመው ሪፖርተር ጋዜጣ በእሑድ ኅዳር 23 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትሙ ፊት ገጽ ላይ ‹‹ብሔራዊ ባንክ በሕጋዊና በጥቁር ገበያ መካከል ያለውን የምንዛሪ ተመን ለማጥበብ ማቀዱ ተሰማ›› በሚል ያቀረበው ዜና የተሳሳተ በመሆኑ ጋዜጣው በሚቀጥለው ዕትሙ በተመሳሳይ ገጽ ላይ ዜናው ስህተት መሆኑን ገልጾ እርማት እንዲያወጣ እናሳስባለን። በወቅቱ ማለትም ረቡዕ ኅዳር 19 ቀን 2016 .ም. የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሦስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ፣ 2016 በጀት ዓመት ዕቅድና የበጀት ዓመቱን የመጀመሪያ ሩብ አፈጻጸም ሪፖርት በተወካዮች ክር ቤት ለፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ኮሚቴ አቅርቧል፡፡

በዚህ ወቅት ክቡር አቶ ማሞ ምሕረቱ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ባቀረቡት ሪፖርት በባንኩ ስትራቴጂካዊ የትኩረት መስኮች ማለትም የተረጋጋ የዋጋና የውጭ ዘርፍ፣ ጤናማና የተረጋጋ የፋይናንስ ሥርዓት፣ እንዲሁም የፋይናንስ አካታችነትና ዲጂታላይዜሽን ማስፈንን፣ የሰው ኃይልና የቴክኖሎጂ ልህቀትን እንዲሁም መልካም አስተዳደርን በተመለከተ በበጀት ዓመቱ የመጀመርያ ሩብ የተከናወኑ ዓበይት ክንውኖችን በዝርዝር አቅርበዋል፡፡

የዋጋ ንረትን ማርገብ ከባንኩ አንገብጋቢና ቁልፍ ተግባራት አንዱ መሆኑን በማስገንዘብ፣ ባንኩ በቅርቡ የወሰዳቸው የገንዘብ ፖሊሲ ዕርምጃዎች የዋጋ ንረትን በማርገብ፣ የባንክ ብድር ዕድገትን በመግታትና የመንግሥትን የቀጥታ ብድር መጠን በከፍተኛ ደረጃ በመቀነስ ረገድ አዎንታዊ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በቅርንጫፎች ብዛት፣ በተቀማጭ ገንዘብ፣ በተከፈቱ አካውንቶች ብዛት፣ በብድር አሰጣጥ፣ እንዲሁም በፋይናንስ ጤናማነት መለኪያዎች አንፃር ሲገመገም፣ የፋይናንስ ዘርፍ ጤናማና ትርፋማና የተረጋጋ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በመጨረሻም የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የባንኩን የዕቅድ አፈጻጸም በጥሩ ጎኑ ገምግሞ የተጀመረው ስትራቴጂክ ዕቅዱም ሆነ የዋጋ ንረትን ለማርገብ የተነደፉ የገንዘብ ፖሊሲ ዕርምጃዎችና የፋይናንስ ዘርፍ እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስቧል፡፡

ይህ ሆኖ ሳለ ጋዜጣው ከአንድ የፓርላማ አባል ቀረበ ከተባለ አስተያየት በመነሳት ከላይ በተገለጸው መልኩ ብሔራዊ ባንክ በውጭ ምንዛሪ ተመን ላይ በቅርብ ጊዜና በከፍተኛ ደረጃ ለውጥ ለማድረግ አቅዷል በሚል ያወጣው ዘገባ ፈጽሞ ስህተት በመሆኑ በጋዜጣው ቀጣይ ዕትም ላይ እርማቱ እንዲወጣ እንጠይቃለን።

                                                         ከሰላምታ ጋር

     ጥላሁን ብናልፍ /ዳይሬክተር የለውጥ ማኔጅመንት፣ ዕቅድና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት

የሪፖርተር ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ምላሽ 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የማስተባበያ ደብዳቤ ይዘት ውስጥ የሪፖርተርን ዘገባ የሚመለከተው የደብዳቤው የመጨረሻ አንቀጽ መሆኑን የዝግጅት ክፍላችን ተረድቷል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለሪፖርተር በላከው የማስተባበያ ደብዳቤ ውስጥ፣ ‹‹…ጋዜጣው ከአንድ የፓርላማ አባል ቀረበ ከተባለ አስተያየት በመነሳት…›› ያወጣው ዘገባ ፈጽሞ ስህተት ነው በሚል አገላለጽ እውነታውን ለማሳነስና ለማድበስበስ መሞከሩ ተገቢ እንዳልሆነ የዝግጅት ክፍላችን በፅኑ ያምናል። 

ምክንያቱም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማው) የአገሪቱ ከፍተኛው የሥልጣን አካልና ሥራ አስፈጻሚውን መንግሥት የሚቆጣጠር ተቋም በመሆኑ፣ በምክር ቤቱም ሆነ በምክር ቤቱ አባላት የሚደረጉ የቁጥጥርና የክትትል ሥራዎችና የሚነሱ ሐሳቦች ትልቅ ዋጋ ሊሰጥባቸው የሚገባ በመሆኑ ነው።

ብሔራዊ ባንክ “ፈጽሞ ስህተት ነው” ያለውን የሪፖርተር ዘገባ ከሥረ መሠረቱ ለማስረዳትም፣ የብሔራዊ ባንክ ገዥ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርታቸውን አቅርበው ካጠናቀቁ በኋላ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ መድረኩን ለጥያቄና መልስ ሲከፍቱ የተናገሩትን ማስታወስ ጠቃሚነት አለው።

የቋሚ ኮሚቴው ዋና ሰብሳቢ፣ ‹‹የብሔራዊ ባንክ ሪፖርት ቀደም ብሎ ለቋሚ ኮሚቴው የተላከ በመሆኑ፣ የቋሚ ኮሚቴው አባላት በጋራ ተመልክተው ማብራሪያ ያስፈልጋቸዋል ያሏቸውን ጉዳዮች ለይተዋል። እነዚህን ማብራሪያ የሚሹ ጥያቄዎች የቋሚ ኮሚቴው አባልና የፋይናንስ ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት ሚኪያስ አየለ (ዶ/ር) እንዲያቀርቡ ዕድል እስጣለሁ፤›› በማለት ነበር መድረኩን ለጥያቄና መልስ የከፈቱት።

የፋይናንስ ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢው ሚኪያስ አየለ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ‹‹በብሔራዊ ባንክ የ2016 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የዕቅድ አፈጻፈምና ተቋሙ በተሰጡት ተልዕኮዎች ላይ ተመሥርተን ያዘጋጀናቸውን ጥያቄዎች አቀርባለሁ፤›› በማለት በርከት ያሉ ጥያቄዎችን አቅርበዋል። ከላይ ከተጠቀሱት የቋሚ ኮሚቴው ዋና ሰብሳቢና የፋይናንስ ንዑስ ኮሚቴው ሰብሳቢ የመግቢያ ንግግር መረዳት የሚቻለውም፣ ጥያቄው የቀረበው ብሔራዊ ባንክ ለቋሚ ኮሚቴው አስቀድሞ የላከውን ሪፖርት የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ በጋራ ተመልክተውና ገምግመው ማብራሪያ የሚሹ ጥያቄዎችን እንዳቀረቡ ነው። 

የፋይናንስ ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢው ካቀረቧቸው ጥያቄዎች መካከልም፣ ‹‹ብሔራዊ ባንክ አየተስፋፋ የመጣው ሕገወጥ የውጭ ምንዛሪ ገበያ በኢኮኖሚው ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ ለመቀነስ ምን እየሠራ ነው? በተለይም በጥቁር ገበያውና በሕጋዊ ገበያው መካከል ያለውን የውጭ ምንዛሪ ልዩነት በማጥበብ ሕገወጦች ሕጋዊ መንገድን እንዲከተሉ ለማድረግ እየተሠራ ያለው ሥራ ምን ይመስላል?›› የሚለው ይገኝበታል።

የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምሕረቱና የሥራ ባልደረቦቻቸው በቋሚ ኮሚቴው ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ቢሰጡም፣ ከላይ በተጠቀሰውና በሌሎች የተወሰኑ ጥያቄዎች ላይ የሰጡት ማብራሪያ አጥጋቢ አይደለም ብለው ያመኑ የተወሰኑ የቋሚ ኮሚቴው አባላት በበቂ ሁኔታ አልተመለሰም ያሉትን ጥያቄ በመጥቀስ ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጥበት ጠይቀዋል።

በዚህም መሠረት ሦስት የቋሚ ኮሚቴው አባላት፣ በሕጋዊውና በጥቁር ገበያው መካከል ያለውን የውጭ ምንዛሪ ልዩነት ለማጥበብ ምን እየተሠራ ነው? በማለት ቋሚ ኮሚቴው ላቀረበው ጥያቄ የተሰጠው ምላሽ የጥያቄውን ዓውድ ያላገናዘበና አጥጋቢ እንዳልሆነ ጠቅሰው የጥያቄውን ዓውድ በተለያየ መንገድ በድጋሚ በማስረዳት ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጥበት ጠይቀዋል።

በዚህም መሠረት በሪፖርተር ዘገባ ላይ የተጠቀሱት የቋሚ ኮሚቴው አባል፣ ‹‹ብሔራዊ ባንክ በሕጋዊው የውጭ ምንዛሪ ተመንና በጥቁር ገበያው መካከል ያለውን ልዩነት በ95 በመቶ የማቀራረብ ዕቅድ ይዟል። ነገር ግን በአሁኑ ወቅት በሕጋዊው የምንዛሪ ተመንና በጥቁር ገበያው መካከል ያለው ልዩነት እጥፍ ነው። ስለዚህ ልዩነቱን በ95 በመቶ ለማጥበብ የተያዘው ዕቅድ በተጨባጭ የሚቻል ነው ወይ? ወይስ ዲቫሉዌሽን ለማድረግ (የብርን የመግዛት አቅም ለማዳከም) አስባችኋል?›› ሲሉ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

አንድ ሌላ የቋሚ ኮሜቴ አባል ደግሞ፣ ‹‹በጥቁር ገበያውና በሕጋዊው የውጭ ምንዛሪ ተመን መካከል ያለውን ልዩነት ማቀራረብ ያልተቻለው ለምንድነው? በእርግጥ 95 በመቶ የማቀራረብ ሥራ እንሠራለን ብላችሁ በዕቅድ ይዛችኋል፡፡ ነገር ግን አንደኛውን ሩብ ዓመት ጨርሰናል፡፡ በዚህ አካሄድ ይሳካል ወይ?›› በማለት ጥያቄያቸውን አቅርበዋል። 

በመሆኑም በዘገባው ላይ የተጠቀሱት የፓርላማ አባል (የቋሚ ኮሚቴው አባል) ጥያቄውን ያቀረቡት በግላቸውና የስሚ ስሚ መረጃ ይዘው ሳይሆን፣ ብሔራዊ ባንክ ለቋሚ ኮሚቴው ካቀረበው የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ ሰነድ ላይ እንደተመለከቱ በመጥቀስ ነው። 

በተጨማሪም በሪፖርተር ዘገባ ውስጥ ከተጠቀሱት የቋሚ ኮሚቴው አባል በተጨማሪ፣ ሌሎች ሁለት የቋሚ ኮሚቴው አባላትም የውጭ ምንዛሪ ተመን ልዩነቱን በ95 በመቶ የማቀራረብ ዕቅድ በመጥቀስ ተመሳሳይ ይዘት ያለው ጥያቄ ማንሳታቸውን አንባቢያን እንዲረዱ እንፈልጋለን። 

በሁለተኛ ደረጃ ምላሽ ለመስጠት የፈለግነው የሪፖርተር ዘገባ፣ ‹‹…ብሔራዊ ባንክ በውጭ ምንዛሪ ተመን ላይ በቅርብ ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ ለውጥ ለማድረግ አቅዷል፤›› በሚለው የብሔራዊ ባንክ ደብዳቤ ይዘት ላይ ነው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክም ሆነ የሪፖርተር አንባቢያን ዘገባውን መልሰው በመመልከት ማረጋገጥ እንደሚችሉት፣ የሪፖርተር ዘገባ ብሔራዊ ባንክ በሕጋዊው የውጭ ምንዛሪ ተመንና በተለምዶ ጥቁር ገበያ በሚባለው የምንዛሪ ተመን መካከል ያለውን ሰፊ ልዩነት በ95 በመቶ ለማጥበብ ማቀዱ እንደተሰማ፣ ነገር ግን ይህንን ዕቅድ መቼና እንዴት እንደሚፈጽመው የታወቀ ነገር እንደሌለ የሚገልጽ ነው። 

በመሆኑም ዘገባው ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ ተመን ልዩነትን ለማቀራረብ ስለማቀዱ እንጂ፣ ብሔራዊ ባንክ ለሪፖርተር በላከው ማስተባበያ ደብዳቤ ላይ እንደገለጸው፣ ‹‹…ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ ተመን ላይ በቅርብ ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ ለውጥ ለማድረግ አቅዷል፤›› አይልም። ነገር ግን አንድ ስማቸው ያልተጠቀሰ ባለሙያን በመጠየቅ ልዩነቱን ለማቀራረብ ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉ የፖሊሲ መሣሪያዎችን (ሥልቶችን) ዘገባው በደምሳሳው ለማሳየት ሞክሯል። 

በስተመጨረሻም፣ ሪፖርተር ይህንን ዘገባ ያቀረበበት መሠረታዊ ምክንያት ምንድነው የሚለውን በአጭሩ ለመግለጽ እንወዳለን።

ዘገባውን በቀረበበት ይዘት ለማውጣት ምክንያት ከሆኑት ጉዳዮች መካከል አንዱ በብሔራዊ ባንክ የ2016 ዕቅድና የሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ላይ የተደረገው ውይይት በዝግ ወይም በሚስጥር የተካሄደ ሳይሆን፣ በፓርላማው ማኅበራዊ የትስስር ገጽ በቀጥታ የቪዲዮ ሥርጭት የተላለፈ መሆኑ ነው። በቀጥታ የተላለፈው የዚህ ውይይት ሙሉ የቪዲዮ መረጃም የሪፖርተር ጋዜጣ ዕትም ወደ ማተሚያ ቤት እስከተላከበት ዓርብ ኅዳር 28 ቀን 2016 ዓ.ም. ምሽት ድረስ በፓርላማው ማኅበራዊ ትስስር ገጽ ላይ እንደነበረ ለመግለጽ እንወዳለን።

በተጨማሪም የተገለጸው ዕቅድ ገና ውሳኔ ያላረፈበት (ገና በዕቅድ ደረጃ ላይ የሚገኝ) መሆኑና ዘገባው ቢወጣ ተጨማሪ ውይይት በመጫር ለፖሊሲ አውጪዎች ጭምር ጠቃሚ ግብዓት ሊያስገኝ ይችላል በሚል እምነት እንደሆነ ለመግለጽ እንወዳለን። 

የዝግጅት ክፍሉ

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...